ሚዲያው ጥንቃቄ ያሻዋል
ይልቃል ፍርዱ
በአለም አቀፍ ሆነ በሀገር ደረጃ ሚዲያው ለማልማትም ሆነ ለማጥፋት ግዙፍ ኃይልና አቅም አለው፡፡ ሚዲያው በጎም ሆነ የተሳሳቱ መልእክቶችን በሰከንድ ውስጥ ለብዙ ሚሊዮኖች የማድረስ አቅም አለው፡፡የተለያዩ የሕብረተሰብ፣ የፖለቲካ ቡድኖችና የግለሰቦች ፍላጎት አይሎና ጣሪያ ነክቶ በሚገኝበት ሁኔታ ውስጥ የግሉም ሆነ የፐብሊክ ሚዲያው በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ መስራት ይጠበቅበታል፡፡
ሀሳብን በነፃነት መግለጽን ጨምሮ የሚዲያ ነጻነት በሕግ የተፈቀደ መብት ነው፡፡ ቢሆንም በስራ ላይ ሲውል ነጻነቱ ስላለ ብቻ በተፈለገ መንገድ የሚኬድበት አይደለም፡፡የሚዲያ ዘገባዎቹ ትክክለኛና በቂ መረጃ ያላቸው ቢሆንም በተለይ ሕዝብን ሊያነሳሱ፣ ሊያስቆጡ፣ አንዱን ሕዝብ ከሌላው ጋር ሊያጋጩ፣ በጅምላ ጥላቻን ሊያስፋፉ የሚችሉ ዘገባዎች በሕጉም መሰረት የተከለከሉ ናቸው፡፡ ጥንቃቄንም ይጠይቃል፡፡
እንደነዚህ አይነት ዘገባዎች፣ ቃለመጠይቆች፣ በሚሊዮኖች መንፈስ ውስጥ የሚያሳድሩት የተነካንና የተደፈርን ቁጭትና ስሜት በቀልን አርግዘው ያልታሰበና ያልተጠበቀ ሀገራዊ አደጋን ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ ወንጀለኞቹን ነጥሎ በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ሲቻል ጉዳዩ በተለይ ከማንነት፣ ከብሔረሰብ ጋር የተገናኘ ሲሆን ልዩ ትኩረት ይሻል፡፡ በሚዲያው የሚከታተለው ሕዝብ በቁጭትና በተነካሁ ስሜት ሌላ ያልተጠበቀ ሁኔታ ውስጥ ሊገባ፣ ጥፋትና እልቂትም ሊያደርስ ይችላል፡፡ይህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተከተሉት ካለው የይቅርታ፣ የምሕረትና የፍቅር መርህ ጋ,ር በእጅጉ የሚጣረስ ነው፡፡ሚዲያውም ሆይ ሆይ ከሚለው ጋር አብሮ የሚጨፍር መሆን የለበትም፡፡ሰከን ብሎ ማሰብን የሚጠይቅ ይሆናል፡፡
ይህ አይነቱ በሚዲያ ነጻነት ስም የሚሰራ ስራ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሀገራዊ ቀውስና አደጋን ያስከትላል፡፡ በመሆም በሀገሪቱ ያሉ የግሉም ሆነ የፐብሊክ፣ የሕትመቱም ሆነ የኤሌክትሮኒክሱ ሚዲያ እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉበት ይገባል፡፡የሚዲያ ነጻነት ማለት ሊያስከትል የሚችለውን ሙያዊ ኃላፊነትም መሸከምን ይጠይቃል፡፡
ዋነኛ የሀገሪቱ የዜና ምንጮች የሆኑት ሜን ስትሪም ሚዲያዎች ሆኑ በግሉ ዘርፍ ያሉት ሚዲያዎች ሙያው ከሚጠይቀው ኃላፊነት አንጻር በተለይ አሁን ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ የገዘፉ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶችና መተነኳኮሶችም አንጻር ኢትዮጵያዊ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምንና መቻቻልን የይቅርታ መንፈስን በሚያጎለብት መልኩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት ተገቢ ነው፡፡
ሚዲያው ሀገሪቱን በተለያየ መልኩ ከሚፈታተኗት ችግሮች ሊታደጋት የሚችለው ሁሉም የሰላሙን አቅጣጫ በዋናነት በመከተል ሲያበረታታና ሲደግፍ ብቻ ነው፡፡የሰላም፣ የመቻቻል፣ የእርቅ፣ የይቅርታ መንገዱን፣ የመደመደርን ምንነትና እውነተኛ ሀገራዊ መልእክቱን በአግባቡ ማድረስ ሲችል ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት አሳሳቢ ሁኖ ተደቅኖብን ከነበረው የመከፋፈልና የመበታተን አደጋና ስጋት ተላቀናል፡፡ ከነበረው የጎሳና የዘር ጥላቻና መናቆር ስጋት ዛሬ ላይ የወጣን ቢሆንም አሁንም ጥንቃቄ የሚሹ ሁኔታዎች አሉ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አመራር ወደ ሰላሙ፣ ፍቅሩና መደመሩ መስመር መግባት ያለባቸው ሁሉ እየገቡ ነው፡፡በዚያው ልክ ብዙ ይቀረናል፡፡ጅምሩ የሚበረታታ ቢሆንም ገና ብዙ መሰራት ያለባቸው ያልተሰሩ የቤት ስራዎች አሉ፡፡ሚዲያው የበለጠ ሰላም እንዲሰፍን የጸረ ሰላም ኃይሎችን ሴራ በማጋለጥና በማምከን ረገድ ግዙፍ ሚና መጫወት ይጠበቅበታል፡፡
ቀድሞ ሳስቶ የነበረው የአንድነት መንፈስ ዛሬ በከፍተኛ ደረጃ ቦታው ላይ ተመልሷል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ያልተዋጠላቸው ጥቂት ኃይሎች የሕዝቡን ወሳኝና ብርቱ የአንድነት መንፈስ ለመናድና ለመሸርሸር እየታተሩ በተለያየ ቦታዎች ላይ በገንዘብ የተደገፈ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲነሳ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ሚዲያው ይሄንን ማጋለጥ አለበት፡፡
በሀዋሳ በጉጂ በኦሮምያ አንዳንድ አካባቢዎች በሶማሌ በንጹሀን ዜጎች ላይ የሞት አደጋ እየደረሱ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ሲሰሩ አስተውለናል፡፡እርስ በእርስ ሕዝቡን በመከፋፈል ለማጋጨት እንዲጠፋፋ ለማድረግ ሴራ ከመሸረብም አልፈው በተግባር ተከስቶ አይተናል፡፡በዚህ እኩይ ሴራ በርካታ ዜጎች ከቤትና ኑሮአቸው የመፈናቀል፣ የአካል ጉዳት፣ የሞት ሰለባ ሆነዋል፡፡ሚዲያው ችግሩን ነቅሶ በማሳየት ሕብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲወስድ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
ይሄን በስፋት የሚያራግቡ ማህበራዊ ሚዲያዎች ይበልጥ አደጋው እንዲስፋፋና እንዲቀጥል ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ከማሰራጨት አልፈው አንዱን በአንዱ ላይ የማዝመት ስራም በስፋት ይሰራሉ፡፡ ይህን እኩይ ድርጊት ሁሉም ዜጋ ሊዋጋው የሚገባ ሲሆን ሚዲያው ነቅሶ በማውጣት ሊያጋልጠው ይገባል፡፡
መንግስት ፍጹም ሀገራዊ ሰላም እንዲሰፍን በመስራት ላይ የሚገኝ ሲሆን ይሀን ጥረት በተናጠልም በጋራም ማገዝ ተገቢ ነው፡፡የተረጋጋ ሰላም እንዲፈጠር እየተሰራ ባለበት አብዛኛው ሕዝብ በለውጡ ሂደት ደስተኛ በሆነበት፣ ድጋፉን አጠናክሮ ለመንግስት እያሳየና ከመንግስትም ጎን በቆመበት በዚህ ልዩ ታሪካዊ ወቅት እንደነዚህ አይነት አዋኪ ድርጊቶችን ማስቆም የመንግስትና የሕዝብ የጋራ ኃላፊነት ይሆናል፡፡ሚዲያው ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡
በተለይም ሜን ስትሪም ሚዲያው በብዙ መልኩ ከሚያቀርባቸው ዘገባዎች ከግለሰቦችና ከቡድኖች ፍላጎት ሊጠነቀቅ ይገባል፡፡በሕብረተሰባችን ውስጥ የሚዲያው ምንነትና ባሕሉ በውል ያልሰረጸ ስለሆነ በሚዲያና በሶሻል ሚዲያው የሚተላለፉትን መልእክቶችና ከግለሰቦችም ጭምር የሚሰጡትን አስተያቶች ሁሉ እውነት አድርጎ የመውሰድ የቆየ ባህል አለ፡፡በጥቅሉ ባልተጣሩና ግርድፍ ወሬ ሆነው ገና መጣራት የሚገባቸውን በመለየት ጥንቃቄ ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡
ሰሞኑን በደብረማርቆስ የተከሰተው መኪናና ሆቴል የማቃጠል አስነዋሪ ወንጀል መነሻው ሶሻል ሚዲያ ነው፡፡እከሌ በዚህ ቦታ ታይቷል፤አሳዳችሁ በሉት፤ ግደሉት፤ አስወግዱት በሚል በከፋ የጥላቻና የበቀል ስሜት ተውጠው የሰው ሕይወት ለማጥፋት ንብረት ለማውደም ሆን ብለው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖችን በተጨባጭ ማየት ተችሏል፡፡ሕግና ስርአት ባለበት ሀገር እንዲህ አይነት የበቀልና የነፍሰ ገዳይነት ስራ ለመስራት ሲሞከር ማየት በእጅጉ ሊወገዝ ይገባል፡፡ የት ነው ያለነው ምንስ እየተደረገ ነው እስከማለት ያደርሳል፡፡
እንዲህ አይነቱ ድርጊት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሚያራምዱት የሰላምና የእርቅ መርህ ውጪ ነው፡፡ የአለፈውን መጥፎ ድርጊት፣ የመጠፋፋት አስከፊ ታሪክ ትትንና እረስተን ሁላችንምይቅር ተባብለን በአንድነት መኖር ላቀ ዋጋ አለው፡፡ በአዲስ መንፈስ ተከባብርን በይቅርታ በፍቅር መንፈስ እንደመር፤ አጥፊ ከነበረው የፖለቲካ ባሕላችን እንውጣ፤ አዲስ ቀን አዲስ ታሪክ እንጀምር፤ ሲጠቃለል ከበቀልና ከጥላቻ ፖለቲካ መውጣትይኖርብናል፡፡ ዛሬም በቀል አርግዘው ቂም በቀላቸውን ለመወጣት ጥርሳቸውን ነክሰው አምርረው ለውጡን የሚጠሉ መኖራቸውን ሚዲያው በተገቢው ተከታትሎ ሊዘግብበት ይገባል፡፡ ታላቅ ጥፋት ለማድረስ እየደገሱ የሚገኙ ስብስቦችን በአይናችን እያየን ነው፡፡ ሚዲያው ይሄን የማጋለጥ ስራ ካልሰራ ነገ ተመልሰን አዙሪት ውስጥ እንዳንገባ ያሰጋል፡፡
በአጭሩ የተጀመረውን ለውጥ ሆን ተብሎ ለማደናቀፍ የሚሰራ ሴራ በገሀድ እየታየ ነው፡፡ በስሜታዊነትና በጥላቻ ወጣቱን እያነሳሱ ለጥፋት ማዝመት ካለህበት ውጣ በለው ግድለው አቃጥለው ማለት ሕግና ስርአት እንዲሁም መንግስት ባለበት ሀገር በፍጹም የማይታሰብ ነው፡፡አይሞከርምም፡፡የጀማና የመንጋ ፍርድ የሚሰጥበት ዘመን ላይ አይደለንም፡፡የሕግና ስርአት መከበር፣ ተጨባጭ ማስረጃና ምክንያታዊነት ነው ተገቢው መንገድ፡፡ሚዲያው በትኩረት ሊሰራበት ይገባል፡፡
ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች በሕገ-መንግስቱ በግልጽ ሰፍሮ የሚገኝ የትኛውም ዜጋ በፈለገው የሀገሪቱ ክፍል የመዘዋወር የመንቀሳቀስ የመስራት የመኖር ለአጭርም ሆነ ለረዥም ግዜ የመቆየት መብት ያለው በመሆኑ ይሄንን በቡድንም፣ በግለሰብም፣ በአድማም ሆነ በመንጋ ተቃውሞ መግፈፍ አይቻልም፡፡ይህ በግልጽ ሕገ-መንግስቱን መጣስ ነው፡፡ ሕግን በመጣስ አመጽና ሁከት የማስነሳት መብትም የላቸውም፡፡ሚዲያው በቸልታ ሊያልፈው አይገባም፡፡
ይህ አይነቱ ድርጊት ሕግን በመጣስ በአደባባይ የማወኩ ጉዳይ የሚያሳየው መንግስት የለም፤ ሕግና ስርአት የለም፤ ስርአተ አልበኝነት ሰፍኗል የሚል ነልዕክትን ያነገበ ነው፡፡
የተገኘውን ሰላምና ነጻነት በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ ሰላምን ለማስከበር በቦታው ለመመለስ ሕገ-ወጦችን ስርአት ለማስያዝ መንግስት በማያከራክር መልኩ ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳል፡፡ ተመልሶ ደግሞ ዲሞክራሲያዊ መብታችን ተጣሰ የሚል ጩኽት ሊመጣ ነው፡፡ሕግና ስርአትን የጣሰ፣ ያላከበረ፣ ልቅ ዲሞክራሲ በየትም አለም የለም፡፡አይኖርምም፡፡ ለውጡን መሸከም የሚያስችል አመለካከት መገንባት ግድ ይላል፡፡
ዲሞክራሲና ዲሞክራሲያዊ መብት ማለት ሕገ-ወጥነት አይደለም፡፡ይልቁንም መብትና ግዴታውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ለመብቱ መከበር በሕጉና በስርአቱ የሚቆም፣ከስሜታዊነት ይልቅ በምክንያታዊነት የሚያምን፣ የሀገሪቱን ሕግና ስርአት አክብሮ የሚቆምና የሕግ ጥሰትን የሚከላከል ዜጋ ነው ዲሞክራሲን የሚፈጥረው፡፡ ከዚህ ውጭ የሚሆን ሁሉ ስርአተ አልበኝነትን ለማስፈን የሚደረግ ሩጫ ስለሆነ መንግስት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣል፡፡ከሕግና ከስርአት ውጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ወደስርአተ አልበኛነት የሚያመሩ ስለሆነ መታገስ አይቻልም፡፡ ሚዲያው ይሄንኑ የማጋለጥና የማሳወቅ ስራዎች ይጠብቁታል፡፡
ይሄንን እውነት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሀዋሳ ላይ ገልጸውታል፡፡በገንዘብ እየተገዙ ሁከትና ግጭት የሚፈጥሩ፣ ለዜጎች ሞት ምክንያት ለሆኑ ሰላም አደፍራሽ ክፍሎች የመጨረሻ ያሉትን መልእክት አስተላለፈዋል፡፡እኛም ሰው ነን ከዚህ በላይ መታገስ አይቻልም የሚል፡፡ሁሉም ዜጋ ያገኘውን ሰላምና ነጻነት አጣጥሞ ለአካባቢው ለሀገሩም ሰላምና መረጋጋት መቆም ይገባዋል፡፡ ሚዲያው በተለየ ትኩረት ሊሰራበት ይገባል፡፡