Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለተቋማቱ ስኬት

0 350

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለተቋማቱ ስኬት

                                                          ሶሪ ገመዳ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በፓርላማ ተገኝተው በቀጣዩ ዓመት የፌዴራል መንግስት ስራ አስፈፃሚ አካላት ስራቸው ውጤታማ እንዲሆን ዕቅዶቻቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር እየተፈራረሙ ወደ ስራ እንደሚገቡ አሳውቀዋል። በዚህ መሰረትም አስፈፃሚ አካላቱ ሰሞኑን ከህዝብ ተወካዩዩች ምክር ቤት ጋር የስራ ውል ተፈራርመዋል።

ይህም የመንግስትን ስራ የሚፈጽሙ አካላት ተቆጥሮ የተሰጣቸውን ስራ ውጤቶችን ቆጥረው እንዲስስረክቡ ለማድረግ ያስችላል። ህግ አውጭው አካል በተቋማቱ ላይ ብርቱ ክትትል በማድረግ ውጤታማ ስራዎችን መፈፀም እንዲችሉም ያግዛል። የተሰሩ ስራዎችን ለማበረታታትና ያልተሰሩትንም በመጠቆም የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ለሚመለከተው አካል እንዲያቀርብም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ይህም ፓርላማው ራስን በራስ የማረም (Check and Balance) ስራዎችን እንዲፈፅም የሚያስችለውና ተቋማቱም ለስኬት እንዲበቁ በማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ባለፉት ዓመታት በአስፈጻሚው መስሪያ ቤት ላይ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ የነበረ ቢሆንም፣ ስራው አጥጋቢ ነው ሊባል የሚችል አይመስለኝም። ከሪፖርት በመነሳት ወቀሳን ከማቅረብ በስተቀር ጠንካራ እርምጃ ወስዷል ማለት አይቻልም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ እየወሰዷቸው ያሉት እርምጃዎች ግን ፓርላማው ስራን ቆጥሮ በመስጠት ቆጥሮ እንዲቀበል የሚያደርግ አሰራርን ከመጪው ዓመት ጀምሮ እንዲሰራ ከፌዴራል ተቋማት ጋር ውል አስሯል። ይህም ፓርላማው አስፈጻሚውን አካል እንዲቆጣጠረው የሚያደርግ ነው።

አሁን እየተከተልን ያለነው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዴሞክራሲያዊ ፓርላማን እየፈጠረ ነው። በህዝብ ተመራጭ የሆነ የፖለቲካ መስመርም የአገሪቱን ፖሊሲዎችንና ዕቅዶችንም የመምራት መብት ይኖረዋል።

እርግጥ በየትኛውም ዴሞክራሲን በሚከተል ሀገር ውስጥ ስራ አስፈፃሚውን የመቆጣጠር ስራ የስርዓቱ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ስለሆነም የአገራችን ፓርላማ ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኖሩም፣ አልኖሩም፤ አስፈፃሚውን አካል የመቆጣጠሩ ስራ ወሳኝ ብቻ ሳይሆን ለውይይት የሚቀርብ አጀንዳ አይደለም። ይህም በተለይ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን የለውጥ ሂደት የሚያግዝ ነው። በአገራችን የተጀመረው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ሂደት እንዳይቀለበስ ያደርጋል።

የፓርላማው አባላት ሰፊና ብቃት ያለው ትግል የሚያካሂዱበት እንዲሁም የስራ አስፈፃሚውን ዝርዝር ዕቅድ በመገምገም ቁጥጥር ማድረግ ህገ መንግስታዊ መብት አላቸው። በፓርላማው ውስጥ በሚያካሂዷቸው መድረኮችና መስክም በመገኘት የቁጥጥር በመከወን የሀገሪቱን የልማት ዕድገት የማስቀጠል አሊያም አሁን ካለበት ይበልጥ እንዲመነደግ የማድረግ ቁልፍ ህገ መንግስታዊና ህዝባዊ ኃላፈነት አለባቸው።

ፓርላማ በህዝብ ይሁንታ የሚገቡት አባላት የዘረፋንና የሌብነትን አካሄድ በመታገል ለህዝብ ጥቅም ይሰራሉ። በፓርላማ ውስጥ የሚገኙት የህዝብ ወኪሎች የዝብን ተጠቃሚነት በማስቀደም በብቃት ህገ መንግስታዊ ሃላፊነታቸውን ይወጣሉ።

ፓርላማ የሚገኙት አባላት የህዝቡ ወኪል እንደመሆናቸው መጠን የህዝቡን ጥቅም በማስጠበቅ አሁን ከተጀመረውና የአገሪቱ ዴሞክራሲ ባህል ለማስፋት ከሚደረግ ተግባር ጋር በተያያዘ ፓርላማው የቁጥጥር ተቋም እንዲሆን እንደሚያደርጉት በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።  

የፓርላማው አባላት አንዳንድ ማናቸውንም ነገሮች በዝምታ ማለፍ የለባቸውም። ዛሬም ይሁን ነገ አባላቱ በሚያምኑበት ዴሞክራሲያዊ መርህ እየተመሩ ተጠያቂነትን በማጎልበት ለውጡን ማበርታት ይኖርባቸዋል። ህዝቡ የሚያነሳቸውን ጉዳዮች በፓርላማው መድረኮች ላይ በማቅረብ ተጠያቂነት ባለው አኳኋን የአስፈፃሚው አካል ስራዎች እንዲከናወኑ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

የፓርላማው አባላት የስራ አስፈፃሚውን ዕቅድ አፈፃፀም በጥብቅ የመፈተሽና የህዝብን ቅሬታዎች የማንሳት ኃላፊነት ያለባቸው ናቸው። አስፈጻሚውን አካል የሚቆጣጠሩበት ምክንያትም ግልፅ ነው። ይኸውም ስህተቶች ካሉ በወቅቱ ታውቀው በፍጥነት እንዲስተካከሉ፣ በህዝቡ የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ካልሆኑ ለማብራራት እንዲቻል፣ ተገቢ ከሆኑ ደግሞ በወቅቱ የመፍትሔ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ስራ አስፈፃሚው የራሱን ዕቅድ ለመገምገም የሚያስችለው አሰራርና ስርዓት ያለው ነው። ይሁን እንጂ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ይህ ብቻ በቂ አይደለም። ምክንያቱም ፈፃሚው አካል ምንም እንኳን ራሱን በራሱ ሲገመግም ትክክለኛ ግምገማ ሊያካሂድ ቢሞክርም፣ ሁኔታዎችን ከራሱ ምልከታ አኳያ ማየቱ ስለማይቀር ነው።

ስለሆነም በአፈፃፀሙ ላይ ያልነበሩ ወገኖች የራሳቸውን ነፃ ግምገማ እንዲያካሂዱ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑ አይቀሬ ነው። ይህን ለመፈጸም ህዝብን ወክለው ፓርላማ የገቡት አባላት ተግባራቸው የላቀ ነው።

በህገ መንግስቱ አንቀፅ 55 ንዑስ አንቀፅ 4 ላይ እንደተገለጸው የፓርላማው አባላት የመላው ህዝብ ወኪል ናቸው። የአባላቱ ተገዥነትም ለህገ-መንግስቱ ለህዝቡና ለህሊናቸው ብቻ ነው። የጠራ ኢትዮጵያዊ ምልከታ ያላቸውም ስለሆኑ አስፈጻሚዎቹ ተቋማት በገቡት ውል መሰረት ስራቸውን እንዲፈጽሙ እንደሚያደርጉ ጥርጥር የለውም።

አብዛኛዎቹ የፓርላማ አባላት ከአፈፃፀም ስራው ነፃ ስለሚሆኑ፤ ከአስፈፃሚው ዕይታ ነፃ በሆነ አኳኋን ሁኔታዎችን የማየት ዕድል ይኖራቸዋል ተብሎ ይታሰባል። እንዲሁም በህዝብ ተወካይነታቸው ከምንም በላይ ነገሮችን ከህዝቡ ጥቅም አኳያ የመመዘን ብቃት ስላላቸው፤ አስፈፃሚውን አካል ከመቆጣጠር አኳያ ትልቅ የግምገማ አቅም መሆናቸው አያጠያይቅም።

የፓርላማው አባላት ከፌዴራል ተቋማት ጋር በተፈራረሙት ውል መሰረት አጣርተው ያገኙትን መረጃ ለአስፈፃሚዎቹ በሚገባ አስረድተው በምን መልኩ ማብራሪያ እንደሚሰጥበት ወይም እንደሚስተካከል ይገልፃሉ። በውሉ መሰረት ያልተሰሩትን ያጋልጣሉ። የእርምት እርምጃ በመውሰድ ከዛሬ ነገ የተሻለ ስራ በግልፅነትና በተጠያቂነት መንፈስ እንዲከናወን ያደርጋሉ።

 

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy