Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስህተትን በስህተት…ለምን?

0 344

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስህተትን በስህተት…ለምን?

                                                       ዋሪ አባፊጣ

የዚህ ፅሑፍ አነሳሽ ምክንያት ከመሰንበቻው የተፈጠረ አንድ ክስተት ነው፤ በምስራቅ ጎጃም ዋና ከተማ በሆነችው ደብረ ማርቆስ ከተማ ውስጥ የተከናወነ። በእውነቱ ክስተቱ እጅግ አሳዛኝና ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው ነው። መቼምና በየትኛውም አካባቢ ቢሆን እንኳንስ ሊደገም ቀርቶ መታሰብ የሌለበት አስነዋሪ ድርጊትም ይመስለኛል። ነገሩም እንዲህ ነበር።…

በዚያች ከተማ ውስጥ ወጣቶች ‘አንድን የቀድሞ አመራር እንፈልጋለን’ በማለት ግለሰቡ ይገኙበታል ብለው ወደ ጠረጠሩት አንድ ሆቴል ያመራሉ። ሆኖም ጉዳዩ ወትሮም ግጭትን ለመፍጠር ሲባል በሁከት ፈጣሪ ሃይሎች የተከናወነ ድራማ በመሆኑ፤ በሆቴሉ ውስጥ ‘ይፈለጋሉ’ የተባሉትን ግለሰብ ሊያገኟቸው አልቻሉም። ወጣቶቹ ግን ‘ግለሰቡን አምጡ’ በማለት የአንድ ባለሃብት ንብረት የሆነውን ሆቴል ድንጋይ በመወርወር ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል። እንዲሁም በቀስቀሰሽ ሃይሎች አማካኝነት ‘የተፈላጊው ግለሰቡ ናት’ ተብላ የተገመተች፣ ነገር ግን ንብረትነቱ የአንድ ኮንስትራክሽን መስሪያ ቤት የሆነች መኪናም እንድትቃጠል አድርገዋል።

ይህ የግለሰብን ንብረቶችን የማውደም ርምጃ በምንም ዓይነት መስፈርት ተቀባይነት ያለው አይደለም። ‘ለምን?’ ከተባለ ሁለት ጉዳዩችን በምክንያትነት ማንሳት ይቻላል። አንደኛው፤ ተግባሩ ህግና ስርዓትን ተከትሎ ያልተከናወነ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ፤ እንዲህ ዓይነቱ ስርዓት አልበኝነት የተጀመረውን የፍቅር፣ የአንድነትና የፍቅር የለውጥ ጉዞ ከማደናቀፍ በስተቀር አንዳችም ፋይዳ የሌለው መሆኑ ነው።

ታዲያ እነዚህን ምክንያቶች ዘርዘር አድርጎ መመልከት ችግሩ የተፈጠረበትን ከተማ ጨምሮ በየትኛውም አካባቢ ለሚገኙ ወጣቶች ትምህርት የሚሰጥ ይመስለኛል። ‘በአንተ ላይ እንዲፈፀም የማትፈልገውን ነገር በሌላው ላይ አታድርግ’ እንደሚባለው፤ ስህተትን በስህተት መፈፀም ሌላው ቀርቶ ከራስ ፍላጎት ጋር መቃረን መሆኑንም ያስረዳልኛል ብዬም አስባለሁ።

ርግጥ ትናንት የህግ የበላይነት በጥቂቶች ተጣሰ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተገፈፉ…ወዘተ. በማለት ለመብታችን ተመሟግተን ለውጡን ያመጣነው ወጣቶች (ቄሮዎች) ዛሬ ህግና ስርዓትን ተላልፈን የታለልንበትን ጉዳይ መልሰን ልንቃረን አይገባም። በአዲሷ ኢትዮጵያ ውስጥ ህግና የበላይነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገቡ ጉዳዩች አይደሉም።

በመሆኑም የቀድሞ አመራርም ይሁን ማንኛውም ግለሰብ ወንጀል ሰርቷል ቢባል እንኳን መጠየቅ ያለበት ህግና ስርዓትን በተከተለ አግባብ እንጂ፣ የህግ የበላይነትን በሚጥስና ስርዓት አልበኝነትን በሚያሰፍን መልኩ መሆን የለበትም። ህግና ስርዓት ባለበት ሀገር ውስጥ የህግ በላይነት ሊከበር እንጂ ሊጣስ አይገባም። እናም ወጣቶች ለህግ የበላይነት ልዕልና በመቆም በአርአያነት ህገ ወጥነትን መታገል ይኖርባቸዋል።

ወጣቶች የለውጡ ተደማሪዎች እስከሆኑና ‘አዲሲቷ ኢትዮጵያ እኔ ነኝ’ እስካሉ ድረስ፤ የመደመራቸው ፋይዳ የሚገለፀው የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ህግና ስርዓት በመፈፀምና በማሰፈፀም ይመስለኛል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በህግ ካለተደነገገ በስተቀር፣ የህግ የበላይነትን በመፃረር ለራስ ፍላጎት ማዋል ፈፅሞ አይቻልም። ሃሳቡ በራሱ ነውር ነው። በዶክተር አብይ የሚመራው አዲሱ አመራር ይህን እውን ለማድረግ እየሰራ ነው።

እናም ሀገራችን ውስጥ የቀድሞም ይሁን የአሁን አመራር አሊያም ማንኛውም ዜጋ እንቅስቃሴዎች የሚመሩት በህግና በስርዓት ብቻ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ይገባል። ይህ ካልሆነ፤ ማንኛውም ዜጋ የመንቀሳቀሰና የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። ዜጎች የመኖር ዋስትናቸውን ባላረጋገጡባት ሀገር ውስጥ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ይጠፋል። እንደ ሰው ለመንቀሳቀስ የማይቻልበት ደረጃም ይደረሳል። መብቶች በህግ ጥበቃ ሳይሆን ጉልበት አለኝ በሚሉ ሃይሎች ስር ይወድቃሉ።

እንዲህ ዓይነቱ ህግና ስርዓትን ባለመከተል የሚፈጠሩ የህግ የበላይነትን የመጣስ ተግባሮች፤ ሁከትን በማንገስ ዜጎች በንትርክ ተሞልተው ፊታቸውን ወደ ልማትና ዕድገት እንዳያዞሩ የሚያደርጉ ናቸው። ሰላምም ያሳጣሉ። የዚህ አበሳ ዋነኛዎቹ ገፈት ቀማሾችም ዜጎች ይሆናሉ። ሀገርም እንደ ሀገር እንዳትቀጥል ስርዓት አልበኝነት ፊቷ ላይ ተደቅኖ ያንገዳግዳታል፤ አሊያም ይበታትናታል።

ርግጥ ወጣቶች ይህ እንዲሆን አይፈልጉም። እናም የህግ የበላይነትን አለማክበር መዘዝ መልሶ ቀስቱ የሚቀለበሰው በዜጎች ላይ መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል። በደብረ ማርቆስ ከተማ የተፈፀመው አስነዋሪ ድርጊት ግን ይህን ካለመረዳት የመነጨ ይመስለኛል። እዚህ ሀገር ውስጥ ህግና ስርዓት እስካለ ድረስ ወንጀል ፈፅሟል የሚባል ግለሰብ ካለ የሚዳኘው በህግ አግባብ ነው። የህግ አግባብን በመጣስ ግለሰቦችን በመፈለግ ምክንያት ራሳቸውን፣ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ለመጥቀም በየአካባቢው የሚሰማሩ ባለሃብቶች ንብረት ሊወድም አይገባም።

የባለሃብቶች ንብረት በየጊዜው የሚወድም ከሆነ በዚያ ከተማ መዋዕለ ነዋያቸውን አፍስሰው ኢንቨስትመንትን ለማካሄድ የሚሹ የሀገር ውስጥም ይሁኑ የውጭ ባለሃብቶች ለንብረታቸው ዋስትና ስለማይኖራቸው ፍላጎት ሊኖራቸው አይችልም። ይህም በእነዚህ ባለሃብቶች ለወጣቶች ሊፈጠር የሚችል የስራ ዕድል እንዳይፈጠር ያደርጋል። እናም በከተሞች፣ በዞኖች፣ በክልሎችና በሀገር ውስጥ ግጭቶችንና ሁከቶች ማራቅ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የለውጡ ግንባር ቀደም ተደማሪ የሆኑት ወጣቶች ደግመው ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል። የደብረ ማርቆሱ ድርጊት አስነዋሪና ተቀባይነት የሌለው የሚሆንበት አንደኛው ምክንያት ከእነዚህ እውነታዎች አኳያ ነው።  

የድርጊቱ ቅቡል ያለመሆን ሁለተኛው ምክንያት፤ የህግ የበላይነትን ከመፃረር ባለፈም ወጣቶች በፊት ለፊት መሪነት ላመጡት ለውጥ ጠብ የሚል ነገር የሌለው መሆኑም ነው። እንዲያውም ቀደም ሲል እንዳልኩት ድርጊቱ አሁን የመጣውን የፍቅርና የይቅርታ ዘመን አስተሳሰብ የሚቃረን ነው። አሁን እየተካሄደ ያለው ለውጥ ማንኛውንም ለመደመር ፍላጎት ያለውን ዜጋ የሚያካትት እንጂ፤ ግለሰቦችንና ቡድኖችን የሚያገል አይደለም። እናም ወጣቶች ማንኛውም ዜጋ ይሁን ቡድን የመደመሩ አካል እንዲሆን የማድረግ ተግባሮችን ብቻ ነው መከወን ያለባቸው።    

እንደሚታወቀው ለለውጡ መፈጠር ምክንያት የሆነው፤ ትናንት ሲፈጠር የነበረው የዜጎች መገፋትና የፈጠረው መጥፎ ጠባሳ ነው። እናም ትናንት በዜጎች ላይ የተፈጠሩትን መጥፎ ጠባሳዎች ለመሻር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ሃይል ከህዝቡ ጋር በመሆን እየሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ ያለፈውን ስህተት በስህተት ልንደግመው አይገባም።

በዚህ በመደመር ዘመን እንደ ትናንቱ የምንገፋው ዜጋም ይሁን ቡድን ፈፅሞ ሊኖር አይገባም። የወጣቶች ተግባር ሊሆን የሚገባው፤ ያልተደመረ አካል ካለ፤ በፍቅር፣ በይቅርታና በምህረት እያወያዩ ለመደመር መጣር ይመስለኛል። ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ራስን ለግጭት ከሚገፋፉ አካላት በማራቅ በለውጡ ስር ሆኖ ልማትንና ዕድገትን ማስቀጠል ነው። የትም ቦታ ቢሆን ግጭትንና ሁከትን ለመፍጠር መሞከር እየተከናወነ ያለውን የለውጥ ሂደት ከማሳት በስተቀር ምንም ዓይነት እርባና የሌለው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

በጥቅሉ ከላይ የጠቀስኳቸውና የደብረ ማርቆሱ ስሀተትን በስህተት የመድገም ድርጊት ተቀባይነት እንደሌለው የሚያስረዱት ምክንያቶች በየትኛውም አካባቢ ለሚገኙ ወጣቶች ተገቢውን ትምህርት የሚያስጨብጡ ይመስለኛል። ይኸውም የህግ የበላይነትን አለማክበርና ከለውጡ ፍላጎት ውጭ አንድን ተግባር ማከናወን ችግሩ መልሶ የሚጎዳው ዜጎችንና ሀገርን መሆኑን ነው። ስህተትን በስህተት መድገም፤ በፍጥነት እየተጓዘ ባለው የለውጥ ሂደት ስር በራስ እጅ ታኮ የማስቀመጥ ያህል የሚቆጠር ነው። እናም ወጣቶች ከስሜታዊነት በተቻለ መጠን ራሳቸውን በማቀብና የገፋፊ አካላትን ፍላጎት በመረዳት፤ ለውጡን እየሄደበት ባለው ፍጥነት ማስቀጠል ቀዳሚ ድርሻቸው መሆኑን ሁሌም ማስታወስ ይገባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy