Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለእኛ የሚበጀን መደመር ብቻ ነው

0 278

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለእኛ የሚበጀን መደመር ብቻ ነው

 

ክፍል አንድ

አሜን ተፈሪ

ልቤ ያለው በኪነ ጥበብ እና በባህል ገደማ ነው፡፡ ሆኖም ሐገሪቱ እንዲህ ያለውን ስሜት ወይም ፍላጎት እንደ ፌዝ የምትቆጥረው ይመስለኛል፡፡ ‹‹ቀልደኛ ገበሬ በሰኔ ይሞታል›› ሊያሰኛት ይችላል፡፡ ኪነ ጥበባዊ እና ባህላዊ ጉዳዮች በሰላማዊ ማህበራዊ አውድ የሚከወኑ ናቸው፡፡ ሰላማዊ – ማህበራዊ ህይወት ደግሞ ፍትህ፣ እኩልነት እና ነጻነት በሰፈነበት የተደላደለ የፖለቲካ ስርዓት የሚከወኑ በመሆናቸው፤ የኪነ ጥበብ እና የባህል ጉዳዮችን ለመሥራት በፖለቲካ ጉዳዮች ማትኮር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ‹‹የጠሉት ይወርሳል፤ የፈሩት ይደርሳል›› እንዲሉ ሆኖ፤ የኪነ ጥበብ እና የባህል ጉዳዮችን ትቼ፤ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ለማትኮር እገደዳለሁ፡፡ የመኖሬ ግብ አድርጌ የምመለከታቸውን ኪነ ጥበባዊ እና ባህላዊ ሥራዎችን ለመሥራት፤ ሰላማዊ – ማህበራዊ ህይወትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የፖለቲካ ስርዓት የሰፈነበት ሐገር ለመፍጠር መስራት ግድ ይሆናል፡፡

 

አሁን የምንገኝበት ሁኔታ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከወታደራዊ መኮንኖች ጋር በተወያዩ ጊዜ እንዳሉት፤ ‹‹ሐገራችን ተወንጭፋ ለመሄድ እና ዘጭ ብላ ለመውደቅ›› በምትችልበት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ሐገራችን በእንዲህ ያለ አሳሳቢ ነገር ተከብባ ባለችበት ሁኔታ ስለ ፖለቲካዊ ችግሮቻችን መነጋገር ይኖርብናል፡፡ የሐገራችንን ጉዳይ በዝምታ ማየት አይገባም፡፡ ዝምታ ከድርጊት ይቆጠራል፡፡ የእኛ ዝምታ የምንጠላው ነገር እንዲመጣ የሚያደርግ ከሆነ፤ ዝምታችን የምንጠላውን ነገር እንዲመጣ ከመተባበር የተለየ ትርጉም አይኖረውም፡፡ አንዳንዶች የምንጠላው መጥፎ ነገር እንዲፈጠር ሲሰሩ እያየን እኛ ዝም ካልን፤ ይህ የምንጣላው ነገር እንዲፈጠር ከመተባበር አይለይም፡፡ መጥፎ ነገርን ከመደገፍ የተለየ ተግባር አይሆንም፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ሁኔታ ዝምታው የሞራል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከወንጀል የሚታሰብም ነገር ሊሆን ይችላል፡፡

 

እንደሚታወቀው የወንጀል ድርጊት የሚፈጸመው፤ በማድረግ (Commission) ወይም ባለማድረግ (Omission) ነው፡፡ በህግ፣ በሞራል ወይም በሥነ ምግባር ደንብ እንዲደረግ የሚጠበቀውን ነገር ባለማድረግ (በኦሚሽን) ወይም እንዳይደረግ የተከለከለውን ነገር በማድረግ (በኮሚሽን) ወንጀል ሊፈጸም ይቻላል፡፡ አንድ ነገር ማድረግን በሚጠይቅ ሁኔታ ውስጥ ሆነን፤ ያም ሁኔታ ሐገርን የሚያክል ትልቅ ነገርን የሚመለከት ነገር ሆኖ ሳለ፤ ህዝብን ያክል ክቡር አካል የሚጎዳ ችግር ሆኖ ሳለ፤ ዝምታ ወንጀል ነው፡፡ ስለዚህ በተለያዩ የሐገራችን አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰተውን እና ለበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነውን ግጭት በዝምታ መመልከት አንችልም፡፡ የችግሩም ምንጭ ባለፉት ዓመታት የመጣንበት የአስተሳሰብ ጎዳና ነው፡፡

 

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለመከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ በተለይ በአሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ወሰን አካባቢ የተከሰተውን አሳሳቢ ግጭት መሐል በመግባት እንዲያበርዱ ትዕዛዝ በሰጡበት አጋጣሚ ሲናገሩ፤ ‹‹ባለፈ ፋሽን የምትመሩ ሰዎች፤ በጠባብ ነገር ውስጥ ገብታችሁ፤  ህዝብን ከህዝብ ከምታጋጩ፤ በለመድነው ትርፍ በማያመጣ ነገር ተሳትፋችሁ ሰውን ከምታፋጁ፤ እስካሁን ባልሞከርነው እና ለሁላችንም የሚበጀውን ሐገራዊ አንድነት በማጠናከር ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ ተግባር ጉልበታችሁን እና ጊዜአችሁን ለሁላችንም ይበጃል›› ብለው ነበር፡፡

 

አያይዘውም፤ አንዳንድ አርቲስቶች፣ አክቲቪስቶች እና ሌሎች ግጭቱን በማባባስ ረገድ አፍራሽ ሚና የሚጫዎቱ ሰዎች ከዚህ አጥፊ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ በማሳሰብ፤ በሚከሰቱት ግጭቶች የሚጎዳው እና የሚሞተው ድሃው ብቻ መሆኑን በማስታወስ፤ በተበላሸ እና ፋሽኑ ባለፈ አስተሳሰብ የሚመሩት ጥቂት ሰዎች እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ብዙሃኑ ህዝብ አጥፊ ድርጊታቸውን ማስቆም ባይቻለው እንኳን ሐሳባቸውን ባለመቀበል የጥፋት ዘመቻቸውን እንዲያመክን ጥሪ አድገርገዋል፡፡ አንዳንድ ፖለቲከኞች እሳቱ እንደማይነካቸው አረጋግጠው፤ የህዝብ ልጆችን የሚለበልብ እና እንደ ቅጠል የሚያረግፍ የግጭት እሣት ይለኩሳሉ፡፡

 

ፖለቲካ የብዙ ሰዎችን ህይወት ሊቀይር የሚችል ውብ ነገር ቢሆንም፤ ነገር ግን በመጥፎ መርህ በሚመራ ሰው (ቡድን) እጅ ሲያዝ፤ እንደ ፖለቲካ አስቀያሚ ነገር አይገኝም፡፡ ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ እንዳሉት፤ ክፉ ፖለቲከኞች የሚያነሱት ሐሳብ ተቀባይ ከሌለው መክኖ የሚቀር ነው፡፡ በመጥፎ መርህ በሚመራ ሰው (ቡድን) የተያዘ ፖለቲካ ህዝብን ምን ያህል እንደሚጎዳ ለመረዳት የሚያስችሉ በርካታ የታሪክ መረጃዎችም አሉ፡፡ ከእነዚህ የታሪክ መረጃዎች አንዱ የአዶልፍ ሂትለር ታሪክ ነው፡፡

 

ሂትለርን መጥፎ የሚያደርገው የፖለቲካ አስተሳሰብ መርሁ፤ እንጂ ፍጥረቱ አይደለም፡፡ የአስተሳሰብ ወይም የመርህ እንጂ የሰው መጥፎ እንደሌለው የሚያስረዳው አርስጣጣሊስ፤ ‹‹ሰው ከእንስሳት ሁሉ የላቀ ማዕረግ እና የተለየ ጸጋ ያለው ፍጡር በመሆኑ፤ በመልካም እሴቶች የታነጸ፤ በፍትህ እና በህግ የተገራ ሰብእና ሲኖረው፤ ከእንስሳት ሁሉ የላቀ ማዕረግ የሚይዘው ፍጡር፤ ከፍትህ እና ከህግ የራቀ ስድ በሆነ ጊዜ ደግሞ ከሁሉም እንስሳት ዝቅ ያለ ፍጡር ይሆናል›› ይላል፡፡

 

የሰዎችን ህብረት ወይም መንግስትን ወይም ሌላ ማናቸውንም ነገር ህብረተሰባዊ ተቋም ለመርመመር የሚሻ ሰው፤ ስለሚያጠናቸው ነገሮች ግልጽ የሆነ እይታ ወይም ግንዛቤ ይኖረው ዘንድ፤ የሚመረምረውን ነገር ወደ ጥንተ ነገሩ ወይም ወደ መነሻ ዘሩ አውርዶ፤ ያ ነገር በዕድገቱ መነሻ (የመጀመሪያ ምዕራፍ) ምን እንደሚመስል ለመረዳት መሞከር ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም፤ በሌላ የሳይንስ ዘርፍ እንደሚደረገው፤ በሥነ መንግስት ወይም በፖለቲካ ጥናት ውስጥ አንድን መንግስታዊ ስርዓት የሚፈጥሩትን ነገሮች ገነጣጥሎ (ፈታትቶ) አዋቃሪ ክፍሎችን (አላባዎችን) ለያይቶ በማስቀመጥ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የአንድ ሙሉ አካል አዋቃሪዎች ተገነጣጥለው እንዲቀመጡ ማድረግ ያስፈልጋል – አሪስጣጣሊስ እንደሚለው፡፡

 

በመሆኑም፤ ህብረተሰብ ወይም መንግስት የብዙ ሰዎች ስብስብ ከሆነ፤ ከሁሉ አስቀድሞ ይህ ስብስብ ሊኖር የሚችለው፤  ተጋበተው ለመውለድ የሚችሉ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ሲኖሩ ነው፡፡ ሴት እና ወንድ ሳይኖሩ ህብረተሰብ ሊኖር አይችልም፡፡ የሰው ዘር በምድር መኖሩን ይቀጥል ዘንድ፤ የአንድ ሴት እና ወንድ መኖር ግድ ነው፡፡ የሴት እና የወንድ ጥምረት የሚፈጠረውም በሰዎች ፈቃድ አይደለም፡፡ በሰዎች ፈቃድ አይደለም ሲባል፤ የሰው ልጆች አምሳያቸውን ተክቶ በማለፍ የተፈጥሮ ዝንባሌ የሚገዙ መሆናቸውን ለመጠቆም ነው፡፡ ይህ ዝንባሌ ከማናቸውም ሌሎች እንስሳት ወይም ዕጽዋት ጋር የሚጋሩት የተፈጥሮ መሻት እና የተፈጥሮ ዝንባሌ ነው፡፡ በዚሁ አግባብ ወንድ እና ሴት የተፈጥሮ ግብራቸውን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ አምሳያቸውን በመተካት ራሳቸውን ህያው ያደርጋሉ፡፡ ወይም ዘራቸው ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ያደርጋሉ፡፡

 

አሪስጣጣሊስ እንደሚለው፤ ተፈጥሮ አንዱን ጌታ ወይም አለቃ፤ ሌላውን ደግሞ ተገዢ አድርጋ ልታኖር አስቀድማ ወስናለች፡፡ አንዱን ገዢ ሌላውን ተገዢ በማድረግ ለማኖር ምርጫ አድርጋለች፡፡ በዚህ መሠረት፤ አንድ ፍጡር አዕምሮውን ተጠቅሞ መጪውን ነገር አስቀድሞ ለማየት ከቻለ፤ ተፈጥሮ ጌታ እና አለቃ አድርጋ ልታኖረው መርጣዋለች ማለት ነው፡፡ በተቃራኒው፤ አንድ ነገር ሲደርስበት በአካሉ ምላሽ ከመስጠት በቀር፤ በህሊናው ኃይል አስቀድሞ መጪውን ለማየት የማይችለውን ፍጡር ተገዢ (ተመሪ) እንዲሆን ደንግጋለች ይላል፡፡ ግን ልዩነቱ የተፈጥሮ አይመስለኝም፡፡

 

አሪስጣጣሊስ እንደሚለው፤ ሰው ገና ሲወለድ አዕምሮ የሚባል ልዩ ጸጋ ታጥቆ የሚወለድ ነው፡፡ ታዲያ ይህ መሣሪያ ለልማትም ሆነ ለጥፋት ሊውል ይችላል፡፡ ይህ የታጠቀው መሣሪያ በአስተዋይነት፣ በግብረ ገብነት እና በትክክለኛ የፖለቲካ መርህ  ተገርቶ በጥቅም ላይ ካልዋለ፤ በአጭሩ ሰው ግብረ ገብነት የሌለው ፍጡር ከሆነ፤ በማዕረጉ ከእንስሳትም የወረደ ርኩስ፣ ጨካኝ ወይም አረመኔ ይሆናል፡፡ መሣሪያ የታጠቀ ኢ-ፍትሐዊነት እና በመልካም እሴት ያልታነጸ አዕምሮ አንድ ናቸው፡፡ በእውር ፍላጎት እና በአልጠግብ ባይነት ስሜት የተሞላ መንፈስ አጥፊ ነው፡፡

 

ሰዎችን እንደ አንድ አካል በሰላም አስተሳስሮ የሚይዝ ማህበራዊ ገመድ ፍትሕ ነው፡፡ የአንድ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ሰላም እና መረጋጋት የሚረጋገጠው በፍትሕ መስፈን ነው፡፡ ሆኖም ሰዎች በእውር ፍላጎት እና በአልጠግብ ባይነት እየተመሩ ሰዎችን በሰላም አስተሳስሮ የሚይዘውን ማህበራዊ ገመድ ወይም ፍትሕን በመጉዳት ሰላም እና ህብረቱን ያጠፉታል፡፡

 

ዝቅተኛው የሰዎች ህብረት ቤተሰብ ነው፡፡ የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት ፍላጎት ለማሟላት የተመሠረተ ህብረት ነው፡፡ ‹‹ቤተሰብ›› በተፈጥሮ የተመሠረተ ህብረት ነው፡፡ ነገር ግን የሰዎች ህብረት በቤተሰብ ብቻ አይወሰንም፡፡ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ በርካታ ቤተሰቦች የዕለት ተዕለት ፍላጎትን ከሟሟላት ከፍ ያለ ሌላ ዓላማን ለማሳካት ህብረት ይፈጥራሉ፡፡ በመሆኑም፤ በዚህ ሂደት በመጀመሪያ ሊፈጠር የሚችለው ህብረት መንደር ነው፡፡ የተፈጥሮ ጎዳናን ተከትሎ በተፈጠረው በዚህ ህብረት (መንደር) ልጆች እና የልጅ ልጆች ይኖራሉ፡፡ አንድ ጡት ጠብተው የሚያድጉት የአንድ ማህጸን ፍሬ ወገኖች በአንድ የሚኖሩበት መንደር ነው፡፡

 

በበርካታ ቤተሰቦች ስብስብ የሚፈጠረውን ህብረት፤ አሪስጣጣሊስ ‹‹ኮሎኒ›› ይለዋል፡፡ በ‹‹ኮሎኒ›› የሚጸናው አስተዳደር ደግሞ ንጉሳዊ አስተዳደር ነው፡፡ ምክንያቱም፤ የእነዚህ ሰዎች ትስስር የደም ትስስር ነው፡፡ ግንኙነቱም ግለሰባዊ ነው፡፡ እያንዳንዱ አባወራ ለልጆቹ እና ለሚስቶቹ ህግን አውጥቶ እንደሚያስተዳድር ንጉሱም እንዲሁ ያደርጋል ማለት ነው፡፡

 

አንዳንድ ሰዎች ርዕሰ ብሔርን፣ ንጉስን የቤተሰብ አስተዳዳሪን ወይም አለቃን የማይለያዩ ነገሮች አድርገው ያያሉ፡፡ እናም በመሠረታዊ ብያኔ ተመሳሳይ መሆናቸውን ያስባሉ፡፡ በእነሱ ሐሳብ የተጠቀሱት አካላት የሚለያዩት በዓይነት ሳይሆን በሥራቸው በሚተዳደሩ ሰዎች ቁጥር መብዛት እና ማነስ ነው፡፡ በቁጥር እንጂ በሌላ አይለያዩም ብለው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ብያኔ የተሳሳተ ነው፡፡ ምክንያቱም መንግስታት በዓይነት ይለያያሉ፡፡ ጉዳዩን በደንብ ለመረመረ ለማንም ሰው ፍንትው ብሎ ሊታየው እንደሚችለው መንግስት በዓይነት ይለያያሉ፡፡

 

ለምሣሌ፤ በጥቂት ሰዎች ላይ የሰለጠነ ሰው ‹‹አለቃ›› (ማስተር)፤ ከዚያ በቁጥር ከፍ ባለ ሰው ላይ የሰለጠነ ‹‹ማናጀር››፤ አሁንም ከዚያ ከፍ ያለ ቁጥር ባላቸው ሰዎች ላይ የሰለጠነ ሰው፤ ‹‹ርዕሰ ብሔር›› ወይም ‹‹ንጉስ›› እንደሚባል ያስባሉ፡፡ በዚህም በትልቅ ቤተሰብ እና በትንሽ ሐገረ ብሔር መካከል ልዩነት የሌለ ያስመስሉታል፡፡ ሆኖም በንጉስ እና በርዕሰ ብሔር መካከል ልዩነት አለ፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት፤ አንድ መንግስት ግለሰባዊ ከሆነ ገዢው ንጉስ ይባላል፡፡ ሆኖም ዜጎች ገዢ የሆኑበት እና በፈንታቸው ደግሞ ተገዢ በሚሆኑበት አውድ የሚሰለጥን ሰው ርዕሰ ብሔር ነው፡፡

 

‹‹ሰው በተፈጥሮ ፖለቲካዊ እንስሳ ነው፡፡ በመሆኑም የመንግስት ምስረታ የአጋጣሚ ሳይሆን ከተፈጥሮ ግዴታ የመነጨ ክስተት ነው›› የሚለው አሪስጣጣሊስ፤ ‹‹መንግስት (ስቴት) የሌለው ሰው፤ አንድም መጥፎ ሰው ነው፤ አለያም ከሰው የላቀ ማዕረግ ያለው ሌላ ፍጡር ወይም መልዐክ ነው›› ይላል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy