Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፋይዳዎቹ…

0 389

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፋይዳዎቹ…

                                                            ታዬ ከበደ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ቀደም ሲል በአገር ውስጥ ያካሄዷቸው ጉብኝቶች በኢትዮጵያውያን መካከል ብሄራዊ መግባባትን ያጠናከረና የሰላም ስጋታችን በእጅጉ እንዲወገድና በዚህም ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው።

በተጨማሪም በውጭ አገራት ያካሄዷቸው ጉብኝቶች፤ ለአገራችን ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን ያስገኙልን ሆነዋል። ጉብኝቶቹ እንደ አገር ወገኖቻችንን ከእስርና እንግልት የመታደግ፣ ለአገራችን ጠቃሚ የኢንቨስትመንት መስህቦችን ማምጣት ከመቻላቸውም በላይ፤ ከአካባቢው አገራት ጋር መልካም ትስስሮችን የፈጠሩ ናቸው። በዚህም ለአገራችን ዘላቂ ሰላምንና ልማትንና እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ችለዋል። እርግጥም የጉብኝቶቹን ፋይዳዎች በርካታ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡ በጥቂት ወራቶች ውስጥ ያካሄዷቸው የተለያዩ ሀገራዊ መድረኮች ውጤታማና ለቀጣይ የሪፎርም ስራዎች ግብዓት የተገኘባቸው ናቸው።

ተግባሮቹ ቀጥተኛ የህዝብ ተሳትፎ መድረኮቹ ዴሞክራሲያዊ ውይይቶችን እውን አድርገዋል። በተጨማሪም የአገልግሎትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በግልፅ የተነሱባቸውና የሰላም መድረኮች ናቸው።

መድረኮቹ የህዝብን አብሮነትና ሰላም ያረጋገጡ እንዲሁም ብሄራዊ መግባባትን በመፍጠር ረገድ ውጤታማዎች ሆነው አልፈዋል። መድረኮቹም ተጠናክረው ይቀጥላሉ። ሰሞኑን በደቡብ ክልል የተፈጠረውን ግጭት በመፍታት ከህዝብ ጋር የሚያደርጉት ውይይቶችም ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግም ግብዓቶች የሚገኙባቸው ይሆናሉ።

ቀደም ሲልም በሀገር ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች ያካሄዷቸው ቀጥተኛ የህዝብ የውይይት መድረኮች ውጤታማና የታሰበላቸውን የሰላም ግብ ያመጡ ናቸው። ሰላም በውይየትና በህዝብ ፍላጎት እውን የሚሆን ነው። ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ባደረጓቸው ውይይቶች ማረጋገጥ ተችሏል። ይህም በአሁኑ ወቅት እየጎለበተ ያለውን አገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባትን የፈጠረ ነው። ባለፉት ጊዜያት አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ታስቦና ታልሞ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማምጣት የተከናወነ ጉዳይ አናሳ መሆኑ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት ግን አንድነትን በማጠናከር ጉልህ ለውጦች እየታዩ ነው። ይህም ከጠንካራ አመራር፣ ከህዝቡ ሰላም ፈላጊነትና ከምንከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት የመጣ ነው።

እርግጥ በአገራችን በመገንባት ላይ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ ደርሷል። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው በአንድነት የሚኖሩበትን አስተማማኝና ህዝቦችን ተጠቃሚ ያደረገ ሥርዓት መፍጠርም ተችሏል።

ይህ ሁኔታም ፌዴራላዊ ሥርዓቱ አንድነትን ለሚያጠናክሩና መሰረቱን ለሚያሰፉ እንጂ ባለማወቅ ወይም ሆን ተብሎ በሚፈፀም አስተሳሰብ ሳቢያ የሚፈጠሩ ብሔር-ተኮር ግጭቶች እንዳይስፋፉ ያደረገ ይመስለኛል። መንግስት የታገለለትንና በህገ መንግሥቱ ውስጥ ተካትቶ ዛሬም ሆነ ነገ በፅናት የሚያምንበትን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የማይገሰሱ መብቶች ላይ ከቶም ቢሆን ድርድር የሚያውቅ አይመስለኝም።

ይህም በተለይ በአሁኑ የለውጥ አመራር በሚገባ እየተተገበረ ነው። የኢትዮጵያዊያን እኩልነትና በሁሉም አካባቢዎች ተዘዋውሮ የመስራት መብቶች እውን እንዲሆኑ ርምጃ በመስራት ጭምር በዶክተር አብይ የሚመራው የለውጥ አመራር እየሰራ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብይ አማካኝነት በውጭ ሀገራት የተካሄዱት ጉብኝቶችም ዲፕሎማሲውን ውጤታማ ያደረጉ ናቸው። የኢትዮጵያ የወጪ ንግድን 90 በመቶ በምታስተናግደው ጂቡቲ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በነበራቸው ቆይታ ከፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ በተለይ ኢትዮጵያ በጂቡቲ ወደብ ልማት ላይ ድርሻ እንዲኖራት ጠይቀዋል።

የእርሳቸው የመጀመሪያ የውጭ ጉዟቸው መዳረሻ ያደረጓት ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ እንድትተሳሰር፣ በሁለቱም መንግሥታት ጥረቶች እንደሚደረጉ ቃል ተገብቷል። ጂቡቲ ኢትዮጵያን ትኩረት በማድረግ በዋናነት ለገቢና ለወጪ ንግዶቿ አገልግሎት ለመስጠት ያለመውን የዶራሌህ ወደብን በ660 ሚሊዮን ዶላር ገንብታ ለአገልግሎት ማብቃቷ ይታወሳል። በዚህ ወደብ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ የ45 በመቶ የዋጋ ቅናሽ አድርጋለች። ይህም በተከታታይ ሲሰራ የመጣው የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ውጤት ነው።

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጂቡቲ ፓርላማባደረጉት ንግግር “ሁላችሁም እንደምታውቁት ታሪካዊ ግንኙነታችን ተምሳሌትነቱ ለኢጋድ አባል አገሮች ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አገሮችም ጭምር ነው። ግንኙነታችን የተለየ ነው። አንድ ዓይነት ሕዝብ ግን በሁለት ሉዓላዊ አገሮች የምንኖር ነን። የኢኮኖሚ ውህደቱን ይበልጥ ለማሳደግና ለማጠናከር እንሠራለን” ማለታቸው በሀገራቱ መካከል ያለው ጠንካራ ግንኙነት ምን ያህል ስር የሰደደ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

በሱዳንና በኬንያ የደረጉት ጉብኝትም ጠንካራ የዲፕሎማሲያዊ መሰረት የጣለ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያደረገችውና በሱዳን ወደብ ድርሻ እንዲኖራት ያላት ፍላጎት፣ በወደብ አገልግሎቶች ላይ የሚከፈለው ዋጋ ተመን ላይ የውሳኔ ድምፅ እንዲኖራት የሚያስችላት ነው።

ኢትዮጵያ በጂቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ የሆነ የወደብ ተጠቃሚነቷን  ለማቃለል የሱዳን ወደብ እንደ አማራጭ መቅረቡ ጠቃሚ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሱዳን ቆይታ የታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ፣ በሁለቱ አገሮች ድንበር አካባቢ ስለሚካሄዱ የንግድ እንቅስቃሴዎችና በጋራ የወደብ ልማት ላይ ያተኮሩ ነበሩ።

ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር በምታደርገው የሁለትዮሽ ውይይት ማንም ሳይጎዳ የጋራ የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ላይ እንደምታተኩር በወቅቱ ግልፅ አድርጋለች። ሱዳንም ሁለቱ አገሮች ቀጣናዊ ሰላምና ደህንነት ላይ በትኩረት እንሰራለን ብላለች።

ሱዳን ለአካባቢው ሰላምና ደህንነት በጋራ ለመስራት እንደምትፈልግ፣ በተለይ በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት በኢጋድና በሁለትዮሽ መንገዶች የምታከናውን ተግባር እንደምታጠናክር፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የተስማማንባቸውና የሱዳን አቋም የሆኑ ጉዳዮች አሁንም እንደሚጠበቁ ማስታወቋ ከሀገራችን ጋር በሁለትዮሽና በቀጠናዊ ጉዳዩች አብሮ ለመስራት ያላትን ፍላጎት የሚያረጋግጥ ነው።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊያፋጥኑ የሚችሉ መሠረተ ልማቶች እስከመዘርጋት የደረሰ ነው። ሱዳን ከኢትዮጵያ የምትገዛው 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይልና ሁለቱን አገሮች የሚያገናኘው የአውቶቡስ ትራንስፖርት ከዓመት በፊት መጀመሩ የግንኙነቱን ደረጃ የሚያሳዩ ናቸው።

ዶክተር አብይ በሱዳን በነበራቸው ቆይታ በሱዳን በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የተከናወነ ነው። ይህም ዜጎችን ከእንግልት የመታደግ ተግባር ነው።

በኬንያ፣ በኡጋንዳና በግብፅ የተከናወኑት ተመሳሳይ ጉብኝቶችም የአገራችንን ጥቅም ከማስጠበቅ ባሻገር፤ ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ለመጓዝ የተለመችው ዕቅድ በሰመረ ሁኔታ እንዲከናወኑ የሚያደርግ ነው። የጉብኝቶቹ ፋይዳዎች ዲፕሎማሲያዊ የመሪነት ሚናችንን ከፍ የሚያደርጉ እንዲሁም የህዝቦችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው።

 

   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy