ጥሪው…!
ገናናው በቀለ
የመደመር ፖለቲካ በአገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም። በቀጠናው ላሉ አገሮች ሁሉ እየተደረገ ያለ ጥሪ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተቀየሰው አብሮ ተጋግዞ የማደግ ፖለቲካ ምስራቅ አፍሪካን በሁለንተናዊ መስኮች ማስተሳሰር የሚችል ነው። ጥሪው እንዴት ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ከጅቡቲ፣ ከሱዳን፣ ከኬንያ፣ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ ጋር ያለውን ሂደት ብቻ በመመልከት መገንዘብ ይቻላል።
በአሁኑ ሰዓት በውስጥ ጉዳያችን መስማማት መጀመራችንና እየተደመርን መምጣታችን ለአፍሪካ ቀንድ አገራትም አርአያ መሆን ችለናል። በምሳሌነትም በቅርቡ የደቡብ ሱዳን መሪዎች ወደ ሰላም መድረክ መመለሳቸውና በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም መስማማታቸውን መጥቀስ ይቻላል። ይህም የመደመር ፖለቲካውና ጥሪው ከሀገር ውስጥ ባሻገር ቀጠናውንም የሚያቅፍ መሆኑን በገሃድ የሚያሳይ ነው።
እንደሚታወቀው ሁሉ በአገር ውስጥ መንግስት ለአደጋ ተጋላጭነታችን በምክንያትነት የሚጠቀሰውን ድህነትንና ኋላቀርነትን በመዋጋት ህዝቡ ተጠቃሚ የሚሆነበትን ፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ሲያከናን ቆይቷል። ይህ ጥረቱም ዛሬ የደረስንበት ደረጃ አድርሶናል።
ባለፉት ዓመታት የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በሚፈለገው መጠን ማረጋገጥ አልተቻለም። ልማቱ በተጨባጭ ህዝቡን ምን ያህል ተጠቃሚ አድርጓል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ተገቢ ሆኗል። በቅርቡ ወደ ሃላፊነት የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በቅድሚያ አገራዊ አንድነትን ማጠናከርና መደመርን በማረጋገጥ ሰላምን በማምጣት የተጀመረውን ልማት ለማሳደግና ወደ ህዝቡ በተጨባጭ እንዲደርስ በመስራት ላይ ይገኛሉ። በዚህም በጥቂት ጊዜ ውስጥ ውጤት ተገኝቷል።
አንድነታችን እየተጠናከረና አገራዊ መግባባታችን ስር በመስደድ ላይ ይገኛል። ይህም ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ በላይ የውስጥ አንድነታችን እንዲጠናከር አድርጓል። የውስጣችን የመደመር ጥንካሬም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተቀባይነት እንዲኖረንና የቀጠናው አገራትም በምሳሌነት እንዲከተሉን አድርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በጂቡቲ፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳና በግብፅ ባደረጓቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶች አገራዊ ጥቅማችንን ማረጋገጥ የቻሉት በውስጣችን በፈጠርነው የመደመር አንድነት ጥንካሬ ውጤት ነው።
እርግጥ እኛ አንድ በሆንን ቁጥር ተፈላጊነታችን ይጨምራል። ብሔራዊ ጥቅማችንንም እናስጠብቃለን። በውስጣችን የምንሰራቸው የመደመር ጥንካሬ ስራዎች የሌሎችም አርአያ እንድንሆን አድርገውናል። ከዚህ አኳያ ደቡብ ሱዳንን መመልከት እንችላለን።
የኢትዮጵያ መንግስት አገራዊና አካባቢያዊ ሰላምን ከማስፈን አኳያ በቀጠናው በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውጤታማ መሆን ችሏል። ይህም በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የምትዋሰነን በጎረቤት ደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰውን የእርስ በርስ ግጭት ለማርገብ የተካሄደው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን አድርጎታል።
ደቡብ ሱዳን ሰፊ የተፈጥሮ ሃብቷ ለታላቅ ዕድገት መብቃት የምትችል አገር ብትሆንም ነፃነቷን በተቀዳጀች በአጭር ጊዜ ውስጥ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገብታለች። ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ቀውስ ልትዳረግም ችላለች። ዜጎቿ ሞተዋል። ሀብትና ንብረታቸውነ አጥተዋል። ተሰደዋል።
በዚያች አገር የተቀሰቀሰውን አለመረጋጋት እልባት ከመስጠት አኳያ የአንበሳውን ድርሻ ከተወጡት የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ መሆኗ ግልፅ ነው። አገሪቱ ከሱዳን ጋር የነበራትን አለመግባባት በመፍታት፣ በዳርፉርና በአብዬ የተከሰቱ ችግሮችን በመቅረፍና የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በማዋጣት የኢትዮጰያ ሚና ከፍተኛ ከፍተኛ ነው።
መንግስት የደቡብ ሱዳን ሰላም ለሀገራቸን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን መፋጠን ካለው ፋይዳ የመነጨ ነው። ምክንያቱም እኛ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመዋጋት የምናደርገው ትግል ሊሳካ የሚችለው ጐረቤቶቻችን ሰላም ሲሆኑ ነው። እርግጥም የጎረቤቶቻችን ሰላም መሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለእኛ ሰላም መጐልበት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ግልፅ ነው።
በአገራችን ሰላም ላይ የቅርብ ተፅዕኖ ይኖራታል ተብሎ የሚታሰበው የደቡብ ሱዳን ችግር ለመቅረፍ በመንግስታችን የተካሄደው ጥረት ምንጩ ለሰላም ካለው ተደማሪነት የመነጨ ነው። ምክንያቱም በጐረቤቶቻችን ላይ የሚያጋጥም ትርምስንና ቀውስን መፈታት ካልተቻለ ጦሱ ለእኛም መትረፉ ስለማይቀር ነው። ከዚህ አኳያ በፀጥታና በስደተኞች አማካኝነት በጋምቤላ በተለያዩ ወቅቶች የተከሰቱ ችግሮችን እማኝ የሚሆኑ ናቸው።
እርግጥ ለነፃነቷ የታገለችውን ያህል ሰላሟን መጠበቅ አልቻለችም። በአዲሷ አገር ውስጥ በሁለቱ ተቀናቃኞች (በፕሬዚዳንት ሲልቫ ኪርና በዶክተር ሪክ ማቻር) መካከል በየወቅቱ እየተከሰተ ያለው ችግር ህዝቦቿ ከነፃነታቸው ማግኘት የሚገባቸውን ትሩፋቶች እንዳያጣጥሙ እንቅፋት ፈጥሯል።
ግጭቶቹ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት የዳረጉና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ደግሞ የስደት ሰለባ ያደረጉ ናቸው። ይህ ደግሞ አገራችንን ጨምሮ ሰላም ወዳድ ኃይሎችን በአያሌው ሲያሳስበ ቆይቷል። አገራችንም እስካሁን ድረስ እያካሄደች የነበረውን ብርቱ ጥረት የሚጠይቅ ሆኖ ቆይቷል።
በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች አማካኝነት የተፈረመው የተኩስ አቁም ስምምነት ለበርካታ ጊዜ ተጥሷል። ይህም የዚያን አገር ዜጎች ህይወት አስከፍሏል። የስደት ገፈትን እንዲቀምሱም አድርጓል። በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ የሀገሪቱን ሰደተኞች ተቀብላ እያስተናገደች ነው። ይህም የአካባቢው ህዝቦች ከለላ መሆኗን የሚያሳይ ነው።
ከሰሞኑም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሁለቱን ተቀናቃኞች ፊት ለፊት ማገናኘትና እንዲወያዩ ማድረግ ችለዋል። ሁለቱን ወገኖች ለማግባባትና ወደ ሰላም እንዲመጡ ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ጥረት ከፍተኛ ነው። ምንም እንኳን ሁለቱ ወገኖች አዲስ አበባ ላይ ሊስማሙ ባይችሉም፣ ኢትዮጵያና ኢጋድ ባደረጉት ጥረት ሰሞኑን የሽግግር መንግስት ለመመስረት መስማማታቸው ተነግሯል።
እነዙህ ሃይሎች ወደዚህ አቋም የመጡት የአገራችን አርአያነት በመመልከት ነው። የመደመር ፖለቲካው አንድነትን እንዲሁም ለአገርና ለሀዝብ ማሰብን የሚያጎናፅፍ መሆኑን በመረዳታቸው ነው። በመደመር አገራዊ ኩራትን መፍጠርና የህዝብን ህይወት መቀየር እንደሚቻል በመገንዘባቸው ይመስለኛል።
ይህን ስለተገነዘቡም ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች ተደምረዋል። ወደፊት ደግሞ በልማትና በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ከቀጣናው አገራት ጋር የበልጥ መደመራቸው አይቀርም። የመደመር ጥሪው ከአገራችን አልፎ ቀጠናውንም ጭምር ያቀፈ ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው።