Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

            ግንቦት 20 በአዲስ ሀገራዊ ድል

0 421

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

            ግንቦት 20 በአዲስ ሀገራዊ ድል

  ይልቃል ፍርዱ

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ በኢትዮጵያዊነት ካልሆነ መቀጠል አንችልም፤ ስንደመር እንጠነክራለን፤ታላቅ ነበርን ታላቅም እንሆናለን የሚለው አስተሳሰባቸው በሕዝቡ ውስጥ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶአል፡፡የአስተሳሰብ ልቀትን  የተጎናጸፈ አሸናፊ ራአይ ነው፡፡ሀገራችን በግንቦት ሀያ ድል የተጎናጸፈቻቸውን ታላላቅ ሀገራዊ የልማትና የእድገት ስኬቶች በአስተማማኝ ደረጃ ለማስቀጠል ተጨማሪ ጉልበት የፈጠረ ነው፡፡

የዘንድሮው ግንቦት ሀያ በአል ከቀደሙት አመታት ሁሉ የተለየ ድባብ በሰፈነበት ስሜት ነው የተከበረው፡፡ባለፉት 27 አመታት በሀገር ልማትና በኢኮኖሚው እድገት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ መንግስታትና አለም አቀፍ ተቋማት የተመሰከረላቸው ታላላቅ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡የዘንድሮው የግንቦት ሀያ ድል በአል በተለየ መልኩ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጽናት የሕዝብን ድጋፍ ዳር እስከዳር በተጎናጸፈ አዲስ ሀገራዊ የድል ስሜት ነው የተከበረው፡፡

በሀገር ውስጥ በመልካም አስተዳደር በሙስናና በፍትሕ እጦት ችግር ለተነሳው ስር የሰደደ የሕዝብ ተቃውሞና ጥያቄ ይህን ተከትሎም የተከሰቱት የዜጎች ሕይወት መጥፋት ከቀኤያቸው መፈናቀል የደረሰው የሀብትና ንብረት ውድመት የዜጎችን ልብ ያደማ ተስፋንም ያስቆረጠ ነበር፡፡

በኢሕአዴግ አመራር ውስጥ የተፈጠረው መሰረታዊ ድክመት ያስከተለው ችግር መሆኑን ያመነው አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሪነት ሰይሞ ከፍተኛ ሀገራዊ ለውጥ ለማምጣት እየተጋ ይገኛል፡፡ይበል የሚያሰኙ ሕዝብን በደስታ ስሜት የፈነቀሉ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሮአል፡፡ሀገራዊ አንድነትን የበለጠ ያጠናከረ ከሁሉም ዜጎች ድጋፍ የተቸረው ሲሆን በውጭ ያለውን ተቃዋሚ ቀልብ መሳብ የቻለም ነው፡፡  የዘንድሮው ግንቦት ሀያ በአል አከባበር የተለየ የሆነበትም ምክንያት ከብዙ ሀገራዊ እውነቶች ጋር ይያያዛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ላይ በወጡ ሁለት ወር በማይሞላው ግዜ ውስጥ ታላላቅ የሕዝብን እርካታና አመኔታ ያስገኙ ለውጦችን አስመዝግበዋል፡፡የግንቦት ሀያ ድሎችን በአስተማማኝ መሰረት ለማስቀጠል የሚያስችሉ መሰረቶች ናቸው፡፡

ሕዝብ በመንግስት ላይ የነበረው እምነት ተሸርሽሮ ቆይቶአል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር ግዜ የሰሯቸው ስራዎች በመንግስት ላይ የጠፋው አመኔታ ተመልሶ እንዲያንሰራራ  ለማድረግ ችለዋል፡፡

ኢሕአዴግ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ አዲስ አመራር ለኢትዮጵያ አንድነት፤ ለሀገራችን ሰላምና መረጋጋት፤ የሕዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ፤የዲሞክራሲ ምሕዳሩን ለማስፋት በእርግጠኝነት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በነዚህ አጭር ግዜያት የወሰዳቸው ቁርጠኛ እርምጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡

በሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ አመራሩን ከተረከቡ በኃላ ኢሕአዴግ የገባውን ቃል ጠብቆ ሁለት ወር ባልሞላ ግዜ ውስጥ የሕዝብን ቀልብና ልቦና ማሸነፍ የቻሉ የሚታዩ ስራዎችን ሰርቶአል፡፡ከቀደሙት ግዜያት ሁሉ በላቀ ሁኔታ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ለማሳካት የሚያስችሉ እርምጃዎችን ወስዶአል፡፡ግንቦት ሀያ የተከበረው በዚህም መንፈስ ውስጥ ነው፡፡

በሕዘብ ውስጥ ሰፍኖ የነበረውን የመበታተንና የመከፋፈል ስጋትና አደጋ  በማስወገድ የተሸረሸረውን ብሔራዊ የአንድነት ስሜት በጸና መሰረት እንዲቆም አድርጎአል፡፡ የዘንድሮው የግንቦት ሀያ ድል በአል አከባባር ከወትሮዎቹ ሁሉ የተለየ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡

በሀገር ውስጥ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ሰፊ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር በማሰብ ከእስር ተለቀዋል፡፡ከእነዚህ ውስጥ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ አመራሮች እንዲሁም ከሳምንት በፊት የግንቦት ሰባት ዋናጸሀፊ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር ተለቀዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የሚወስዷቸው እርምጃዎች የሚመሩት መንግስትና የድርጅታቻው ኢሕአዴግ አቋም ነው፡፡ለዚህ ነው ኢሕአዴግ  በመሰረታዊ ለውጥ ላይ ነው የሚባለው፡፡

እርምጃዎቹ የሚያሳዩት ኢሕአዴግ ስርነቀል ለውጥና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር  የዲሞክራሲ ምሕዳሩን ለማስፋት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ በመራመድ ላይ መሆኑን ነው፡፡ከእነዚህ መሰረታዊ ቁልፍ ነጥቦች አንጻር ሲታይ ኢሕአዴግ በወሳኝ ለውጦች ውስጥ መገኘቱ የዘንድሮውን ግንቦት ሀያ በአል ልዩ ያደርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገር ውስጥ በሁሉም ክልሎች በሚባል መልኩ ጉብኝት አድርገው ከሕዝቡ ጋር ተወያይተዋል፡፡ሕዝቡ ላነሳቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡ተጀምረው  ያልተሰሩ ለሕዘብ አገልግሎት የሚውሉ መንገድ የውሀ የመብራት የልማት ጥያቄዎች በስፋት ተነስተዋል፡፡የተጀመሩትን ለማጠናቀቅ ያልተሰሩትንም ለመስራት መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀስ ገልጸዋል፡፡

በግንቦት ሀያ ድል መነሻነት ሀገራችን ከዚህ በፊት ያልታዩ ያልነበሩ ግዙፍ ሀገራዊ የልማትና የኢኮኖሚ እድገት ውጤቶችን አስመዝግባለች፡፡በትምህርት ዘርፍ በጤናው መስክ፤በመላ ሀገራችን መንገድን ከተሞችን በማስፋፋትና በማሳደግ፤ግብርናውን በማዘመን፤አርሶአደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ በማድረግ፤የተፈጥሮ ድርቅን አለም አቀፍ እርዳታ ከመድረሱ በፊት በራስ አቅም ለመቋቋም መቻሏ የከፍተኛ ሀገራዊ ስኬቶች ማሳያ የግንቦት ሀያ ድል በረከቶች ናቸው፡፡

አለም አቀፍ ተቋማት የአለም ባንክና አይኤምኤፍ ጭምር በቅርቡ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ቀውስ ውስጥ በነበረችበት ወቅት እንኳን መቀጠሉን በመግለጽ  ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡እነዚህ የላቁ ስኬቶች ወደፊትም ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡ በግንቦት ሀያ ድል መነሻነት ሰፊ ሀገራዊ የልማት ስራዎች ተከውነዋል፡፡

የተለያዩ ግድቦች ለኃይል ማመንጫነት መሰራታቸው በተለይም ስራው ሲጠናቀቅ 6000 ሜጋዋት እንደሚያመነጭ የሚጠበቀው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከሀገራዊ ጠቀሜታውና ኢኮኖሚያችንን ለማሳደግ ከሚያበረክተው የላቀ አስተዋጽኦ በተጨማሪ የጎረቤት ሀገራትን በኢኮኖሚ የማስተሳሰር ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ጎረቤት ሀገራት በውጭ ምንዛሪ እየከፈሉ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ያገኛሉ፡፡ ግድቡ በራሱ ሰፊ በሆነ መስክ ለዜጎች የስራ እድል የመፍጠር አቅም አለው፡፡የግንቦት ሀያ ትሩፋትና ድል ውጤት ነው፡፡

ሰሞኑን የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር በአፍሪካ ኢኮኖሚክ አዳራሽ ከጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ጋር በመሆን ቀጣዮቹን መሪዎች ለማፍራት በሚል ርእስ በተዘጋጀው ፓናል ላይ ሲወያዩ ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸውን የኢኮኖሚ ድሎችና ስኬቶች አምነው በመቀበል አድንቀዋል፡፡ተቋማቸው ኢትዮጵያን ለማገዝና ለመርዳት አብሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

የግንቦት 20ን በአል አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላለፉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔኦ በበኩላቸው በዶክተር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ለሚመራው መንግሥት አገራቸው ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል፡፡አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ትልቅ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት ባላቸው ቁርጠኝነት በቅርብ ዓመታት የተመዘገበውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማስቀጠል ሙሉ ድጋፋችን አይለያቸውም” ነው ያሉት፡፡ ለኢትዮጵያ ልማትና የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ እገዛና አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ በእርግጠኝት መናገር ይቻላል፡፡

መጪው ዘመንና ግዜ ጠንክረን ከሰራንበት ብሩህና ታላቅ ተስፋን የሰነቀ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከወትሮው የተለየ የሕዝብን ስሜት ያነበበና ያዳመጠ አካሄድን መከተል በመጀመሩ የግንቦት ሀያን ድል የበለጠ አድምቆታል፡፡ስኬቶቹን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠልና ለማሳደግ የበለጠ ውጤትም ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ሀገራችን ከጎረቤቶቿና ከውጭው አለም ጋር ያላት የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተጠናከረ መልኩ ቀጥሎአል፡፡የግንቦት ሀያ ድሎች በአዲስ መልክ  ቀጥለዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy