Artcles

የተቀደደው መጋረጃ

By Admin

June 29, 2018

የተቀደደው መጋረጃ

                                                                ዋሪ አባፊጣ

መጋረጃ። ጥቁር። የፅላሎት ምልክት። የድቅድቅ ጨለማ ተምሳሌት። ለ20 ዓመታት የዘለቀ። በሁለቱ ሀገራት መካከል “ሞት አልባ ጦርነት”ን ክስተት ያሰመረ። ፉክክርንና ብሽሽቅን በማንገስ የሀገራቱን ህዝቦች ያለ ተጠቃሚነት ሲያስጉዝ የነበረ። አሁን ግን ፅልመቱ እየሻረ ነው። የጥቁር ደመናው ጨለማ ጉም እየገፈፈ ነው። የብርሃን ውጋጋን ሊፈነጥቅ በሩ ተከፍቷል—መጋረጃው ተቀዶ።

አሁን ለሰላም የተዘረጉ እጆች አምሳያቸውን አግኝተዋል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶከተር አብይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ላይ፤ ‘ከኤርትራዊያን ወንድሞቻችን ጋር የእውነት ሰላም ለመፍጠር ከልብ እንፈልጋለን’ በማለት  ላቀረቡት የሰላም ጥሪ፤ የኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ አሳይያስ አፈወርቂ ከሁለት ሳምንት በኋላ ምላሽ መስጠታቸው ይታወቃል።

ፕሬዚዳንቱ በሀገረ ኤርትራ በየዓመቱ በሚከበረው የአርበኞች ቀን ላይ፤ በድንበር ጉዳይ ላይ የሚነጋገርና ገንቢ ውይይት የሚያደርግ የሀገራቸውን ልዑክ ወደ አዲስ አበባ እንደሚልኩ በመግለፅ ለሰላም ጥሪው ምላሽ ሰጥተዋል። ይህም ጎረቤት ኤርትራ ለሰላም ያላትን ፍላጎት የሚያሳይ ከመሆኑ ባሻገር፤ ፍቅርና በጋራ ተተያይዞ ማደግን እንደምትፈልግ ማረጋገጫ የሰጠ ምላሽ ተደርጎ የሚቆጠር ይመስለኛል።

የፕሬዚዳንት ኢሳይያስን ምላሽ ተከትሎ ኤርትራ ከመሰንበቻው ልዑካን ቡድኗን ወደ አዲስ አበባ ልካለች። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ የተመራው የኤርትራ ልዑክ የፕሬዘዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አማካሪና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የማነ ገብረአብን እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት የኤርትራ አምባሳደር የሆኑትን አቶ ዓርኣያ ደስታን ያየዘ ነው። ልዑኩን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንዲሁም አትሌቶችና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች ተቀብለውታል።

በኢትዮጵያ መንግስትና በኤርትራ ልዑካን መካከል የተካሄደው ውይይት የሰላምና የፍቅር ድባብ የሰፈነበት ነበር። ዶክተር አብይ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ጥቁር መጋረጃ መቀደዱን በወቅቱ ይፋ አድርገዋል። ይህ ጥቁር መጋረጃ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች በአንድነት ተያይዞ የማደግ ህልምን ያመከነ፣ ወንድማማች ህዝቦችን የነጣጠለና ዳግም እንዳይተያዩ ያደረገ እንዲሁም በቀጣናው ውስጥ የሚፈለገው ሰላም እንዳይመጣ ምክንያት የሆነ ነው።

እናም መቀደድ ብቻ ሳይሆን ሊሸረከትም ይገባዋል። የጥቁር መጋረጃው ፅልመት፤ በደም፣ በባህል፣ በወግና በታሪክ እንዲሁም በአንድ ሀገርነት እንኖር የነበርነውን ህዝቦች ለያይቶናል። በዘለቄታዊ ጥቅማችን ላይ ምንም ዓይነት ረብ በሌለው እንካ ሰላንቲያ ውስጥ እንድንጓዝ አድርጎናል።

የጨለማው ተምሳሌት ጥቁሩ መጋረጃ፤ ውጥረት ውስጥ ሆንን አንዳችን በሌላችን ላይ ጣታችንን እንድንቀስር ምክንያት ሆኗል። ሁለታችንንም ጥላቻንና ቂም በቀልን እንደ ፀጋ ይዘን በውጥረት ውስጥ ማለፍ ግድ እንዲለን ከማድረግ ባሻገር፤ ለብዙ ልማታዊ ጥቅም ልናውለው የምንችለውን ሃብትና የሰው ሃይል ያለ ያለ ስፍራውና ያለ ቦታው እንድናውለው ያደረገን ነው።

ይህ ሁኔታም ከሰላም፣ ከፍቅርና ከመደመር የምናገኘውም ሁለንተናዊ ጥቅማችን በዜሮ እንዲባዛ ያደረገ ነው። እናም የፀብና የቁርሾ ፅላሎት መጋረጃው መቀደዱ ለሁለቱም ሀገራት አዲስ የሰላም ብርሃን እንዲፈነጥቅ የሚያደርግ ነው ማለት ይቻላል። ለዚህም ይመስለኛል—ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በደስታ ውስጥ ሆነው የጨለማው መጋረጃ መቀደዱን ያበሰሩት።

ርግጥ ጥላቻና ብሽሽቅ አሁን በምንገኝበት የስልጣኔ ዘመንም ይሁን ዕድሜ አዋጭ አይደለም። ለሁለቱም ሀገራት አይጠቅምም። ዓለም ዘምኖ አንድ በሆነበት በዚህ የሉላዊነት (Globalization) ዘመን መደመር እንጂ፣ መነጠል ቦታ የለውም። ሰላምና ፍቅር እንጂ፣ ሁከትና ጥላቻ ፋይዳ ቢስ ናቸው።

እስካሁንም በሰላምና በፍቅር ተደምረን ቢሆን ኖሮ የትየለሌ በደረስን ነበር—“ከአንድ ብርቱ፣ ሁለት መድሃኒቱ” እንደሚባለው። ያም ሆኖ አሁንም አልረፈደም። በጋራ ተጠቃሚነት እሳቤ ተባብሮ የመስራት ፍላጎቱ እስካለ ድረስ ተያይዞ ማደግና የሀገራቱን ህዝቦችን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል። ዋናው ነገር ለትክክለኛ ሰላም፣ ፍቅርና ለህዝቦች አንድነትና ልማታዊ ተጠቃሚነት አብሮ መስራቱ ነው።

የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ ኤርትራን በመወከል ከ20 ዓመት መለያየት በኋላ አዲስ አበባ የተገኘው ልዑክም፤ ስለ ሰላምና ስለ ፍቅር እንዲሁም ባለፉት ዓመታት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ስላጡት ጥቅም በቁጭት ሲናገሩ አድምጫለሁ። ሌላው ቀርቶ ልዑኩ ለሰላም የተዘረጉትን እጆች ለመጨበጥ ባህር አቋርጦ አዲስ አበባ መምጣቱ፤ ኤርትራ ለሰላም ያላትን ቁርጠኛ አቋም የሚያመላክት ይመስለኛል።

አስመራ ለሰላም ያላት ጠንካራ ፍላጎት የተራራቁ ህዝቦችን ይበልጥ የሚያቀራርብና ሊገኝ ከሚችለው የጋራ ተጠቃሚነት በአዲስ መንገድ እንዲተሳሰሩ የሚያደርግ ነው። አንዱ ከሌላው ልምድ እየቀሰመም ልማትን እንዲያጎለብት ዕድልና ምቹ ሁኔታ ይከፍታል። እናም ይህ የተከፈተው የሰላም በር የዕድገት ማስተሳሰሪያ ሊሆን የሚችል ነው።

ይህን ፅሑፍ ሳሰናዳ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የተመራው የኤርትራ ልዑክ፤ ሀዋሳ ከተማ በመገኘት የኢንዱስትሪ ፓርክን እየጎበኘ መሆኑን ነግረውኛል። የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት በኢንቨስትመንት መስክ ያለውን ልምድ ለመቅሰም ያለመ መሆኑም ተገልጿል። የሀዋሳው ኢንዱስትሪ ፓርክ በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ እንደሆነና እስካሁንም ለ18 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩ በጉብኝቱ ወቅት ተብራርቷል።

በጉብኝቱ ወቅት ኢትዮጵያም የኢንዱስትሪ ፓርኩን ውጤቶች ወደ አስመራ በመላክ ኤርትራን የምርቶቿ መዳረሻ ለማድረግ ሃሳብ እንዳላትም ተመልክቷል። ይህም ሁለቱ ሀገራት ሰላማቸው ደርቶ በንግድም ጭምር ተሳስረው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ይመስለኛል።

ርግጥ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም ወደፊት ያቀና ዘንድ ዕቅድ ተያዟል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በቅርቡ ፊት ለፊት ተገናኝተው ይወያያሉ። አዲስ አበባ ላይ ከኤርትራ መንግስት ከፍተኛ ልዑክ ቡድን ጋር የተደረገው ውይይት፤ እንዲመጣ ለሚፈለገው ሰላም ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው። የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም አካሄድ ትልቅ ተስፋን የፈነጠቀና ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋትም የራሱን ድርሻ ሊያበረክት እንደሚችል ከወዲሁ መግለፅ ይቻላል።

ይህ የተስፋ ብርሃን ፍንጣቂ ሙሉ ደማቅ ብርሃን እንዲሆን የተያዘው የመግባባት መንፈስ ጎልብቶ ወደ አንድ ተጨባጭ እመርታ መዝለቅ ይኖርበታል። አሁን ባለው የሁለቱ ሀገራት ሁኔታ ይህ መሆኑ አይቀሬ ይመስለኛል። ምክንያቱም ሀገራቱ እየተጓዙበት ያለው የሰላም ጎዳና፤ ለ20 ዓመታት ዘልቆ የቀየውን ያለመግባባት መንፈስ የሚያስወግድና የተጋረደውን የፅልመት መጋረጃ ደጋግሞ መቅደድ የሚችል አቅም ያለው ነው ብዬ ስለማምን ነው። እናም መጪው ጊዜ ለሁለቱም ሀገራት ህዝቦች የሰላምና የፍቅር ይሆን ዘንድ፤ ኤርትራዊ ወንድሞቹን እንደናፈቀ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ምኞቴ ከልብ ነው።