Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የታራሚዎቹ መለቀቅና አንድምታው

0 365

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የታራሚዎቹ መለቀቅና አንድምታው

                                                         ሶሪ ገመዳ

መንግስት በቅርቡ በአገራችን በህግ ጥላ ስር የነበሩ ዜጎች በምህረት፣ በይቅርታና ክስ በማቋረጥ ለቋል። ይህ የሆነውም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እንደሆነ አስታውቋል። የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ፤ የይቅርታና ክስ የማቋረጥ ሂደቱ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም መንግስት ህብረተሰቡ በተለያዩ ጊዜያት በፍትህ ዘርፍ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አካል ነውም ብለዋል።

እስካሁን ድረስ መንግስት በሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ የ27 ግለሰቦችና አራት ድርጅቶች ክስ እንዲቋረጥ፤ 576 ታራሚዎችም በይቅርታ እንዲለቀቁ እንዲሁም በሽብር ወንጀል የተከሰሱ 137 ተጠርጣሪዎች ክስ እንዲቋረጥ አድርጓል። እርግጥ ይህ የይቅርታና ክስ የማቋረጥ ሂደት ዋና ዓላማ የህብረተሰቡን ጥቅም ማስጠበቅ ነው።

የተቋረጡት ክሶችም ሀገራዊ መግባባትን፣ ሳላምና ደህንነትን የሚያመጣ እንዲሁም ህብረተሰቡ ከፍትህ ስርዓት ጋር ተያይዞ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በመመለስ ረገድ ሚናው የላቀ ነው። ሂደቱም የህግ መሰረት ያለውና መስፈርቱም የህዝብ ጥቅም መሆኑ ግልፅ ነው።

የተጠርጣሪዎችን ክስ ማቋረጥና ታራሚዎችን በይቅርታ መልቀቅ በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርዓት ውስጥ አዲስ ነር አይደለም። ከበፊት ጀምሮ የነበረና ሲሰራበት የመጣ አሰራር ነው። ይሁን እንጂ የአሁኑን ለየት የሚያደርገው በጥልቅ ተሃድሶው ወቅት ሰዎች አላግባብ ይታሰሩ እንደነበርና የፍትህ መጓደልም በስፋት ይታይ እንደነበር ህብረተሰቡ ሲያነሳ ለነበረው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ነው።

ከሁሉም በላይ የእስረኞቹ መለቀቅ የኢህአዴግ ስራ አስፈሚ ኮሚቴ በእስር ላይ ያሉ ሰዎችን መልቀቅ የገባውን ቃል ለመፈጸምምና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትም የተወሰደ እርምጃ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ። የክስ መቋረጡ ዋና ዓላማ የተፋጠነ ፍትህ ባልተሰጠበት አግባብ እነዚህን ሰዎች በማረሚያ ቤት አስቀምጦ እነርሱንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ማንገላታት የህግ የበላይነትን የማያረጋግጥ ስለሆነ ነው። እናም እዚህ ላይ ተርፍና ኪሳራን መመዘን ያስፈልጋል። መንግስትም ያደረገው ይህንኑ ነው።

እርግጥ በህብረተሰቡ ውስጥ ‘በሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት ግለሰቦችና ድርጅቶች ክስ መቋረጥ መንግስት በፀረ ሙስና ትግሉ ላይ ያለው አቋም ተለሳልሷል’ የሚል ብዥታ ተፈጥሯል። አንዳንድ ወገኖችም ይህን ብዥታ ለማጎን ጥረት እያደረጉ ነው። ብዥታው ግን ትክክል አይደለም።

መንግስት መቼም ቢሆን የፀረ ሙስና ትግሉን በተደራጀና በተቀናጀ እንዲሁም በመረጃና ማስረጃ ላይ ተመስርቶ የተፋጠነ ፍትህ ሊያሰጥ በሚችል መልኩ ከማካሄድ አይቦዝንም። በሙስና ላይ ያለው አቋም የማይናወጥ ነው። ለዚህም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሙስናን ተግባር በቀይ መስመርነት አስምረው በቁርጠኝነት ወደ ስራ መግባታቸውን በእማኝነት መግለፅ ይቻላል።

እርግጥ ሙስና የአስተሳሰብ ጉዳይና በአቅራቢያችን የምናውቀው በመሆኑ ሁሉም አስተሳሰቡንና ተግባሩን መፀየፍ ብሎም መታገል ይኖርበታል። ተግባሩን መኮነንና መታገል የመንግስት ተግባር ብቻ መሆን የለበትም። ህዝቡም በነቂስ ችግሩን ፊት ለፊት በመጋፈጥ የመፍትሔው አካል መሆን ይኖርበታል።

በሙስና ተግባር ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን፣ ሰጪዎችንም፣ ተቀባዮችንም፣ አገናኞችንም በቁጥጥር ስር ማዋልና ለህግ ማቅረብ የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባራት ወይም የአሰራር ችግሮችን ከመፍታት አንፃር እንደ አንድ የማስተካከያ እርምጃ ብቻ የሚታይ ነው።

ዋናው ጉዳይ ህብረተሰቡ በፀረ ሙስና ትግሉ ላይ ለመሳተፍ ያለው ቁርጠኝነት ነው። ከዚህ አኳያ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ስንመለከት ቀደም ባሉት ጊዜያትም ይሁን በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ባለው የፀረ-ሙስና ትግል ህብረተሰቡ የላቀ አስተዋፅኦ እንደነበረው ለመገንዘብ አይከብድም።

መንግስት ለፀረ ሙስና ትግሉ አዲስ አይደለም። የኢፌዴሪ መንግስት ያለፉት ተግባሮች እንደሚያስረዱት ይዞት የመጣው የግምገማ ባህል ለፀረ ሙስና ትግሉ የበኩሉን ድርሻ አበርክቷል። እያበረከተም ነው። በአሁኑ ሰዓትም እየተካሄደ ባለው የፀረ ሙስና ትግል ይህንኑ የግምገማ ባህል በመጠቀም አጥፊዎችን ወደ ህግ ፊት ያቀርባል። ይሀን እንጂ በዚህ አሰራሩ ውስጥ ህብረተሰቡ ግልፅ ጥቆማ በመስጠት ጉልህ ሚና ሊጫወት ይገባል።

እንደሚታወቀው የሙስና ተግባር በባህሪው ውስብስብ በመሆኑ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት ተችሏል ማለት አይችልም። ሰዎችን ያለ መረጃና ማስረጃ በማሰር ፍትህን የማዛባት ተግባሮች እንደነበሩ መንግስት ገልጿል።

ታዲያ ይህን ችግር በመቅረፍ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ በማስፈለጉ እስረኞችን ለቅቋል። ይህም መንግስት በሙስና ላይ የተለሳለሰ አቋም ያለው መሆኑን የሚያሳይ ሳይሆን ጉዳዩን ከህግ የበላይነትንና የዜጎችን ጥያቄ ከመመለስ ጋር የተያያዘ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ መንግስት አሁን እየወሰዳቸው ያሉ ርምጃዎች ለዓመታት እየተንከባለሉ የመጡትን ችግሮች በአፋጣኝ በመፍታት በቀጣይ ትኩረቱን በልማት እና ብሄራዊ መግባባት መፍጠር ላይ እንዲያተኩር የሚያግዙ ናቸው። በመሆኑም እምጃዎቹ አስፈላጊ መሆናቸውን በመገንዘብ ለብሄራዊ መግባባትና ለሀገር ግንባታ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከመንግስት ጎን መቆም አለበት።

እስረኞችን በይቅርታ፣ በምህረትና ክስ በማቋረጥ መልቀቅ ፍትህን የሚያፋጥን ተግባር ይመስለኛል። የህግ የበላይነትንም ያረጋግጣል። በአንድ ዴሞክራሲያዊ አገር ውስጥ የህግ የበላይነት ልዕልና ካልተጠበቀ የህዝብን ጥያቄ በተገቢው መንገድ መመለስ አይቻልም። የህግ የበላይነት በቸልታ ከታለፈ የዜጎች መብቶች ሊሸራረፉ ይችላሉ።

የመብት መሸራረፎች ደግሞ አንዱ እንዳሻው እንዲፈነጭ ሲያደርገው ለሌላውን ያለ አንዳች መረጃና ማስረጃ በእስር ቤት ውስጥ እንዲማቅቅ ሊያደርገው ይችላል። ይህም ህግና ስርዓትን አክብሮ ለሚንቀሳቀስ ዜጋ አሉታዊ ትምህርት የሚሰጥ ነው። ወደ ተሳሳተ መንገድ እንዲያመራ ሊያደርገው ይችላል።

ስለሆነም የዴሞክራሲ አንድ ዘውግ የሆነው የህግ የበላይነት በተገቢው ሁኔታ መረጋገጥ አለበት። የህግ የበላይነት ካልተረጋገጠ ዴሞክራሲው እውን ሊሆን አይችልም። ዴሞክራሲ እውን ካልሆነ ሁሉም በእኩልነት የሚንቀሳቀስበትን የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት አይቻልም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy