Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ደቡብ ሱዳን ያለ ኢትዮጵያ…”

0 305

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ደቡብ ሱዳን ያለ ኢትዮጵያ…”

ገናናው በቀለ

የዛሬ ሶስትና አራት ወራት በቀውስ ውስጥ የነበረችው አገራችን አሁን ላይ የምዕራቡን አለም ጭምር ቀልብ መያዝ ጀምራለች። የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግስታት አገሪቱን እየደረፉ ነው፤ አብረው ለመስራትም ቃል ገብተዋል። የደቡብ ሱዳን መንግስት ስለ አዲሲቷ ኢትዮጵያ መንግስት አስመልክቶ “ደቡብ ሱዳን ያለ ኢትዮጵያ አይሆንላትም” በማለት ጭምር አስተያየቱን ሰጥቷል።

 

ይህም በትንሽ ጊዜ ውስጥ የውጭ ገጽታችን በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል እያሳየ መምጣቱንና አገራችንም ገብታበት ከነበረው የችግር ማጥ ውስጥ መውጣት መጀመሯን ጠቋሚ ነው። ዛሬ አገራችን ባካሄደችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በታላላቅ ሀገሮች ዘንድ ተፈላጊነቷ እየጨመረ መጥቷል። ይህ የሆነውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና መንግስታቸው ያላቸው ተቀባይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለመጣ ነው።

 

ከዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ጋር ያለን ከ100 ዓመታት በላይ የዘለቀ ግንኙነትም የሞቀና በጠንካራ ወዳጅነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰሞኑን ‘ለግንቦት 20 የድል በዓል እንኳን አደረሳችሁ’ በማለት ካስተላለፈው መረጃ ለመረዳት አይከብድም።

የአሜሪካ መንግስት ከእኛ ጋር በሰላም፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድና መሰል ጉዳዩች እንዲሁም በሽብርተኝነት ዙሪያ አብሮ የመስራት ፍላጎት አለው። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ድጋፍ በመስጠት ከለውጥ አመራሩ ጋር አብሮ መስራት እንደሚፈልግም አስታውቋል። ይህም አዲሱ አመራር ያለውን የተቀባይነት ደረጃ የሚያሳይ ነው።

አገራችን ከእንግሊዝ ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነትም በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ ነው። ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጋር ያላት ስደተኞችን በመቀበልና በፀረ-ሽብርተኝነት እንዲሁም በንግድና በኢንቨስትመንት ጉዳዩች ዙሪያ አብራ እየሰራች ነው። ይህ ጥረትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብሪታንያ ከለውጥ አመራሩ ጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳላት አስታውቃለች።

አገራችን ከእንግሊዝ ጋር ለረጅም ጊዜያት የዘለቀ ጠንካራ፣ በመተማመንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ግንኙነትን መስርታለች። በሁለቱ ሀገራትና ህዝቦች መካከል ያለው ይህ ግንኙነት ዛሬም ድረስ ያለ አንዳች ሳንካ የቀጠለ ነው። አገሪቱ አሁን ደግሞ ለአዲሱ አመራር ማንኛውንም ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታለች። ይህም በፊት በነበረን ወዳጅነትን ይበልጥ የሚያጠብቅና በጋራ ለመስራት ተጨማሪ ዕድል የፈጠረ ነው። ይህ የሆነው እንዲሁ አይደለም። አዲሱ አመራር በውስጥም ይሁን በውጭ ያላውን ተቀባይነት ከግምት ውስጥ አስገብተው ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ የሰላም ጠባቂ ብቻ ሳትሆን፤ ከቀጣናውና ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር ጠንክራ በመስራት ላይ ትገኛለች። በልማትና በትብብር እንዲሁም በጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታዋ ለአገራቱ ወሳኝ ስለሆነች ነው። ይህ ሁኔታ ለለውጥ የተነሳ አመራር ሲታከልበት የግንኙነቱን ስፋት ከፍ የሚያደርገው ነው።

ከላይ ያነሳኋቸው እውነታዎች ሃያላኑ አገራት እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ታላላቅ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያላት ትስስሮች ጠንካራና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የሚያሳዩ ከመሆናቸውም በላይ፤ የሀገራችን ገፅታ እየተለወጠ መሄዱንና በዲፕሎማሲው ረገድም ተፈላጊ እየሆነች መምጣቷን የሚያረጋግጡ ይመስለኛል።    

ሃያላኑ አገራትና የዓለም የፋይናንስ ተቋማት ከእኛ ጋር ተቀራርበው ለመስራት የሚፈልጉት የስጋ ዘመዶቻቸው ስለሆንን አይደለም። አገራቱና ተቋማቱ እኛን የሚፈልጉንና አብረናቸው እንድንሰራ የሚሹት ያለ አንዳች ምክንያት አይደለም። ርግጥም እነርሱ ይህ ሀገርና ህዝብ በአዲሱ አመራር ባለ ተስፋ እንደሆኑ ተገንዝበው ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ውስጥ እየተከናወነ ያለው የልማት ስራ በቁርጠኛ አመራር ከታገዘ ሁሉንም ዜጎች በፍትሐዊነት ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል፣ ልማቱ ከተሳለጠም ከኢትዮጵያ ህዝቦች ባሻገር ለቀጣናውና ለአፍሪካ ህዝቦች እንደሚጠቅም ከሃያላኑ አገራት የተሰወረ አይደለም። በልማቱ ሳቢያ እነርሱም በንግድና በኢንቨስትመንት ተሳትፈው የጋራ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይገነዘባሉ። አሁን ባለው ሁኔታ የነገ ባለ ተስፋና ባለራዕይ ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋር ተቀራቦ መስራት የማይሻ አገርሊኖር አይችልም።

ሃያላኑ አገራት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካም ይሁን በአፍሪካ ስትራቴጂክ የፖለቲካ ማዕከል እንደሆነች ይረዳሉ። ከቀጣናው ሀገራት ጋር በዲፕሎማሲ መስክ ያላትን ቁርኝትና ተሰሚነትንም ይገነዘባሉ። ሀገራችን የጎረቤቶቿን ሰላም በማስከበርና ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ እንዳለችም ከእነርሱ የተሰወረ አይደለም።

ኢትዮጵያ የአፍሪካዊያን የፖለቲካ መናኽሪያ እና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ በህብረቱ ወሳኝ ጉዳዩች ውስጥ ያላት አዎንታዊ ሚና እና ተሰሚነት በጋራ ለመስራት ከሚፈልጉት አካላት የተሰወረ አይመስለኝም። ታዲያ ይህን መሰል ተቀባይነትና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካላት ኢትዮጵያ ጋር ሃያላኑ አገራት በጋራ ጥቅም ላይ የተመረኮዘ ተግባርን አብሮ ለማከናወን ብሎም አዲሱን አመራር ለመደገፍ ማሰባቸው ትክክለኛ ነው።

ኢትዮጵያ ገፅታዋን ለመገንባቷ እንዲሁም ተቀባይነቷን ለማጎልበቷ ዋነኛው ምክንያት አዲሱ አመራር ከቀውስ ለመውጣት የወሰዳቸውና እየወሰዳቸው ያሉት ትክክለኛ እርምጃዎች ናቸው። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘው አስተማማኝ ሰላም፣ የተመዘገበው ፈጣንና ተከታታይ ልማት እንዲሁም የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ ለማስፋት እየተደረገ ያለው ጥረትና በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገኘው ውጤት ለገፅታችንና ለተቀባይነታችን መጨመር ምክንያት ሆኗል።

አገራችን ስትከተለው የመጣችው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የትኛውንም አገር በጠላትነት የማይፈርጅና በሰላምና በጋራ ተጠቃሚነት አብሮ ማደግን መሰረት ማድረጉ ለገፅታችንና ለተቀባይነታችን መለወጥ ገፊ ምክንያት ነው።

እርግጥ ኢትዮጵያ በውጭ ፖሊሲዋ ላይ ከየትኛውም ሀገር ጋር የሚኖራትን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ እንዲመሰረት ማድረጓ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር የውስጥ ችግርን መፍታትና በዚያውም ልክ የውጭ ተቀባይነታችንን መለወጥ ይቻላል ብላ ማመኗ ለዛሬው ዓለም አቀፍ ተቀባይነታችን መሰረት የጣለ ነው።

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው አዲሱ የለውጥ መንገድ ሃያላኑም ይሁን የቀጣናው ጎረቤቶቻችን በእኛ ላይ እንዲተማመኑብንና በድጋፍ አብረውን እንዲሰሩን ያደረገ ነው። የአዲሲቷ አገር ደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር “ደቡብ ሱዳን ያለ ኢትዮጵያ አይሆንላትም” ማለታቸው አገራችን ያለችበትን ሁኔታ ከመገንዘብ፣ እስካሁን ድረስ ለአገሪቱ እያደረገች ያለውን አቋሟንና ሰላም ወዳድነቷን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው። በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግስታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለገፅታ ግንባታችንና ለተቀባይነታችን መለወጥ የመሪነት ሚናውን በመወጣታቸው ሊመሰገኑ ይገባል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy