Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለጨናቂው ችግር እየደረሱ ያሉ መፍትሄዎች

0 524

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለጨናቂው ችግር እየደረሱ ያሉ መፍትሄዎች

አለማየሁ አ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ተከታታይ እድገት ማስመዝገቡን ከኢፌዴሪ መንግስት መግለጫዎች በተጨማሪ ዓለም አቀፍ የገንዘብና የኢኮኖሚ ተቋማትም ምስክርነታቸውን ሰጥተወታል። አጠቃላይ ዓመታዊ ምርትና አገልግሎት ለአንድ ተኩል አስርት ዓመታት ያህል ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ እድገት፣ አንዳንድ ምስክርነት ሰጪዎች እንደሚሉት ደግሞ ለሁለት አሃዝ የተጠጋ እድገት ቢያሳይም የሃብት ክፍፍሉ ግን ችግር እንዳለበት በተጨባጭ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያመለክታል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) እ ኤ አ የ2017 ዓ/ም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አፈፃፀምና ቀጣይ ሁኔታዎች ገምግሞ መስከረም ወር ላይ ይፋ ባደረገው ሪፖርት የአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት በ9 በመቶ እንደሚያድግ መግለጹ ይታወሳል። ሃገሪቱ ለዓለም ገበያ የምታቀርባቸው ሸቀጦች ዋጋ ቢቀንስም፤ የድርቅ ተፅእኖ በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች ቢታይም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እነዚህን ፈተናዎች ከመቋቋም አንፃር ጠንካራ አፈፃፀም እንደነበረውም የተቋሙ ሪፖርት አመልክቷል። የሃገሪቱ የወጪ ንግድ አፈፃፀም ግን ባለበት መቆሙን ነበር የተቋሙ ሪፖርት የሚያሳየው። በተለይም በዓለም አቀፍ ገበያ  የሸቀጦች ግብይት መቀዛቀዝና የወጪ ንግዱን ያግዛሉ ተብለው የሚጠበቁ ፕሮጀክቶች መጓተት አፈፃፀሙ ዝቅተኛ እንዲሆን ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል።

አይ.ኤም.ኤፍ ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2018 ዓ/ም ከፍተኛ እድገት እንደምታስመዘግብ በጥር ወር ይፋ ባደረገው ትንበያው አመልክቷል። የደርጅቱ ትንበያው እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2018 ዓ/ም የ8 ነጥብ 5 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ታስመዘግባለች። የሃገሪቱ የድህነት ምጣኔም እ ኤ አ 2000 ከነበረበት 44 በመቶ በ2015/16 ወደ 23 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ማለቱንም ገልጿል።

ከላይ የተገለዑት በገለልተኛ አካል የቀረቡ የአፈጻጻም ሪፖረቶችና ትንበያዎች በሃገሪቱ የተመዘገበው እድገትና በድህነት ቅነሳ ላይ የታየው ውጤት ተጨባጭ መሆኑን ያመለክታሉ።

የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደኢንደስትሪ ለማሸጋጋር ከ2003 እስከ 2007 ዓ/ም ተግባራዊ የተደረገው የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ፤ እንዲሁም ከ2008 እስከ 20012 ዓ/ም ተግባራዊ የሚደረገው ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች እድገቱን ማስሰቀጠል ቢችሉም፣ በተለይ በማኑፋክቸሪንግና የወጪ ንግድ ላይ የተገኘው ውጤት ደካማ ነው። የአይ ኤም ኤፍና የሌሎች ገለልተኛ የገንዘብና የኢኮኖሚ ተቋማት ግምገማዎችም ይህን አረጋግጠዋል።

በተለይ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን የኢኮኖሚ ድርሻ በማስፋት የወጪ ንግድን ለማሳደግ ተይዞ የነበረው እቅድ አለመሳካት፣ በግብርና ምርቶች ዘርፍ የወጪ ንግድ እድገትም ላይ ከታየው ድክመት ጋር ተዳምሮ ሃገሪቱ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተጋልጣለች። በሃገሪቱ ከሶስት ወራት በፊት በሃገሪቱ የነበረውና አሁንም አልፎ አልፎ ብልጭ የሚለው ግጭት የፈጠረው ፖለቲካዊ ሁኔታ የፈጠረው ስጋት ባለሃብቶች ሃብታቸውን በውጭ ምንዛሪ ቀይረው እንዲሸሽጉ፣ አንዳንዶቹም ከሃገር እንዲያሸሹ ያደረገበት ሁኔታም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ላይ ድርሻ እንዳለው የታመናል። በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሃገሪቱ ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታ በመቃወም ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዳይልኩ የተደረገው ቅስቀሳም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ያባባሰ ምክንያት ነው።

በሃገሪቱ የተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የጥቁር ገበያን የምንዛሪ ምጣኔ ከባንክ የምንዛሪ ምጣኔ ከ35 በመቶ በላይ እንዲያሻቅብ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል። የጥቁር ገበያው የውጭ ምንዛሪ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍጠነት ማሻቀብ በቀጣይ የበለጠ ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋትና ተስፋ መፍጠሩም የምንዛሪ ፍላጎትን በማሳደግ የምንዛሪው ምጣኔ ማሻቀብ የተጋነነ እንዲሆን አድርጓል። የውጭ ምንዛሪ ጭማሪው የታየው በጥቁር ገበያ ላይ ቢሆንም፣ በባንክ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመኖሩ ህጋዊ አስመጪ ነጋዴዎችም ጭምር ጥቁር ገበያውን ወደመጠቀም በማዘንበላቸው በተለይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጨማሪ ታይቷል። በህጋዊ መንገድ ብቻ የሚገቡት ምርቶች ላይም እጥረት አጋጥሟል። ብዙም የተጋነነ አይሁን እንጂ ህይወት አቆዪ የሆኑ መድሃኒቶች ላይ ጭምር እጥረት ተፈጥሮ ዜጎች ለከፍተኛ ሰጋት ተዳርገው እንደነበረ ይታወቃል።

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በተወነ ደረጃም ቢሆን ለኑሮ ውድነት ምክንያት ከመሆኑና ለምርት እጥረት ሰበብ ከመሆኑ ባሻገር፣ ሁኔታው ካልተለወጠ በቀጣይ የኢኮኖሚውን በሚፈለገው ልክ ማሳደግ የማይቻልበትን ሁኔታ ደቅኗል። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ማሳደግ፣ ለኢኮኖሚው እድገት ወሳኝ የሆኑ የመሰረተ ልማት ማስፋፋት ስራዎች ወዘተ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይጠይቃሉ። እጥረቱ መፍትሄ ሳያገኝ ከዘለቀ የኢኮኖሚው እድገት ከመገታቱም ባሻገር የውጭ ንግዱ በእጅጉ የሚዳከምበት ሁኔታ የፈጠራል። በመሆኑም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ማቃለል የሚያስችሉ መፍትሄዎችን ማበጀት ፋታ የሚሰጥ ጉዳይ አይደለም።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ የሚመሩት የለውጥ አመራር በሃገሪቱ ለተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ልዩ ተኩረት ሰጥቷል። ችግሩን ለማቃለል ወቅታዊ እርምጃዎችን ወስዷል። ከተወሰዱት እርምጃዎች መሃከል ከተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ አልጋ ወራሽ ጋር 1 ቢሊየን ዶላር በአጭር ጊዜ የብሄራዊ ባንክ ክምችት ውስጥ እንዲገባ የተደረሰው ስምምነት ተጠቃሽ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በሃገሪቱ ባለሃብቶች አማካኝነት የ2 ቢሊየን ዶላረ ኢንቨስትመንት እንዲከናወን ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ይህ ብቻ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያራምዱት የእርቅ፣ የይቅርታ፣ ምህረትና መደመር መርህ በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ላይ ቀና አመለካከት እንዲኖራቸው አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚህ ቀና አመለካካት ላይ ተመስርተው ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ለዘመድና ወዳጆቻቸው በህጋዊ መንገድ ገንዘብ እንዲልኩ፣ እንዲሁም በቀን እሰከ 1 ዶላር የሚደርስ ገንዘብ በትረስት ፈንድ አማካኝነት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ለዚሀ ጥሪ በጎ ምላሽ እየሰጡ ነው። የድጋፍ ተረስት ፈንድ የባንክ ሂሳብም ይፋ ተደርጎ የድጋፉ እንቅስቃሴ ተጀመሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ የውጭ ምንዛሪ ወደብሄራዊ ባንክ እየገባ መሆኑን አመልክተዋል። ምናልባት የተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች መንግስት ቃል የገባው 1 ቢሊየን ዶላር ወደባንክ ክምችት መግባት ጀምሯል የሚል ግምት አለ። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚለኩት ሬሚታንስም እድገት እያሳየ የመስላል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን መነሻ በማደረግ፤ የውጭ ገንዘቦች የጥቁር ገበያ ምንዛሪ ምጣኔ ማሽቆልቆሉ ስለማይቀር፣ የውጭ ምንዛሪ ደብቀው ያከማቹ ግለሰቦች ወደባንክ ሄደው እንዲመነዝሩ፣ ባንኮችም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብለው እንዲመነዝሩ አዘዋል። ይህን ተከትሎ የጥቁር ገበያ ምንዛሪ ከባንክ ምንዛሪ ጋር ተቀራራቢ ሆኗል። የውጭ ምንዛሪ የሸሸጉ ግለሰቦች ጥሪውን ሰምተው ገንባቸውን ወደባንክ ካልወሰዱ አሰሳ በማደረግ የህግ እርምጃ እንደሚወሰድ ማስጠንቀቂያ አዘል ማሳሰቢያም ሰጠተዋል። አሁን የውጭ ምንዛሪ የሸሸጉ ሰዎች ገንዘባቸውን ከጓዳ እያወጡ ወደባንክ አየወሰደዱ ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዳመለከተው ሰሞኑን ወትሮ በሳምንት የማይመጣ የውጭ ምንዛሪ መጠን በቀን ወደባንኩ እየመጣ በመመንዘር ላይ መሆኑን አሰታውቋል።

በአጠቃላይ እነዚሀ ሁኔታዎች የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ችግር የሚያቃልሉ ዋነኛ መሳሪያዎች ባይሆኑም  አሁን የተፈጠረውን አስጨናቂ ችግር በመፍታት ረገድ ድርሻ ይኖራቸዋል። የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ለዘለቄታ መፍታት ግን የወጪ ንግዱን በጉልህ ከማሳደግ፣ የቱሪዝም ኢንደስትሪውን በሃገሪቱ አቅም ልክ ከማሳደግ ውጭ አማራጭ የለውም።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy