Artcles

ከህዝብ በላይ ማን ይታመናል?

By Admin

June 06, 2018

ከህዝብ በላይ ማን ይታመናል?

                                                    ዘአማን በላይ

አሳማኝና ጆሮ ገብ ነው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ያደረጉት ንግግር። አዋጅን ማንሳት ቀርቶ፤ ቢያጸኑም እንኳን የሚያነሷቸው የሃሳብ ደርዞች ፈር ያላቸውና መሰረታዊ ናቸው። ምንም እንኳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲታወጅ እርሳቸው በጠቅላይ ሚኒስትርነት ባይሰየሙም፤ በተመረጡ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ አዋጁ መነሳቱን ሲገልፁ፤ ያነሱት ሃሳብ ዓይንና ጆሮን የሚስብ እንዲሁም ህዝብን የማመን ዳርቻዊ አፅናፍ እስከ የትኛው ጫፍ ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል ያሳየ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ታዲያ የአዋጁን መነሳት በእዝነ ልቦናዊ አርምሞ የተመለከተ ማንኛውም ሰው፤ ዶክተር አብይና መንግስታቸው በህዝብ ላይ ያላቸውን የአመኔታ ልኬታ ደርዝ ከፍታን ቀና ብሎ ሊመለከተው ይችላል። እኔም የተመለከትኩት እዚያ ከፍታ ላይ ነው። ማማው ላይ።

በእኔ ግላዊ ብያኔ መሰረት፤ ህዝብ የየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ምሶሶና ማገር ነው። ህዝብ ሉዓላዊ ስልጣን ያለው ኃይል ነው። ህዝብ በችግር ጊዜ ብርታትና ተቆርቋሪ ምርኩዝ እንዲሁም በተድላና ፍሰሐ ወቅት የማይነጥፍ ወዳጅ ነው። ህዝብ ከሀገሩ ሰማይ በታች የማያውቀው፣ የማያየው፣ የማይሰማው የማያገናዝበው ጉዳይ የለም።

ህዝብ ሚዛናዊ ነው። ማናቸውንም ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዩችን በትክክለኛው ሚዛን ላይ አስቀምጦ ይሰፍራል። ስፍሩም አያጋድልም። አይዛነፍም። ትክክል ነው። እንደ ፍትህ ሚዛንም 180 ዲግሪ ቀጥ ያለ የጎንዮሽ መስመር ነው። ታዲያ ይህን የሀገር አድባር፣ ምሶሶ፣ ወጋግራና ሁሉን-አወቅ ባለ ስልጣን ኃይል በምን ዓይነት አመክንዮ አለማመን ይቻል ይሆን?…አዎ! ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና መንግስታቸው ይህን መሰሉን ህዝብ ማመናቸው ተገቢ ነው።

በእኔ እምነት፤ ይህን የህዝብ ጥቅል ብያኔ ወደ ሀገራችን ስንመልሰው፤ የታላቋ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝብ ዶክተር አብይ እንዳሉት፤ የረጅም ዘመን ታሪክ ያለው፣ አኩሪና በዘመን የተፈተነ የአብሮነት ልክ የማይደራደርበት የሞራል ጥግን ያካበተ ነው። እንዲሁም ራሱንና ሌሎችንም ጭምር የሚጠብቅበት ባህላዊ የሰላም መቀነቻ ድግና ትላንቱን ዘክሮ፣ ዛሬውን መርምሮና ነገውንም ተንብዮ ሀገር አድባሩን በሰላም የሚሞላ ነው። እንዲህ ዓይነት ህዝብ ላላት ድንቅ ሀገር ኢትዮጵያ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ከቆየችው በላይ ትቆይ ዘንድ የሚመጥናት አይሆንም። እናም አዋጁ እንዲሳ መደረጉ መነሻውና መድረሻው ይኸው ኩሩና ሰላም ወዳድ ህዝብ ነው። ይህን የምለው በውስጤ ያለው ኢትዮጵያዊ ማንነቴ ነሸጥ አድርጎኝ አሊያም የህዝቡ አካል በመሆኔ ‘እኛ እንዲህ ነን’ ከሚል የመታበይም መንፈስ በመነጨ አይደለም—የሀገሬ ህዝብ ትክክለኛ መገለጫው ይኸው ስለሆነ እንጂ።

አዎ! የኢትዮጵያ ህዝብ ኩሩና ጨዋ እንዲሁም በሰላሙ ጉዳይ ፈፅሞ የማይደራደር ነው። ይህ ህዝብ የሰላምን ጠቀሜታ በሚገባ ያውቃል። ሁሌም በየአካባቢው ለሰላሙ ዘብ እንደቆመ ነው። አይታክትም። በመጀመሪያውም ይሁን ለሁለት ወራት በቆየው ሁለተኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት መሪ ተዋናይ በመሆን ቀየውን ዋስትና ሰጪ ኃይል ሆኖ ጠብቋል። ይህ ህዝብ ከኮማንድ ፖስቱና ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ተቀናጅቶ ያከናወናቸው ሰላምን የማረጋገጥ ተግባሮች ይህን ሃቅ እጃቸውን አውጥተው የሚሰክሩ ናቸው። ለዚህም ይመስለኛል— ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ “…የሀገራችን እና የህዝቦቿ ሰላም ከውጫዊ አዋጅና ክልከላ ሳይሆን ከዜጎች ፍላጎትና የሰላም ወታደርነት የሚፍለቅ እንዲሆን ጥረት ተገርጎ በሁለት ወራት ውስጥ አንፃራዊ ሰላም ተገኝቷል” ያሉት።

አዎ! አዲሱ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ በርካታ ነገሮች ተለውጠዋል። አመራሩ ሰላማችንን በአጭር ጊዜ እንድንጎናጸፍ አድርጎናል። ከሁከት፣ ከብጥብጥና ከስጋት የሰርክ ሃሳብ ወጥተን ወደ አንፃራዊ ሰላም ጥርጊያ መንገድ አቅንተናል። ይህ የሆነውም በዋነኛነት ህዝቡ የሰላሙ ባለቤት እንዲሆን በመንግስት በኩል በርካታ ስራ በመከናወኑ ነው።    

ርግጥ ኩሩው የሀገሬ ህዝብ በሁለቱም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ወቅት፤ ወጣቶችን ከጥፋታቸው የመመለስ፣ የተሃድሶ ትምህርት ከወሰዱም በኋላ ወደ የቀያቸው ሲመለሱ ምክርና ተግሳፅ የመስጠት እንዲሁም የየአካባቢያቸውን ሰላም በኃላፊነት ስሜት እንዲጠብቁ በማስተባበር ወደር የሌለው ስራዎችን ሲከውን ነበር። ይህ ክዋኔውም፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰላምን በጊዜያዊነት እንጂ፣ በዘላቂነት መዋጀት እንደማይቻል እንዲሁም ያለ ህዝቡ ፍላጎትና ይሁንታ የሰላም ጥርጊያ መንገድ ሊዘጋጅ እንደማይችል በግልፅ የሚያስረዳ ይመስለኛል።  

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ሁለተኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት ምክንያትን ሲገልፁ፤ አዋጁ ለነበርንበት ችግር ወቅቱ የሚጠይቀው አማራጭ ውሳኔ ሆኖ ቢያሻግረንም፤ ለማደግና ለመለወጥ እንደሚታትር ታላቅ ህዝብ ደግሞ ያስከተላቸውና የሚያስከትላቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች መኖራቸው የማይካድ ነው ብለዋል። ትክክል ነው። ርግጥም አዋጁ የታወጀው ሀገራችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባጋጠማት የፖለቲካ አለመረጋጋት ሳቢያ የሰላም እጦት በመከሰቱ ነው። አዋጁ በጊዜዊ መፍትሔነትና በህዝቡ ፍላጎት ሰላማችን ወደ ነበረበት እንዲመጣ እንዲሁም ለተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዩች ምቹ ሁኔታዎችን ቢፈጥርም፤ ያጣናቸው ነገሮች ግን የሉም ማለት አይቻልም።

በእኔ እምነት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለበት ሀገር ውስጥ የሚፈለገውን ያህል ኢንቨስትመንት ማንቀሳቀስ አይቻልም። የውጭም ይሁን የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በሀገር ውስጥ መዋዕለ ነዋያቸውን ደፍረው ሊያፈሱ አይችሉም። በገፅታ ግንባታም በኩል በጎ ምስል የሚያሰጥ አይደለም። “ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ” በመባል የሚታወቀው የቱሪዝም መስክም የተፈለገውን ያህል ጎብኚዎችን ሊያስተናግድ አይችልም።

ታዲያ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት እንደ ሀገር ለመከወን በታሰበው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ አሉታዊ ለውጥ ማስከተሉ አይቀርም። ህዳሴያችንን ባያቆመውም፣ በነረበት አሊያም በላቀ ፍጥነት እንዳይጓዝ ሊያደርገውም ይችላል። በመሆኑም ሁለተኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሁለት ወራት በላይ እንዳይጓዝ በመንግስት በኩል መወሰኑ፤ የምናጣቸውን ነገሮች መልሰን እንድናገኛቸው የሚያደርገን በመሆኑ ውሳኔው ምስጋና ሊቸረው የሚገባ ነው።

ከሁሉም በላይ ውሳኔው በአጠቃላይ በሀገራችን ህዝብ ላይ እምነት በመጣል የተደረገ መሆኑ እንደዜጋ እንድንኮራ የሚያደርገን ነው። ይህ እምነት የተጣለበት ህዝብ፤ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎችን፣ በየደረጃው የሚገኙ የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎችን፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባሎች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት አባቶችን ያካትታል።

በተጨማሪም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና የሚዲያ ሰዎች፣ የሀገራችን ምሁራንና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ በውጪ ሀገሮች የዚህች ሀገር ደግ ቀን እንዲነጋ በተለያዩ መንገዶች በማድረግ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖችን አደራ የሚል ነው። ይህ ባለ አደራ የሀገሬ ህዝብ መጪውን ጊዜ ሰላም በማድረግ የሀገሪቱን ጥሪ እንደሚመልስ ጥርጣሬ የለኝም።

ርግጥ ለሰላሙ ቀናዒ የሆነው ኩሩው የሀገሬ ህዝብ ካልታመነ ሌላ ማንም ሊታመን አይችልም።…ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ስለ ማንሳትና ህዝቡንም ወደ መደበኛው የአስተዳደር፣ የህግና የፍትህ መስመር ስለ መመለስ ሲያስብ፤ አዋጁን ለማወጅ ካስገደዱት ተግዳሮቶች አንጻር ያለውን ችግር በተመለከተ የመፍትሄውን ቁልፍ በማግኘት በኩል ሙሉ እምነቱ ያለው በህዝቡና በህዝቡ ላይ ብቻ ነው” በማለት የገለፁት የዚህን ህዝብ ሰላም ወዳድነት እንዲሁም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተፈጠረውን ውስጣዊ አንድነቱን ከግምት ውስጥ አስገብተው ይመስለኛል።

ርግጥ በህዝብ ላይ እምነቱን የጣለ የትኛውም ወገን አትራፊ ነው። “ምንትስን ያመነ፣ ጉም የዘገነ” የሚለው አሮጌ አባባል፤ ከህዝብ አኳያ ቦታ የለውም አይሰራም። ይልቁንም ህዝብን ያመነ እንኳንስ በተከታታይ ጥረት ሊመጣ የሚችልን ሰላምን ቀርቶ ጉምንም ቢሆን ሊዘግን የማይችልበት ምክንያት አይታየኝም። እናም በህዝብ ላይ አመኔታን መጣል ራሰን መልሶ የሚከፍል አስተሳሰብ ነው—ማንኛውም ተግባር ገቢራዊ የሚሆነው በህዝብ ፍላጎትና ዋስትና ብቻ ነውና።

አዎ! ህዝብን በማመን ተአምር መስራት ይቻላል። የሰውን ልጅ በማመን ውስጥ ያለውን አዎንታዊ ዋጋንም መቀበል ይቻላል። በአንፃሩም ህዝብን ያላመነና ለህዝብ ያልታመነ የትኛውም አካል ራሱን ሊያምን በራሱም ሊታመን ስለማይችል፤ ማመን ከቻለው ወገን ተቃራኒውን “ክፍያ” ማግኘቱ የሚቀር አይመስለኝም።  

ያም ሆኖ ኩሩው የሀገሬ ህዝብ፤ ሰላሙ የልማቱ፣ ሰላሙ ዕድገቱ፣ ሰላሙ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱ መሰረት መሆኑን በሚገባ ቢያውቅም ቅሉ፤ ወደ ነበርንበት የቀውስ አዙሪት እሽክርክሪት ውስጥ ተመልሰን እንድንገባ የሚሹ አንዳንድ ሃይሎች መኖራቸውን መገንዘብ ይኖርበታል እላለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም “መንግስትና ህዝብ አዋጁን በማንሳት የሀገራችንን ሰላምና የዜጎችን ደህና ወጥቶ ደህና የመግባት መብት፣ ምኞትና ጸሎት እውን ለማድረግ በሚታትሩበት ወቅት፤ ጉዳዩን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመግፋትና ዞረን ተዟዙረን የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንድንዳክር ለማድረግ የሚጥሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ሊኖሩ የመቻላቸውን ነገር ለአፍታም ቢሆን ቸል ልንል አይገባም” በማለት የገለፁት ይህን እውነታ ለማሳየት ይመስለኛል።

የሀገሬ ህዝብ ባለፉት ጊዜያት እነዚህን ሃይሎች የሰላም በትርን ይዞ እንደተቋቋማቸው ሁሉ፤ ነገም ይሁን ከነገ በስቲያ የሰላም ባለቤትነቱን የበለጠ በማጠናከር በየቀየውና በየደብሩ ለሰላሙ ወታደር መሆን ይኖርበታል እላለሁ። ምክንያቱም አዋጁ የተነሳው ህዝብንና ህዝብን ብቻ በማመን ስለሆነ ነው። ከህዝብ ወዲያ የሚታመን አካል ስለሌለም ነው። የሰላሙ ባለቤነት በእምነት ላይ ተመስርቶ ጫንቃው ላይ እንዲያርፍ የተደረገው ይህ ህዝብ፤ በወሮታው ለመንግስት የሚከፍለው ነገር ቢኖር የሚገኝበትን ቀየ፣ አድባርና አውጋር በንቃት በመጠበቅ ሰላሙን ማረጋገጥ ብቻ ነው። ሰላማችን ይብዛልን!