Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“Caffee Araaraa” —የእርቅ መንደር

0 793

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“Caffee Araaraa” —የእርቅ መንደር

 

  • ከ“ሞት አልባው ጦርነት” ወደ ሰላም አምባነት

 

                                  ዘአማን በላይ

(ክፍል ሁለት)

በቀዳሚው ፅሑፌ ላይ የአሁኗ አራት ኪሎ የቀድሞዋ “ጨፌ አራራ” (Caffee Araaraa) የእርቅ መንደር፤ ኢትዮጵያን በሰላምና በፍቅር ከመሙላት አልፋ የምስራቅ አፍሪካ ብሎም የአፍሪካ መድን ትሆን ዘንድ ምኞቴ መሆኑን ገልጨ ነበር። ዛሬ ስዕለቷ እንደ ሰመረላት መበለት ደስ ብሎኛል። ምኞቴ የሳምንት ዕድሜ እንኳን ሳይሞላው፤ የእርቅ መንደሩ ጉዞ አንድ ርምጃ ጨምሯል። መንደሩ ለሁለት አስርት ዓመታት የዘለቀውንና በእነዚያ ዓመታት የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ውዝግብን ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም ይዟል።

እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም በሁለቱ ሀገራት መሪዎች የተፈረመውን የአልጀርሱን ስምምነትና እርሱን ተከትሎ የሁለቱን ሀገራት አጨቃጫቂ ድንበር ያካለለውን የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽንን (Eritrea-Ethiopia boundary Commission “EEBC”) ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ በመቀበል በቁርጠኝነት ለመተግበር መዘጋጀቱን አስታውቋል። የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ የሰላም ጥሪውን እንዲቀበልም ጥሪ አድርጓል።

ርግጥ “ጨፌ አራራ” የእርቅና የሰላም መንደር በመሆኑ፤ ስለ ህዝቦች የደምና የባህል እንዲሁም ታሪካዊ ግንኙነት ትስስር ብሎም ስለ ሰላምና ከእርሱም ሊገኝ ስለሚችለው የጋራ ተጠቃሚነት ሲባል ያሳለፈው ውሳኔ ትክክለኛና ተገቢ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም። ምናልባት እዚህ ላይ አንዳንድ ወገኖች “እንዴት?” የሚል ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ። የምንኖርበት ዴሞክራሲያዊ ሀገር ማናቸውም ዓይነት ሃሳቦች የሚነሱበት አውድ እየሰፋ በመሆኑ፤ ጥያቄውን በአክብሮት በማስተናገድ የግሌን ምላሽ ግን ኋላ ላይ እመለስበታለሁ። ምክንያቱም በቅድሚያ ስለ ድንበሩ ውዝግብ ስረ-ነገር በልኬታው ማውጋት፤ በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ዕውቀት እንድንይዝ ያደርገናል ብዬ ስለማምን ነው።

የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ውዝግብ መነሻው በርካታ መሆኑ ቢነገርም፣ ዋነኛው ገፊ ምክንያት ግን ሁለቱ ሀገራት እንደ አንድ ሀገር ይኖሩ ስለነበር ድንበራቸው በአግባቡ ባለመካሉ ነው። ይህ ሁኔታም የኤርትራ መንግስት ባድመንና አካባቢውን እንዲወር ምክንያት ሆኖታል። ታዲያ የኢትዮጵያ መንግስት ወራሪውን ሃይል ከሉዓላዊ ግዛቱ እንዲወጣ ቢጠይቀው፤ በወቅቱ ቀልድ ‘ታንኮቼ ወደ ባድመና አካባቢው የገቡት ሳር ለማጨድ ነው’ የሚል ዓይነት ምላሽ ይሰጣል። በዚህም ሳቢያ ከ1990 ዓ.ም እስከ 1992 ዓ.ም ድረስ እጅግ ዘግናኝና ደም አፋሳሽ እንዲሁም ከሁለቱም ወገኖች በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን የቀጠፈ ጦርነት ተካሄደ። በስተመጨረሻም የኤርትራ መንግስት ከያዛቸው ግዛቶች በሽንፈት ጠቅልሎ ለመውጣት ተገደደ። በዚህም ከአጨቃጫቂ ድንበሮቹ ባሻገር ‘በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤርትራና የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ሃይል’ /United Nations Mission In Ethiopia and Eritrea (UNMEE)/- “አንሚ” በኤርትራ ግዛት ውስጥ 50 ኪሎ ሜትር ገብቶ እንዲሰፍር ኤርትራ ተስማማች።…በሂደቱም የአልጀርሱ ስምምነትን ተከትሎ ጉዳዩን  የድንበር ኮሚሽኑ የአየር ላይ ካርታ አነሳ። ጉዳዩን ከዓለም አቀፍ ህጎች፣ ከቅኝ ግዛት ውሎችና ከሌሎች ህጋዊ ማዕቀፎች አኳያ ተመልክቶም ድንበሩን በማካለል ውሳኔውን አሳወቀ።

በወቅቱ ውሳኔውን ኢትዮጵያ በመርህ ደረጃ ብትቀበለውም፤ ወደ መሬት ወርዶ ሲተገበር አንድ መኖሪያ ጎጆን ለሁለት ቦታ የሚከፍልና በአፈፃፀሙም ለህዝቦችም የማይጠቅም መሆኑን አሳወቀች። አስከትላም የድንበር ማካለሉ ጉዳይ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ መመስረት እንዳለበት በማሳሰብ፤ ባለ አምስት ነጥብ የሰላም ሃሳቦቿን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይፋ አደረገች። የኤርትራ መንግስትም በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት የተፈረደልኝ መሬት ካልተሰጠኝ በምንም መንገድ ስለ ሰላም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አልነጋገርም አለ። ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ውጥረትን አነገሰ። የኤርትራ መንግስትም “አንሚ” የተሰኘውን የሰላም አስከባሪ ሃይል ከግዛቱ አስወጣ።…ላለፉት 20 ዓመታትም በውጥረት ውስጥ ኖርን። እውነታው በአጭሩ ይህን የሚመስል ነው።…    

አዎ! በሁለቱ ሀገራት መካከል ላለፉት 20 ዓመታት የነበረው ግንኙነት የስጋት ደመና ያንዣበበበት ነበር።…በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ስለ ነበረው ሁኔታ ብዙ ማለት ቢቻልም ቅሉ፤ ያለነው “ጨፌ አራራ” የእርቅ መንደር ውስጥ በመሆኑ፣ ስለ እርቅ፣ ስለ ሰላምና ስለ ህዝቦች ተጠቃሚነት ማውሳት የግድ ይለኛል። በእርቅ መንዱ ውስጥ ስላለፈው የጦርነት ሁኔታ ማውጋት ምንም ዓይነት ፋይዳ የለውም— ለሁለቱም ወንድም ህዝቦች የሚጠቅመው አንዳችም ነገር የለምና። በእኔ እምነት፤ ካለፈው ታሪክ መማር እንጂ ያለፈውን ኩነት እያስታወሱ ‘እንዴት እንዲህ ይሆናል’ ማለት ትርጉም የለውም። የሰው ልጅ በህይወት ዑደቱ ውስጥ መኖር ያለበት ትናንትን አይደለም—ዛሬንና ነገን ብሎም ከነገ በስቲያን እንጂ። ትናንትን በትውስታ ማህደር ውስጥ አስቀምጦ ከክስተቱ በመማር ለነገና ለተነገ ወዲያ ማሰብ ብልህነትና አርቆ አሳቢነት ነው። የእርቅ፣ የፍቅርና የሰላም መሃንዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያደረጉት ይህን በመሆኑ፣ የአክብሮት ባርኔጣዬን ከፍ ላደርግላቸው ወደድሁ።

ያም ሆኖ አንዳንድ ሚዲያዎች የ20 ዓመቱን የውጥረት መንገድ “No war, No peace” በሚል ሲገልፁት ቆይተዋል። ዳሩ ግን ዶክተር አብይ አህመድ ይህን ፅሑፍ ሳሰናዳ፤ አገላለፁን እንደማይቀበሉት ማስታወቃቸውን አድምጫለሁ። በእርሳቸው እምነት፤ የስጋት ደመናው ውጥረት መባል ያለበት “ሞት አልባ ጦርነት” ነው። እኔም የእርሳቸውን ሃሳብ እጋራለሁ። የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ የጦርነቱን መነሻ ቦታዎች አውቃቸዋለሁ። በእነዚያ ቦታዎች ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የነበረው የውጥረት አውድ ጦርነትም ሰላምም የለሌለበት ሁኔታ አልነበረም። ሆኖም አያውቅም። ለነገሩ “ተመጣጣኝ ርምጃ” ባለበት አውድ ውስጥ “No War” ብሎ ነገር ቀልድ ይመስለኛል።   

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ፤ ከኤርትራ ጋር የሚዋሰኑት የትግራይና የአፋር ጠረፍ አካባቢ ህዝቦች በተለይ፤ በእነዚህ ዓመታት ያሳለፉት የህይወት መስተጋብር  እጅግ የሚያሳዝን ነበር። እነዚያ ህዝቦች ‘ከአሁን አሁን ምን ሊፈጠር ይችላል?’ በሚል የጭንቀትና የስጋት ስነ ልቦና ውስጥ ወድቀዋል። በዚህም ሳቢያ በአንድ ልብ ወደ ልማት ተሰማርተው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና አካባቢያቸውን እንዲሁም ክልላቸውንና ሀገራቸውን መጥቀም አልቻሉም። ይህ ሁኔታ በጠረፍ አካባቢዎቹ በሚገኘው ጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን እያንዳንዱ አባል ውስጥ፣ ውጊያ ባይኖርም የስነ ልቦና ጦርነትን (Psychological warfare) የፈጠረ እንደነበር ግልፅ ነው። እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ክስተት የእኛ ብቻ አይደለም— የኤርትራ ህዝብና ሰራዊትም ጭምር እንጂ። ጠብ የማይል ነገር የሌለውና የሁለቱንም ሀገራት ህዝቦችን የጎዳ አዝጋሚ ሂደት። እናም የ“ጨፌ አራራ”ው ሰው ዶክተር አብይ አህመድ፣ ድርጅታቸውና መንግስታቸው፤ ይህን “ሞት አልባ ጦርነት” አውድ ወደ እርቅ፣ ፍቅርና ሰላም አምባነት ለመቀየር የአልጀርሱን ስምምነት ተቀብለው የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር መወሰናቸው፤ የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ የሰላም ጎህ እንዲቀድና በልማት እጅ ለእጅ ተያይዞ ለማደግ ደማቅ የተስፋና የአብሮነት ዕድገት ጮራን የሚፈነጥቅ ነው። እናም ድርጅታቸውንና መንግስታቸውን እየመሩ ላሉት የእርቅ መሃንዲሱ በድጋሚ ባርኔጣዬን ከፍ ከፍ ማድረግ እፈልጋለሁ።  

“ጨፌ አራራ” (የዛሬዋ አራት ኪሎ) የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች፣ ታላቁ ቤተ መንግስት፣ በተለምዶ ‘የላይኛው’ ወይም ‘የምኒሊክ ቤተ መንግስት’ እየተባለ የሚጠራው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የሚገኙበት ቦታ ነው። ባለፉት ሁለት ወራት በእነዚህ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚከናወኑ ጉዳዩች የዜማ ቅኝታቸው ተቀይሯል። የአንቺ ሆዬ፣ የባቲ፣ የአምባሰል…ወዘተ. ቅኝታቸው፤ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት ሆኗል—በእርቅ መሃንዲሱ በዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት። ዶክተሩ ድርጅታቸው በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደሰየማቸው የ20 ዓመቱን የውጥረትና “ሞት አልባ ጦርነት” ጉዞ፤ ወደ ፍቅርና ሰላም ለመለወጥ የወሰኑት ድርጅታቸው እምነቱን ጥሎባቸው በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ ዕለት ጀምሮ ነው። በዕለቱም “…ከኤርትራ መንግስት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን፤ የበኩላችንንም እንወጣለን። በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለት ሀገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለለፅኩ፤ የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ማለታቸውን እናስታውሳለን።

ታዲያ ሁሌም ከኢትዮጵያ በኩል ለሚቀርብበት ወቀሳዎችም ይሁኑ ለእንዲህ ዓይነቱ የሰላም ጥሪዎች ከብርሃን በሚልቅ ፍጥነት በሚመስል ሁኔታ ምላሽ የሚሰጠው የኤርትራ መንግስት፤ የበኩሉን ለማለት የወሰደበት የሰዓታት ጊዜ ብቻ ነበር። እናም በቃል አቀባዩ በአቶ የማነ ገብረመስቀል አማካኝነት፤ ሰላም ሁለቱን አገሮች ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው በመግለፅ፣ “ኤርትራ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ልትደራደር የምትችለው ባድመ ከተመለሰላት ብቻ ነው” ማለታቸው አይዘነጋም። አክለውም፤ የድርድር ኳሱ በኢትዮጵያ እጅ እንደሆነና ኢትዮጵያ ባድመን ጨምሮ በኃይል የያዘቻቸውን የኤርትራ ግዛቶች በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት መልቀቅ ይኖርባታል ብለዋል።

እንግዲህ ልብ እንበል። በአሁኑ ወቅት ዶክተር አብይና ድርጅታቸው በገለፁት መሰረት፤ የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት በመቀበል የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር ወስኗል። በኢትዮጵያ በኩል ተቀምጦ የነበረው ባለ አምስት ነጥብ የሰላም ሃሳብም ተነስቷል። ለሙሉ ህጋዊ ተባባሪነት ሀገሬ ዝግጁ መሆኗን ግልፅ አድርጋለች። አሁን የሚቀር ምንም ነገር የለም። ዳሩ ግን ከኢትዮጵያ ጋር ለሚኖረው ግንኙነቶች ሁሌም ‘በመጀመሪያ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ አዲስ አበባ ማከበር ይኖርባታል’ በማለት ቅድመ ሁኔታ ሲያቀርብ የነበረው የአስመራው መንግስት፤ ይህን ፅሑፍ እስካሰናዳሁበት ጊዜ ድረስ ለሰላም ጥሪው በየትኛውም ቋንቋ ምላሽ አልሰጠም። ሆኖም በእኔ እምነት፤ አሁን ኳሷ ከአዲስ አበባው ሜዳ በመልስ ምት ተጠልዛ የምትገኘው አስመራው ሜዳ ላይ ነው። እናም የኤርትራ መንግስት የሰላም ጥሪውን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ መቀበል ያለበት ይመስለኛል። ይህም በመግቢያዬ አካባቢ በይደር ወዳቆየሁትና ዶክተር አብይ፣ ድርጅታቸውና መንግስታቸው የወሰኑት ውሳኔ ‘ትክክለኛና ተገቢ ነው’ በማለት ያቀረብኩትን ድምዳሜ አንዳንድ ወገኖች “እንዴት?” የሚል ጥያቄ ካነሱ ምላሽ የሚሰጥልኝ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

ርግጥ በእርቅና ፍቅር መሃንዲሱ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት፤ የሁለቱን ሀገራት ሁኔታ ከ“ሞት አልባው ጦርነት” ወደ ሰላም አምባነት ለመለወጥ ያቀረቡት ህግና ስርዓትን የተከተለ ውሳኔ ትክክልም ተገቢም ነው። በእኔ እምነት፤ አንድ ወገን በዓለም አቀፉ ህግ እዳኛለሁ ብሎ ከተስማማ በኋላ፣ ላለመስማማቱ ሌላ ምክንያት ካቀረበ ስምምነቱን ያልተቀበለበትን ምክንያት በተጨባጭ ማስረጃዎች የማስረዳት ሃላፊነት (Proof of burden) ይወድቅበታል። ያልተቀበለበትን ምክንያት ከሁኔታዎች ጋር በመመልከት (ማለትም ጥቅምና ጉዳቱን አመዛዝኖ) ሊሰርዘውና ገዥ የሆነውን የዓለም አቀፍ ውሳኔ ሊቀበል ይችላል። ከዚህ ቀደም የተከተለው መንገድ ያልሰራ ከሆነም፤ ለሀገሩና ለተጎራባቹ ሀገር ህዝቦች ሰላምና የጋራ ተጠቃሚነት ሲል፤ ‘ተገቢ ነው’ ያለውን መንገድ ሊከተል ይችላል። የ“ጨፌ አራራዎቹ” የሀገሬ መሪዎች ያደረጉትም ይህንኑ ነው። ዛሬ በእርቅ መንደሩ ውስጥ የፍቅር፣ የሰላምና የቀጣናው ህዝቦች አብሮነት እንጂ፤ የጦርነት አታሞ እንደማይደለቅ እንዲሁም የጥላቻና እንደ ህፃን ልጅ “የእኔ እበልጥ’ መንፈስ ፈፅሞ እንደማይረብ ለዓለም ህዝብ በይፋ አሳውቀዋልና።

ይህ የመንደሩ ማንነት ሰሞኑን በ“ጨፌ አራራው” ሌላኛው ሰው፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አማካኝነት በስካንዴቪያን ሀገራት እየተገለፀ ነው። ሚኒስትሩ ለየሀገራቱ አቻቸው ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የነበራትን የድንበር ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደምትሻ ከማሳወቃቸውም በላይ፤ የሀገራቸው ርምጃ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል። ይህ ወቅቱን የጠበቀ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት፤ ሀገራችን በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ፍቅር እንዲነግስ ያላትን ፍላጎት የሚያሳይ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ዶክተር ወርቅነህ ይህን እውነታ ለማሳወቅ በተንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር የፊት ለፊት ግንኙነት እንዳደረጉት ሁሉ፤ ኢትዮጵያዊያኑም እንደ ዜጋ አምባሳደርነታቸው የሀገራችንን የሰላም ምሳሌትነት በያሉበት ቦታ ማሳወቅ የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል—የውጭ ግንኙነት ስራ ለውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ብቻ የተተወ ተግባር አይደለምና።          

እናም የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ የሁለቱንም ሀገር ህዝቦች የሚጠቅም መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ማንኛውም የሀገሬ ሰው ይህን ሃቅ መገንዘብ ያለበት ይመስለኛል። ከውጥረትና ከጭነቀት ኪሳራ እንጂ ትርፍ አይገኝም። እናም፤ ለህዝቡ ፍቅር እንዳለው ዜጋ፤ ከኤርትራ ጋር በሚያዋስኑን አካባቢዎች የሚኖሩት እንደ ሁመራ፣ ዛላንበሳ፣ ኢሮብ-አሊቴና፣ ባድመና አካባቢው የመሳሰሉ እንዲሁም በአፋር አካባቢ የሚኖሩ ተጎራባች ኢትዮጵያዊያን የሰቀቀን ህይወት ዘልቆ ሊሰማን ይገባል። ህመማቸው ሊያመን ይገባል። ‘ነገ ምን ይፈጠር ይሆን?’ ከሚል የስጋት ደመና ልንታደጋቸው ይገባል። ሁሌም “ከአጋም ጋር የተጠጋች ቁልቋል፣ ሁሌም ስትደማ ትኖራለች” በሚል ብሂል ውስጥ ከተናቸው ህይወታቸውን ሲኦል ልናደርግባቸው አይገባም። ኢ-ግብረ ገባዊም ነው። ይልቁንም “በሚያደማው አጋም” እና “በቁልቋሉ” መካከል የፍቅርና የሰላም ግንኙነትን በመፍጠር ዘላቂ ሰላም የሚመጣበትን መንገድ ማሰብ ያስፈልጋል። ያኔም የህዝብን የጭንቀት ጥያቄ መመለስ ይቻላል። በእነዚያ “ሞት አልባ ጦርነት” ዓመታት ውስጥ የድንበር አካባቢዎች ያለው ሰራዊት ‘ዛሬ እቀየር፣ ነገ እቀየር’ እያለ እንዳያስብና በሙሉ ስሜቱ ሀገራዊ ተልዕኮው ላይ ብቻ እንዲያተኩር ማድረግ እንደ ዜጋ ወታደርም መሆን ይመስለኛል።…የ”ጨፌ አራራ”ው ውሳኔ ይህን ፊት ለፊት አግጥጦ የሚታይ ህዝባዊ እውነታን የመለሰ ነው።   

የውሳኔውን ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ሌላ ጉዳይ ላንሳ። እንደ ኢትዮጵያ ያለች ህዳሴዋን ለማረጋገጥ ደፋ ቀና የምትል ሀገር፤ ዋነኛ ሃብቷ የሆነው ህዝቧን በልማት ስራ ላይ በነቂስ ማንቀሳቀስ ይኖርባታል። ለዚህ ደግሞ ሃሳብን የሚከፋፍሉና ሰላም የታጣባቸውን ጉዳዩች ለይቶ ማስወገድ ያስፈልጋል። በተለይ ከኤርትራ ጋር የሚዋሰኑ ህዝቦች ሙሉ ኃይላቸውንና አቅማቸውን ልማት ላይ ማዋል አለባቸው። በእነዚያ አካባቢዎች አርሶና አርብቶ አደሩ፣ ነጋዴው፣ የዕለት ሰራተኛው…ወዘተ. መንቀሳቀስ አለበት። እንደ ሌላዎቹ የቀጣናው ሀገራት ሁሉ፤ ከኤርትራ ጋር የነበረው የድንበር ንግድ ህግና ስርዓትን በተከተለ መንገድም መቀጠል አለበት። ከዚህም ሁለቱም ሀገሮችና ህዝቦች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ታዲያ ይህ እንዲሆን “ጨፌ አራራ” እስከ ዛሬ ድረስ የነበረውን ሁኔታ በመቀየር ወደ ድሮው ሰላማዊ ቦታው መመለስ ይጠበቅበታል።

ርግጥ ነው— የ“ጨፌ አራራ” የፍቅርና የሰላም መንደር መገኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ይሁን እንጂ፤ ግብሩ ግን ኢትዮጵያዊ ብቻ አይደም። ኤርትራዊም፣ ሱዳናዊም፣ ዱቡብ ሱዳናዊም፣ ኬንያዊም፣ ሩዋንዳዊም፣ ኡጋንዳዊም…ወዘተ. ነው። አፍሪካዊም ነው—ሰላምንና ውህደትን የሚያልም።

አዎ! የአርቅ መንደሩ ኢትዮጵያ በቀጣናውም ይሁን በአፍሪካ ያለባትን ሰላምን የማረጋገጥ ሃላፊነቷን እንድትወጣ በትጋት እየሰራ ነው፤ በሀሉም መስኮች። “ጨፌ አራራ” የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ለማገናኘት ቀዳሚውን የቀንዲልነት መቅረዙን በመያዝ ውሳኔውን ያሳለፈውም ለዚሁ ይመስለኛል። እኔም ውሳኔውን ‘ትክክልና ተገቢ ነው’ ያልኩት ከጠቀስኳቸው እውነታዎች በመነሳት ነው። በመጨረሻም፤ የእርቅ መንደሩ የ“ሞት አልባው ጦርነት”ን አውድ ለአንዴና ለመጨረሻ ዘግቶ፤ ወደ ሰላም አምባነት መቀየር ይቻለው ዘንድ፤ መላው የሀገራችን ህዝብ ከላይ የጠቀስኳቸውን የውሳኔውን አሳማኝ ምክንያቶች በውል በማጤን፤ ከ“ጨፌ አራራው” የእርቅ መሃንዲስ ጎን ቆሞ እንደ የዜጋ አምባሳደርነቱ ለሀገራቱ ሰላም ስኬት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል እላለሁ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy