የመጨረሻው ግብ
ዳዊት ምትኩ
አገራችን ውስጥ የኢኮኖሚ ሪፎርም በአዲስ ሁኔታ እየተካሄደ ነው። ሪፎርሙ ህዝብንና አገርን የሚጠቅም እንዲሁም ከገባንበት ጊዜያዊ ችግር ሊያወጣን የሚችል ነው። የልማት ድርጅቶችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ በመንግስት እጅ ያሉት የልማት ድርጅቶች አብዛኛዎቹ ያለባቸውን ዕዳ እንኳን መክፈል ያልቻሉ ናቸው። የሃብት ብክነትም የሚታይባቸው ናቸው።
እርግጥ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለአገሪቱ እጅግ እንደሚያስፈልግና በየወቅቱ ተመሳሳይ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ ኢኮኖሚው ወደ ኋላ የሚመለስና አገራዊ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። እንደሚታወቀው ሁሉ አገሪቱ ላለፉት ዓመታት ስትበደር ቆይታ አሁን መክፈያው ጊዜው ሲደርስ ለመክፈል ከፍተኛ ችግር ተፈጥሯል። ይህም የኢኮኖሚ ሪፎርሙ እንዲተገበር ምክንያት ሆኗል።
ታዲያ እዚህ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ያሉትን መገንዘብ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ይበልጥ የሚያስረዳ ነው። እርሳቸው እንዳሉት፣ ተበድሮ መክፈል የማይችል አገር አይታመንም። ወደፊትም ለመበደር የሚቸገር ይሆናል። የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረግ ይህን ችግር ለማረም የሚያግዝ ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ ፕሮጀክቶችን መጀመር እንጂ መጨረስ አልተቻለም። እንዲሁም በአገራችን የተፈጠረውን የገንዘብ እጥረት ሪፎርሙን እውን በማድረግ ለመቅረፍ ይቻላል። እናም መንግሥት ስራውን ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ወጪ ወይም የሃብት አጠቃቀምንና ብክነትን ለመከላከል ካስፈለገ በእጁ ባሉት ግዙፍ የልማት ድርጅቶች ላይ ሊያተኩር ይገባል። አዲስ ሃብት በሽያጭ በማመንጨት ኢኮኖሚውን ለማስቀጠል ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።
የልማት ድርጅቶቹ ሽያጭ ሙሉና ከፊል ሽያጭ በልማታዊ መንግስት ማዕቀፍ ውስጥ በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚከናወን ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ ልማታዊ መንግስት ወደ ካፒታሊስት ስርዓት የሚያደርስ ድልድይ እንጂ፣ በራሱ ግብ አይደለም። በኒዮ ሊበራሊዝምና በልማታዊ መንግሥት መካከል ካፒታሊዝም ሥርዓትን በመገንባት ረገድ ልዩነት የለም።
በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት የካፒታሊዝምን ስርዓት ለመገንባት በምን መንገድ መጓዝ አለብን የሚለው ጉዳይ ነው። ይህም በልማታዊም ይሁን በኒዮ ሊበራሊዝም መንገድ የመጨረሻው ግብ ካፒታሊዝምን መገንባት እንደሆነ የሚያመላክት ነው።
በአገራችን እየተገነባ ያለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው ሁለት ፈርጆችን ያቀፈ ነው፤ ልማትንና ዴሞክራሲን። ልማቱም ይሁን ዴሞክራሲው አብዛኛውን ህዝብ ተጠቃሚ በማድረግ ላይ የሚመረኮዝ መስመር ነው። በዚህም ጥቂቶችን ሳይሆን ብዙሃኑን ተጠቃሚ የሚያደርግ የልማት አቅጣጫን ይከተላል።
በአገሩ ውስጥ የሚያከናውነውን ልማት እውን ለማድረግ፣ የግሉ ባለሃብት ልማታዊ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት በተመረጡ የልማት አውታሮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት ልማቱ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ይጥራል። በዚህም በልማቱ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ የሚያሳርፉ ትላልቅ የልማት አውታሮችን በማስተዳደር ባህሪው ይታወቃል።
እንደ እኛ ያለ በማደግ ላይ የሚገኝ ህዝብ በዋነኛነት ምጣኔ ሃብቱን አሳድጎ የነገ ሰውነቱን እውን ለማድረግ በዋነኛነት መጠቀም ያለበት የራሱን ገንዘብ፣ ዕውቀትና ጉልበት ነው። ኢኮኖሚውም ሙሉ ለሙሉ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ጥገኛ መሆን የለበትም።
በአመዛኙ አገር በቀል መሆን ይኖርበታል። እውነታውን የሀገራችን ኢኮኖሚ አሁን ባለበት ሁኔታ አኳያ ስናየው ምጣኔ ሃብታችን ታዲጊና ለጋ ሆኖ እናገኘዋለን። ምንም እንኳን የግሉ ባለሃብት ለኢኮኖሚያችን ማደግ ተገቢውን ሚና እየተወጣ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ያለው አቅም በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የታዳጊ አገር ባለሃብት በመሆኑም አቅሙ ወደፊት እያደገና እየጎለበተ የሚሄድ ነው። እናም ይህ ባለሃብት ባለፉት ዓመታት በግሉ ዘርፍ ማከናወን ያልቻላቸውን ጉዳዮች የገበያ ክፍተት እንዳይፈጠር ልማታዊው መንግስት በተመረጠ አኳኋን ጣልቃ ሲከውን ነበር። አሁን ግን ሃብት አንድ ቦታ በማይከማችበት ሁኔታ በልማት ሂደቱ ውስጥ የመንግስት አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ለግሉ ባለሃብት ማደግ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።
እንዲሁም መንግስት ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነውና የኢኮኖሚያችን ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆነው አርሶ አደር በሚገኝበት ገጠር ወስጥ ትምህርት ቤቶችን፣ ክሊኒኮችን፣ መሰረተ-ልማቶችን…ወዘተ. ገንብቶ ለህዝቡ ሊሰጥ የሚችልበት አቅም የለውም። የገንዘብ እጥረት ስላለበትም የጀመራቸውንን ያቀዳቸውንየልማት አውታሮች መፈፀም አይችልም። እናም ታላላቅ የልማት ድርጅቶችን በከፊልም ይሁን ሙሉ ለሙሉ መሸጥ የግድ ይለዋል።
መንግስት በአገራችን ውስጥ ልማታዊ ተግባራት ለመከወን ገንዘብ ማግኘት አለበት። ስለሆነም የሀገሩን ታላላቅ ተቋማት በገንዘብ ምንጭነት በማሰብ የኢኮኖሚ ሪፎርም መከወን አለበት።
ስለሆነም እንደ ቴሌ፣ አየር መንገድ፣ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ የመሳሰሉ ተቋማትን ለባለ ሃብቱ ማስተላለፍ አለበት። ከእነርሱ የሚገኘው ገንዘብም አብዛኛውን የሀገሪቱን ህዝብ ወደ አዲስ የልማት ጎዳና እንዲያመራ ያስችለዋል
ልማታዊው መንግሰት በነደፋቸው ፖሊሲዎችና ስትትራቴጂዎች እየተመራ ላለፉት ዓመታት ህዝቡን በማሳተፍ ድህነትን ለመቀነስ ችሏል። ልማታዊ መንግስት ፈጣን ልማትን ያረጋገጠና ለወደፊቱም ይበልጥ ሊያረጋግጥ የሚችል የፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓት ቢሆንም ዋነኛው ግቡ ካፒታሊዝም ስርዓትን መገንባት ነው። ስርዓቱ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠርና በቀጣይም በተጠናከረ ሁኔታ ሊፈጥር የሚችል አቅጣጫን የሚከተል ነው።
ባለፉት ዓመታት መንግስት በቀየሰው ውጤታማ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በማህበራዊ ዘርፎች መስክ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት ተከናውነዋል። እነዚያ ውጤቶች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል። ይህ እንዲሆንም ጊዜያዊውን ችግር መፍታት ያስፈልጋል። ለዚህም አሁ በደረስንበት ደረጃ የልማት ድርጅቶቹን በመሸጥ ለካፒታሊዝም ስርዓት ግንባታው በር መክፈት ተገቢ ነው።
በአጠቃለይ በአሁኑ ወቅት መንግስት እየተከተለ ያለው የህዝብን ተጠቃሚ ያረጋገጠውንና ፈጣን ልማት ያመጣውን የልማታዊ መንግስት መርህን በፖሊሲነት ተከትሎ ነው። በዚህም የልማታዊ መንግስት መጨረሻ ግብ በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግስትን ሚና በማሳነስ በተቃራኒው የግል ባለሃብቱን ሚና አጎልብቶ የካፒታሊስት ወይም የሊበራል ኢኮኖሚ መገንባት ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ነው። ታዲያ አሁን በምንገኝበት የኢኮኖሚ አቅም እንዲሁም ያለንበት ወቅታዊ ሁኔታ መንግስት በኢኮኖሚው በኩል ተገቢ ነው ያለውን የኢኮኖሚ ሪፎርም እርምጃ መውሰዱ ተገቢ ነው።