Artcles

ግጭት አክስሮናል

By Admin

June 30, 2018

ግጭት አክስሮናል

 

ስሜነህ

 

ባሳለፍናቸው ሶስት አመታት  በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ወደሌሎች አካባቢዎችም በመዛመት የሰዎች ህይወት ጠፍቷል፤  ቁጥራቸውን መጥቀስ በሚያሳፍር ደረጃ በርካታ ዜጎችም ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ ተገደዋል። የሰሞንኛውን እንኳ ብንወስድ የጉጅና ጌዲዎ ዞን ተፈናቃዮች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን የተመለከቱ መረጃዎች ወጥተዋል።

 

በምዕራብ ጉጂና ጌድዮ ዞኖች የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ መድረሱን የተመ የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ የገለፀ ሲሆን፤ ቁጥሩ ያሻቀበዉ የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ ነው ብሏል። የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንም የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው መለዋወጥ የእርዳታ ስራዉን አስቸጋሪ እንዳደረገበት ገልጿል።

 

በኦሮሚያ ክልል ጉጅ ዞንና በደቡብ ክልል ጌዲዎ ዞን አዋሳኝ ቦታዎች ከሁለት ወራት በፊት በተቀሰቀሰዉ ግጭት ሳቢያ በርካታ ሰዎች ከቤት ንብረታቸዉ ሲፈናቀሉ እንደነበር ሲገለፅ ቆይቷል።ይህንን ግጭት ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ድርጅት በምህፃሩ ኦቻ ከሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 2 መቶ ሺህ መሆኑን ዘግቦ ነበር።ድርጅቱ በዚህ ሳምንት ባወጣው ሌላ ዘገባ ግን ቁጥሩ በእጥፍ መጨመሩንና በጉጅ ዞን ከ170 ሺህ በላይ ሰዎች በጌዲዎ ዞን በኩል ደግሞ ከ520 ሺህ በላይ ሰዎች ከቀያቸዉ መፈናቀላቸዉን ነው ያመለከተው ።የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ አሃዙ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣሉ።«የሰብዓዊ እርዳታ ጉዳይ ፅ/ቤት ያወጣዉ አሃዝ ከመንግስት ጋር አብሮ የሚሰራ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን ቁጥር የተባለው ነው ።በጉጅ በኩል የተፈናቀሉ ሰዎች አሉ።በጌዲዮ ዞንም የተፈናቀሉ ሰዎች አሉ።የሁለቱም ድምር ከ አምስት መቶ ሺህ በላይ ነው።ሪፖርቱ ላይ የተቀመጠዉ»ማለታቸውን ከቢቢሲ ዘገባ ተመልክተናል።

 

እንደ ኦቻ ዘገባ ባለፈው ሚያዚያ በአካባቢው የተቀሰቀሰው ግጭት አሁንም ድረስ እልባት ባለማግኘቱ የሚፈናቀሉና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ። ድርጅቱ እንደሚለው የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት ግጭቱን ለማስቆም ጥረት አድርገዋል። ሆኖም በምዕራብ ጉጂ ዞን በተለይ በአባያ፣በብርብርሳ ከድዋ ፣ በቡሌ ሆራ፣በገላና እንዲሁም ቀርጫን በመሳሰሉ ወረዳዎች በሰኔ ወር መጀመሪያ አዳዲስ ግጭቶች ተከስተዋል። በግጭቱም ቤቶች መቃጠላቸዉንና ንብረት መዉደሙን እንዲሁም በርካቶች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን የድርጅቱ ዘገባ ያሳያል። የእርዳታው እና የተፈናቀሉ ዜጎችን የተመለከተው ነጥብ መሰረታዊ ጉዳይ ቢሆንም ዜጎችን ለስደት ሞትና መፈናቀል እየዳረገ ያለውን ጥያቄ መመለስ ዘላቂነት ላለው መፍትሄ ጠቃሚ ይሆናል።

 

በቆዳ ስፋቱ ከአገሪቱ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የኦሮሚያ ክልል፤ ከሁለተኛው ሰፊ የሶማሌ ክልል ጋር የሚያዋስነው 1410 ኪሜ ድንበር አለው። ይህ ድንበር ግን ክልሎቹ አሁን ያሉበትን ቅርጽ ይዘው ከተመሰረቱበት ጊዜ አንስቶ ውዝግብ አያጣውም። ውዝግቡን ፈትቶ ወሰኖቹን መልክ ለማስያዝ ታስቦም ሕዝበ ውሳኔ ከ400 በሚበልጡ ቀበሌዎች በጥቅምት ወር 1997 ዓ.ም መደረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

 

በሕዝበ ውሳኔው መሰረት ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ቀበሌዎች በኦሮሚያ አስተዳደር ሥር እንዲጠቃለሉ የተወሰነ ቢሆንም የወሰን ማካለል ሥራው ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል። ይህም በየጊዜው ለሚነሱ ግጭቶች አባባሽ ምክንያት መሆኑን እነዚሁ ጥናቶች ጠቁመዋል።

 

ባለፈው ሚያዝያ ግን የሁለቱም ክልሎች ፕሬዚዳንቶች ሕዝበ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላል የተባለ ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ “ትልቅ ድል” መገኘቱን ሲገልፁ፥ የሶማሌ ክልል አቻቸው አብዲ መሃመድ በበኩላቸው “በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ዳግመኛ ግጭት አይኖርም።” ብለው የነበረ መሆኑ ይታወሳል።

 

የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋም የችግሩ ምንጭ ”የድንበር ጉዳይ እንዳልሆነ የሚያረጋግጥልን፤ ድንበር በማንጋራባቸው አካባቢዎች ጭምር ጥቃት ሲፈፀም ነበረ ማለታቸውንም ስናስታውስ ለዚህ ሁሉ ሰብአዊ ቀውስ በተለይ አሁን የተጀመረውን ለውጥ የሚያደናቅፉ ሃይሎች ስለመኖራቸው ያመላክታል። በሃዋሳ የሆነውም በተመሳሳይ የቦታና የክልል ጉዳይ ሳይሆን ድብቅ አጀንዳ ያላቸው አካላት የመዘዙት አጀንዳ ስለመሆኑም ጥፋቱን ተከትሎ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ ከክልሎቹ ህዝብ ጋር ያደረጉት ውይይትና ይህንኑ ተከትሎ በአመራሮች ላይ የተወሰደው እርምጃ የሚያጠይቅ ነው።  ስለሆነም ድንበርና ወሰን በነዚህ እንቅፋቶች የሚፈበረክ አጀንዳ እንጂ የግጭት ምክንያት አይሆንም ማለት ስለሆነ ፖለቲካውን ማሰማመር ይጠይቃል ማለት ነው። ከላይ በተመለከተው መልኩ ለሚሊዮኖች መፈናቀልና ስደት እንዲሁም ሞት በምክንያትነት የሚጠቀሰው ሌላኛው አጀንዳ የተፈጥሮ ሃብት ፉክክር ነው።

 

በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር የሚገኙ የኦሮሞ እና የሶማሌ ክልል አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አድር ሕዝቦችን ግንኙነት ያጠኑት የማኅበረሰባዊ ሥነ-ሰብ ተመራማሪው ፈቃዱ አዱኛ ነገሩኝ ሲል ቢቢሲ ባሰፈረው ዘገባ ፉክክርና ግጭት በተለይ የቦረና ኦሮሞዎችና የአካባቢው ሶማሌ ጎሳዎች መገለጫዎች ሆነው ቆይተዋል ይላሉ። ፉክክርና ግጭቶቹ በብዛት ውሃ እና የግጦሽ መሬትን በመሳሰሉ የተፈጥሮ ሃብቶች ተጠቃሚነት ዙርያ የሚያጠነጥኑ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ አንስቶ የብሔር መልክ እየያዙ መምጣታቸው ይወሳል።

 

በአገሪቱ ፖለቲካዊ አወቃቀር የብሄር ድንበሮች የፖለቲካ ድንበሮች ጭምርም በመሆናቸው፤ በማኅበረሰቦቹ ዘንድ ያለውን የፉክክር መንፈስ ክልላዊ ገፅታ አላብሶታል ሲሉ ይከራከራሉ አቶ ፈቃዱ ሲል የቢቢሲ መረጃ ይጠቁማል። ለዚህም በማሳያነት የሚጠቅሱት ከዚህ ቀደም በአንፃራዊነት ሰላማዊ ግንኙነት የነበራቸው የአርሲ ኦሮሞና አጎራባች የሶማሌ ጎሳዎች ደም ወዳፋሰሰ ግጭት መግባታቸውን ነው።

አካባቢዎቹ ለድርቅ ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ መሆኑ በተፈጥሮ ሃብት ፍላጎቶች ላይ ለሚነሱ ቅራኔዎች ተጨማሪ ነዳጅ የሆኑ ይመስላል።ያም ሆኖ ግን እንደተመራማሪው ይህም መሰረታዊ የግጭት መነሻ አለመሆኑና የሌቦች እጅ ያለበት መሆኑን የሚያጠይቅ ነው። ጥናቶች ሌላም መነሻ ይጠቅሳሉ። የሕዝበ-ውሳኔ ጉዳይን።

 

ለተመራማሪው ፈቃዱ አዱኛ፤ መንግሥት ለአካባቢዎቹ ወሰን ተኮር ግጭቶች ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ባደረገው እንቅስቃሴ ሕዝበ-ውሳኔ ማከናወኑ የአካባቢዎቹን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው። የአካባቢው ኗሪዎች በአብዛኛው አርብቶ አደሮች እንደመሆናቸው ከሥፍራ ሥፍራ ይንቀሳቀሳሉ። ይህም ወሰኑን ቁርጥ ባለ ሁኔታ ማስቀመጥን አዳጋች ያደርገዋል።ዞሮ ዞሮ እነዚህ መነሻ ምክንያት ያልሆኑና ሊሆኑ በማይችሉ አጀንዳዎች ሌቦቹ ያተረፉልን ጦስ ሞትና መፈናቀልን ነው።

 

ባለፈው ነሐሴ የተካረሩ ግጭቶችን ያስተናገደው የሚኤሶ አካባቢ ለወትሮውም ለዚህ መሰል ፍጭቶች ባይታወር አይደለም። ሕዝበ ውሳኔን ባስተናገደው የ1997 ዓ.ም በመኢሶና በቦርደዴ አካባቢዎች በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንዲፈናቀሉ ያስገደዱ ግጭቶች ተከስተዋል ይላል የአይ ዲ ፒ ፕሮጄክት ሪፖርት።

 

በ2005 ዓ.ም ደግሞ በሞያሌ አካባቢ በተቀሰቀሰ የሁለቱ ብሔር አባላት ግጭት ከ20ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ሸሽተው ኬንያ መግባታቸውን የኬንያ ቀይ መስቀል ማህበር በዚሁ ወቅት አስታውቆ ነበር። በወቅቱ ለግጭቱ መቀስቀስ ምክንያት ተደርጎ የተጠቀሰው በግጦሽ መሬት ይገባኛል ቢሆንም ግጭቶቹ ብሄር ተኮር ይዘት እንዳላቸውም አብሮ ተዘግቧል።

 

በምንም መልክ ከላይ የተመለከቱት አጀንዳዎች የግጭትና መፈናቀል ምክንያት ሊሆኑ እንደማይችሉ ለቢቢሲ ሃሳባቸውን የሚያጠናክሩለት አቶ ፈቃዱ፤ የኦሮሞና ሶማሌ ሕዝቦች ከምስራቅ ኩሽ የቋንቋ የዘር ግንድ የሚመዘዙ ሲሆን በኢትዮጵያ ሶማሌዎችና በተለይም እስልምና በገነነባቸው የኦሮሞ አካባቢዎች መካከል መልካም የሚባል ግንኙነት ተመስርቶ መቆየቱን የሚያነሱት ፤ ባሌ ውስጥ የሚገኘው የሼክ ሁሴን መስጊድ በሁለቱም ሕዝቦች እንደ ቅዱስ ቦታ መቆጠሩን ያስታውሳሉ።

 

የሶማሌና የኦሮሞ ሕዝብ አብሮ ከመኖሩ አንፃር በርካታ አንድ የሚያደርጓቸው ነገሮች እንደሉ የሚጠቅሱት የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ፤ ምንም እንኳን እነዚህ ግዛቶች በወሰን ቢከፋፈሉም አሁንም የሁለቱ ህዝቦች የሚንቀሳቀሱባቸው ከተሞች አሉ፤ በማለት የሁለቱ ሕዝቦች አብሮነት እንደማይቋረጥ በማረጋገጥ ነው።ስለሆነም የፖለቲካ ሌቦችን አደብ ማስያዝ ለዘላቂ መፍትሄ ወሳኝ ጉዳይ ሲሆን የተፈናቀሉ ዜጎችን መርዳትና ወደቀደመው ኑሯቸው መመለስ ለውጥን መደገፍ ዲሞክራሲን ማበርታት ነው።

 

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ በሰጡት የመደመር አቅጣጫ መሰረት በሁሉም አካባቢዎች ላይ በመንግስት እንዲሁም በየአካባቢው ማህበረሰብና አመራሮች አማካኝነት እነዚህን ተፈናቃዮች ለመደገፍ ጥረት ኢየተደረገ ቢሆንም ከቁጥራቸው መብዛት አንፃር የሚደረገዉ እርዳታ በቂ ሆኖ አለመገኘቱን የአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን ገልጿል።

 

እንደኮምሽኑ ገለጻ  የሚፈናቀሉ ሰዎችን ለመደገፍ በመንግስት በኩል የአቅርቦት ችግር የለም ። ይሁንና ቁጥሩ የሚለዋወጥና በፍጥነት የሚያሻቅብ በመሆኑ አስቀድሞ ለማቀድና ተጎጅዎቹን በሚፈለገዉ ደረጃ ለመርዳት አስቸጋሪ ሆኗል።  የግጭት እርዳታ አቀራረብና የድርቅ ይለያያል።የድርቅ አደጋ በሚደርስበት ጊዜ የሚቀርበው እርዳታ በተጠና አግባብ ሰዎችን በመለየት ነው።ግጭት ግን በባህሪው ይለያል።ግጭቱ እስከቀጠለ ድረስ የመፈናቀሉ ሁኔታ ይጨምራል።  ሪሶርስ ባልጠፋበትም የአደጋው ባህሪ የሚፈጥረው ችግር በመሆኑ የሁሉንም ተሳትፎ ይጠይቃል።

 

ባለፈው ጥቅምት ወር በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማንነት ላይ ያነጣጠረውን ጥቃት  ተከትሎ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ይልቁንም ከኦሮሚያ የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ህዝቦችን የኦሮምያ ክልል የያዘበትን እና መፍትሄ ለመስጠት እየሄደበት ያለውን መንገድም ሌሎቹ ክልሎች በተሞክሮነት ሊወስዱ ይገባል።

የአማራ ክልልን ወክለው ተፈናቃዮችን የመመለስ እና የማቋቋማው ሥራ የሚያስተባብሩት በቤንሻንጉል ክልል የብዐዴን ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ኃይሉ ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ እንደተመለከትነው የፀጥታ ችግሮችን ከመቅረፍ በዘለለ ተመላሾቹ ወደቀደመ መተዳደሪያቸው እስኪመለሱ ድጋፍ የመቸር አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ነው። እርሳቸው እንደሚሉት ወደ ቤንሻንጉል ጉምዝ ተመልሰው ለሄዱ ሰዎች የቤት ውስጥ ቁሳ ቁስ እየተከፋፈለ ይገኛል፤ የእርሻ ወቅት በመሆኑ ጸረ አረምና መርጫ ተገዝቷል፤ የሳርና እንጨት ቤት የተቃጠለባቸው ሰዎች ተለይተው በክልሉ ድጋፍ ቤት ይሰራላቸዋል።

 

እንደ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር መረጃ በግጭቶች ምክንያት በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ከመኖሪያ ቀያቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች የኑሮ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ማህበሩ እንደሚለው መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ የምትገኝበት ሁኔታ ከግዜ ወደ ግዜ አስከፊ እየሆነ መጥቷል። እንደ ቀይ መስቀል ማህበሩ ከሆነ ከአጠቃላይ ሕዝቡ ግማሽ ያህሉ አስቸኳይ እርዳታን ይሻል፤ እንዲሁም ከአምስት አንዱ በግጭት ምክንያት የመኖሪያ ቀየውን ለቆ ይሸሻል። በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብ፣ በቂ የሆነ መጠለያ እና የመጸዳጃ ቤቶች አገልግሎቶችን አያገኙም። በእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች እና ሠራተኞች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት አስፈላጊ ቁሶች ለተፈናቀዮች እንዳይደርስ ከፍተኛ እክልን ፈጥሯል።ይህ የሚያጠይቀው በግጭት መክሰራችንን እና መፍትሄውም መደመር መሆኑን ነው። ይህን ለማጠቃለልም የክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ የነሃሴ 16 መልእክት ገዥ ስለሚሆን በእርሱ እናሳርግ

 

ዶ/ር አቢይ አህመድ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ከላይ በተጠቀሰው ቀን ባደረጉት ንግግር ጥላቻ አክስሮናል፤ ፍቅር ያተርፈናል ብላችሁ አክብራችሁ ስለጠራችሁን እንጂ ከፊታችን እንደ ተራራ የደረጀውን ችግር ገና ባልናድንበት ወቅት ከፊታችሁ የመቆም ሞራሉ አይኖረንም ነበር ብለዋል። ስለሆነም በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኘሁት አዲሱ አመራር ወደ ሃላፊነት ከመጣበት ቀን አንስቶ ላሳያችሁን አለኝታነት ላከብራችሁ፣ ፍቅር የተራበች ነገር ግን ለሁላችንም የሚበቃ ሃብት ያላት ሀገር እንዳለችኝ ልነግራችሁ፣ ጥላቻንና ቂምን ከበጣጠስን የእድገት ማማ ላይ እንደምንወጣ ላበስራችሁ ነውም ብለዋል።

 

መሪ ያለ ህዝብ ፍቅርና አንድነት ከንቱ ነው ያሉት ዶ/ር አቢይ አህመድ ለውጥ በጥቂት ተጨዋቾችና ብዙ ተመልካቾች የሚፈፀም ሳይሆን ሁላችንን በያለንበት፣ በየአቅማችንና እንደ ድርሻችን የምንሳተፍበት ነው ያሉ ሲሆን፤ምሁራን የበሰለ ሃሳብ በማመንጨት፣ ባለሙያዎች አዳዲስ አሰራሮችን በመፍጠር፣ የሃይማኖት አባቶች ዘረኝነትንና ሙስናን ኮንናችሁ ለድሆች ፍትህ በመቆም፣ በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ባላችሁበት ሁሉ ሀገራችሁን በማሰብ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለፈውን ረስታችሁ ለመደመር ዝግጁ በመሆን፣ ወጣቶች ጠንክራችሁ በመስራት፣ ተማሪዎች በርትታችሁ በማጥናት የለውጡ ባለቤት መሆን አለባችሁ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።በልቦናችን ያሳድርልን፤አሜን።