Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ይህ ሃሳብ ለምን?

0 275

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ይህ ሃሳብ ለምን?

                                                           ሶሪ ገመዳ

አንዳንድ ወገኖች እዚህ ሀገር ውስጥ እየተደረገ ያለው ውጤታማ የለውጥ ስር የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ፍላጎት ብቻ ይመስላቸዋል። ለውጡ ቀደም ሲል የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወሰነው መሰረት እየተከናወነ ያለ ነው።

የለውጡ መሃንዲስ ዶክተር አብይ ቢሆኑም ውሳኔው የድርጅታቸውና የመንግስታቸው ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሃሳብ ለምን ይነሳል? ብለን ብናጠይቅ፣ ጉዳዩ ውጤታማውን ዶክተርና ድርጅታቸውን ሆን ብሎ ለመነጣጠል መሆኑ ግልፅ ነው።

ይሁን እንጂ ፍላጎቱም ይሁን ተነሳሽነቱ የእርሳቸው ብቻ ሳይሆን የድርጅታቸውና የመንግስታቸው መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ አንድ መሪ የራሳቸው ብቃት ታክሎበት የሚያከናውኑት ነገር መኖሩ ግልፅ ነው።

ሆኖም ተግባራቸው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የሚከናወን መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት። እርሳቸው የሚያከናውኑት ስራ የግላቸውን ሳይሆን፣ የመንግሥት ሥራ ነው። በመንግስትና በመሪ ድርጅቱ አመራር መለወጥ ምክንያት እየመጣ ያለው ለውጥ በግልፅ የሚታይ ቢሆንም፤ ዞሮ…ዞሮ ግን ምንጩ አንድ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያደረገው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በርካታ አበረታች ውጤቶች የተገኙበት ቢሆንም፣ በሚፈለገው ደረጃ ጥልቀት ያልነበረው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተመልሰን ወደ አዘቅቱ የመመለስ ጉዳይ ሊኖር እንደሚችል ስጋቱን ገልፆ ነበር።

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩት ደም አፋሳሽ ግጭቶች በዋነኛነት የድርጅቱ አመራር ያሳየው ድክመት የፈጠራቸው መሆናቸውን በሚገባ በመገንዘቡም በግምገማው ማጠቃለያ ላይ ገዥ የሚሆን ውሳኔ አስተላለፏል። ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታትም ቃል ገብቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እያከናወኑ ያሉት ይህንን ተግባር ነው—ምንም እንኳን ችግሩን በመፍታት የእርሳቸው በተግባር በሚታይ ብቃት የተመራ ቢሆንም።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢህአዴግ በሀገሪቱ በመታየት ላይ የሚገኙት በዋነኛነት ከልማት፣ ከመልካም አስተዳደርና ከሰላም ጋር የተያያዙ ችግሮች የማያዳግምና መሠረታዊ የሆነ መፍትሔ ለመስጠት ቃል ገብቷል።

እስካሁን በተደረጉት ግምገማዎችም የችግሮቹን ዓይነተኛ ባህሪዎችና ዋነኛ መንስዔዎች አስመልክቶ ዝርዝር ውይይት አድርጎ በአመራሩ ዘንድ ከመቼውም ጊዜ በላቀ አኳኋን የአስተሳሰብ አንድነት መፍጠር መቻሉ ይታወሳል።

የአስተሳሰብ አንድነት ለተግባር አንድነት መሰረት በመሆኑም ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሰጡትን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደ ወትሮው በላቀ ደረጃ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል። ከዚህ ውሳኔ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በትክክለኛው የድርጅቱ ጎዳና ላይ በመራመድ የራሳቸውን ብቃት አክለውበት እየፈፀሙት ይገኛሉ።

ድርጅቱ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በፈጠረው ተስፋና የተከመሩ ፖለቲካዊ ችግሮች ፊቱ ላይ በደቀኑት ስጋት መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ገብታለች። የአንድን ችግር መንስኤ ማወቅ የችግሩን መፍትሔ ግማሽ ያህል የማወቅ ያህል ይቆጠራል እንደሚባለው፤ ድርጅቱ በችግሮቹ አስኳል ጉዳዩች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረሱ ለተፈጠረው ችግር ምላሽ ለመስጠት የሚያስቸለው ነው።  

ቀደም ሲል በድርጅቱ የተሰጠው ውሳኔ አገራችን የጀመረችውን ፈጣን ዕድገትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እስካሁን የመጣበትን ርቀት ለማሳካትም ሆነ ወደፊትም ለማስቀጠል በር የሚከፍት ነው።

በድርጅቱ አራት ብሔራዊ አባል ድርጅቶች ውስጥ የነበረውና ያለው አኩሪ በመተጋገል ላይ የተመሠረተ አንድነት ይህን ለማድረግ አስችሎታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንደ ግለሰብ ያላቸው ብቃት በድርጅቱ ውሳኔ ላይ ታክሎ በሁለት ወራት ውስጥ ሰላምን እውን ማድረግ ችሏል።

ዶክተር አብይ በድርጅቱ ውሳኔ መሰረት የተጓዙበት መንገድ አገሪቱን ከመስቀለኛ መንገድ የታደገ፣ በተቀመጠለት አቅጣጫ በመተግበር ላይ ያለና የህዳሴውን ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩና የድርጅታቸው ተግባር በመንግስት ስራ ላይ በተሰማሩት ሲቪል ሰርቫንቶች ዘንድ መነቃቃትን ከመፍጠር ባሻገር ለበለጠ ስራ እንዲነሳሱ ያደረጋቸው ነው። ህዝቡም ቢሆን ቀስ በቀስ ከማማረር ወጥቶ ችግሮች በሂደት ሊፈቱ እንደሚችሉ እንዲመለከት በር ከፍቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጥ እንደሚያመጡም እምነቱን አሳድሯል።

የዶክተሩ የተለያዩ ተግባሮች ፌዴራላዊ ስርዓት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ማናቸውንም ችግሮች የአመራር ብቃት ታክሎበት የመፍታት ብቃትና አቅም ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ኢህአደግ እያከናወነ በመጣው የአመራር መተካካት አሰራር መሠረት የተወሰኑ አመራሮች በዕድሜ መግፋት ምክንያት በጡረታ ተሰናብተዋል። ይህም ድርጅቱ ስራውን በአዲስ አመራሮችና አመለካከት ለማወከናወን ከማሰብ የመነጨ ነው።

በለውጥ ሂደት ላይ የሚገኝ ሀገርን ለመምራት በመጀመሪያ ድርጅቱ ራሱ መለወጥ ይኖርበታል። እናም ማናቸውንም ጉዳዩች በአዲስ አስተሳሰብ ለመምራት እያደረገ ያለው ጥረት የሚያስመሰግነው ነው።

ምንም እንኳን ችግሮች ባለፉት ዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ቢሆኑም በአንድ ጀንበር ሊወገዱ የሚችሉ አይደሉም። ሆኖም ችግሮቹ ገዥ እንዳይሆኑና የሚፈጥሩትን ተፅዕኖ እጅግ አነስተኛ እንዲሆን መስራት ይገባል። በእኔ እምነት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኢህአዴግን አቅጣጫ ተከትለው ከህዝቡ ጋር በመሆን እያከናወነኑት ያሉት ተግባር የሚያስመሰግናቸው ነው።

ያም ሆነ ይህ ዶክተር አብይ የድርጅቱንና የመንግስታቸውን አቋም ይዘው እየፈፀሙ ያሉት የለውጥ ተግባር ህዝባዊነትን መሰረት ያደረገ የድርጅታቸው ዕቅድ ነው። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ተግባራቸው የእርሳቸው ብቻ አይደለም—የድርጅቱና የመንግስታቸው ጭምር እንጂ። ስለሆነም ለውጡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍላጎት ብቻ ተደርጎ የሚወሰደው ሃሳብ የተሳሳተ በመሆኑ ሊታረም ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy