Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ውሸትን ያጣ፤ ወደ ‘ሹክሹክታ’ ይምጣ!”

0 737

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ውሸትን ያጣ፤ ወደ ‘ሹክሹክታ’ ይምጣ!”

                                                     ሸረፋ ከድር

የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲኖር፤ የመኖር ፋይዳው በጎ ወይም ሰናይ ምግባሮችን ከውኖ ለማለፍ ይመስለኝ ነበር። ግና ይህ ሃሳቤ በሁሉም ሰው ዘንድ እንደማይተገበርና “ዳቦ” እስካስገኘ ድረስ ማናቸውንም ፈጠራዎች እየወለዱ አሊያም እያዋለዱ መኖርና ማለፍ እንደ ትክክለኛ መርህ የሚወሰድበት ህይወት መኖሩን መታዘቤ አይደለም። ጨዋው የአገሬ ህዝብ በህይወት መስተጋብሩ ውስጥ “ሰናይ” እና “እኩይ” ብሎ የሚፈርጃቸው ግብረ-ገባዊ አተያይ አሉት። እነዚህ አተያዮቹ በመስተጋብሩ ውስጥ ሰናይነትን ተላብሶ ህይወቱን እንዲመራ ያስቻሉት መንገዶች ናቸው።

መዋሸት እንደ ባልና ሚስት ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት ሲባል ሊደረግ ይችላል—ለበጎ ተግባር የዋለ በመሆኑ በሰናይነት የሚመዘገብ ክዋኔ ነውና። ሆኖም ተግባሩ ህዝብን ለማጋጨት፣ ሰላማዊ ህይወቱን ለማናጋትና በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የተጋጋለ የለውጥ ሂደትን ለማደናቀፍ ከሆነ፤ ተግባሩ የሚሆነው ሀገርን በጦር መልሶ ከኋላ የመውጋት ያህል ነው። እንዲህ ዓይነቱ ‘እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል’ ትረካዎች፤ አንድም፣ የግለሰቦችን መልካም ስምና ዝና ለማጉደፍ፤ ሁለትም፣ ሀገር በአዲስ የለውጥ ሂደት ስትጓዝ አይናቸው ደም የሚለብስ የማህበራዊ ሚዲያ ተከፋይ ጉደኞች ተግባር በመሆኑ ፈፅሞ ተቀባይነት ሊኖራቸው አይችልም። ለህሊናም የሚዘገንን ተራ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው።

ታዲያ እዚህ ላይ ውድ አንባቢዎቼ ‘ምነዋ እንዲህ አመረርክ?!’ ልትሉኝ ትችላለችሁ። የምሬቴ መነሻና መድረሻ ሀገሬን ከመውደድ የመነጨ ብቻ ነው። ይኸውም ሀገሬ አሁን የምትገኝበት የለውጥ መንገድ፤ የተቀባይነት ቄጠማ የረበበባት፣ የሰላም አየር የነፈሰባትና ብሔራዊ መግባባት የናኘባት ሁኔታዋ ባለ ተስፋ ምድር እንድትሆን ያደርጋታል ብዬ ስለማስብ ነው። ከነበርንበት የችግር ማጥ ውስጥ የወጣነው በአዲስ አስተሳሰብ በሚጓዙ የለውጥ አራማጆች እንዲሁም በመላው ህዝባችን የጋራ ጥምረት መሆኑን አምናለሁ። የዚህ የለውጥ ሂደት ዘዋሪዎችና እና አንቀሳቃሾች ዘአማን በላይ የተሰኙ ፀሐፊ እንደገለጿቸው፤ የፍቅርና የእርቅ ኩነት የሚካሄድበት “በጨፌ አራራ” (Caffee Araaraa) /የአሁኗ አራት ኪሎ/ ውስጥ በሚገኙት የኢትዮጵያ መሪዎች ናቸው።

ታዲያ በእኔ እምነት፤ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት እነዚህን የለውጥ ቀንዲል ለኳሾች በውሸት ወሬ ተመስርቶ የሰዎችን ስም ለማጉደፍ መጣር፤ መሪዎቹ እያካሄዱ ያሉትን ለሀገር የሚጠቅም ተግባር ለማኮላሸት ከማሰብ የመነጨ ነው። ሌላ ምንም ዓይነት ትርጓሜ የሚሰጠው አይደለም። ከእነዚህ መሪዎች ውስጥ በአሁኑ ወቀት ውሸትን ተንተርሶ ስማቸው እንዲጎድፍ የተደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ይገኙበታል።

ከመሰንበቻው ‘ሹክሹክታ’ የተሰኘው የአሉባልታ መጋለቢያ ፈረስ ድረ ገፅ፤ በዶክተር ገበየሁ ወርቅነህ ላይ የከፈተው የስም ማጥፋት ዘመቻ አሳፋሪና የማህበራዊ ሚዲያውን ተቀባይነት አፈር ድሜ የሚያስበላው ይመስለኛል። ርግጥ ‘ሹክሹክታ’ የሀገራችንን አዲስ የለውጥ ሂደት በማይሹ ጥቂት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ረብጣ ብር ተመድቦለት የሚሰራ መሆኑ ግልፅ ነው። ዓላማውም እዚህ ሀገር ውስጥ እየተከናወነ ያለውን አዲስ አስተሳሰብና የለውጥ መንገድ ለማደናቀፍ አሜኬላ እሾህ ሆኖ መቆም ብቻ ነው። በዚህም ባህር ማዶ በሚገኙ “ሆድ-አደር” ግለሰቦች አማካኝነት ፌስ ቡክና ዩ ቲዩብን በመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች አሉባልታን እያወሩ ሀገራቸውን ለማደናቀፍ በሚሯሯጡ ግለሰቦች ቅጥፈት እንደ እውነት ይነገድበታል። እንደ ‘ሹክሹክታ’ እና ‘ዘ ሃበሻ’ ያሉ ድረ ገፆች በአገራችን ውስጥ የተፈጠረው መልካም ጉዞ ያበሳጫቸውና ስጋት ላይ የጣላቸው እንዲሁም ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማቆርፈድ ሰርክ የሚባትሉ ናቸው።

በተግባራቸውም ግዑዙን ፍራሽ ሳይቀር በሰውኛ እያናገሩና በልቦለድ ዓለም ውስጥ እየቀዘፉ የግለሰቦችን መልካም ስም ለማጉደፍ ‘ምንትስ እንዲህ ሆነላችሁ…’ እያሉ ያለ አንዳች ሃፍረት ለአድማጮች የሚያቀርቡና ኢትዮጵያዊ ግብረ ገብነት ያልፈጠረባቸው ስብስቦች ናቸው። የውሸት ፈረስ ሽምጥ ጋላቢዎች።

ከእነዚህ ውስጥ በቆርጦ ቀጥልነት የሚታወቀው ‘ሹክሹክታ’፤ የዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን ስም ለማጥፋት ‘ኦሮሞ አይደሉም…የምንትስ ብሔር አባል ናቸው…’ እያለ ጭምር ማንነታቸውን ለመቀየር የሚደፍር የጉደኞች ስብስብ ነው። ምንም እንኳን በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ መስጠት እንኳንስ እንቅልፍ አልባ ሆነው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ላይ ታች እያሉ ለሚገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ቀርተው፤ ምላሽ መስጠቱ እኔንም ተራውን ግለሰብ እንኳን የሚመጥን አይደለም። ያም ሆኖ ግን፤ አካፋን ‘አካፋ!’ ማለት ስለሚገባ ስም አጥፊውን አንሸኳሿኪ በተነሳበት ልክ መንገር ያስፈልጋል።

በቅድሚያ በኢትዮጵያዊነቱ አንድም ቀን ተደራድሮ የማያውቀው የኦሮሞ ህዝብ በስርዓቱ ውስጥ ሌላውን ብሔረሰብ አቅፎና ደግፎ የመያዝ የኮራ ወግና ባህል ያለው መሆኑን አንሸኳሿኪዎቹ ሊያውቁት የሚገባ ይመስለኛል። በኦሮሞ ብሔር ስርዓት መሰረት፣ አንድ ግለሰብ ከኦሮሞ ባይወለድም፤ ህዝቡን እስከወደደና አብሮ መኖር እስከፈለገ ድረስ ኦሮሞ የመሆን መብት አለው። ይህ ስርዓት የሌላው ብሔረሰብ አባል የሙሉ ልጅነት ማዕረግ የማግኘት (ጉዲፈቻ) የመሆን ዕድልን ይሰጣል። እንዲሁም ሙሉ ኦሮሞ (ሞጋሳ) የመሆንን ዕድልም ያጎናፅፋል። ምን ይህ ብቻ። ከሌላ ብሔር የመጣው ግለሰብ በ“አመቺሳ” ሙሉ ኦሮሞ የመሆን ማንነትን ሊያገኝ ይችላል።

እኔ እስከማውቀው ድረስ፤ ‘ደምህ እገሌ የሆነ ብሔር ስለሆነ ከእኛ ጋር አትኖርም’ ሳይል፤ በግለሰቡ ሙሉ ፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ ሌላውን ብሔር የሚቀበል ብቸኛው ማህበረሰብ የኦሮሞ ብሔር ነው። ይህም ብሔረሰቡ ምን ያህል በዴሞክራሲ እንደሚያምን፣ ደምና ዘር ሳይቆጥር የትኛውንም የህብረተሰብ ክፍል የራሱ አድርጎ እንደሚኖር የሚያሳይ ሃቅ ነው። ማንም ኢትዮጵያዊ በዚህ እጅግ አስገራሚ ባህል ሊኮራ የሚገባው ነው። እነ አንሾኳሿኪዎቹም ይህን ሃቅ እየመረራቸውም ቢሆን መጋት ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ።   

ታዲያ ይህን ስል፤ የኦሮሞ ብሔር ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ያለውን አኩሪ ዴሞክራሲያዊ ባህላዊ መስተጋበርን ለመግለፅ እንጂ፤ ዶክተር ወርቅነህ በ”ጉዲፈቻ”፣ በ”ሞጋሳ” ወይም በ”አመቺሳ” ኦሮሞ ሆነዋል እያልኩ አይደለም። በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ሃቅን ደፍጥጠው በሬን በማዋለድ የሚታወቁት አንኞኳሿኪዎቹ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን እንደለመዱት ‘ትራስ አንሸኳሸከልን’ ብለው እንደማይቀባጥሩ ተስፋ አለኝ—ውሸትን መደረት ልማዳቸው ነውና። እናም ዶክተር ወርቅነህ ውልደታቸውና ዕድገታቸው በግልፅ የሚታወቅና የዘር ሐረጋቸውም ከኦሮሞ የሆነ ምርጥ የኢትዮጵያ ልጅ ናቸው።

የድረ ገፅ ገበያ የተምታታባቸውና በከሰረ ፖለቲካ የሚናውዙ አንሸኳሿኪዎች ግን፤ ‘እገሌ ኦሮሞ አይደለም፣ አባቱ አማራ ነው፣ እናቱ ትግሬ ናት፣ አያቱ ከማሺ ነው፣ ቅድመ አያቱ ኤርትራዊ ነው…ወዘተ’ እያሉ ዘር ይቆጥራሉ፤ ጎራውን በአሉባልታ ያስሳሉ፤ እግራቸው እስኪነቃም ይዞራሉ። የጥላቻ ፖለቲካ አራማጅ በመሆንም የድረ ገፅ ላይ የአሉባልታ አታሞን ይደልቃሉ። በእውነቱ እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ የማህበራዊ ሚዲያው ‘ተረት-ተረት’ ለፋፊዎች፤ በኦሮሞ ህዝብ ጠንካራ ትግል ውስጥ መሪ ተዋናይ የሆኑና ራሳቸውን ለትግሉ አሳልፈው የሰጡ ግለሰቦች፤ በወሬ የማይፈቱ እንዲሁም ትግላቸው ከብረት የጠነከረ መሆኑ እንኳን ገና በቅጡ ያልገባቸው ጨቅላዎች ናቸው። ለዚህም ነው— ዶክተር ወርቅነህ ‘አያታቸው ትግሬ ነው’ የሚል አሉባልታን ቀምረው በትስስር መረቡ ቀጭን ገመድ ላይ ሽምጥ የሚጋልቡት።

ምንም እንኳን የአንሸኳሿኪዎቹ ዓላማ ለሀገር የሚሰሩ ጠንካራ ግለሰቦችን ሆን ብሎ በፈጠራ ብያኔ ማሸማቀቅ ቢሆንም፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ የዶክተሩ አያት ትግሬም ይሁኑ አማራ፣ ጎጃሜም ይሁኑ ጋምቤላ…ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ ምንም ማለት አይደለም— የአንሸኳሿኪዎቹን የሴራ ፖለቲካ ፍጆታ ጥቅም ለማዋል ካልሆነ በስተቀር። በሀገሬ የለውጥ መሃንዲሶች “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን” እየተባለ በሚነገርበት በዛሬም የአንድነት ዘመን፤ እንዲህ ዓይነቱ የፀጉር ስንጠቃ ዙረት የትም የሚያስኬድ አይደለም። እንዲያውም ነገርዬው “ዓይነ ስውር ቢሸፍት ጓሮ ድረስ ነው” ከመባል የሚያልፍም አይሆንም።  

ያም ሆነ ይህ፤ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች እንዳወጉኝ፤ የዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አያት ኦሮሞ ናቸው፤ ስማቸውም “ነገዎ” ይሰኛል። ዶክተሩም 17 የዘር ግንዳቸውን መቁጠር የሚችሉ የሻሸመኔ ሰው ናቸው። እናም በተገኘው የፖለቲካ ነፋስ ውስጥ ከመኢሶን ጀምረው ሲዳክሩ የነበሩት እነ ዶክተር መረራ ጉዲና ዓይነት ፖለቲከኞች፤ በ1980ዎቹ ዶክተር ገበየሁን ፖለቲካ ሳይንስ ሲያስተምሯቸው የአያታቸው ስም “ወልደማርያም” አሊያም “ገብረማርያም” ነበር ብለው የአንሸኳሿኪዎቹ እማኝ ሆነው መቅረባቸው ብዙም አይደንቅም። የተሳሳቱም አይመስለኝም። የዶክተሩ አያት የትግራይ ስም ሊመስል ይችላል። እኔ እራሴ ነፍሳቸውን ይማርና ‘ወልደአማኑኤል ዱባለ’ የተሰኙ የብሔረ ሲዳማ ተወላጁን የቀድሞው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ መሪን አስታውሳለሁ። ‘ገብረ እገሌ፣ ወልደ እገሌ…’ በሚል ስያሜ የሚጠሩ ኦሮሞም ይሁን አማራ ጓደኞች አሉኝ። እንዲህ ዓይነቱ አጠራር ህዝቦች ካለፏቸው ስርዓቶች ዕይታ ጋር አብሮ የሚያያዝ በመሆኑ የሚገርም አይደለም።

ያም ሆኖም ግን ዶክተር መረራም ይሁኑ ደቀ መዝሙሮቻቸው በዶክተር ወርቅነህ አያት ዘመን የነበረውን የመንግስትና የሃይማኖት አንድነትንና በዚህም ሳቢያ የክርስትና መስፋፋት ጥግ ላይ የደረሰበት ወቅት ይዘነጉታል ብዬ አላስብም። እናም የዶክተር ገበየሁ አያት ኦቦ ነገዎ፤ ከወቅቱ መንግስታዊና ሃይማኖታዊ ሁኔታ አኳያ በክርስትና ስማቸው ቢጠሩ ብዙም የሚያስደንቅ አይደለም። በዚያን ዘመን እንኳንስ የሰው ስም ቀርቶ ከተሞች እንኳን ሳይቀሩ በክርስትና ስም ሲጠሩ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው። (እዚህ ላይ ውድ አንባቢያን ደብረዘይት፣ ናዝሬት…ወዘተ. የመሳሰሉ ከተሞችን ከዛሬ መጠሪያቸው ጋር በማገናዘብ ልብ ይሏል!) እናም የማያውቁትን ነገር አንድ ጫፍ አንጠልጥሎ በመያዝ የዶክተር ገበየሁን ስም በውሸት ጥላሸት ለመቀባት የሚደረግ ክንዋኔ ይህን እውነታ እንኳን በቅጡ የማያውቅ እንዲሁም ማንኛውም አሉባልታ “ዳቦ” ብቻ ሆኖ የሚታየው “የሆድ አደሮች” መሰሪ ተንኮል ከመሆን የሚዘል አይደለም። እጅግ አሳፋሪም ተግባርም ጭምር።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የአቋም ሰው ናቸው። መንግስት በሚመድባቸው የትኛውም የስራ ስምሪት ዘርፍ ተግባራቸውን በቅንነትና በታማኝነት የሚያከናውኑ ጠንካራ ሰው ናቸው። ሌላው ቀርቶ የቅርቡን ብናስታውስ እንኳን፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስምምነት አዲስ አበባ ውስጥ የሶስትዮሽ ውይይት ሲካሄድ እስከ ለሊቱ አስር ሰዓት ድረስ በመሟገት የሀገራቸውንና የህዝባቸውን ጥቅም ማረጋገጥ የቻሉ በሳል ምሁር ናቸው። በዚህም መንግስት የሰጣቸውን ተልዕኮ ማናቸውንም ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎችን በብቃት በመከወን ይታወቃሉ።

ዶክተሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር ስር ሆነው ያለ እረፍት የሀገራችንን ዲፕሎማሲያዊ ተግባሮችን እንዴት እየተወጡ እንደሆነ ከኦሮሞም ይሁን ከኢትዮጵያ ህዝብ የተሰወረ ጉዳይ አይደለም። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጋር በመሆን አሊያም በተናጠል በሚያደርጓቸው ማናቸውም የስራ ስምሪቶች ለውጥን ያጋጋመና በሁሉም መስኮች የህዝባችንን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው። እናም ይህ ውጤታማነታቸው ቀንና ለሊት እንቅልፍ የነሳቸው የጥላቻ ፈረስ ጋላቢዎች ህዝብን በመከፋፈል ስራ ላይ እንዲጠመዱ ምክንያት የሆናቸው ይመስለኛል። እነ ዶክተር አብይና ዶክተር ወርቅነህ ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም እንቅልፍ አልባ ሆነው ይዞራሉ፤ አንሾካሿኪዎቹ ግን ለሀገር ጥፋት ቀንና ለሌት ቁጭ ብለው ያድራለሁ። እንዲህ ዓይነቱን ‘ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ’ ዓይነት አስተሳሰብ “አጃኢብ ነው!” በቻ ብዬ አልፈዋለሁ።

ርግጥ የተግባር ሰው መሆን መተዳደሪያቸውን በውሸት ላይ ለመሰረቱ ሰዎች አይዋጥላቸውም። የተግባር ሰው መሆን የደራው የፈጠራ ድራማቸውን እንዲቀዘቅዝ ያደርጋል። ከፍ ሲልም በህዝቡ ሚዛናዊ ፍርድ እንጀራ ገመዳቸው ሊበጠስ ይችላል። ሌላ ሌላም።… እናም ይህ እንዳይሆንም ዘንድ እነርሱ ‘ለውጡን በማጋጋል ላይ ናቸው’ ብለው በሚያስቧቸው ሰዎች ዙሪያ የልቦለድ ድርሰት እየከተቡ በጥላቻ መንፈስ ይንጣጣሉ። የቅጥፈት ትረካቸው አልፋና ኦሜጋ መነሻውም ሆነ መድረሻም ይኸው ነው።

ያም ሆኖ ዛሬ ላይ በእነርሱ በውሸት የታጀለ ሴራ የሚከፋፈል ድርጅት ሀገሬ ውስጥ የለም። ዛሬ ዶክተር ወርቅነህ የሚገኙበት የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦህዴድ) ከምንግዜውም በላይ አንድነቱን ያጠናከረበት ወቅት ነው። ድርጅቱ በፍትህና እኩልነት ከማመን ባለፈ፤ በተግባርም እያሳየን ነው። ራሱን በማጥራት በትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ መንገድ እየተጓዘ መሆኑን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ሃቅ ነው—ከጥላቻ ሃሳብ አራማጆቹ በስተቀር።

በተለምዶ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ስም የሚጠራውና “የኦቦ ለማ ቲም” የሚባለው የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ እያከናወነ ያለው ጠንካራ የኢትዮጵያዊት ተግባር ለሌሎቹ ህብረ ብሔራዊ ድርጅቶች አርአያ መሆን የሚችል ነው ብዬ አስባለሁ። ለአብነት ያህልም፤ የኦሮሚያ ክልል ሰሞኑን ባካሄደው የማጥራት ስራ አንዱ ኢትዮጵያዊነትን በሚያላሉ ጉዳዩች ላይ ተሰማርተዋል የተባሉ የታችኛው እርከን ባለስልጣናት ላይ ርምጃ መወሰዱ ነው። ይህም የመከፋፈል አጀንዳ በኦሮሚያ ሰማይ ስር ያከተመለት መሆኑን በግላጭ የሚያሳይ ይመስለኛል።  እናም አንሸኳሻኪዎቹ በዚህ ወቅት ኦሮሞን ብሎም ኢትዮጵያን ለመከፋፈል የሚያደርጉት ጥረት ከከንቱ ልፋትነት አይዘልም፤ ‘ውሃ ቢወቅቱት እምቦጭ አለ’ የሚሉት ዓይነት። ‘ለምን?’ ከተባለ ዛሬ እዚህ ሀገር የተፈጠረው ጠያቂና ሞጋች ህዝብ፤ በሚዛናዊ እይታ የሚጓዝና ብስሉን ከጥሬው የሚለይ እንጂ፤ እንደ ቦይ ውሃ በቀደዱለት መንገድ የሚጓዝ የዋህና ተላላ ባለመሆኑ ነው።

እናም እንደ ‘ሹክሹክታ” ያሉ ‘ምን ዓይነት ውሸት አውርቼ ልኑር’ ባይ የጥላቻ ፖለቲካ ፈረስ ሽምጥ ጋላቢዎች፤ በኦሮሚያ ክልልም ይሁን በታላቋ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀለቀለ ያለውን የለውጥ ቋያ እሳት የማይገነዘቡ ሞኝ አዝማሪዎች ናቸው። እነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፣ እነ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና እነ ኦቦ ለማ መገርሳ እንዲሁም ሌሎች የሀገሬ መሪዎች በአዲስ አስተሳሰብ እያነጿት ያሉትን አዲሲቷን ኢትዮጵያ አያውቋትም። የሚያርሱትም በድሮ በሬ ነው። አሮጌን ወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ላይ ለመገልበጥ የሚሹ አሳፋሪዎች ናቸው። እኔ በበኩሌ ዶክተር ወርቅነህን በተመለከተ ያስወሩት ውሸት በእነርሱ ቦታ ሆኜ ለማፈር ተገድጃለሁ። በመሆኑም እነዚህ ‘በአንድ ሲደመር አንድ ሶስት ነው’ የቅጥፈት ስሌት ለሚንቀሳቀሱት ፀረ ለውጥ ኃይሎችን፤ “ውሸትን ያጣ፤ ወደ ‘ሹክሹክታ’ ይምጣ!” የሚል ይትብሃል ቋጥሬላቸዋለሁ። ምክንያቱም “ተግባርህን ንገረኝና ማንነትህን ልንገርህ” እንዲሉ ታታሪዎቹ ጃፓኖች፤ የጥላቻና ከፋፋይ ፖለቲካ አራማጀነታቸውን እንዲሁም የትስስር መረብ ላይ የውሸት ታንኳ ቀዛፊነታነት ግብራቸውን በሚገባ ይገልፅልኛል ብዬ ስለማምን ነው። እናንተስ ምን ትላላችሁ?…

  

  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy