Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የልማት ድርጅቶቹ ለምን ይሸጣሉ?

0 347

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የልማት ድርጅቶቹ ለምን ይሸጣሉ?

                                                              ዘአማን በላይ

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በቅርቡ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በከፊል ሊብራላይዝድ ለማድረግ ያሳለፈው ውሳኔ፤ በርዕሴ ላይ ያነሳሁትን ጥያቄ ወልዷል ማለት ይቻላል። በርካታ ሀገር ወዳድ ዜጎች፤ በኢኮኖሚው ከፊል ሊብራላይዝድ መሆን ሳቢያ ‘የልማት ድርጅቶቹ ለምን ይሸጣሉ?’ በሚል ሃሳባቸውን እየሰነዘሩ ነው። በአንዳንድ ቦታዎች ጉዳዩ የመወያያ ርዕስም ሆኗል። በእኔ እምነት፤ ይህ የዜጎች ውይይት፤ ሀገርን ከመውደድ፣ ይበልጥ ተጠቃሚነትን ከማሰብ እንዲሁም እንደ አየር መንገድና ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ድርጅቶች “ኢትዮጵያዊ” ብቻ እንዲሆኑ ከመመኘት የመነጨ ቀና እሳቤ ነው። እናም በጉዳዩ ላይ ከ“እኔነት” ስሜት በመነሳት የሚሰነዘሩ ሃሳቦች መንሸራሸራቸው፤ ዜጎች ምን ያህል የመንግስትን ተግባሮች በቅርበት እንደሚከታተሉ አመላካች ክስተት ይመስለኛል።

ርግጥ በመንግስት ስር የሚገኙ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴልና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግሉ ዘርፍ እንዲተላለፉ ተወስኗል። እንዲሁም የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግስት ይዞ፤ ቀሪው አክሲዮን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፍ ውሳኔ ላይ ደርሷል።

ድርጅቶቹን የማስተላለፍ አፈፃፀሙም የልማታዊ መንግስት ባህሪያትን በሚያስጠበቅ፣ የአገራችንን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በሚያስቀጥልና የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲመራ እንዲሁም ዝርዝሩ በባለሙያዎች ተደግፎ በጥብቅ ዲሲፕሊን ተግባራዊ የሚደረግ ነው። ይህም ማለት በተለያየ ደረጃ ወደ ግል ይዞታነት የሚደረገው ዝውውር፤ ግልፀኝነትን፣ ተጠያቂነትን፣ ፍትሃዊ የገበያ ውድድርን ማዕከል ባደረገ እንዲሁም ሞኖፖሊን በማይፈጥር ሁኔታ ይከናወናል ማለት ነው። እንግዲህ ይህ ውሳኔ ነው—ዜጎችን “ለምን?” የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ ያደረጋቸው። የዚህ ፅሁፍ ዓላማም “ለምን?” ለሚለው ጥያቄ ከግል እይታዬ በመነሳት ምላሽ መስጠት ነው። ታዲያ ምላሼን በተገቢው መንገድ ለማስቀመጥ በድሚያ የሀገራችንን ኢኮኖሚ ነባራዊ ሁኔታዎችን በጥቂቱ መዳሰስ ያስፈልጋል።

ባለፉት 15 ዓመታት ሀገራችን በፈጣንና ተከታታይ የዕድገት ዑደት ውስጥ እንደነበረች አይታበይም። ይህ ዕድገት መሬት ላይ ሲወርድ የሚቀሩት ጉዳዩች እንዳሉት ግልፅ ቢሆንም፤ የህዝቡን ህይወት ከሞላ ጎደል አልለወጠም ማለት ግን አይቻልም። ይሁንና ዕድገቱ ወደ መሬት ሲወርድ፤ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ ምን ያህል ለውጥ አምጥቷል? የሚለው ጉዳይ ምላሽ የሚያስፈልገው ነው። ይህን ሁኔታ ለመፍጠርም፤ እንደ ማንኛውም ልማታዊ መንግስት በአሁኑ ወቅት ከምንገኝበት የዕድገት ደረጃ ጋር የሚመጣጠን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። ስለሆነም ፈጣን ዕድገቱ ዜጎችን አካታች በሆነ መልኩ በመጥቀም ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ለማድረግ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የአክስዮን ድርሻ እንዲኖራቸው መደረጉ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ።

ከዚህ መሳ ለመሳም፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለረጅም ጊዜያት በሀገራቸው ልማት ለመሰማራት ያላቸውን ምኞት የማረጋገጥ አስፈላጊነትም የሚያጠያይቅ አይደለም። ዜጋ ማለት ሀገር ውስጥ ያለው ብቻ አይደለምና። እንዲሁም የዕድገቱን ፍጥነት ይበልጥ ለማስቀጠል ብሎም እውቀትና የውጭ ምንዛሪ ካፒታል ያላቸው የውጭ ባለ ሃብቶች በዕድገታችን ላይ ተገቢውን አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ማስቻል ይገባል—የልማታዊ ምንግስት አንዱ መለያ ባህሪ ይኸው ነውና። እናም በእኔ እምነት፤ እነዚህ እውነታዎች ኢኮኖሚውን ከፊል ሊብራላይዝድ የማድረግ አስፈላጊነትን የሚወስኑ አስቻይ ሁኔታዎች (Enabling Environments) ናቸው።

የፖሊሲ ማስፈፀሚያ የሆኑት እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድና ቴሌን የመሳሰሉ ታላላቅ የልማት ድርጅቶች በከፊል እንዲሁም በፖሊሲ ማስፈፀሚያነት ያልያዙት ሌሎቹ ድርጅቶች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ወደ ግሉ ባለሃብት የሚተላለፉት፤ አራት ምክንያቶችን ላሳካት ነው። አንደኛው፤ ለመንግስት ከፍተኛ የፋይናስ አቅም ለመፍጠር ነው። ሁለተኛው፤ የኢኮኖሚውን ዕድገት አጠናክሮ ለማስቀጠል ሲሆን፤ ሶስተኛው፤ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ነው። አራተኛው ደግሞ፤ ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ለማካሄድ ታሳቢ ለማድረግ ነው። እነዚህን አራት ተያያዥ ጉዳዩች ዘርዘር አድርጎ መመልከት ጠቃሚ ነው።

መንግስት ሀገራችን በውጭ ምንዛሬ እጥረት ውስጥ እንደምትገኝ ደጋግሞ ገልጿል። የውጭ ምንዛሬ እጥረት ዳፋው እስከ የት ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል ደግሞ ማንኛውም ዜጋ የሚገነዘበው እውነታ ይመስለኛል። አዎ! በአጭር ቋንቋ፤ የውጭ ምንዛሬ ከሌለ ከውጭ የሚገባ ማንኛውም ዓይነት ፍጆታ ቀጥ ብሎ ይቆማል። ሰሞኑን የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነት ዶክተር ይናገር ደሴ ለመገናኛ ብዙሃን ሲገልፀ እንዳደመጥኩት፤ ኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ፤ ለነዳጅ፣ ለፍጆታ ዕቃ፣ ለግሉ ዘርፍና ለኢንቨስትመንት ውጪ እንዲሁም ለነባር ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያና ለውጭ እዳ ክፍያ ከ13 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋታል። ታዲያ ይህን ችግር ለመቅረፍ በመንግስት በኩል የተቀመጠው፤ ለፖሊሲ ማስፈፀሚያነት የሚውሉትን እንደ አየር መንገድና ቴሌ የመሳሰሉ የልማት ድርጅቶችን በከፊል (መንግስት ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ) እንዲሁም የፖለሲ ማስፈፀሚያ ያልሆኑትን ተቋማት የባለቤትነት ድርሻ ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ይዞታ ማስተላለፍ ነው።

ታዲያ የዚህ ርምጃ መነሻውም ይሁን መድረሻው የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ለመቅረፍ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ለውጭ ምንዛረ እጥረቱ ዋነኛ ምክንያት፤ ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ አለመመጣጠኑ ነው። ላለፉት ረጅም ዓመታት ሀገራችን ለገቢ ምርት እስከ 17 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ስታወጣ ብትቆይም፤ የወጭ ንግድ ገቢዋ ግን ከሰስት ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ አልፎ አያውቅም። ይህም ጤናማ ኢኮኖሚ እንዳይኖረን አድርጓል። እናም የልማት ድርጅቶቹን በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ይዞታ ባለቤትነት ማዞር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ታዲያ ይህ ርምጃ የአጭር ጊዜ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የረጅም ጊዜ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው መንግስትና ህዝቡ የወጭ ንግዱን ለማሳደግ በሚያደርጉት ጠንካራ ጥረት ላይ የሚወሰን መሆኑ አጠያያቂ አይደለም።

በእኔ እምነት፤ እንደ አየር መንገድና ቴሌ የመሳሰሉ ድርጅቶች አብዛኛው ይዞታ በመንግስት እጅ በመሆኑ መንግስትና ህዝብ እምብዛም የሚጎዱ አይመስሉኝም። አንድ ምሳሌ ላንሳ። እንበልና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካፒታሉ 10 ቢለየን ዶላር ነው። ከዚህ ውስጥ መንግስት 51 በመቶውን ቢይዝ አምስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ድርሻ አለው። 49 በመቶውን ከሚገዛው (ከሚገዙት) ኩባንያ (ዎች) አራት ነጥብ ዘጠኝ ቢለዮን ዶላር ገቢ ያገኛል። ይህ አራት ነጥብ ዘጠኝ ቢለዮን ዶላር (ማለትም የገዥው ኩባንያ የአክሲዩን ድርሻ ማለቴ ነው) በዓመት ውስጥ የሚያመጣው ትርፍ አንድ ቢሊዮን ዶላር ቢሆን፤ ከዚህ የትርፍ ህዳግ ውስጥ መንግስት 35 በመቶ በታክስ መልክ ያገኛል። በዚህ ላይ ኩባንያው የሚመጣው ባዶ እጁን አይደለም—የእውቀትና የቴክኖሎጂ ክህሎትንና ሽግግርን ይዞ እንጂ። በዚህም አየር መንገዱ ተጠቃሚ ይሆናል። እናም እኔ እሰከሚገባኝ ድረስ መንግስት አየር መንገዱን በመሸጡ የሚያጣው ነገር ወይም አሳልፎ የሚሰጠው ቀደም ሲል በእውቀትና በቴክኖሎጂ ያጣውን ገቢ ነው። አሊያም የሚያጣው ገቢ ይህን ያህል ጎልቶ የሚታይ አይመስለኝም—የገቢ ትንሽ ባይኖረውም። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ቋፍ ላይ እንድንቆም ያደረገንን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በጊዜያዊነት በዚህ መንገድ ፈትቶ፤ በዘላቂነት  ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት የወጭ ንግድ ላይ ለማተኮር ማሰብ ትክክለኛ አተያይ ይመስለኛል። በዚህ ላይ ሙሉ ለሙሉ የሚሸጡት ድርጅቶች ገቢም የመንግስትን የውጭ ምንዛሬ ችግር በመቅረፍ የፋይናንስ አቅሙን የሚያጠናክሩለት ይሆናሉ።

የፕራይቬታይዜሽን ስራ ለሀገራችን አዲስ ጉዳይ አይደለም። በመንግስት እጅ ያሉ የልማት ድርጅቶች እንዲሸጡ ገዥው ፓርቲ የወሰነው ከ18 ዓመታት በፊት በ1992 ዓ.ም እንደነበር አስታውሳለሁ። እናም የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ፕራይቬታይዝ የማድረግ ስራው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሲተገበር የመጣ ነው። ይህም የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም በተወሰነ መልኩ ኢንቨስትመንትን እየሳበ ዛሬ ድረስ መጥቷል። ኢንቨስትመንት ደግሞ ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግርንም አብሮ የሚያመጣ ነው። በመሆኑም ዛሬም ይህን ኢንቨስትመንት ለመፍጠር የልማት ድርጅቶቹ መሸጣቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይመስለኝም። ያለ ኢንቨስትመንት ልማት የለምና። እናም የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠል ያሉትን ሃብቶች ወደ ግል ይዞታነት በማዞር የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በአስተማማኝ ሁኔታ መቅረፍ ያስፈልጋል።  

ኢንቨስትመንትን መሳብ የሚችል ማንኛውም ልማታዊ መንግስት የጀመራቸውን የዕቅድ ትልሞች በአስተማማኝ ሁኔታ ዛይዛነፉ ግለታቸውን ጠብቆ ሊፈፅማቸው ይችላል። ለዚህ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ማጠናከር አለበት። የግሉ ባለሃብት ሊሰራቸው የማይችላቸውን ፕሮጀክቶች ለመከወንና ልማቱን ዜጎችን ያቀፈ ለማድረግ ከውጭ ምንዛሬ ቀውስ መውጣት ያስፈልጋል። ለዚህም ነው—መንግስት በእጁ የሚገኙትን የልማት ድርጅቶች በከፊል አሊያም ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ይዞታ ባለቤትነት የሚያዞረው።

ልማታዊ መንግስት አቅሙን ለማጠናከር ባሉት ኢንቨስትመንቶች ላይ ብቻ አይወሰንም—ተጨማሪ መንግስታዊ ኢንቨስትመንቶችን ማስፋፋት ይኖርበታል። ታዲያ ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋትና ህዝብ አቀፍ ተጠቃሚነትን ለመፍጠር አሁንም የገንዘብ እጥረቱን መፍታት አለበት። መንግስት የሚያካሂዳቸው ኢንቨስትመንቶች ግዙፍ እንደ መሆናቸው መጠን ከውጭ በሚገቡ ግብዓቶች የሚከናወኑ ናቸው። ግብዓቶቹን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬን ማፍራት ይጠይቃል።

ርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ያላት ግዙፍ ሃብት ህዝብ ነው። እጥረቷ ደግሞ ገንዘብ ነው። ታዲያ ያላትን ግዙፍ ሃብት (ህዝቧን) በሁሉም መስኮች ለማሳደግ በቅድሚያ መፍታት ያለባት የገንዘብ እጥረቷን ነው። እጥረቱን በዘላቂነት ኢንቨስትመንትን ከማስፋፋት በምታገኘው የወጭ ንግድ ገቢ የመቅረፉ ቀጣይ ርብርብ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ እንደ አጭር ጊዜ ርምጃ የልማት ድርጅቶቿን ከመሸጥ ውጭ አማራጭ ያላት አይመስለኝም። ያም ሆኖ፤ በዚህ ፅሑፍ ከላይ ያቀረብኳቸው ማብራሪያዎች፤ ‘የልማት ድርጅቶቹ ለምን ይሸጣሉ?’ ለሚሉ ቅን አሳቢ ዜጎች የተወሰነ ግንዛቤ አስጨብጠዋል ብዬ አምናለሁ። እናም መጪው ጊዜ በዚህ በኩልም የሀገራችን ችግር ተፈትቶ የምናይበት ይሆንልን ዘንድ እየተመኘሁ ፅሑፌን በዚሁ ቋጫለሁ።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy