Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

  “1 ሺህ ተበድሬ ይህን ህዝብ ላንጫጫው ”

0 550

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

  “1 ሺህ ተበድሬ ይህን ህዝብ ላንጫጫው ”

 

ስሜነህ

 

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ መልካም አጋጣሚዎቹን በማበላሸት ወደር የለውም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እርግማን ያለ ይመስል ከውይይት ይልቅ መተናነቅ፣ ከተፎካካሪነት ይልቅ መጠላለፍ፣ ከመደማመጥ ይልቅ መጯጯህ፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ መጠፋፋት ርስታችን የሆነ ይመስላል፡፡  

 

ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየሙት ዶክተር ዓብይ አህመድ ባለፉት ሁለት ወራት ይህ ዓረም ተወግዶ አገር በአዲስ መንፈስ እንድትነሳሳ አድርገዋል፡፡ቂምና ቁርሾን በማስወገድ ይቅር መባባል እንደሚያስፈልግ በአደባባይ እየሰበኩ ነው፡፡ ይህ መልካም ተነሳሽነት በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድም ተቀባይነት እያገኘ ነው፡፡ ይሁንና ከዚያ አሳዛኝ የመጠፋፋት ስሜት ውስጥ መውጣት ያቃታቸው ደግሞ፣ ቀናውን ጎዳና ለማሰናከል ጥረት እያደረጉ መሆኑ ከሰሞኑ እየተስተዋለ ነው፡፡ በአንዳንድ ወገኖች በማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ የሚንፀባረቀው የነውጠኝነት ባህሪ አሁንም ገና የሚቀር ሥራ እንዳለ አመላካች ነው፡፡ ሰላማዊ ነን እያሉ ሰላም ለማደፍረስ የሚተጉ፣ በዴሞክራሲ ስም እየማሉ የሌላውን መብት የሚጋፉ፣ የሁሉም ነገር ሰጪና ከልካይ ለመሆን የሚዳዳቸውና ዘመኑ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር እኩል መራመድ የተሳናቸው  በጠቅላይ ሚንስትሩ ቋንቋ የቀን ጅቦች እዚህም እዚያም እየታዩ ነው፡፡ አገር ከቂምና ከጥላቻ አስተሳሰብ ተላቃ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በፍትሐዊነት የሚስተናገዱበት ዓውድ እንዳይፈጠር፣ ዛሬም አክራሪ ብሔርተኝነትን ሙጥኝ ያሉ መኖራቸው ከሰሞኑ በሚገባ ታይቷል፡፡ ጥላቻ እስከ አንገታቸው ድረስ የዋጣቸው ደግሞ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያለያይ አደገኛ የዘር ልዩነት ቅስቀሳ እያካሄዱ ነው፡፡

 

ሌላው መሠረታዊ ችግር የኃላፊነት ስሜት መጥፋት ነው፡፡ አገርንና ሕዝብን ማዕከል ያላደረጉ ነገር ግን ሁሌም ከብሽሽቅና ከፋይዳ ቢስ ተቃርኖ መውጣት የማይፈልጉ አሉ፡፡ ለአንዳንዶቹ ይህ ድርጊት ከህልውና ጋር የተያያዘ ንግድ ስለሆነ፣ አገር ውስጥ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሲጀመር አይመቻቸውም፡፡ሥልጣኑ ከመዳፉ ውስጥ ያፈተለከበት የሚመስለው ለአገር የማያስብ ስብስብና ዕድሜ ልኩን ተቃውሞን የእንጀራ ገመዱ ያደረገ ቡድን፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መልካም ጅምር ሲታይ ያቃዣቸዋል፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው ምንድነው በማለት በጥልቀት ከመፈተሽ ይልቅ፣ የራስንና የቡድንን ጥቅም በማስቀደም የሚናውዙ ወገኖች  ዛሬም በስፋት መኖራቸው ታይቷል። ጠቅላይ ሚንስትሩ የኢድ አልፈጥር በአልን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክትና በዚሁ ቀን ይህ ጸሃፊ በቀጥታ ስልክ የሬዲዮ ውይይቱ ከተሳታፊ አድማጮቹ የተገነዘበውም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።

 

አሁን ባለው ሁኔታ የእነዚህን ሃገር አጥፊ ሃይሎች አሉባልታ እየሰማን የምንጽፈው ጽሑፍ፣ የምንለጥፈው ፎቶ፣ የምንሰጠው ትምህርት፣ የምናቀርበው ምስክርነት፣ የምንሠራው ሥራ፣ የምንለግሰው ሐሳብና የምንገልጸው አቋም የቆምንበትን ዓላማ ለማስረዳትና አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት መሆኑ ቀርቶ ሌላውን ለማናደድ፣ ለማቃጠል፣ ለማበሳጨት፣ አንጀቱን ለማሣረርና ቆሽቱን ለማድበን፣ ጨጓራውን ለመላጥና ጥሎ ለማንኮታኮት እየሆነ መሆኑን ያስተዋልን አይመስልም ፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ የመንግስትም ችግር ያለ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። የኮሙዩኒኬሽን መዋቅሩ ጠቅላይ ሚንስትሩ በሰጡት አቅጣጫ ልክ እየተመራና እየሰራ አይደለም።

 

አሁንም ድረስ የፀጥታ ችግሮች የሚከሰቱባቸው  አካባቢዎችን በተመለከተ የየአካባቢው የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን መዋቅር ተገቢውን መረጃ መስጠት የሚጠበቅባቸው ቢሆንም አንዳንዶች የማይሰጡበት፣ አንዳንዶች ደግሞ ቢሰጡም ተገፍተው በውጭ ሚዲያዎች ጫና እንጅ ህዝቡ ትክክለኛውን መረጃ የማወቅ መብት አለው ከሚል እንዳልሆነ ማወቅ አይከብድም። በጠቅላይ ሚንስትሩ አቅጣጫ ልክ የመረጃ ፍሰት ቢኖርማ ህዝብ ለተለያየ አሉባልታ ባልተጋለጠ ነበር።  ስለሆነም ማህበራዊ ሚዲያው የእነዚህ የቀን ጅቦች መስሻ ቦይ ሆኗል።

ዳንኤል ክብረት ይህንኑ በመታዘብ ሰሞኑን ባሰፈረው መጣጥፉ ‹ጠላት እርር ይበል›፣ ‹እነ እንትና ቅጥል ይበሉ›፣ ‹እገሌዎች ዓይናቸው ደም ይልበስ›፣ ‹አንጀታቸው ይረር፣ ደማቸው ይምረር› የሚሉት አገላለጦች ማኅበራዊውን ሚዲያ እያጥለቀለቁ ነው፡፡” በብሽሽቅ የሚገኝ ድኅነት፣ የሚሳለጥ ፖለቲካ፣ የሚገነባ ሀገር፣ የሚሠለጥንም ሕዝብ አይኖርም፡፡ የሚኖረው ሰሞኑን በደቡብ የተመለከትነው አይነት መተላለቅ እና መፈናቀል ነው።  የሚቀርቡልንን መረጃዎች ሳናላምጥ ከመዋጥ አባዜ እስካልወጣን እና የሚመለከተንን እንደየድርሻችን ካልሰራን በስተቀር በማያገቡን ጉዳዮች ላይ ሁሉ ጥልቅ ማለትን እስካላቆምን ድረስ አደጋው የሚቀጥል እንደሆነም አያጠያይቅም። አንዲቷ አድማጬም እንዲህ ነበር ነገሩን ያጠነከረችልኝ።

 

ሴትዮዋ ምስኪን ለማኝ ነበረች የምትለው አድማጭ “ይህች ለማኝ ለማኝ ሆና እንዲህ ያማረባት እንዴት ነው፤ የሚለውን የአካባቢው ነዋሪዎች ሃሜት ትሰማና ቢገርማት አንድ ቀን ትነሳና ይህን ህዝብ 1 ሺህ ብር ተበድሬ ላንጫጫው ትላለች።እንዳለችው ምሽት ሲገባ 10 ብር ያስለመዳትን ባለሃብት ነዋሪ ጋሼ የዛሬ ሳምንት በዚህ ሰአት የምመልሰው  1ሺህ ብር ያበድሩኝ ትላለች።ጋሼም ቆጠር ቆጠር አድርገው ይሰጧታል። ይህን ያየች አንዲት ጎረቤት ከየት አምጥታ ልትመልስ ነው በማለት ለሌላኛይቱ ጎረቤት ተነፈሰች። ሰፈሩ ሁሉ ከየት አምጥታ ልትመልስ ነው በሚል ሳምንት ስራ ፈታ።ተበዳሪት አስቀድሞ ልታንጫጫ ነበርና ተበድራ ምንም ሳታጎድል ያስቀመጠችውን ገንዘብ ባለችው ቀንና ሰዓት ስትመልስ የተመለከተ ህዝብ በመመለሷ ሳይደነቅና ሳያፍር ከየት አምጥታ ነው የመለሰችው ሲል ሌላ ጫጫታና ስራ መፍታቱን ቀጠለበት” ዛሬም እየሆነ ያለው ተመሳሳይና በአሉባልታ መነዳት ነው።

 

የጠቅላዩም የኢድ መልእክት የሚያጠይቀው ይህንኑ እና የአደጋውን ልክ ነው። በኢትዮጵያችን በሙስሊሙ በአል ክርስቲያኑ፤ በክርስቲያኑ በአል ዋቄፈታው፤ በኢድ- በፋሲካው- በገና በእሬቻው የእንኳን አደረሰህ፣ እንኳን አደረሰሽ ቅብብሉ መልካም ምኞት እስከታከለበት ዝይይር በሚዘልቅ የፍቅር ሸማ ተከብክቦ ይሄው ዛሬ ደርሷል፡፡ ቅዱሱ የረመዳን ወር፣ የጾም፣ የጸሎት እና ከፈጣሪ ጋር የመገናኛ ልዩ ወር እንደመሆኑ መጠን፣ ኢድ አልፈጥርም፣ የፍቅር እና የበረከት፤ የይቅርታ እና የአብሮነት ድንቅ በአል ነው፡፡

 

የምንሳሳላቸው፣ የምናከብራቸው፣ የምንወዳቸው እና መስከረም ጠብቶ አዲስ ወር በባተ ቁጥር “ሊመጡልን ነው…” በሚል ጉጉት በስስት የምንናፍቃቸው መንፈሳዊ እሴቶቻችን ሁሌም የደስታችን ምንጭ የሚሆኑት እና በአብሮነታችን ውስጥ እያደር የሚፈኩትበፍቅር የሚደምቁት ይህች ሀገር ሰላም ስትሆን ብቻ ነው፡፡

 

የሀገራችን ሙስሊሞች እና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንደሁልጊዜው ሁሉ በረመዳን ወር የነበሩንን የሰላም፣ የመረዳዳት፣ የመከባበር እና የመጠያየቅ ባህል በማስቀጠል የሀገራችንን ሁለንተናዊ ለውጥ እና ህዳሴ ለማረጋገጥ የበኩላችሁን እንድትወጡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ ይህ መልእክት ከባድ ትርጉም ያለውና የስጋቱን ደረጃ የሚያሳይ ነው።  

 

የሰው ልጅ በተፈጥሮ ከመኖር የሚቀድም አላማ የለውም ፡፡ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ፤ ወልዶ ለመሳም፤ ዘርቶ ለመቃም እና የህይወትን በረከቶች በሙሉ ለማጣጣም ፤ ሰላም መተኪያ የሌለው ብርቱ መሳሪያ ነው ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት እያጋጠሟት የነበሩት ቀውሶች እና ህዝቧን ስጋት ላይ ጥለው የነበሩት ግጭቶች ተወግደው ሁሉም ዜጋ በሰላም መኖር ይችል ዘንድ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል ፡፡ ነገር የተበደሩ ባየንና ባበደሩን ቁጥር የምንጫጫ ከሆነ ግን ጥረቱ ሁሉ ከንቱ መሆኑ አያከራክርም።

 

የመንግስት ፣ የህዝብና የወዳጆቻችን ጥረትና ምኞት ፍሬ አፍርቶ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በመላ አገራችን ሊያሰኝ በሚችል መልኩ አንጻራዊ የሰላም አየር መንፈስ በመጀመሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰላማዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል ፡፡ በአገራችን ውስጥ እያከናወንናቸው ያሉ የለውጥ እንቅስቃሴዎችና በውጭ አገርም ያስመዘገብናቸው ዲፕሎማሲያዊ ድሎች የዚሁ ሰላምና መረጋጋታችን ውጤቶች ናቸው ፡፡አሁን ላለንበት ነባራዊ ሁኔታ እንድንበቃና በተሻለ አገራዊ ቁመና ላይ እንድንገኝም ዋናው ተዋናይ ህዝብ ነው፡፡በየማህበራዊ ሚዲያው ከቀን ጅቦች ነገር እየተበደረ የሚያንጫጫንን ጥቂት ሃይል ደግሞ ይህ ሰፊ ህዝብ በብስለት ፤ መንግስት ደግሞ በመረጃ ፍሰት ሊያመክኑት ይገባል።

 

መንግስትም ህዝቡን በማሳተፍና ያለመታከት በመስራት የዜጋውን ጥያቄ ለመመለስ በፍጹም ቁርጠኝነት መንፈስ በመስራት ላይ የሚገኝ ስለመሆኑ የጠቅላይ ሚንስትሩ የለት ተለት እንቅስቃሴዎች እያረጋገጡ ነው ፡፡ ይኸው ትግል ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነም አያያዛቸው እያመላከተ ነው ፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች፤ ጥረት ውጤቶቻችንን ከማጨናገፍና ሩጫችንን ከማደናቀፍ ውጪ፤ ለማንም ምንም የሚበጁ አይደሉም ፡፡ ከነዚህ የነውጥ ድርጊቶችም የሚያተርፍ አንድም ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ በፍፁም አይኖርም ፡፡

 

ያለ ሰላም እስከየትም መጓዝ አንችልም ፡፡ ያለ ሰላም የምናስበው ብልፅግናና እድገት ፤ ለውጥና ታላቅነት ፤ ፍቅርና ማህበረሰባዊ ልህቀት በአገራችን ሊሰፍኑ አይችሉም፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ ፤ ለሰላሙና ለሃገራዊ አንድነቱ ዘብ የመቆም ሃገራዊና ሞራላዊ ግዴታ አለበት ፡፡ በዋናነት ግን የሁሉ መጀመሪያ የሆነውን ነገር ላለመበደር ማስተዋልን ይጠይቃል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy