Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህ.ወ.ሓ.ት እና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ።

0 1,113

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህ.ወ.ሓ.ት እና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ።
(TPLF & Democracy In Ethiopia)

አዘጋጅ ፣ ልኡል ገብረመድህን (ከአገረ-አሜሪካ)
ወረሐ ሰኔ 2018.
ግላዊ ትንተና ።

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ አስከፊ የደርግ ስርአት በትጥቅ ከተፋለሙት ቀደምት ድርጅቶች አንዱ ነበር። ይህ ድርጅት ትግል ሲጀምር በቂ የተደራጀ የስው ኃይልና ትጥቅ አቅርቦት እንዳልነበረው የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።ድርጅቱ (ህ.ወ.ሓ.ት) በ1960ዎቹ ወደ ትግል ሜዳ ለመዝመም ካስገደዱ ምክንያቶች አንዱ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ስርአት ዲሞክራሲ አልባ ፣ አምባገነንና ጨቋኝ (Dictatorship ) ሰለነበረ ነው። ለትግሉ የተመረጠ ቦታ የአሁኑ የትግራይ ክልል ልዩ ቦታው ደደቢት ነበር። በእርግጥ የድርጅቱ ቁመና በጥልቀት የሚያሳይ በፅሁፍ የተከሸነ እንዲሁም በአግባቡ የተደራጀ መረጃ እስከአሁን ባላገኝም ባለኝ የተጨለፈ መረጃ መሠረት ህ.ው.ሓ.ት አነስም በዛም ግርድፍ የመታገያ ፅንስ -ሀሳቦች (declaration of policies and strategies ) እንደነበሩት በግሌ እገነዘባለሁ።
የህ.ወ.ሓ.ት ትግል መነሻ የነበሩ ሶስት ጣምራ አበይት መሰረተ ሃሳቦች ስላም፣ዲሞክራሲና ልማት ነበሩ። የእነዚህ  መሰረተ ሐሳቦች ጠቀሜታና ባህሪ ዘመን ተሻጋሪ ነው። ዲሞክራሲ የመብት ተሟጋች ነው።ልማት የኢኮኖሚ ዋልታ ነው። ስላም ደግሞ የሁሉም ገዢ ነው። የትግራይ ህዝብ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ባለፉት  ስርአቶች በደልና ጭቆና ተደርሶበታል ። የተፈጥሮ ድርቅ በአንድ ጎን በሌላ ጎን ደግሞ ሰው ሰራሽ (የስርአት)  በደሎች በተለይ ለትግራይ ህዝብ ፈታኝ ክስተቶች ነበሩ። የትግራይ ህዝብ በነበረው  የኑሮ ችግርና የሰላም እጦት ምክንያት የደርግ ስርአት በትግል ለመለወጥ በአካባቢው ይንቀሳቀስ ለነበረው ህ.ወ.ሓ.ት ሁሉም አይነት ድግፍ ያደርግ ነበር። ህ.ወ.ሓ.ት በ1977 ዓ.ም በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ድርቅ የትግራይ ህዝብ የከፋ ጉዳት ሳይደርስበት ህዝቡ ወደ ሱዳን ማሻገር ችሎ ነበር።

ህ.ወ.ሓ.ት ባካሄደው መራር የትጥቅ ትግል ብዙ ፈታኝ ችግሮች አሳልፏል። ከችግሮች ውስጥ በየወቅቱ የሚያጋጥሙ ጥቅል ድርጅታዊ ችግሮች ነበሩ። ለምሳሌ ፣ የአመለካከትና የሀሳብ ልዩነት የሚስተናገዱበት አካሄድ በከፊል የዲሞክራሲ ባህሪዎች ነበራቸው። ኢዲሞክራሲያዊ የሆኑ ድርጅታዊ እርምጃዎችም ይወስዱ ነበር። የህ.ወ.ሓ.ት መስመር ያልተከተለ ህዝብ እንዲሁም የህ.ወ.ሓ.ት አባል  አስፈላጊ ያልነበሩ ፍረጃዎችና የስነልቦናዊ ችግሮች  ይደርስበት ወይም ይገለል ነበር።  ታጋይ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ (በሪሁ) በህ.ወ.ሓ.ት ትግል ውስጥ በክብርና ጀግንነት የሚዘከሩ ተወዳጅ የህዝብ ልጅ ናቸው። ህ.ወ.ሓ.ት ሲነሳም ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ስማቸው አብሮ ይነሳል። ምክንያቱም በትግራይ ህዝብ የተከበሩና የተወደዱ በሳልና አርቆ ተላሚ የህ.ወ.ሓ.ት መሪና ታጋይ ነበሩ። ዶ/ር አረጋዊ በርሄ የትግራይ ህዝብ ችግርና ፍላጎት በአግባቡ የሚረዱ ፣ ከህዝብ ጋር የወገኑ ፣ የትግራይ ህዝብ ብሎም የኢትዮጵያ ህዝብ የኢኮኖሚያዊ ኑሮው እንዲሻሻል ራአይ የነበራቸው የህዝብ ልሳን ነበሩ ክቡር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ። እኝሁ ሰው ከህ. ወ.ሓ.ት አመራሮች በነበራቸው የሀሳብ ልዩነት በድርጅቱ  ደንብና አሰራር ሳይሆን ኢዲሞክራሲያዊ በሆነ ካድሬያዊ አሰራር ከትግራይ ህዝብና ከድርጅታቸው ህ.ወ.ሓ.ት በሻጥር እንዲወገዱ ተደረገ ። ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በትጥቁ ግዜ ተራማጅ ሃሳብ (progressive thinking )የነበራቸው እንዲሁም የብሄር ፓለቲካ የማይደግፉ አርቆ አሳቢ ስው ነበሩ። ይህ አስተሳስባቸው በህ.ወ.ሓ.ት ካድሬዎች አልተወደደም ነበር። ይህ የሚያሳየው አብይ ጉዳይ ቢኖር ህ.ወ.ሓ.ት ገና ከጅምሩ ዲምክራቲክ አልነበረም። ሲቀጥልም ለይስሞላ ካልሆነ ዲሞክራሲያዊ አስራሮች(መትከሎች) =Real Democratic Tools= አልነበሩትም። ህ.ወ.ሓ.ት የሀሳብ ልዩነት የማስተናገድ ችግር ነበረበት። ህ.ወ.ሓ.ት አንድ የማይታለፍ ሀቅ አለው። ይህውም አስከፊው የደርግ ስርአት በፅናት የተፋለመ በመጨረሻም ከሌሎች አገር በቀል የትግል ድርጅቶች ጋር ለድል የበቃ ድርጅት ነው። ህ.ወ.ሓ.ት ለዚህ አኩሪ ተግባር አድናቆት ብቻ ሳይሆን ዘለአለማዊ ክብር ይገበዋል። በዚህ አጋጣሚ ከታላቅ አክብሮት ጋር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ወደ አገራቸው ተመልሶ ሰላማዊ የፓለቲካ ትግል እንዲያደርጉና የህዝባቸውን ኢኮኖሚና ፓለቲካዊ ጥቅሞች አንዲሻሻሉ የበኩላቸው አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው ስል ጥሪ አስተላልፋለሁ።

የትግራይ ህዝብ ጨቋኙ የደርግ ስርአት ለመታገል 60,000 ልጆቹ ለሞት የገበረ ህዝብ ነው። ከ 100, 000 በላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ልጆች አሉት። ታድያ ለዚህ  ህዝብ ምን ስያሜ እንስጠው? ጀግና ፣ የሰላም ሀዋርያ፣ የብርሃን አምድ፣ የድህነት ጠላት፣ የብልፅግና ፈር ቀዳጅ፣ የኢትዮጵያ ልብና አይን፣ ወይስ ሌላ ሌላ—- ይህ ሁሉ ህዝቡ ለፈፀመው አስደናቂ ትግል የሚመጥን ቃል ያለ አይመስለኝም። እኔ በግሌ የምንኮራበት ህዝብ ነው የትግራይ ህዝብ። እዚህ ላይ ብዙ ቀና ልቦና ያላቸው.ኢትዮጵያውያን የሚያነሱት ጥያቄ አለ። ይህውም ለኢትዮጵያ ስላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ የተስዋ ህዝብ ለምን ትርጉም ያለው ልማትና ዲሞክራሲ በትግራይ አልታየም በማለት ቅሬታቸው ያስተጋባሉ። ጉዳዩ እውነታነት አለው። የትግራይ ህዝብ ሌላ ቀርቶ በከተማም ሆነ በገጠር የሚጠጣ ንፁህ ወሃ ለማግኘት የሚቸገር ህዝብ ነው። በልማት ፣በመልካም አስተዳደር ፣በዲሞክራሲ ፣ በድህነት የዳከረ ህዝብ ነው።ለዚህ ሁሉ ግንባር ቀደምት ተጠያቂ መሪ ድርጅቱ ህ.ወ.ሓ.ት. ነው።ለዛም ድርጅቱ ለትግራይ ህዝብ ይቅርታ ጠይቀዋል። ህዝቡ ልማት ና መልካም አስተዳደር በማስፈን እክሳለሁ ብለዋል ። የህ.ወ.ሓ.ት. መሪዎች ከተማ ከተማ እንሽተት ብሎ የትግራይ ህዝብ ረስቶ ለ 27 አመታት የራሳቸው ንግድና ኑሮ ሲያደላድሉ የነበሩ ናቸው። የትግራይ ህዝብ በትጥቅ ትግሉ ለህ.ወ.ሓ.ት ዋስትና ነበር ።በብዙ ምክንያቶች አሁን ግን አይደለም። ከምክንያቶቹ አንዱ ህዝቡ የከፈለው ዋጋ በልማት ፣በመልካም አስተዳደርና በዲሞክራሲ አልተደበስም።ታድያ ምን ገዶት ነው ለህ.ወ.ሓ.ት ዋስትና የሚሆነው?።

ህ.ወ.ሓ.ት የትግራይ ህዝብ እንደባንክ ተቀማጭ ገንዝብ ይገለገልበታል። በትግራይ ህዝብ ይነግዳል። ህ.ወ.ሓ.ት. እና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው ይላል። እንዴት ህዝብና የፓለቲካ ድርጅት አንድ ይሆናሉ?። ይህ ንፁህ ቅጥፈት ነው። ህ.ወ.ሓ.ት የትግራይ ህዝብ ውክልና ሊኖረው ይችላል እንጂ ህዝብ ሊሆን ፈፅሞ አይችልም ። አረና ትግራይ እና የትግራይ ህዝብ አንድ አይደሉም። ኦ.ህ.ዴ.ድ እና የኦሮሞ ህዝብ አንድ አይደለም። ድርጅቱም ብሎ አያውቅም ።ብ.አ.ዴ.ን እና የአማራ ህዝብ አንድ አይደሉም። ድርጅቱም አንድ ነን ብሎ አያውቅም ። ታድያ በምን መለኪያ ህ.ወ.ሓ.ት እና የትግራይ ህዝብ አንድ ይሆናሉ?። ህ.ወ.ሓ.ት በትግራይ ህዝብ ስም የሂሳብ ምርመራ የማያደርጉ ከ 30 በላይ የንግድ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ያንቀሳቅሳል። የድርጅቶች የንግድ ገቢ ገንዘብ ተቀማጭነት የት አገር እንደሆነ ከጥቂት የህ.ወ.ሓ.ት ሰዎች በስተቀር የሚጠይቅም የሚያውቅም የለም።የትግራይ ህዝብ በከፈለው መስዋዕትነት ጥቂቶች በለፀጉበት።ይህ ፍትሀዊ አልነበረም ። ሰንት  የጦርነቱ ተጎጂዎች የትግራይ ታጋዮች  የድህነት ካባ ለብሶ ይኖራሉ። ሌላው ቀርቶ ህ.ወ.ሓ.ት. አካለ ስንኩልንና የጦር ጉዳቶኞች በተገቢው ሁኔታ ከድርጅቱ ሀብት አላካፈላቸውም። የድርጅቱ ገንዘብ በህይወት ያሉ እንዲሁም የተስዉ ታጋዮች ጭምር የጋራ ሀብታቸው ነው።

ከደርግ ውድቀት በኃላም ህ.ወ.ሓ.ት የአፈና መዋቅሮች እንጂ በተግባር የተፈተኑ የዲሞክራሲ  መዋቅሮች አልነበሩትም። በመሆኑም ህገ መንግስታዊ ስርአቱ በሚጣረስ አኳኋን እንዲሁም የትግራይ ህዝብ ፍላጎት ያላሟላ ድርጅት ነው። ድርጅቱ (ህ.ወ.ሓ.ት) ከኢትዮጲያ እና -ኤርትራ አውዳሚ ጦርነት(1999-2000 በምዕራቡ ቀመር)  መልስ የውስጥ መሰንጠቅ አጋጥሞት ነበር። መነሻ ችግሮች ሁለት ነበሩ።
አንደኛው መነሻ  ፣ የኤርትራ የባድሜ የሀይል ወረራ አስቀድሞ መከላከል ይቻል ነበር። ለመንግሥት ያቀረብነው ሪፓርት መንግስት አድህቦ (ቀልብ) አልሰጠውም በማለት እነ አቶ ስየ አብርሃ መንግስት ሲወነጅሉ ጠቅላይ ሚኑስተር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ደግሞ እነ ስየን በሙስና በስብሳችዋል በማለት ወነጀሉ። በሙስና መበስበሱ እውነት ሊሆንም ላይሆንም ይችላል ። ጦርነቱ በተመለከተ ግን ሁሉም ኃላፊነት ነበረበት።
ሀለተኛው መነሻ ፣በህ.ወ.ሓ.ት ሰዎች ውስጥ ጥላቻና ከፍተኛ መናናቅ ነው። የተማረና ያልተማረ የሚል ውስጠ ክፍፍል ነበር። ሄዶ ሄዶ የእነ አቶ መለስ ቡድን ስየን ዘብጥያ ሲያወርደው ሌሎች ደግሞ ከድርጅቱ አባረራቸው ።አንጃዎች የሚል ቅፅል ስምም ተበረከተላቸው። ህ.ወ.ሓ.ት ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ የድርጅቱ ታጋዮች ሳቀር ከበሬታ የማስጥ በወያናይ ዲሞክራሲ ስም የተሽፈነ የኮሚኑስቶች ስብስብ ነው።

ህ.ወ.ሓ.ት. በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እንዲስፋ፣ ሰብአዊ መብት እንዲከበር ፣የህግ የበላይነት እንዲጠናከር በግንብ ቀደምትነት ማስፈጸም ነበረበት። የአምባገነንነት ባህሪ ከደርግ ስርአት መማር ነበረበት ።የትግራይ ህዝብ ተልዕኮ ማስፈጸም ነበረበት ።ህ.ወ.ሓ.ት የትግራይ ህዝብ ክብርና ዝና ማስጠበቅ አልቻለም ። ድርጅቱ የብሄር ክፍፍልና ሴሬ የተጠናወተው ከመሆኑም በላይ ከአዳዲስ አስተሳሰቦችና ለውጦች ጋር ለመላመድ አልቻለም። እስከ አሁን ህ.ወ.ሓ.ት በደርግ ሂሳብ ያስባል።የትግራይ ህዝብ ከሌላ ህዝብ ጋር ለማጋጨት ደርጋውያን ተነሱብህ፣ ሻዕቢያ ተነሳብህ፣አማራ ተነሳብህ፣ኦሮሞ ተነሳብህ  ይሉታል።ለምን በህዝብ ስም ፓለቲካ ይነገዳል?። ለምሳሌ ፣ ቅዳሜ ሰኔ 16/2010 ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር እብይ አህመድ በአጭር ግዜ ውስጥ ባከናወኗቸው መልካም የሰብአዊ መብት አያያዝና የዲሞክራሲ ጉዞ ድጋፍ ለመስጠት እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማመስገን በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ በተጠራበት ቀን የተቃውሞ ሰልፍ በመቀሌ ማድረጉ ምን ይበጃል። ይህ ቅንነትና ሀላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው። ህ.ወ.ሓ.ት በአሁኑ ግዜ ለትግራይ የሚጠቅም ድርጅት አይደለም። የትግራይ ህዝብ ሌላ አማራጭ የፓለቲካ መስመር መቀየስ አለበት እላለሁ ።

የዶ/ር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ መመረጥ ለህ.ወ.ሓ.ት መልካም አጋጣሚ ነው። በተለያዩ ወንጀሎችና የአገር ሀብት የስረቁ የህ.ወ.ሓ.ት ሰዎች ጥሩ እንቅልፍ (good night sleep)  እንዲተኙ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ከፍትኛ ሚና ተጫውቷል ። በይቅርታና እርቅ አመክንዮ ፈላጭ ቆራጭ የነበሩ የህ.ወ.ሓ.ት ሰዎች በሰላም ከቤተ መንግስት ተሽኝተዋል። አወጣጣቸው ያማረ ነበር ማለት ይቻላል። ህ.ወ.ሓ.ት በውስጥ ድርጅታቸው የመጣም የአስተሳሰብ ለውጥ ከመደገፍ ሌላ አማራጭ የላቸውም ። በተበላ እቁብ እቁብ የለም። አሁን ግዜው የለውጥ ነው። በለወጡ ጎደና አብሮ ማዝገም ያስፈልጋል ። ተጠቃሚውም እሱ መንገድ ነው። ህ.ወ.ሓ.ት የሰላምና የዲሞክራሲ መነቃቃት በምን ሁኔታ የማደናቀፍ የስብዕና ዝግጅት የለዉም። የህዝብ ለውጥ ፍላጎት ማስቆም ከቶ አይቻልም ። በዚህ አጋጣሚ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ፣ እንዲሁም አይና ጀሮ በመሄኖ ከፍ ሲልም አገራችን ኢትዮጵያ በሰላም፣በልማት በትልቁ ደግሞ ሰብዓዊ መብት የሚከበርባት፣ ዝህቦች የማይፈናቀሉባት፣ ዲሞክራሲ የስፈነባት ፣ሲቀጥልም በቀጠናው ተፅእኖ ፈጣሪ አገር እንድትሆን የሚያደርጉት መልካም ጅማሮ እንዲጠናከር ከጎኖት መሆኔን ስገልፅ በታላቅ አክብሮ ነው።

ለስላም ፣ ልማትና እውነተኛ ዲሞክራሲ ሁሉም ይትጋ!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy