ጥላቻ አክስሮናል።
አዘጋጅ ፣ ልኡል ገብረመድህን (ከአገረ-አሜሪካ)
ወረሐ ሴኔ 2010(2018)
ግላዊ እይታ
♦በሴኔ 16/2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በቦምብ አደጋ ለሞቱት ኢትዮጽያውያን ወንድሞቼ አፈሩ ገለባ ይቅለላቸው። በህክምና ላሉም ድህነቱን ይስጣቸው ። በአጠቃላይ የተጎጂ በተስቦችና ወዳጅ ዘመዶች መፅናናት ከፈጣሪ ያገኙ ዘንድ ፅሎቴ ነው። ድርጊቱ ከሰው ልጅ ከፍ ሲልም ከወገን የሚጠብቅ አልነበረም። በመሆኑም የተወገዘ የአገር ውስጥ የሽብር ተግባር (Domestic Terror) ነው። ለጊዜው ጉዳዩ ለመርማሪ አካል መተው ይበጃል እላለሁ ። የምርመራ ውጤት በአጭር ጊዜ ለህዝብ እንደሚገለጽ ይጠበቃል።ሰኔ 16/2010 በመስቀል አደባባይ የፈነዳው ቦምብ ለ2 ሰዎች ህይወተ ህልፈት እንዲሁም በ165 ሰዎች ቀላልና ከባድ አካላዊ አደጋ አድርሰዋል።
♦ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ አስፈፃሚ የስራ ሪፓርት ባቀረቡበት ወቅት የሚከተለው ይቅርታ አዘል መልዕክት ተናግሮ ነበር፣
[ የኢትዮጵያ ህዝብ እኛን(መንግስት) በምክንያት ማስር ይችል ነበር ግን ይቅርታው ችሮናል] ።
ይህ አባባል መንግስት በግልጽና ያለግልፅ የህግ ጥሰት ይፈፅም እንደነበረ ያሳያል። በይቅርታ ማቀፍ የማይካተቱ
በስው ሰቃይ የሚደስቱ የደህነት ሀላፊዎች ገራፉዎችና ገዳዮች (Serial Killers) ጭምር ለፍቅርና አንድነት ሲባል የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ አድርጓል ። በኢትዮጵያ ውስጥ ከደርግ ስርአት ባልተናነስ ለ27 አመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሰብአዊ ግፎች ሲፈፀሙ ቆይተዋል። ይቅርታ ለማያውቁ ሰዎችም ጭምር የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ አስተዳደር ይቅርታ ተፈፅሟል ። ይህ የመንግስት በሳል መፍትሔ በመልካምነቱ በሁሉም የኢትዮጵያውያን ተቀባይነት አግኝቷል ።
♦ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 24/2010 ዓ.ም ቃለ መሀላ ገብቶ መንበረ ስልጣን ከተቀበሉ ጥቂት ሳምንታትና ወራት በኢትዮጵያ መንግስትነት ማህደር አይተናቸውና ስምተናቸው የማናውቅ በርካታ መልካም አገራዊ እንዲሁም አህጉራዊ ጉዳዮች ለማከናወን ችላዋል። በአገር ውስጥ በብሄር ወጥመድ ተይዞ የቀየ በዘርና በብሄር ላይ ተመስርቶ የቆየ የፓለቲካ ጥላቻ እንዲቀረፍ በከፍተኛ አገራዊ መንፈስ ሰርተዋል ። በልዩ ልዩ ምክንያቶች ማለትም በአሽባሪነት፣ በፓለቲካ፣ እንዲሁም በመልካም አስተዳደር ችግር (ሙስና) ታስሮ የቆዩት ኢትዮጵያውያኖች ከእስር ተፈተዋል ።ከተፋካካሪ የፓለቲካ ድርጅቶች ጋርም ከጥላቻ በፀዳ አኳኋን በአገራዊ ጉዳዮች ለመወያየት እድሎች ተፈጥረዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር ጊዜ አመርቂ አህጉራዊ የዲፕሎማሲ ስራዎች አከናውነዋል ። በተለያዩ የአፍሪቃ አገራት በእስር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከእስር የመፈታት እድል አግኝተዋል።ይህ ተግባር በኢትዮጵያውያን ዘንድ በራስ የመተማመን ከፍ ሲልም መነቃቃት ፈጥረዋል። ኢትዮጵያውያን እስረኞች የማስፈታት ተግባር ለኢትዮጵያውያን አዲስ ክስተት ነበር። ይህ መልካም ስራ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያውያን ልብ ሰፍራ እንዲያገኙ እድል ፈጥረዋል። ከአገር ውጭ መንግስት የሚቃወሙ ኢንዲሁም የትጥቅ ትግል የሚያካሄዱ ድርጅቶች ወደ አገራቸው ተመልሶ ሰላማዊ የፓለቲካ ስራቸው እንዲከውኑ በይቅርታ መንፈስ ጥሪ አስተላልፈዋል። ሌላ የጠቅላይ ሚኑስትሩ አህጉራዊ ክንውን የአጔራባች አገሮች ወደብን በጋራ ማልማት እቅድ ሃሳብ ነው። ይህ መልካም ሀሳብ ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ትስስሮች (Economic Integration) በር ከፋች ነው።
♦ መልካም ያደረገ መሪ ማመስገን ባህሉ ያደረገ የኢትዮጵያ ህዝብ በራሱ ተነሳሽነት ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ ለማመስገንና በአጭር ጊዜ ላከናወኑት ሁሉም አቀፍ ክንውን ድጋፍ ለማድረግ ቅዳሜ ሰኔ 16/2010 በመስቀል አደባባይ በተገኘው ህዝብ ላይ በታቀደና በተጠና መንገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል ለስልፈኛው ህዝብ ንግግር ካደረጉበት ቦታ አጭር ርቀት ላይ የቦንብ ፍንዳት ተከሰተ። ይህ የቦንብ አደጋ ይህ ፅሁፍ እስከተጠናቀቀ ድረስ በሁለት የዕለቱ የምስጋናና የድጋፍ ተሳታፊዎች ላይ የሞት እንዲሁም በ165 ንፁሓን ኢትዮጵያውያን ላይ ቀላልና ከባድ አደጋ ደርስዋል። በዚህ አጋጣሚ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዲሁም ሌሎች ሆስፒታል ባላሞያዎች የወገናቸው ህይወት ለመታደግ ላደረጉት ሞያዊ ርብርብ የኢትዮጵያ ህዝብ እጅጉኑ ያመስግናል። ባደረጋችሁት ህይወት የማትረፍ ተግባር ኢትዮጵያውያኖች ኮርተንባቸዋል። The Ethiopian people deeply proud of the Tikur Anbesa Hospital and other hospital health professional personnel for their humble dedication to save massive life of the Sene 16/2010 Mesqel Adebabay bomb attacked victims. The Ethiopian people have always thanked you for your coordinated and professional support to those who have been injured of a bomb attack during the massive rally of Sene(ሰኔ) 16 of 2010.
♦ በሌላ በኩል ደግሞ የመንግስት ስራተኞች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ፣ እንዲሁም ለወገን ተቆርቋሪ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የቦምብ ጥቃት የደረስባቸው ወገኖች ህክምና የሚከታተሉበት ድረስ በመሄድ እንዲሁም ደም በመለገስ ላሳዩት የወገን ፍቅርና እርዳታ የሚመሰገን ተግባር ነው። It’s an absolute honor that those who have visited victims of the Sene (ስኔ)16/2010 bomb attacked at all locations where the victims have been received treatments. Also, have special thank to those who have donated blood to save the life of the bomb attacked victims. በዚህ አጋጣሚ ክብር ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ ላደረጉት የደም ልገሳ መልካም ምግባር በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና የላቀ ነው።በተጨማሪ ሀላፊነት በማይስማቸው ፣ የግል ጥቅም በጎደላቸው ፣ ይቅርታና ፍቅር በማይገባቸው እኩይ የቦምብ ግድያ ምኮራ (Assassination Attempt) መትረፎ የሚያስተዳድሩት ህዝብ ደስታው ወስን የለውም ።
♦ ከብሄር ፓለቲካና ከጥላቻ ምን ተጠቀምን?♦
ብዙ ሳንርቅ ጎረቤት ሪዋንዳ በ1994(በምዕራቡ ቀመር) በሁለት ጎሳዎች መካከል የተፈፀመው የዘር እልቂት አለምን ያስደነገጠና ያሳዘነ ነበር። መነሻው ምንም ይሁን ምን እልቂቱ ከሰው ልጅ የማይጠበቅ አሳፋሪ ድርጊት ነበር። የዘር ጥቃቱ ቱትሲዎች ላይ ያነጣጠረ ነበር። በሥልጣን ላይ የነበረ የቱቱ ብሄር አስተዳደር አናሳዎቹ የቱትሲ ብሄር ተወላጆች የቱቱዎች እርምጃ ለመከላከልም ሆነ ለማስቆም ፍላጎት አልነበረውም ።
ምክንያቱም የችግሩ መነሻ የስልጣን ጥያቄ ነው ብሎ ያምን ሰለነበር የቱቱ መንግስት በዘር ጥላቻ የቱትሲ ብሄር ላይ የዘር ማጥፋት ተግባር ተፈጸመ ።አንደ መቶ ቀናት ባልሞላ ጊዜ ከአምስት መቶ ሸህ በላይ የሩዋንዳውያን ህይወት ተቀጠፈ።ልብ በሉ ይህ በሁለት ብሄር የተፈፀመ ወንጀል ነው። በኢትዮጵያ ሰንት ብሄር ነው ያለው? ። ኢትዮጵያ በብሄር ብዛት ከሩዋንዳ በ99.98 ፐርስንት ትበልጣለች። ከአፍሪካ ሁለተኛ ታላቅ አገር ኢትዮጵያ ከስማንያ በላይ ብሄሮች አሏት ። ይህ ደግሞ አብይ ፀጋ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ቂም በቀልና ጥላቻ የሚጠይፍ ህዝብ ነው። ፈሪሃ ፈጣሪ ያካበተ ህዝብ ነው።የመሪዎችና ፓለቲከኞች ሴራ በሚገባ ይገነዘባል።የኢትዮጵያ ህዝብ ክፍፍልና ማንነት ለፓለቲካ ንግድ እንዲውል የሚፈቅድ ህዝብ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ማን ለማን ይጠላል? ማን ለማን ያጠቃል? ማን ለማን ይጎዳል? ። ህዝቡ በደምና እምነት የተዋቀረ ፣ የተዛመደ፣ የተዋለደ፣ ነው። የአንዱ ጉዳት ለአንዱ ያመዋል፣ የአንዱ ጥቃት ለአንዱ ይስመዋል፣ የአንዱ ችግር ለአንዱ ያሳስበዋል።
ለላፉት 30 አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ መልካም የልማት ጅምሮች የመኖራቸው ያህል በሰብአዊ መብቶችና የተረጋጋ ስላም ዙርያ አበይት ችግሮች ነበሩ። የኢህአዴግ አስተዳደር በሀሳብ የሚሞጉት ሰው ለእሥራትና ስደት ይዳረግ ነበር። ይህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የህዝብ ብሶት ፈጠረ።ላለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት የአማራ ንቅናቄ (በጎንደር) እንዲሁም የኦሮሞ ህዝባዊ ተቃውሞ የኢህአዴግ አስተዳደር ችግር ውስጥ ከተቱት። ህዝባዊ አመፆች መነሻቸው የፍትህ ችግሮች ፣ የመብት ጥያቄዎች ፣ የሥራ እጦት፣ የተጠቃሚነት ጥያቄዎች ነበሩ ። የኢህአዴግ አስተዳደር የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት ተደጋጋሚ የተሀድሶ ግምገማዎች አከናውነዋል ።አንዱ የኢህአዴግ አስተዳደር የተሀድሶ ውጤት ለኢትዮጵያ ህዝብ አስተዳደራዊ በደሎች ፈፅሜያለሁ ይቅርታ ይደረግልኝ ማለቱ ነበር። ሌላው የተሀድሶ ውጤት አዲስ ሊቀመንበር መምረጡ ነበር።
♦ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ በህዝባዊ ግፊት(public pressure) ከኢህአዴግ አባል ድርጅት ኦ.ህ.ዴ.ድ. የተገኙ ታላቅ የህዝብ መሪ ናቸው። እኝህ መሪ መደመርን የፓለቲካ መሪ ቃል(political philosophy) መሠረተ አድርጎ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ለማጎልበት የሚጥሩ ብልህና ለውጥ አራማጅ መሪ ናቸው። ለብዙ አመታት የተከማቹ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተረክበዋል። ለጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ፈታኝ ጉዳይ የድርጅታቸው ኢህአዴግ የለውጡ አካል የማድረግ ችግር ነው። ለአንዳንድ የኢህአዴግ ሰዎች የዶ/ር የለውጥ ሀሳብ ፈፅሞ አይዋጥላቸውም ወይም ከለውጡ ጋር ለመራመድ ዝግጁ አይደሉም ። ስኔ 16/2010 ጠቅላይ ሚኒስተሩ ለመግደል በመስዋቀል አደባባይ የተሞከረው የቦምብ ፍንዳታ ለውጥ ከማይቀበሉ ሰዎች እንደተቃጣ ይገመታል። ከሰው ፍጡር የማይጠበቅ ድርጊት ነበር። ለነፃነት የሚታገሉ መሪዎች ብዙ ወዳጅ እንዳላቸው ሁሉ ብዙ ጠላት እንዳላቸው ይታመናል። 16ተኛ የአሜሪካ ፕረዚደንት ነበር አብርሀም ሊንከን (1861-1865) የተገደለው ከጥቁር አሜሪካውያን ነፃነት ጋር በተያያዘ ምክንያት ነበር። የፕረዚደንት ጆን ኬነዲ ግድያም ተመሳሳይነት ያለው ነበር። የጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ የግድያ ምኮራ ከእነ አብርሀም ሊንከን ግድያ ጋር ተመሳሳይነት አለው። የሚለየው ቢሮር አገሩንና ወቅቱ ብቻ ነው። ነፃነት ያለ መስዋዕትነት አይገኝም ።
♦ የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ቀጠይነት ሁኔታ ♦
በአሁኑ ጊዜ የኢህአዴግ ስርአት እንደ ስርአት በጥምረት ለመቀጠል የሚያስችለው ቁመና ላይ ያለ አይመስለኝም። አብዮታዊ ዲሞክራሲ አደጋ ላይ ነው። በድርጅቱ ሁለት አብይት ሀሳቦች ተፈጥረዋል። የለውጥ ሀሳብ አራማጆች ( Radical change Thinkers) እና ለውጡን የማይደግፉ ወይም የማይፈልጉ የድርጅቱ ውስጣዊ ሀይሎች ( Internal Resistance Forces) በግልጽ አቋማቸው ተለይተዋል። የሁለቱ ሀሳቦች የሀይል አስላለፍ ሲታይ የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ያመዝናል።የኢትዮጵያ ህዝብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ወግነዋል። ነባር የኢህአዴግ ታጋዮች እንዲሁም በለወጡ ሂደት የግል ጥቅም የሚያጡ ውስን የኢህአዴግ ሰዎች የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ የለውጥ መንገድ አደናበሯቸዋል። ኢህአዴግን እንደ ሀይማኖት የሚያዩ አንዳንድ ግብዝ ኢህአዴግ ነን ባዮች ደግሞ ከመንግስትነት ወደ ሽብርተኝነት ሽግግር ላይ ናቸው።የሲዳማና ወላይታ፣ የአሶሳ እንዲሁም ሌሎች ግጭቶች በአገር ውስጥ አሽባሪዎች የተፈፀሙ አስነዋሪና አሳፋሪ የሽብር ድርጊቶች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በነበራቸው ስልጣናዊ ሰንሰለት በመጠቀም አልያም በገንዘብ ድጎማ በተለያዩ ክልሎች ግጭት ለመፍጠር እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተዋል። እነዚህ የደባ ጉድጔድ ቆፋሪ ትባ ትባ የኢህአዴግ ስዎች ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ ከኢህአዴግ ዓላማ ውጭ የተቃዋሚዎችን ጉዳይ አስፈፃሚ ሆነዋል በማለት ሚኒስትሩን ይከሱታል፣ይወነጅሉታል፣ ያንኳሱሱታልም። አንዳንድ የኢህአዴግ ሰዎች የለውጥ ሃሳብ እንደውርደት የሚቆጠሩ የመኖራቸው ያህል የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካም ጉዞ የሚያደንቁና የሚደግፉ ይኖራሉ። የኢህአዴግ አስተዳደርና መንግስት የሚመራበት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፓለቲካዊ ፍልስፍና ከስብአዊ መብት አያያዝ ፣ከዲሞክራሲ ግንባታ፣ ከፀጥታና ስላም አንፃር ሲገመገም ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚመጥን ድርጅት ሊሆን አልቻለም። ላለፉት 27 አመታት አንፃራዊ የልማት ጅማሮ ካልሆነ በቀር በሰብአዊ መብቶችና ጥበቃዎች አልተሳካለትም ። በአጭሩ ወደቀዋል(Failed State) ማለት ነው። ለብዙ አመታት የተከማቹ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዳይደገሙ ተቋማት ቶሎ መጠናከር ይኖርባቸዋል። የኢህአዴግ የውስጥ ችግሮች የድርጅቱ ቀጣይ ህልውና የሚፈታተኑ በመሆናቸው ችግሮች ወደ አባል ድርጅቶች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች መስራጨቱ አይቀሬ ነው። የብሄረ አማራ ድርጅት (ብ.አ.ዴ.ን.) ፣ የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲ ድርጅት (ኦ.ህ.ዴ.ድ.) እንዲሁም አብዛኛው የድቡብ ህዝቦች ድርጅት አባሎች የጠቅላይ ሚኒስተር ሀሳቦች የተቀበሉና የደገፉ ድርጅቶች ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ እንዲመረጥ ከፍትኛ ድርሻ ነበራቸው። በአንፃሩ ትንንሽ አጋር ድርጅቶች ይዞ የቀረ ህ.ወ.ሓ.ት. ከጅምሩ የዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት የሚደግፍ ድርጅት አልነበረም ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመረጡም የድጋፍ ድምፅ አልሰጠም ። ይህ በዲምክራሲ ትንትና ክፍት የለውም ምክንያቱም ድርጅቱ የመወስን መብት አለው።በጥቅል ሲታይ ግን ህ.ወ.ሓ.ት. አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል እንዲሁም ተራቁተዋል ማለት ይቻላል። አንዳንድ የህ.ወ.ሓ.ት. ደጋፊዎች በማህበራዊ መገናኛ ሰለ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ፍታሃዊና ወቅታዊ ሰለ አይደሉ ቢታረሙ እንዲሁም ከእውነታዎች ጋር ቢጣጣሙ መልካም ነው እላለሁ ።በስሜት ህዝብ ማሳሳት ያለብን አይመስለኝም ።
♥ የኢትዮጵያ ህዝብ ማድረግ ያለበት♥
(1) የጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ የሰላምና የፍቅር ጥሪ አጠናክሮ መቀጠልና ማስቀጠል።
(2) ህዝብ ከህዝብ ጋር የሚያገዳድሉ አንዳንድ የኢህአዴግ ሰዎች ላይ የቅርብ ክትትል ማድረግና ለሚመለከተው አካል መጠቆምና ማጋለጥ ያስፈልጋል ። እነዚህ ሰዎች የኢህአዴግ ድርጅት የሚወክሉ አይደሉም። በድርጅት ስም የሚነግዱ የቀን ጅቦች ናቸው። በስው ጉዳትና ሰቃይ የሚደስቱ ጉማሬዎች ናቸው። በ IT ቴክኖሎጂ እንቅስቃሴዎች መቆጣጠር ።ለምሳሌ ፣ በፎቶግራፍ የተደገፉ መረጃዎች ማህበራዊ መገናኛ ላይ መጫን።
(3) በማንኛውም ግጭቶች ያለመሳተፍ።
(4) በወገኑ ላይ ምንም አይነት የጥፋት እርምጃዎች አለመፈፀም።ይህ ንብረት ማውደምም ያጠቃልላል። ከገንዘብ ይልቅ የወገን ህይወትና ፍቅር ማስበለጥ ያሻል።
(5) የተጀመሩት የልማት እንቅስቃሴዎች ለፍፃሜ የበቁ እንዲሆኑ ህዝቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ።
♥ መልዕክት ለጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ♥
አገራችን ኢትዮጵያ ካላት የስብ ሀብት እንዲሁም የተፈጥሮ በምስራቅ አፍሪቃ ፣በአፍሪቃ እንዲሁም በአለም አቀፍ ተፅእኖ ፈጣሪ ለማድረግ እየተከሄደ ያለው መንገድ መልካም ነው። የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝብ ማቀራረብ ደግሞ የበለጠ የዲፕሎማቲክ ስኬት ነው። ሰብአዊ መብቶች እንዲከበር ፣የህግ በላይነት እዲስፍን፣ መልካም አስተዳደር ኢንዲኖር፣ እስራትና ስደት እንዲቆም ፣ ዜጎች ከቀያቸው እንዳይፈናቀሉ እየተከናወኑ ያሉ መልካም ጅማሮዎች የተሻለ መረጋጋት አንደሚያመጡ ይጠበቃል። የሁሉም መልካም ተግባሮች መስረት የሆነው ፍቅርና ስላም እንዲጎለብት፣ እንዲያብብ ብዙ ጥረት ይጠይቃል። የዘር ጥላቻ እንዲወገድ ፣ማስወገጃድ መንገዱ ደግሞ ፍቅርና ይቅርታ መሆኑ ትክክልና የሚደገፍ ነው። በአገራችን የማህበረ ኢኮኖሚ እድገት ለማሳካት ይረዳ ዘንድ በአገራዊ መግባባት መንፈስ መደመር ይኖርብናል።
በአገራችን ሥራ እጥነት እንዲቀንስ፣ ሰላምና መረጋጋት አንዲስፍን፣ መልካም አስተዳደር እንዲጠናከር ፣ ህገ ወጥ ንግድ እንዲቆም፣ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ፣ ፍትህ በገንዘብ መወሰን እንዲያቆም የፍትሕ ተቋማት በመስኩ ባለሞያዎች እዲመሩ እንዲሁም ገለለተኛ ተቋም መሆን አለባቸው እላለሁ ። ሌላው በተለያዩ ክፍለ -አለማት የሚኖሩ ትውልደ የኢትዮጵያውያን ድርብ ዜግነት ይኖራቸው ዘንድ የኢትዮጵያ መንግስት ለጉዳዩ አድህቦ(ትኩረት) እንዲስጠው ለማሳሰብ እፈልጋለሁ ።
ክብርና ምስጋና ለኢትዮጵያ ህዝብ።