Artcles

“Cafee Araarraa”—የእርቅ መንደር

By Admin

June 02, 2018

 

“Cafee Araarraa”—የእርቅ መንደር ዘአማን በላይ ከአዘቦቱ ቀናት በአንደኛው በቅርበት የማውቀው ወዳጄ ስልኬን አስጮሃት። መቀራባረባችን የጠነከረ ስለነበር ፈጥኜ ለማንሳት ጊዜ አልወሰደብኝም። እንዲህም አለኝ—“ወዳጄ ሆይ! ስለ ‘ጨፌ አራራ’ (Cafee Araarra) ሰምተህ ታውቃለህን?” በእውነቱ ርግጠኛ አልነበርኩም። ግና የቦታው ስም ለትውስታዬ ብዙም የራቀ አልነበረም። ሆኖም ‘አውቃለሁ’ ወይም ‘አላውቅም’ ለማለት አልደፈርኩም። በዝምታ ተዋጥኩ።…የስልክ ውስጥ ፀጥታዬን ያጤነው ወዳጄ፤ “ጨፌ አራራ የቀድሞው የአራት ኪሎ መጠሪያ ስም ነው” አለኝ። የአዕምሮዬ የትውስታ ጓዳ ተነቃቃ። ወዲያውኑ ከትውስታ ማህደሬ ውስጥ የ“ጨፌ አራራ” ምንነት ተግተልትሎ ይታየኝ ጀመር፤ በወዳጄ የአየር ሞገድ ድምፅ ማብራሪያ ታጅቦ። የዛሬዋ አራት ኪሎ የያኔዋ “ጨፌ አራራ” ‘Cafee Araarra’ የእርቅ መንደር ነበረች። በዚህች መንደር ውስጥ፤ ተጣልቶ ያልታረቀ፣ ፈንክቶ አሊያም ተፈንክቶ “ጉማ” (ካሳ) ያልከፈለ አሊያም የተቀበለ፣ በውስጡ የያዘውን ቂም ለሀገር ሽማግሌ (አባ ገዳ) ነግሮ ያልሻረ፣ ይቅር ባይነትን ተምሮ ያላስተማረ፣ በቀልና ቂምን አሽቀንሮ የእርቅ ማዕድን ያልተቋደሰ፣ መጠላለፍንና ጎትቶ መጣልን ትቶ በሽማግሌ ፊት በአንድ ሽክና አብሮ ያልጠጣ አዲስ አበቤ አለ ለማለት አያስደፍርም—ያኔ በዚያ ዘመን። አዎ! በዚያን ዘመን “ጨፌ አራራ” በእርቅ መንደርነቷ ትታወቅ እንደነበር አስታወስኩ። የተዥጎደጎዱት ሃሳቦቼ መቋጫ አላገኙም። ግና ወዳጄ በአየር ሞገድ ላይ ሆኖ ስለ “ጨፌ አራራ” ከመናገር አልተቆጠበም። በመሃሉም “ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ‘ጨፌ አራራ’ ወደ ድሮ ስራዋ እንድትመለስ አደረጓት” አለኝ። ሃሳቡን ወዲያውኑ አብላላሁት። ወዳጄንም ተሰናበትኩት። ስንብቴም ይህችን አጭር ፅሑፍ እንዲህ ለማሰናዳት ነበር።… ርግጥ “በጨፌ አራራ” ስራዋን በአዲስ መልክ ጀምራለች—በእርቅና በአንድነት ማሃንዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት። የ42 ዓመቱ ጎልማሳው ዶክተር አብይ አህመድ እንደ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸውና እንደ ገዥው ፓርቲ ሊቀመንበርነታቸው ቤተ- መንግስታቸው ከሚገኝበት “ጨፌ አራራ” (አራት ኪሎ) ሆነው የሚሰጧቸው ውሳኔዎች፤ ሰውዬውን ልክ እንደ እኔ በእቅና በአንድነት መሃንዲስነት ያልተመለከታቸው፣ ተመልክቶም የወደፊቷ ኢትዮጵያ ብስራት መሆናቸውን የተገነዘበ የሀገሬ ሰው በርካታ እንደሚሆን እገነዘባለሁ። ገና ከጅምሩ በበዓለ-ሲመታቸው ላይ “ጨፌ አራራ” ውስጥ ሆነው “…ከኢህአዴግ ውጪ ያሉ ፓርቲዎችን የምናይበት መነፅር እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ፣ እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሃሳብ አለኝ ብሎ እንደመጣ ሀገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው።” በማለት መጪው ጊዜ የእርቅና የአንድነት እንዲሁም ለአንዲት ሀገር አብሮ የሚሰራበት መሆኑን ያበሰሩት ዶክተር አብይ፤ ‘ትንቢት ይቀድም ለነገር’ እንዲል መፅሐፉ፣ ይህን የእቅርና የአንድነት ቃል ከገቡበት ዕለት ጀምሮ እንደምን ሊፈፅሙት እንደሚችሉ ለመገመት ነብይ መሆንን የሚጠይቅ አልነበረም። አዎ! በፓርላማ ያደረጉት መሳጭ ንግግር የህዝቡን ቀልብ የገዛና ተቀባይነታቸውን ከፍ ያደረገ ነው። በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት፤ 84 በመቶ የሀገራችን ህዝብ ዶክተር አብይ ለውጥ ያመጣሉ ብሎ እንደሚያምን ማስነበቡ የዚህ እውነታ አስረጅ ነው። ዶክተር አብይ ለስድሳ ቀናት ሳይሆን ለስድስት ዓመታት ሀገሪቱን የመሩ ይመስላሉ። ምክንያቱም የፈፀሙት የእርቅና የአንድነት ተግባሮች እጅግ የገዘፉ በመሆናቸው ነው። በስልጣን ዘመናቸው ሁለት ወራት ውስጥ በተለይ ብሔራዊ መግባባትን ከመፍጠር አኳያ የፈፀሟቸው ጉዳዩች ሀገራችንን ከነበረችበት የሁከትና የትርምስ መንገድ አላቆ ወደ ሰላም አውድ የመለሳት መሆኑን ዓይን ያለው ፍጡር የሚክደው አይመስለኝም። ተግባራቸውን ከብዙ በጥቂቱ እንዲህ ማንሳት ይቻላል። የእርቅና የአንድነት መሃንዲሱ በተመረጡ ማግስት ፈታ አላገኙም። ሀገራቸው ያለችበትን ሁኔታ ስለሚያውቁ፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር ህዝቡ ያለበትን ችግር በቅርበት ማድመጥን ነው ቅድሚያ ያደረጉት። በመቐለ፣ በጅግጅጋ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በአሶሳ፣ በጋምቤላ፣ በደምቢ ዶሎ…ያደረጓቸው ህዝባዊ ውይይቶች በሀገር ውስጥ ብሔራዊ መግባባትን የፈጠረ ነበር። በወቅቱ ህዝቡ በግልፅ ያለበትን ችግር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሁሉም ችግሮች በአንድ ጀንበር እንደማይፈቱ በማሳሰብ፤ በመንግሥት በኩል አቅም በፈቀደ መጠን የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኝነቱ መኖሩን አረጋግጠዋል። በተለያዩ አካባቢዎች የተካሄዱት ህዝባዊ ውይይቶች በመተማመን ላይ የተመሰረቱ፣ ህዝቡም እንደ ህዝብ መወጣት ያለበትን ሃላፊነት ያስገነዘቡና መንግሥትም የራሱን የቤት ስራ እንዲወስድ ያስቻሉት ነበሩ። እናም “የመሃንዲሱ” ህዝባዊ መድረኮች፤ የሰመሩ፣ ሀገራዊ ፍቅርን፣ አንድነትንና የጋራ መግባባትን ማምጣት የቻሉ ሂነው አልፈዋል። ሀገር ቤት ውስጥ ባደረጓቸው ጉዞዎች “አዲስ አስተሳሰብ ማለት በፊት የነበረውን፣ አሁን ያለውንና የወደፊቱን አስተሳሰብ በማስታረቅ የተሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር ነው” በሚል እሳቤ ብሔራዊ መግባባትን በዋና ዋና ጉዳዩች ዙሪያ ለመፍጠር የሰሩት የፍቅርና የሰላም መሃንዲሱ ዶክተር አብይ፤ ወደ ውጭ አቅንተው ሀገራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ ያደረጓቸው ጥረቶችም ስኬታማ ነበሩ። በጂቡቲ፣ በሱዳንና በኬንያ ያደረጓቸው ጉብኝቶች፤ ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ብሔራዊ ጥቅሟን እንድታስከብር ያደረጉ ናቸው። በዚህም ባህር አልባ (land locked) የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በጂቡቲ፣ በፖርት ሱዳንና በኬንያ ላሙ ወደቦችን በጋራ ማልማት የምትችልበትን ሁኔታ እንድታገኝ በማድረግ ተስማምተዋል። በእኔ የግል እይታ፤ ይህ ታላቅ የዲፕሎማሲ ድል ከወጨና ገቢ ንግድ የሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር፤ ሀገራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ለሚያስችሉ እንደ “ወታደራዊ ቤዝ” ዓይነት ተግባራትን ለመከወን የሚያስችል ይመስለኛል። ይህም እንደ እኔ ዓይነቱ ‘ባህር ኃይል የለንም’ እያለ ለሚቆዝም ሀገር ወዳድ ዜጋ ምናልባትም ፈጣንና ትክክለኛ ምላሽ የሚሰጥ እንዲሁም በሶስቱም ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያት ከእስር ነፃ እንዲሆኑ በማድረግ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ተግባር ነው። ከሁሉም በላይ በዶክተር አብይ ብልስለት የተሞላበት አካሄድ እንድንኮራ የሚያደርገን ነው። እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤት ሀገራት ያደረጓቸው ጉብኝቶች “በአንድ ድንጋይ በርካታ ወፎችን” የመቱ፣ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ወዳለ ማማ ላይ የሰቀሉና ዜጎችም “ለካስ መንግሥትታችን ለእኛ ይቆረቆራል” ብለው ውስጣቸውን በጥሞና እንዲመለከቱ ያደረገ ተግባር ስለሆነ፤ አድናቆቴን ከመቀመጫዬ ተነስቼ እንድገልፅ የግድ ይለኛል። ታዲያ ውድ አንባቢ ሆይ! የዚህ ክንዋኔ መነሻው የእርቅ መንደር በሆነችውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀድሞ ስራዋን እንድትጀምር ባደረጓት “ጨፌ አራራ” መንደር መሆኑን ልብ ይሏል! የ“ጨፌ አራራ”ው የይቅር ባይነትና የፍቅር ጥንስስ በእርቅና በአንድነት መሃንዲሱ አማካኝነት ወደ መካከለኛው ምስራቅም ተሻግሯል። ጉዞዎቹ የስኬት ካባን የደረቡልን ነበሩ። ቀደም ሲል በርሳቸው አማካኝነት እዚህ ሀገር ውስጥ የተሰሩት ስራዎች አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ አንድ ያደረጉ ናቸው። አንድነታችን የጥንካሬያችን ምንጭ ስለሆነም፤ ሳዑዲ አረቢያም ሆነች የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች “ምን ትፈልጋላችሁ?” ነበር ያሉት—በዶክተሩ የተመራውን የልዑካን ቡድን። ርሳቸው ባቀረቡት ጥያቄም በሳዑዲ የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን እስረኞች ተለቀዋል። የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ስላልተስማሙ እንጂ፤ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ባለ ሃብት ሼህ መሃመድ አላሙዲንንም ይዘዋቸው ወደ አዲስ አበባ ይመጡ ነበር። ግና ሼሁ በቅርቡ እንደሚለቀቁ ቃል ተገብቶላቸዋል። ምን ይህ ብቻ። በህክምና ስህተት ሳቢያ ከ12 ዓመታት በላይ የአልጋ ቁራኛ የነበረ ታዳጊ ወጣት የ21 ሚሊዮን ብር ካሳ (እዚህ ላይ በመግቢያዬ አካባቢ ያነሳሁትን የ“ጨፌ አራራ” ጉማ ስርዓትን ያስታውሷል!) እንዲያገኝና ወደ ሀገሩ እንዲመለስ አድርገዋል። በተባበሩት አረብ ኢምሬቶችም የሀገራችንን ጥቅም የሚያስጠብቅ የሁለትዮሽ ስምምነቶች በማድረግ፤ ኢትዮጵያዊ ማንነት፣ ተቀባይነትና አንድነት ከፍ…ከፍ እንዲል አድርገዋል። ይህ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እዚህ ሀገር ውስጥ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ያደረጓቸው አንድነትን የመፍጠር ስራዎች ስኬታማ በመሆናቸው ነው። “ስንደመርና አንድ ስንሆን ሁሉም ያከብረናል” በማለት የተናገሩት አባባል ትክክለኛ መገለጫው ከላይ የጠቀስኳቸው ተግባራት ይመስሉኛል። ዶክተር አብይ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት በወሰነው መሰረት እጅግ በርካታ ታራሚዎችን በምህረትና በልዩ ይቅርታ ክሳቸው እንዲቋረጥ አድርገዋል። ይህም በተለያዩ ወንጀሎች በእስር ላይ የነበሩ ዜጎችን በመፍታት እንዲሁም በሽብርተኝነት ወንጀል ሞት የተፈረደባቸውና የአርበኞች ግንቦት ሰባት ፀሐፊ የነበሩት እንዲሁም ከአራት ዓመታት በፊት ከየመን አየር መንገድ በፀጥታ ሃይሎች ተይዘው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንዲለቀቁ በማድረግ አዲስ የፖለቲካ አየር ኢትዮጵያችን ውስጥ እንዲነፍስ አስችለዋል። በእኔ እምነት፤ ይህ ክስተት በ“ጨፌ አራራ” (cafee Araarra) የእርቅ መንደር ውስጥ፤ የጥላቻና የቂም በቀል ፖለቲካ ማክተሙን፣ የይቅር ባይነትና የፍቅር መንፈስ መፈጠሩን እንዲሁም የተለየ ሃሳብ መያዝ ሃጢያት ወይም ግፍ አለመሆኑን አረጋግጧል። በተለይ ገዥው ፓርቲ ቀደም ባሉ ዓመታት በሽብርተኝነት ይመለከታቸው የነበሩት እንደ አቶ አንዳርጋቸው እዲሁም በውጭ የነበረውና በኦቦ ሌንጮ ለታ የሚመራው የ“ኦዴግ” ልዑክ ዓይነት የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች ለሰላም የተዘረጉ እጆችን በመቀበል “ጨፌ አራራ” ውስጥ ገበተው በፍቅር ሲጨባበጡ መመልከታችን፤ ይቅር ባይነትና ፍቅር ብሎም ኢትዮጵያዊነት ልኬታው እስከ የት ድረስ ሊሆን እንደሚችልና እንደሚገባው የሚያመላክት ይመስለኛል። የአንድነት ጥግ እስከየት ድረስ ሊጓዝ እንደሚገባውም እንዲሁ። ርግጥ ሰዎች የተለየ አስተሳሰብ ስላላቸው ብቻ ይዞ በማሰር ለውጥ ማምጣት አይቻልም። በመረጃና በማስረጃ ላይ ተገድፎ ሰዎችን በህግ ጥላ ስር ማዋል እንጂ፤ አስሮ መረጃ ማፈላለግም አግባብ ያለው አሰራር አይደለም። እንዲህ ዓይነቱን ተግባር መፈፀም ለታሳሪው እውቅና የመስጠት ያህል የሚቆጠር ይመስለኛል። ጀግና ያልሆነውን የማጀገን፤ የማይታወቀውን የማሳወቅ። አንዳችም ትርፍ የለውም። እንዲያውም ትርፉ የሚሆነው፤ በተገላቢጦሽ የራስን በጎ ምግባርና ክንዋኔ እንዲሁም ገፅታን በዓለም ፊት ማኮሰስ ብቻ ነው። አክሳሪ ተግባር። እናም በእኔ እምነት፤ ታራሚዎቹ መለቀቃቸው በአንድ በኩል፤ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ፤ ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር ጉልህ አስተዋፅኦ ብዬ አስባለሁ። ይህ በመደረጉም ከሀገር ቤት እስከ ውጭ ድረስ ያለውን ስሜት ለዚህ ፅሑፍ አንባቢ መንገር ለቀባሪው የማርዳት ያህል ይቆጠርብኛል። “ጨፌ አራራ” አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም—ቀጣናውን ያካለለ ነው። ‘ጎረቤቶቻንን ሰላም ሲሆኑ፣ እናም ሰላም እንሆናለን’ በሚል እሳቤ፤ ለጂቡቲ፣ ለኬንያና ለሱዳን፣ ለሶማሊያና ለአዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ሰላም ይጨነቃል። ጭንቀቱ የዜጎቻችንን መስዕዋትነት እስከሚያስከፍለው የሰላም አስከባሪ ሰራዊት እስከማዋጣት ድረስ የሚዘልቅ ነው። በዲፕሎማሲው ረገድም ስለ እርቅና ስለ አንድነት ያስባል። ያልተግባቡ ወገኖች ችግራቸውን በመነጋገር እንዲፈቱ ለማድረግ ከዋናው የዲፕሎማሲ ባሻገር፣ “የኮሪደር ዲፕሎማሲ” ተግባቦትንም ይከውናል— “ጨፌ አራራ” የእርቅ መንደር ነውና። ይህን ፅሑፍ ሳሰናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት “የኮሪደር ዲፕሎማሲ” በሚል የፌስ ቡክ ላይ የለቀቀው አጭር ፅሑፍ፤ በደቡብ ሱዳን ሰላም ላይ አዲስ አበባ ውስጥ የተነጋገረው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በስኬት ተጠናቋል። በ“ጨፌ አራራ” የምትመራው ኢትዮጵያም ለውጤቱ መገኘት የ“ኮሪደር ዲፕሎማሲ”ን በማከናወን የአንበሳውን ድርሻ መጫወቷን አትቷል። ለዚህም “የጨፌ አራራው” ሰው፣ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ሁለቱንም ወገኖች ሰፊ የሆነ የኮሪደር ዲፕሎማሲ በመጠቀም ሊያግባቧቸው ችለዋል። ይህም የእርቅ መንደሩ እጅ እስከ ደቡብ ሱዳን ድረስ በመዝለቅ ወጤታማ መሆኑን የሚያሳይ ነው። አዎ! “ጨፌ አራራ” (Cafee Araarra) የእርቅ መንደር ከኢትዮጵያችን አልፎ የምስራቅ አፍሪካ ብሎም የአፍሪካ መድን የሚሆን ይመስለኛል። በመንደሩ ውስጥ ቤተ- መንግስታቸውን ያደረጉት የሀገሬ መሪዎች፤ ዛሬ ስለ ይቅር ባይነት፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ሀገርና ስለ ህዝብ እየታገሉ ነው። ይህን አዲስ አስተሳሰብ ሀገሬ ብቻ ሳትሆን አፍሪካዊያንም ተጠምተውታል። ደራሲ በዓሉ ግርማ የአንድን ፀሐፊ ፍልስፍና ተውሶ በአንድ መፅሐፉ ላይ “ወደፊት የማይሄድ ሁሉ ወደ ኋላ በመጓዝ ላይ ነው” እንዳለው፤ እኔም የ“ጨፌ አራራ” መንገድ ኢትዮጵያን አቅንቶ፣ ቀጣናውን አረጋገቶና ፍቅርንና አንድነትን በአፍሪካ አምጥቶ ወደፊት እንዲገሰግስ እመኛለሁ። እናም የዚህ አዲስ አስተሳሰብ ዝማሬ ፋና ወጊው፣ የፍቅርና የአንድነት መሃንዲሱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቀየሱት መንገዳቸው በበለጠ ስኬት እንዲታጀብ ከጎናቸው በመቆም ልንደግፋቸው ይገባል እላለሁ።