Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ግንባር ቀደሞቹ…

0 457

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ግንባር ቀደሞቹ…

ገናናው በቀለ

በአሁኑ ሰዓት የአገራችን ወጣቶች በስፖርት ማዘውተሪያዎች ያልተገባ ስነ ምግባር ለኢትዮጵያ ስፖርትም ይሁን ለሚደግፉት ቡድን ምንም ዓይነት ጠቀሜታ የለውም። ስፖርት ለሰላም፣ ለወዳጅነትና ለአንድነት የሚለውን መርህንም የጠሰ ስርዓት አልበኝነት ይመስለኛል። ይህ ክስተት ማንንም ስለማይጠቅም መቆም ይኖርበታል።

በስፖርት ምክንያት የሚፈጠር ስርዓት አልበኝነት ምክንያተቱ ምንም ይሁን ምን ተግባሩ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የሌለው ስለሆነ ወጣቶች ድርጊተ ማቆም ይኖርባቸዋል። የአንድ አገር ወጣት ለሰላም እንጂ ለጠብ ግንባር ቀደም መሆን የለበትም። ግንባር ቀደምትነቱ ለፍቅር፣ ለሰላም፣ ለይቅርታና ለልማት መሆን ነው ያለበት።

በመሆኑም መጪው ጊዜ ክረምት እንደመሆኑ መጠን ወጣቶች አገርንና ወገንን የሚጠቅሙ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመሳተፍ ግንባር ቀደምነታቸውን ማስመስከር ይኖርባቸዋል። ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱ ነው።

ወጣቶች በእረፍት ጊዜያቸው የማንበብ ልምድ ከማዳበር ከማዳበር ባሻገር ክረምቱንም ወገንን በሚጠቅም ተግባር ላይ ተሰማርተው ነገ የሚረከቧትን አገራቸውን ከወዲሁ ማቅናት ይጠበቅባቸዋል። ስለሆነም በክረምት ወራት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ውስጥ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ታቅፈው የህብረተሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን አለባቸው።  

በማደግ ላይ ባለ አገር ውስጥ ከልማት እንጂ ከብጥብጥ የሚገኝ ትርፍ የለም። በብጥብጥ የሰው ህይወት ይጠፋል የነበረውንም ሃብት ይወድማል። በስፖርት ሳቢያ የሚፈጠር ሁከት ዛሬም ድረስ በአንዳንድ አካባቢዎች ብቅ ጥልም እያለ በመታየት ላይ ይገኛል። ሆኖም ሁከት የነበረውን ይዞ ከመጥፋት ውጭ የሚያስገኘው ምንም ዓይነት ጥቅም የለም።

የሁከቱ አራማጆች እኛን በማባላት ሊበሉን የተዘጋጁ የቀን ጅቦች እንጂ የትኛውንም የአገራችንን ህዝብ የሚወክል አይደለም። ህዝቡ ከመልካም አስተዳደርና ከብልሹ አሰራር ጋር ተያይዞ ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች መንግስት አቅም በፈቀደ መጠን ምላሽ እየሰጠ ነው። ከዚህ በመለስ የሁከቱ ባለቤቶች ሌሎች ናቸው፤ አገራችን ውስጥ እየተከናወነ ያለው ከውጥ ያስደነገጣቸው የቀን ጅቦች። ስለሆነም ወጣቱ የለሊት ድብቅ ተግባራቸውን ትተው በቀን ህዝቡን ለማባላትና ለመብላት የተሰለፈ መሆናቸውን ተገንዝቦ ከእነርሱ ተግባር መራቅ ይኖርበታል።

የእነርሱን ተግባር በመኮነን ብቻ ሳይወሰንም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ለአገሩ የበኩሉን እገዛ ማድረግ አለበት። የአገራችን ወጣት አገሩን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማገዝ ውዴታውም ግዴታውም ይመስለኛል። ምክንያቱም እንኳንስ የአገራችን ወጣት ቀርቶ ከአገራችን ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላት የቱርክ ዩኒቨርሲቲ ወጣት ተማሪዎች የዛሬ ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ ድረስ መጥተው ለሳምንታት አገልግሎቱን ስጠታቸውን ስለማስታውስ ነው።

የቱርክ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ ከገቡ ከሰዓታት በኋላ በደበብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ በ35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዳለቲ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት አገልግሎት ሰጥተዋል። ተግባራቸውም ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን ምቹ የመማርና የማስተማር ሁኔታ ለመፍጠር የማስዋብ ስራን ማከናወን ነበር።

በዚህም አገልግሎት ሰጪ ቡድኑ ለትምህርት ቤቱ 42 የተማሪዎች መቀመጫዎችን የመለገስ፣ የተሰባበሩ መስታወቶችን የመተካትና የመማሪያ ክፍሎች በስዕል የማስዋብ ተግባሮችን አከናውነው ተመልሰዋል። ይህን እውነታ ያነሳሁት እንኳንስ የእኛ አገር ተረካቢ ወጣቶች ቀርቶ የሌላ አገር ወጣቶችም እዚህ ድረስ መጥተው አገልግሎቱን እንደሚሰጡ ለማሳየት ነው።

እርግጥ በአሁኑ ወቅት በአገራችን የበጎ አገልግሎት ስራ ጨምሯል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በበጎ ስራ አገልግሎት ተሰማርተዋል። እየተሰማሩም ነው። ቁጥሩም ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው። ለምሳሌ ያህል በአዲስ አበባ ውስጥ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባለፉት ዓመታት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ተሳትፎ ማድረጋቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ።

ይህም ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመሳተፍ ያላቸው ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ ነው። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ በጤናው ዘርፍ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ናቸው። በተለይ ባለፈው ዓመት ወጣቶቹ በደም ልገሳ፣ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ንቅናቄ፣ በጽዳት አገልግሎትና በእጅ ማስታጠብ ቀን ተግባራት በመዲናችን ሁሉም ክፍለ ከተሞች ያከናወኑት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሽ ነው።

እርግጥ በአገልግሎቱ ከአንድ ሺህ 500 በላይ ወጣቶች ደም መለገሳቸው፣ ከአተት በሽታ ጋር በተያያዘ በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች የጽዳት ዘመቻ መሳፋቸው እንዲሁም ከማጠናከሪያ ትምህርት በተጓዳኝ  ስለ ኤች.አይ.ቪ /ኤድስ እና ስለ አተት በሽታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠታቸው ወጣቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ዘልቀው በመግባት የህብረተሰቡን ችግር መቅረፍ እንደሚችሉ አረጋጋጭ ሁኔታ ሆኖ አልፏል። እንዲህ ዓይነቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠ አለበት።

የበጎ ፈቃድ አገልግልት ለመስጠት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው። ወጣት መሆን ደግሞ ሁሉንም ነገር መስራት የሚቻልበት እድሜ ነው። ይህን አፍላ እድሜ ለማህበረሰባዊ አገልግሎት ማዋል የህብረተሰቡን ችግር መቅረፍ ነው። ወጣቶች ተማሪዎች ብቻ አይደሉም። በሁሉም የስራ መስኮች ውስጥ የሚገኙና በዚያ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉትንም ይመለከታል።

በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራን ተማሪዎችም ይሁኑ ሙያ ያላቸው ወጣቶች ሊከውኑት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ አንድ ነርስ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ብትሰማራ የኤች.አይ.ቪ ምርመራውን እየፈለጉ ሳያገኙ የቆዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገቢውን ምርመራ እንዲያገኙ ማድረግ ትችላለች።

በእርሷ ተግባር ውስጥም ተማሪዎች በመቀስቀስ፣ ወረፋ በማስያዝ፣ በመመዝገብና በሌሎች ቀላል በሚመስሉ ስራዎች ውስጥ በመሳተፍ ድጋፍ ሊያደርጉ ይችላሉ። በዚህም ሁሉም በየአቅሙ ማህረሰቡን ይረዳል ማለት ነው። አገር የምታድገው የተወሰኑ ሰዎች በሚያደርጉት ተሳትፎ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የአቅሙን ሲያከናውን ነው።

ከዚህ አኳያ በማደግ ላይ የምትገኘው አገራችን ተረካቢዎች ወጣቶች ናቸው። ከ20 ቀናት በኋላ ክረምት ይገባል። ማህበረሰቡ ከክረምት ጋር ተያይዘው የተለያዩ ችግሮች ሊፈጠሩበት ይችላሉ። በስፖርት ምክንያት እዚህም አዚያም ከመጋጨት ወጣቶች ነገ የሚረከቧትን አገራቸውን ለመጥቀም በተመቻቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን አለባቸው። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ራስንም ህብረተሰብንም የሚጠቅም በመሆኑ ወጣቱ ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል። በመሆኑም በሁሉም የአገራችን ክፍሎች በአገልግሎቱ በመሳተፍ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ለሚረከቧት ኢትዮጵያ ማዋል ይኖርባቸዋል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy