Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መተማመን የፈጠረው ጭማሪ

0 251

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መተማመን የፈጠረው ጭማሪ

                                                       ይሁን ታፈረ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላም እንዲፈጠር ባደረጉት ጥረትና ለጉብኝትም ወደ ኤርትራ በማቅናታቸው ምክንያት በአገራችን ውስጥ በርካታ ለውጦች ተከስተዋል። ከለውጦቹ ውስጥ አንዱና ዶላር መር የሆነው የኢትዮጵያ የቦንድ ሽያጭ በእጅጉ መጨመሩ ነው።

“ሬውተርስ” (Reuters) የተሰኘው የዜና አውታር ሰሞኑን እንደዘገበው በቦንድ ሽያጩ ላይ የአገራችን የቦንድ ሽያጭ ጭማሪው ዋጋ ባለፉት 10 ሳምንታት ውስጥ ከታዩት ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል። ጭማሪው በዜሮ ነጥብ 583 ዶላር ሳንቲም ዕድገት ማምጣቱንና ይህም አንድ የኢትዮጵያ ቦንድ የዶላር ሽያጭ ሶስት ዶላር ጭማሪ እንዲያሳይ ምክንያት ሆኗል።

የዜና አውታሩ በዋቢነት የጠቀሳቸው የ“ስታንቢክ” (Stanbic) ባንክ እና የምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ባሙያ የሆኑት ጂብራን ቁረይሽ፣ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቦንድ ሽያጭ እድገት ያሳየው በአገሪቱ እየተወሰደ ያለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ሳቢያ እንደሆነ መናገራቸውን አትቷል። ይህ ሁኔታም በባለ ሃብቶች ዘንድ የኢትዮጵያ ቦንድ የተሻለ ፍላጎትና መተማመን እንዳሳደረም አብራርቷል።

ከዚህ ዘገባ የምንረዳው ነገር ቢኖር አገራችን ሰላም ስትሆን ባለሃብቶች እምነት እንደሚያድርባቸውና መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንደሚኖራቸው እንዲሁም ለእድገታችን መፋጠን ወሳኝ የሆኑ ጉዳዩች በመተማመን መንፈስ ጭማሪ እንዲያሳዩ የሚያደርግ መሆኑን ነው።

ሰላማችን በተጠናከረና የስጋት ደመናዎች በተገፈፉ ቁጥር ነገም በርካታ ለውጥ አምጪ ጭማሪዎችን ልናስመዘግብ እንችላለን። ስለሆነም ሁሉም ዜጋ በየአካባቢው ሰላሙን በመጠበቅና ለስጋት ምንጭ የሆኑ ጉዳዩችን ሊደፍን ይገባል።

ህዝቡ በየቀየው ላለው የሰላም ሁኔታ ዋነኛ መሰረት ነው። በማንኛውም አካባቢ ለሚከሰት ማናቸውም የሰላም አለመኖር ድርጊት መልሶ የሚጎዳው እርሱን ነው። አገርን ነው። አገር ሰላም እንዲሆን በቅድሚያ መንደር ሰላም መሆን ይኖርበታል።

ዛሬ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዛሬ እንደ ትናንቱ ጦርነት ያንዣበበትን የሰቆቃ ህይወት አይመሩም። ሁከት አይፈልጉም። ራሳቸው በፈጠሩት የለውጥ ማዕበል ውስጥ ናቸው። ይህ በለውጡ ምክንያት በአገራችን የተፈጠረው አስተማማኝ የሰላም የኋሊት እንዲቀለበስ የራሳቸው ድብቅ የፖለቲካ ፍላጎት ካላቸው ውጭ የትኛውም ዜጋ አይፈልግም።

ስለሆነም በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን የሰላምና የመረጋጋት ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር መተባበር ያስፈልጋል። እርግጥ በየትኛውም ሀገር ውስጥ እውን እንዲሆን የሚፈለግ ሰላም ያለ ህዝቡ ተሳትፎ ምንም ዓይነት ውጤት ሊያመጣ አይችልም። የሰላም ዋጋን ዋነኛ መዛኙ ሃይል ህዝብ ስለሆነ።

እርግጥም ለአንድ ሀገር ልማትና ዕድገት ሰላም ከምንም በላይ የገዘፈ ዋጋ ያለው መሆኑ አያጠያይቅም። እንደ እውነቱ ከሆነ የሰላም ዋጋ በምንም አይነት ምድራዊ ዋጋ ሊለካ የሚችል አይመስለኝም። ሰላም የሚተመንበት አሊያም የሚሰፈርበት ልኬትም የለውም።

ስለሆነም ዜጎች መብትና ግዴታዎቻቸውን ሲያውቁና ሌላውን ለማስተማር ሲነሳሱ የሀገር ሰላም ይረጋገጣል። ልማትና ዕድገትም ይደረጃሉ፤ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችም በዚያው መጠን እያበቡ ይሄዳሉ። የውጭ ባለሃብቶችም በአገራችን ተማምነው “ሮይተርስ” የዜና ወኪል እንደገለፀው ኢኮኖሚያችን እንዲያንሰራራ ምክንያት ይሆናል።

የአገርን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ የመንግስት ብቻ አይደለም። ዋነኛው ተዋናይ መሆን የሚገባው ህዝብ ነው። ህዝቡ በያለበት ሆኖ ሰላሙን ከጠበቀ ሰላምን ለማደፍረስ የሚሮጥ የትኛውም ሃይል አቅም አይኖረውም።

እርግጥ የሰላምን ምንነት የሚገነዘብ ህዝብ ውስጥ ሁከት ፈጣሪዎች ሊኖሩ አይችሉም። ስለሆነም ህዝብ የሚጠቀምባቸውን ማንኛውንም ዓይነት ንብረቶችንና የግለሰቦችን ሃብት ሊወድሙ አይችሉም።

የለውጥ አደናቃፊ ሃይሎችን አሉባልታ የማይሰማ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የዜጎች ንብረት በምንም ዓይነት መንገድ እንዲወድም እድል አይሰጥም። ወጣቶች እንደ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ መሆን ይሻሉ። ተጠቃሚነታቸውን ማሳካት ያለባቸው ግን በህጋዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ መሆን ይገባዋል። ይህ ህጋዊነትም ባለሃብቶች በእኛ ላይ አመኔታ እንዲኖራቸው ያደርጋል።

ሰላም ከሌለ ምንም ነገር ስለማይኖር በሰላም ጉዳይ መደራደር አያስፈልግም። ሰላም ከሌለ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚመኘውን ተጠቃሚነት እውን ማድረግ አይችልም። ሰላም ከሌለ ልማትንም ይሁን ዴሞክራሲን ማስፋትና ማረጋገጥ አይቻልም። ሰላም በሌለበት ሁኔታ ከእነዚህ መሰረታዊ መብቶች ባሻገር ዋነኛውና በህይወት የመኖር ዋስትና ሊኖር አይችልም።

የሰው ልጅ በህይወት መኖር ካልቻለ ደግሞ ስለ ሌላው መሰረታዊ መብቶች ማሰብ ትርጉም የለውም። ስለሆነም ሁሉም ዜጋ ስለ አገሩ ሰላም ይበልጥ ማሰብና መጨነቅ ይገባዋል። የሰላም መፈጠር የቦንድ ሽያጭን እንደጨመረው ሁሉ የህዝቦችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ከፍ እንደሚያደርግ ግንዛቤ መያዝ ያስፈልጋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና መንግስታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስፋ ሰጪ ለውጦችን እያስመዘገቡ መሆናቸው የውጪው ዓለምና ባለሃብቶቻቸው ሳይቀሩ እየመሰከሩለት ይገኛሉ።

እነዚህ የልማት አጋሮች ለውጡን ከመመስከር ባለፈም በመተማመን መንፈስ የአገራችንን ቦንድ እየገዙ ነው። ይህም ኢትዮጵያ በውስጧና ከጎረቤቶቿ ጋር በተለይም ከኤርትራ ጋር ለፈጠረችው ሰላም የተሰጠ ምላሽ ነው።

የቦንድ ሽያጩ ጭማሪ ወትሮም በምስራቅ አፍሪካ ፈጣን ዕድገት ኢትዮጵያ ተደማሪ አቅም ነው። ጭማሪው እያደገ የመጣውን የህዝቧን ፍላጎት ለማሟላት አቅም እንድትፈጥር ከማድረግ ባሻገር በርካታ ባለሃብቶች አገራችን ውስጥ ሃብታቸውን እንዲያፈሱ ያደርጋል።

ለውጡ የፈጠረው ሰላም መተማመንን ፈጥሮ ወደፊትም አገራችን የባለሃበቶች መናኸሪያ እንድትሆን የሚያደርጋት ነው። ስለሆነም ለውጡ ተጨማሪ ድሎችን እንዲያስገነዝብ ሁሉም በያለበት ሰላሙን መጠበቅ ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy