Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ውሳኔው

0 460

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ውሳኔው…!

ዳዊት ምትኩ

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ኤርትራን ድንበር በተመለከተ ገዥ የሆነውን የአልጀርሱን ስምምነት አገራችን ሙሉ በሙሉ እንደምትቀበለው ገልጿል። ይህ እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም የተፈረመው ስምምነት፤ ላለፉት 18 ዓመታት በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው ‘ሞት አልባ ጦርነት’ እንዳይቀጥልና በህዝቦች መካከል ሰላም እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው።

ይህም በመካከለኛው ምስራቅ በሳውዲ አረቢያ እና በኢራን መካከል ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ በአፍሪካ ቀንድ እያስከተለ ያለውን ጂኦ-ፖለቲካ ሁኔታ የሚቀይር ውሳኔ ነው። ምክንያቱም ሁለቱም የመካከለኛው ምስራቅ አገራት የየራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ የአገራቱን ፖሊቲካዊና ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ሊጠቀሙባቸው ስለሚችሉ ነው።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን የሚፈጥር በመፍጠር የተመቻቸ ሰላምን ለቀጠናው ሊያመጣ የሚችል ነው። ውሳኔው አንዳንድ ወገኖች በተሳሳተ መንገድ እንደሚሉት በግማሽ ቀን የተደረገ ሳይሆን፤ በኮሚቴው ሲብላላና ውይይት ሲደረግበት የቆየ እንዲሁም በበቂ ጥናት ላይ ተመስርቶ የተሰጠ ነው። ይህም የሁለቱንም አገራት ህዝቦች ለመጥቀና ቀጠናውን ካላስፈላጊ ሽኩቻ ነጻ ለማድረግ ይጠቅማል።

ልማትን በማከናወን ዕድገቷን እያፋጠነች ላለችው ኢትዮጵያ ሰላም ወሳኝ ጉዳይ ነው። ሰላምን በአገር ደረጃ ለማምጣት ደግሞ በውስጥም ይሁን በውጭ ያሉትን የማያግባቡ ጉዳዩችን በመያዳግም ሁኔታ መዝጋት ያስፈልጋል። ውሳኔው ለኤርትራም ይሁን ለኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት፣ ሰላምና ካላቸው የተፈጥሮ ጸጋዎች በጋራ ተጠቃሚ ሆነው እንዲያድጉ በር የሚከፍት ነው።

እርግጥ ሰላም ከሌለ ምንም ዓይነት ተግባር መፈፀም አይቻልም። እንኳንስ በአገር ደረጃ አንድ ነገር ማከናወን ቀርቶ በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ወጥቶ መግባት አስቸጋሪ ይሆናል። የሰላምን ጠቀሜታ መለኪያ ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ የሚያውቀው የለም። ይህ ህዝብ ከትናንት በስቲያ በፊውዳላዊው አገዛዝ ስር የማቀቀ፣ ትናንት ደግሞ በአምባገነኑ የደርግ ስርዓት የአፈና መዋቅር ውስጥ ሁለንተናዊ መብቶቹ ተረግጠው በስቃይ ውስጥ የኖረ ነው።

ይህ ህዝብ የደርግን የጭቆና ቀንበርና ስቃይ አልቀበልም ብሎ ደርግን በሚገባው ቋንቋ ለማናገር ለ17 ዓመታት ያህል በጦርነት ውስጥ ያለፈ ነው። እንዲሁም በኢትዮ ኤርትራ ድንበር ላይ ባካሄደው ፍትሐዊ ጦርነት ሉዓላዊነቱን ያስከበረና ይህን ለማድረግ መስዋዕትነት የከፈሉ ልጆቹን ሁሌም የሚዘክራቸው ቢሆንም የጦርነትን አስከፊነት የተመለከተ ነው።

በመሆኑም ጦርነት ምን ያህል አስከፊ፣ ምን ያህል የሰው ህይወት ቀጣፊ፣ ምን ያህል ንብረት አውዳሚና ትውልድን አሸማቃቂና የማይረሳ ጠባሳ ጥሎ አላፊ እንደሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቀዋል። በዚህም ምክንያት በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሳቢያ ሰላም ሲታወክ የሰላሙ ባለቤት ሆኖ በቀዳሚነት የሚሰለፈውም ለዚሁ ይመስለኛል።

አዎ! ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝብ ለሰላም ዋጋው ከፍተኛ ነው። የአገራችን ህዝብ ሰላም ከቁሳቁስ መጥፋትና መውደም ጋር ብቻ እንደማይያያዝ የሚገነዘብ ነው። ነገ የሚገነባው ትልቅ ምጣኔ ሃብት ያለውና ለዘመናት ተነፍጎት የነበረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ስር እንዲሰድ ሰላሙን ይፈልጋል።

ያለፈባቸው የልማት ውጣ ውረዶች በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ተጨባጭ ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ በተሻለ ቁመና ይገኛሉ። እርሱንም በተሻለ ማማ ላይ እንደሚያወጡት በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እንደሚሆን ያውቃል። የዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር ዕድገቱ ወደ እያንዳንዱ ዜጋ መመንዘር እንዳለበት ለህዝቡ ቃል በመግባት በላቀ ፍጥነት ለመስራት ተዘጋጅቷል።

ሰላሙም እውን ሆኖ የታሰበው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በማስመዝገብ ሂደት ውስጥ ሁሉም ዜጋ ድህነት በሚባለው አንገት አስደፊ በሽታ ላይ መዝመት ችሏል። ይህ ተግባርም መጠናከር አለበት። ምክንያቱም ይህ ህዝብ ህዳሴውን ለማረጋገጥ እየተጋ በመሆኑ ነው። የአንድ አገር ህዳሴ እንዲሁ በምኞት የሚገኝ አይደለም። ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም በዚያች አገር ውስጥ መኖር አለበት።

እንደሚታወቀው ሁሉ የአንድ አገር ህዳሴ የሚረጋገጠው የተወሰኑ አካባቢዎች በሚያደርጉት የልማት እንቅስቃሴ ብቻ አይደለም። በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ዜጎች ያለ አንዳች መሸማቀቅ ለልማት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል።

ከዚህ አኳያ በትግራይና በአፋር የኤርትራ አዋሳኝ የሚገኙ ዜጎች ከሰቀቀን ህይወት ወጥተው የልማት ተጠቃሚ መሆን ይኖርባቸዋል። እነዚህ ዜጎች ላለፉት 18 ዓመታት በሞት አልባ ጦርነት ውስጥ ሆነው ለራሳቸውም ይሁን አገሪቱ ለምታስመዘግበው ዕድገት የበኩቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል።

ይህ እንዲሆንም በድንበር አካባቢ ያለው የሁለቱ አገራት ውጥረት መርገብ አለበት። ለዚህም የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ መቀበልና ለተግባራዊነቱ መዘጋጀት ይኖርበታል። የውሳኔው ትክከለኛነት ከዚህ አንፃር መታየት ያለበት ይመስለኛል።

እርግጥ ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግስታት አደራዳሪነት የአልጀርሱ ስምምነት ቢደረግም፣ ላለፉት 18 ዓመታት በሁለቱ ወንድማማች ሀገሮች የነበረው ሁኔታ የትኛውንም ወገን ተጠቃሚ ያደረገ አይደለም።

በእነዚህ ዓመታት የሁለቱን አገራት ወዳጅነት ወደ ነበረበት ለመመለስ የተደረጉ ሙከራዎች በሙሉ ውጤት ያመጡ አይደሉም። በዚህም ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ አገራት መካከል ተዓማኒ ሰላም ለማስፈን ከቀድሞው የተለየ አቋምና አካሄድ መያዝ አስፈላጊ ነው። ይህም የአገራቱን ህዝቦች ከመጥቀም ባለፈ ቀጠናው የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች ወታደሮች የስጋት ቀጠና እንዳይሆን ያደርጋል።

እስካሁን ድረስ በርካታ ለሁለቱ እህትማማች ሀገሮችም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው እድሎች አምልጠዋል። ሁኔታው እዚህ ላይ ማቆም ይኖብርታል። በደም፣ በባህል፣ በቋንቋና በረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ የተሳሰሩት የሁለቱ አገራት ህዝቦች ከተፈጥሮ ጸጋዎቻቸው ተጠቃሚ መሆን አለባቸው።

ኢትዮጵያና ኤርትራም ሆኖ ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አገራት አንዱ ያለውን ለሌለው በመስጠት፣ በትብበርና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ እጅ ለእጅ ተያይዘውም ማደግ ይኖርባቸዋል። ቀጣዩቹ ዓመታት የአፍሪካ ቀንድ አገራት የአንድነት እንጂ የልዮነት ማስተናገጃ እንዳይሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ቀዳሚውን ድርሻ መጫወት ይኖርበታል። በመሆኑም የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑ ትክክለኛ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy