Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የደባ ፖለቲከኞች

0 237

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የደባ ፖለቲከኞች

                                                               ይሁን ታፈረ

ኢትዮጵያ በሰላም ደሴትነት ስትጠቀስ የኖረች አገር ናት። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት ሰላምን ሲያደፈርሱ ይስተዋላሉ። የእነዚህ አካላት ተግባር በምንም መስፈርት ህብረተሰቡን የሚወክል አይደለም። በመሆኑም ህብረተሰቡ በየአካባቢው ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ተቀራቦ በመስራት ሰላሙን መጠበቅ እንዲሁም ጥቅማቸው የተነካ አካላት የሚያደርጓቸውን የደባ የፖለቲካ አካሄድ መቃወም ይኖርበታል።

በየትኛውም አገር ውስጥ በሁከትና ነውጥ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙ እአይችሉም። ህብረተሰቡም ቢሆን አለኝ የሚላቸውን ጥያቄዎች ለተገቢው አካል በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ማቅረብ ይኖርበታል። ምንም እንኳን አለመግባባቶች መቼምና የትም ሊፈጠሩ የሚችሉ ቢሆኑም፣ ህብረተሰቡ ግጭቶችን መፍታት የሚያስችል የዳበረ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴት ያለው ነው። ስለሆነም አለመግባባቶችን ስር ሳይሰዱ በወቅቱ የመቅረፍ አካሄድን መከተል ይኖርበታል።

በተለይ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ወላጅ አባቶችና እናቶች እንዲሁም አጠቃላይ ማህበረተሰቡ ወጣቶችን በመምከርና በመገሰጽ ከብጥብጥ ምንም ዓይነት ትርፍ እንማይገኝ ማስተማር አለባቸው። በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ የቆዩ የመቻቻል እሴቶችን ተተኪው ትውልድ እንዲቀስማቸው ለማድረግ ሁሉም ሃላፊነቱን በተገቢው መንገድ ከተወጣ የደባ ፖለቲከኞችን መመከት የማይቻልበት ምክንያት የለም።

እንደሚታወቀው ሁሉ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች መነሻውን ድንበር በማድረግ የሚከናወኑ የግጭት ተግባራት አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንዳሉት ግን በክልሎች መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰን እንጂ ድንበር አይደለም። ይሁን እንጂ እነዚህ ግጭቶች መነሻቸው ህዝብ አይደለም። ህዝብ ለሰላም እንጂ ለግጭት ቦታ ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም ለግጭት የሚሆን ምህዳርን ለማጥበብ የደባ ፖለቲከኞችን መታገል  ይገባል።

እርግጥ የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ከመልካም አስተዳደር ችግር፣ ከሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዘ ህዝቡን በማወያየት እርምጃ እየወሰዱ ነው። ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ አመራሮችም ሃላፊነታቸውን እንዲለቁ እያደረጉ ነው።

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት መስራት የግድ ነው። የህልውና ጉዳይም ነው። ምክንያቱም ችግሩ በቅርቡ በተወሰኑ የሃገራችን አካባቢዎች ለሰላም እና መረጋጋት መጥፋት መንስኤ ሆኖ ስለተስተዋለ ነው። ሰላም ደግሞ የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑ ይታወቃል። መንግስትም ይህን ተገንዝቦ ሰላምን ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሰራ ነው።

መንግስት ችግሮቹን ለሚፈታበት መንገድ ተባባሪ መሆን ሲገባ አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ ግጭት ለመግባት የሚደረገው ጥረት ህዝቡን የማይወክል በመሆኑ በምንም ዓይነት ስሌት ተቀባይነት አይኖረውም።

እርግጥ ከማናቸውም ችግሮች በስተጀርባ ግጭቶችን ተገን አድርገው የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳከት የሚጥሩ የደባ ፖለቲከኞች መኖራቸው ግልጽ ነው። እነዚህ ጥቅማቸው የተነካባቸው የደባ ፖለቲከኞች፤ የሠላም፣ የመልካም አስተዳደርና የህዳሴ ጉዞ ለመቀልበስ በመሯሯጥ ላይ የሚገኙ ናቸው። በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሰላማችንን ለማድፍረስ፣ የዕድገት ግስጋሴያችንን ለማደናቀፍ ደፋ ቀና የሚሉ ሊያባሉን የተነሱ ሃይሎች ናቸው።  

ሃይሎቹ የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ሊሆኑ ይችላሉ።

ህብረተሰቡ እነዚህን በልተው የሚያባሉ ሃይሎች በማገዝ ብቻ መመለስ የለበትም። አምርሮ ሊታገላቸው የግድ ይላል። የደባ ፖለቲከኞች እንዲህ ተፈፀመብህ፣ ይህ ተከናወነብህ…እያሉ ህዝቡ በግጭት ውስጥ ሲማስን እነርሱ በለመዱት መንገድ ተራ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሯሯጡ ናቸው። በህዝብ ስቃይ የራሳቸውን ምቺት ለማደላደል ያሰፈሰፉ የሌቦች ስብስቦች ናቸው።

በተለይም የሃይማኖት አባቶች እነዚህ ሃይሎች ከመገሰፅ ባለፈ ወጣቱን መምከር ይኖርባቸዋል። የሃይማኖት አባቶች ምዕመኖቻቸው የሚከተሉት ቅዱስ መፅሐፍ በሚፈቅደው መሰረት ስለ ሰላም፣ መቻቻልና አብሮ በጋራ ተካፍሎ ስለመብላት፣ ባለ ፀጋዎች ድሆችን ማገዝ ስላለባቸው ጉዳዩች ተከታዩቻቸውን ሊያስተምሩ ይችላሉ።

ምዕመናን ለሀገራቸው ሰላም መሆን የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ፣ በሀገራቸው ውስጥ ሰላም በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ እንዲስተጓጎል በር የሚከፍቱ ክስተቶችን እንዲቃወሙና የሰላም ዋጋን እንዲገነዘቡ ማድረግ ይችላሉ።

እንዲሁም እርስ በርስ ተከባበሮና ተሳስቦ የመኖርን ጠቀሜታ በማሳወቅ እንዲሁም ከጥላቻና ከቂም በቀል አስተሳሰብ ምንም ዓይነት ሰማያዊ ትርፍ እንደማይገኝ በየእምነታቸው ውስጥ በማስገንዘብ አባታዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ የሚችሉ ይመስለኛል።

የሃይማኖት አባቶች በምዕመኖቻቸውና በመንግስት መካከል ድልድይ ሆነው የሰላም ሃዋርያነታቸውን መወጣት አለባቸው። ለዚህም ይመስለኛል— ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በአንድ ወቅት አባቶች ስለ ሀገራቸው ሰላም መትጋት እንዳለባቸው የገለፁት።

የሃይማኖት አባቶች የሰላምና የእርቅ መገለጫ በመሆን ኃላፊነታቸውን በሚፈለገው መልኩ መወጣት እንደሚኖርባቸው ማስገንዘባቸውም፤ ሁሉም ሃይማኖቶች ስለ ሰላም እንጂ ስለ ሁከት የማይሰብኩ፣ በምዕመናቸውና በአገራቸው ሰላም ዙሪያ ፋና ወጊ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ማሳያ ይመስለኛል።

እርግጥ የሃይማኖት አባቶች በአካባቢያቸውና በሀገር አቀፍ ደረጃ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በማሰማት የህግ የበላይነት እንዲሰፍንና የሰው ልጆች መብት እንዲጠበቅ ያለ ፍርሃት የጥፋት ኃይሎችን መገሰጽ አለባቸው። ይህም የምዕመኖቻቸውን መብቶች በማስጠበቅ ከሁከት ርቀው ወደ ሰላም መስመር እንዲመለሱ በማገዝ የአገርን ጥቅም የሚያረጋግጥ ይሆናል። የደባ ፖለቲከኞችን የጥፋት ስብከትም ያስቀራል።

አባ ገዳዎች፣ ወላጅ ቤተሰቦችና የአገር ሽማግሌዎችም ወጣቶችን በመገሰጽ ከደባ ፖለቲከኞች ተንኮል ሊታደጓቸው ይገባል። የደባ ፖለቲከኞች ቀደም ሲል በተለያዩ ምክንያቶች ተጠቃሚ የነበሩና በአሁኑ ወቅት በህዝቡ የተጠናከረ ትግል ምክንያት ተጠቃሚነታቸው የቀረባቸው ሃይሎቸ ናቸው። ያንን ተጠቃሚነታቸውን ለማስመለስ የማይቆፍሩት የተንኮል ጉድጓድ የለም። መጠቀሚያ የሚያደርጓቸውም ወጣቶችን ነው። በመሆኑም ወጣቶች በእነዚህ ሃይሎች የተሳሳተ ተራ የፖለቲካ ንግድ ውስጥ እንዳይገቡ ማህበረሰቡ አዎንታዊ ሚናውን መጫወት ይኖርበታል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy