Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰላም ባለቤትነት

0 349

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰላም ባለቤትነት

                                                              ታዬ ከበደ

በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቃቅንንና አልፎ አልፎም ከበድ ያሉ የሚመስሉ የፀጥታ ችግሮች ሲከሰቱ ይስተዋላል። ወደፊትም ሊከሰቱ ይችላሉ። ምክንያቱም ማህበረሰብ እስካለ ድረስ አነስተኛ ግጭቶች መኖራቸው ስለማይቀር ነው። ሆኖም ችግሮቹ ከመደበኛው የፀጥታ መዋቅርና በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ አይችሉም።

በአሁኑ ወቅት የአገራችን አጠቃላይ ሁኔታ ሰለማዊ አውድን የተጎናፀፈ ነው። እዚህና እዚያ የሚታዩ ጥቃቅን ችግሮች አጠቃላዩን ሁኔታ የሚወክሉ አይደሉም። እስካሁን ድረስ የአገራችንን ሰላም በባለቤትነት ስሜት የሚጠብቀው ህብረተሰቡ በመሆኑ፣ ዛሬም ይሁን ነገ የፀጥታ ችግሮች በሚስተዋሉባቸው ጥቂት አካባቢዎች የሰላም ባለቤትነቱን ህዝቡ እንደ ወትሮው ማጠናከር ይኖርበታል።

እርግጥ ችግር ለምን ኖረ ብሎ መጠየቅ አይቻልም። ምክንያቱም በየትኛውም ማህበረሰብ መስተጋብራዊ ግንኙነት ውስጥ  ግጭት መፈጠሩ ስለማይቀር ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ እንዴት አድርገን ልንፈታቸው እንችላለን የሚለው ነው፡፡

ግጭት ሁሉ መጥፎ አይደለም፡፡ ግጭት ለውጥን መሰረት ባደረገ አስተሳሰብ ከተቃኘ፣ ግጭት የለውጥ መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት መቻቻልን ያመጣና በሂደትም በመጎልበት ላይ ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም የስርዓቱ አወቃቀር ብዝሃነትን እንደ ውበት አድርጎ የሚነሳ በመሆኑ ነው፡፡

ስርዓቱ አንድነትን በማጠናከር የመቻቻል መንፈስ እንዲዳብር ተደርጎ በህዝቦች የተዋቀረ ነው፡፡ ሆኖም ፌዴራሊዝም ከግጭት የጸዳ ነው ማለት አይደለም፡፡ ግጭቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ዋናው ጉዳይ በሰከነ ሁኔታ መፍታቱ ላይ ነው፡፡

ያም ሆኖ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች መነሻውን ድንበር በማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት አሉ። እነዚህ ተግባራት መነሻቸው ህዝብ አይደለም። ህዝብ ለሰላም እንጂ ለግጭት ቦታ ሊኖረው አይችልም። ይሁንና አሁንም ቢሆን ለግጭት የሚሆን ምህዳርን በተቻለ መጠን ማጥበብ ይገባል።

እንደሚታወቀው የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ከመልካም አስተዳደር ችግር፣ ከሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዘ ህዝቡን በማወያየት ዕርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሱ ነው።

በክልሎች በተካሄዱ ሰፋፊ የውይይት መድረኮች ከህዝቡ በተገኘው ግብዓት መሠረት ጥፋት በፈፀሙ አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰድም ተጀምሯል፤ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል። በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል የታየው ሁኔታ አስተማሪ ነው።

እርምጃውን በጥልቀትና በስፋት በማስቀጠል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት መሥራት የግድ ነው። የህልውና ጉዳይም ነው። ምክንያቱም ችግሩ በቅርቡ በተወሰኑ የሃገራችን አካባቢዎች ለሰላም እና መረጋጋት መጥፋት መንስኤ ሆኖ ተስተውሏልና። ሰላም ደግሞ የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።

እርግጥ ከማናቸውም ችግሮች በስተጀርባ ግጭቶችን ተገን አድርገው የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳከት የሚጥሩና ሊያባሉን የተነሱ ኃይሎች መኖራቸው የግድ ነው። እነዚህ የተጀመረውን የሠላም፣ የመልካም አስተዳደርና የህዳሴ ጉዞ ለመቀልበስ በመሯሯጥ ላይ የሚገኙ ኃይሎች ናቸው።

እነዚህ የእነ ዶክተር አብይ የለውጥ መንገድም የተመቻቸው አይደሉም። እነዚህ ሃይሎች የሚሰሩት በውስጥም በውጭም ነው። በተለያዩ የስልጣን እርከኖች ውስጥም ሊኖሩ ይችላሉ።

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሰላማችንን ለማድፍረስ፣ የዕድገት ግስጋሴያችንን ለማደናቀፍ ደፋ ቀና እያሉም ነው። ህዝቡ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።  

ይሁን እንጂ አሁንም ምክንያቶችን መድፈን ይገባል። ለግጭት ሃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳርን ማሳጣት ወሳኝ ነው። ይህን ለመከወን የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ኃይሎችን በቁርጠኝነት መታገል ያስፈልጋል። ከውጭ ያሉትንም እኩይ ዓላማቸውን መታገል ይገባል።

በተለይ ወጣቱ ጥቅማቸው የተነካባቸውን እነዚህን ሃይሎች በግልፅ መታገል አለበት። ወጣቱ ግጭት አራጋቢዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት በፈጠሩት እኩይ ሴራ አንድም ስንዝር መራመድ ያቃታቸው መሆናቸውን ሊገነዘብ ይገባል።

በዘመናት የትስስር ድር የተጋመዱት ህዝቦችን የአእምሮ ዕድገትና የፈጠራ ክህሎት እንዳይዳብር፣ ተወዳዳሪነታቸው እንዲደናቀፍና ድህነትና ኋላቀርነት በክልሉ ስር ሰዶ እንዲቆይ ያላቸውን ክፉ ምኞት ለመተግበር ጥረት እያደረጉም እንደሆነ ማወቅ አለበት።

የኢትዮጵያ ህዝቦች በተፈጥሮ በተቸራቸው ቋንቋ የመጠቀም መብታቸው ለዘመናት ተነፍጎ ከኖረበት ሁኔታ ራሳቸውን በማላቀቅ ዛሬ ላይ ቋንቋቸው የሳይንስ፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የእድገት ምንጭ በመሆን ከፍተኛ ለውጥ አስመዝግበዋል። ዛሬ ደግሞ በአዲስ የለውጥ መንገድ ላይ ናቸው።

የህዝቦች አዲስ ኢትዮጵያዊ መንፈስና አንድነት የሚያሳበዳቸው እነዚህ ግጭት አራጋቢዎች አዲስ የፍቅር መንገድ ሲያዩ የጥፋትና የብተና አቋሞቻቸው ከመቃብር በታች ይውሉብናል በሚል ስጋት የሞት ሽረት ትግል ሊያደርጉ ይችላሉ።

በመሆኑም ሁሉም ህዝቦች የእነዚህን እኩይ ሃይሎች ትክክለኛ ፍላጎት በመገንዘብ ተግባራቸውን ዛሬም እንደ ትናንቱ ሊያመክኑት ይገባል።

የሰሞኑ ግጭት አራጋቢዎች የህዝቡ ፍላጎት ያልሆነን አጀንዳ በመምዘዝ በደቡብ ክልል ውስጥ የ15 ሰዎች ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም አድርገዋል። ተገቢ የሆኑ የህዝቦችን ጥያቄዎች ከመጠን በላይ በማጎንና ለግጭት መንስኤ እንዲሆን በማድረግ እንዲሁም የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎችን በማጦዝ እኩይ ሴራቸውን ፈፅመዋል። እጅግ አሳዛኝ ተግባር ነው። ሆኖም መንግስት በዚህ ተግባር ላይ የተሳተፉ ሃይሎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ወስኗል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳም በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የታየው ግጭት በመደበኛው የህግ ማዕቀፍ ሊስተካከል የሚችል ነው። ይሁን እንጂ በውጭም ይሁን በውስጥ የሚገኙ ግጭት አቀጣጣዩች በድንበርና በሌሎች ግጭትን ሊያባብሱ በሚችሉ ጉዳዩች ዙሪያ የሚያራምዱትን አቋም ህብረተሰቡ ሊያወግዝና በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን በማቅረብ ምላሽ የማግኘት ባህልን ማዳበር ይኖርበታል። ይህም እንደ ወትሮው በተጠናከረ ሁኔታ የሰላሙ ባለቤት እንዲሆን ያደርገዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy