Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

…ምን ዓይነት ይሁኑ?

0 342

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

…ምን ዓይነት ይሁኑ?

                                                      ይሁን ታፈረ

የአገራችን መደበኛ ሚዲያዎች የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ማተኮር የሚኖርባቸው የህዝብን ጥቅም በሚያስቀድሙ፣ ሰላምን በሚያረጋግጡና ህዝቦችን በሚያቀራርቡ ጉዳዩች ላይ መሆን ይኖርበታል። ይሁን እንጂ አንዳንድ መደበኛ ሚዲያዎች የጥቂት ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ የለውጥ ፍላጎትን የሚያደናቅፉ ሃሳቦችን ሲያራምዱ እየተስተዋሉ ነው። በተለይ አንዳንድ መደበኛ ሚዲያዎች ከማህበራዊ ሚዲያው በባሰ መልኩ የህዝቦችን አብሮነት የሚሸረሽሩና ለአገራችን አንድነት እንቅፋት የሚሆኑ ዘገባዎችን ሲያስተናግዱ እየተመለከትን ነው።

በእኔ አስተሳሰብ እንዲህ ዓይነት ዘገባዎች የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት የሚጻረሩ ስለሆኑ መታረም የሚገባቸው ይመስለኛል። አሁን በምንገኝበት ወቅታዊ ሁኔታም ይሁን በሌላ ጊዜ የህዝቡን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ሰላማዊ ፍላጎት የሚሸረሽሩ ዘገባዎች ከሙያው አኳያም ቢሆን ተገቢ አይደሉም።

መገናኛ ብዙሃን የህብረተሰቡን መሰረታዊ ፍላጎት ተመርኩዞ ሚዛናዊና ትክክለኛ ዘገባዎችን መስራት ይጠበቅባቸዋል። በህዝብ ሃብት የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙዙሃን ጥብቅናቸው መሆን ያለበት ለህዝቡ ነው። መጠበቅ ያለባቸው የህዝቡን ፍላጎት ነው። የህዝቡን ፍላጎት ተጻርረው መቆም አይችሉም።

መገናኛ ብዙሃን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስኬታማነት የህዝብን ተሳትፎ የሚያጎለብት አጀንዳ በመንደፍ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት አለባቸው። እንዲሁም የመንግስት አሰራር ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ ሙስናንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማሳወቅ ከፍ ሲልም በማጋለጥ አገራዊ ተግባራቸውን ያረጋገግጣሉ። ሆኖም ዘገባዎቻቸው ከህዝብ ፍላጎት ጋር የሚያቃርኑና ሃላፊነት የጎደላቸው ሊሆኑ አይገባም።

ሲሆን…ሲሆን መገናኛ ብዙሃን የህግ የበላይነት ለሁሉም ዜጎች የተሰጠና ምንም ዓይነት ልዩነት የማይደረግበት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ መሆኑንም ማሳወቅና ማስተማር ይገባቸዋል። ይህም አንዳንድ ወገኖች ውስጥ ያለን የተዛባ አመለካከት ለመቅረፍ ያግዛል።

መገናኛ ብዙሃን ለዘገባቸው የሚሆን የዳበረና ተዓማኒ መረጃና ማስረጃ ማግኘት አለባቸው። ለዚህም የስማ በለው አዘጋገብ ስልትን መከተል አይኖርባቸውም። ዋነኛ የዴሞክራሲ ማስፈኛ ተቋማት የሚባሉትን እንደ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የመሳሰሉ የመረጃ ምንጮችን በተገቢው መንገድ ሊጠቀሙባቸው ያስፈልጋል።

በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 ላይ በተቀመጡት መሰረታዊ ድንጋጌዎች መሰረት መገናኛ ብዙሃን ተግባራቸውን በሚገባ መወጣት ይኖርባቸዋል። ህዝቦች በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡትንና እያከናወኗቸው የሚገኙትን የለውጥ ሂደት በማንፀባረቅ የበኩላቸውን ድርሻ መጫወት አለባቸው።

መገናኛ ብዙሃን የህዝብ ፍላጎት ከድህነት መለወጥ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ለውጡ አንድነትና ተደምሮ ወደ ተሻለ ደረጃ መድረስ እንደሆነ ማወቅ ይገባቸዋል። ይህም ህዝቦች ካሉበት የድህነት አዙሪት ቀለበት ነፃ እንዲሆኑና በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ እገዛ የሚያደርግ ነው።

ህዝብን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ለማላቀቅ፣ ፈጣን ሀገራዊ ለውጥን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ትክክለኛ የልማት ሃሳቦችን ህብረተሰቡ እንዲገነዘባቸው፣ እንዲያምንባቸውና በአተገባበራቸውም በንቃት እንዲሳተፍ የሚያደርግ እንዲሁም የዴሞክራሲ የለውጥ እሴትንም ማጉላት አለባቸው።

ለዚህም ራሳቸውን ለህዝብ ከማይጠቅምና ለውጥን ከሚቀለብስ የጥቂቶች እሳቤ ማራቅ አለባቸው። ይልቁንም በየጊዜው በሚካሄዱ የልማት ተግባራት ውስጥ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ነቅሰው በማውጣት የህዝቡ ዓይንና ጆሮ ሆነው ሊሰሩ ይገባል። የህዝቡን ፍላጎት ለማገዝም ለምሳሌ አንድ የልማት ፕሮጀክት በዕቅድ ደረጃ እንደሚከናወን የገለፀ መገናኛ ብዙሃን፣ ምርቃቱ ላይ ብቻ ለመገኘት ቀጠሮ መያዝ አይኖርበትም። ፕሮጀክቱ በየጊዜው ያስመዘገበውን ዕመርታ፣ በሂደቱ ውስጥ ያጋጠሙት ተግዳሮቶችና ብልሹ አሰራሮች ካሉም እንዲሁም እየተከታተለ መስራት አለበት።

መገናኛ ብዙሃን ልዩነቶች የሚስተናገዱባቸው የውይይት መድረክም መሆን አለባቸው። የሚተላለፉት ልዩነቶች ግን የህዝቡን ሰላም የሚያውኩ፣ አንድነትን የሚያናጉና የተጀመረውን ለውጥ የሚያፋልሱ መሆን ያለባቸው አይመስለኝም። ከዚህ ይልቅ ለለውጡ ተደማሪ የሚሆኑና አገራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ ስራዎች መሆን አለባቸው።

በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ሁሉም ዜጋ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ሊኖረው ስለማይችል የሁሉም ድምፅ መሆን ከመደበኛው መገናኛ ብዙሃን የሚጠበቅ ነው። ስለሆነም መገናኛ ብዙሃኑ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አመለካከቶች ሰላምን በመያውክና የህዝቦችን ፍላጎት በማያጨልም መልኩ ሚዛናዊ በማድረግ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

መገናኛ ብዙሃን ከስሜታዊነት፣ ከአሉባልተኝነትና ከጭፍን ጥላቻ ርቀው ብሎም እንደማንኛውም አገር የአገራቸውን ሀዝቦች ፍላጎቶች ተከትለው መስራት አለባቸው። በፍፁም ጥላቻ ላይ ተመርኩዘው ሁልጊዜ ፅንፈኛ አስተሳሰቦችን ብቻ እያራመዱ ህዝብን ወዳልሆነ አቅጣጫ መምራት አይኖርባቸውም።

መገናኛ ብዙሃኑ የአንዳንድ ግለሰቦችን ፍላጎት በማንፀባረቅ ላይ መጠመድ አይኖርባቸውም። በመሆኑም ሁሌም ‘ዘገባችን ምን ዓይነት ይሁን?’ ብለው ራሳቸውን በመጠየቅ ለአብዛኛው ህብረተሰብ የሚጠቅምና የለውጥን እሴት በሚያጎሉ ጉዳዩች ዙሪያ ማተኮር ያለባቸው ይመስለኛል።

ዛሬ በአገራችን ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተግባራቸውን አቅም በፈቀደ መጠን እየተወጡ ቢሆንም፤ አንዳንድ መደበኛ (mainstram) መገናኛ ብዙሃን እንደ ማህበራዊ ሚዲያ በመቁጠር ተገቢ ያልሆነ ምልከታን እየፈጠሩ ነው።

በማህበራዊ ሚዲያ የሚሳተፉት የዜጋ ጋዜጠኞች ናቸው። ያገኙትን ሃሳብ ሁሉ በገጻቸው ላይ ያቀርባሉ። መደበኛ ሚዲያዎች ተጠሪነትና ሃላፊነት ያለባቸው ስለሆኑ እንደ እነርሱ ያገኙትን ነገር ሁሉ በጅምላ ሊያቀርቡ አይችሉም። ባለሙያዎቻቸውም የሰለጠኑ ጋዜጠኞች ናቸው። የራሳቻው የስነ ምግባር መመሪያም አላቸው።

ስለሆነም ለህዝብ ጠቃሚ በሆነ መንገድ ተግባራቸውን መወጣት አለባቸው። ከእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታም በምርመራ ጋዜጠኝነት ዘውግ መስራት ይኖርባቸዋል። አራተኛው መንግስት መሆን አለባቸው።

መንግስትና ህዝብ ከፍተኛ የልማት ስራ ሲያከናውኑ ሂደቱ በምርመራ ጋዜጠኝነት ዘገባ መደገፍ አለበት። የህዝብን ጥቅምና የለውጥ ፈላጎት ባማከለ መልኩ ተግባራቸውን በመወጣት የመደመርና የአንድነት መስመርን ማስተጋባት ይኖርባቸዋል። ይህን ለማድረግም ሁሌም ‘ዘገባችን ምን ዓይነት ይሁኑ?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy