Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በከፍታ ላይ ከፍታ

0 276

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በከፍታ ላይ ከፍታ

                                                      ይሁን ታፈረ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አመድ በምስራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና ቀጠናው በኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲተሳሰር ለማድረግ በአጭር ጊዜ በርካታ ስራዎችን አከናውነዋል። በዚህም የአገራችንን የወደብ አገልግሎት ለማስፋትና የወደብ አማራጮችን ለማብዛት የተደረገው ጥረትና ስኬቶች፣ ከጅቡቲ ወደብ በተጨማሪ በሶማሊያ፣ በኬንያና በሱዳን የተከናወኑት ውይይቶች ስኬታማ ሆነዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው አገሮችን በመሰረተ ልማት የማስተሳሰር ስምምነቶች በጠቅላይ ሚኒስትሩ መደረጋቸውም ውጤታማ ክዋኔዎች ናቸው። “ሞት አልባ ጦርነት’’ የነበረው የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ወደ መቀራረብና መደጋገፍ እንዲሁም በፍቅር ወደ መደመር እንዲሸጋገር አድርገዋል።

በተጨማሪም የደቡብ ሱዳን መንግስትና የተቀናቃኙ ቡድን ድርድር ፈር መያዝ መጀመሩ፣ የአገራችን ኢኮኖሚ የገጠመውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እፎይታ እንዲያገኝ መደረጉ፣ እንዲሁም በታሪካችን እስካሁን ተደረጎ በማይታወቅ ሁኔታ አንድ ቢሊዮን ዶላር በቀጥታ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ በማድረግ አገሪቱን ከጭንቅ መታደግ ብሎም በአጭር ጊዜ ውስጥ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉ አገራችን በከፍታ ላይ ሌላ ከፍታ ጨምራ እንድትጓዝ ያደረጋት ነው።

ለእነዚህ ሁሉ ተግባሮች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ድርጅታቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። በተለይ ዶክተር አብይ መሪ ማለት በጭንቅ ወቅት አገርንና ህዝቧን በእፎይታ ጸዳል የሚያላብስ የመፍትሔ አካል አሳይተውናል። እንደ ዜጋ ምስጋናዬ የላቀ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያና ጅቡቲ በመሪዎቻቸው በኩል የደረሱት የመሰረተ ልማት የባለቤትነት ድርሻ ልውውጥ አገራችንን በጅቡቲ የወደብ ድርሻ ባለቤት ጅቡቲንም በኢትዮጵያ በተመረጡ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ ባለ ድርሻ እንድትሆን ያደርጋታል። ይህ የሰጥቶ መቀበል መርህ ሁለቱን አገራት ተጠቃሚ የያደርጋቸው ነው።

ሁለቱ አገራት በወደብ ልማት፣ በእርሻ ልማት፣ በመንገድ ልማትና ሃገራቱን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን መስማማታቸው የከፍታው ምንጭ ነው።

ኢትዮጰያ በጂቡቲ የወደብ ባለቤትነት ድርሻ ይኖራታል። ይህም ኢትዮጵያ በወደብ ክፍያ ውሳኔ ላይ ድምጽ እንዲኖራት የሚያስችል ወሳኝ ስምምነት ነው። በኢትዮጵያ በተመረጡ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ በተመሳሳይ መልኩ ባለድርሻ ያደርጋታል። ስለሆነም በዚህ ስምምነት የአገራችን ጥቅም እንዲጠበቅ ተደርጓል።

ከሱዳን ጋርም ፖርት ሱዳን ላይ ኢትዮጵያ ብቻ የምትጠቀምበት ወደብ በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር የተደረሰው ስምምነት አገራዊ ጥቅማችንን ያማከለ ነው። አዲስ አበባና ካርቱምን በባቡር መስመር ለማስተሳሰር፣ የንግድ የኢንቨስትመንት ልውውጡ እንዲጠናከር ለማድረግና በተለይም ካሏቸው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር አኳያ ያላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጥበቅ እየተሰራ ያለው ተግባር ተገቢ ነው።

በወደብ ልማት በኩል ልማቱንና በጋራ የማስተዳደሩ ስራው በፍጥነት ወደ ተግባር እንዲገባ አገራቱ መስማማታቸው በመካከላቸው የግንኙነቱ ጥንካሬ ማረጋገጫ ነው። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የሱዳን ወደብን ለሰሜንና ሰሜን ምእራብ አካባቢዎች ስትጠቀም መቆየቷ የሚታወቅ ቢሆንም፤ አሁን የተፈረመው ትብብር ተግባሩን ወደ ላቀ ከፍታ የሚያዘልቅ ነው። ይህ ከፍታም ይበልጥ ሊጨምር ይገባዋል።

የሁለቱ ወንድም አገራት ህዝቦች ትስስር እንዲጠናከር በጋራ ድንበር አካባቢ ነፃ የንግድ እንቀስቃሴ እንዲኖር ሁለቱ መሪዎች መስማማታቸውም የአገራቱን ኢኮኖሚ ይበልጥ በማሳለጥ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርሰው ነው። እነዚህ ተግባሮች የተፈፀሙት ዶክተር አብይ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ነው።

ኬንያና ሶማሊያ ከአገራችን ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲደረጅ ከአገራቱ ጋር በተለይ በወደብ አጠቃቀም ረገድ የተደረገው ስምምነት ተጠቃሽ ነው። ስምምነቱ አገራችን የኬንያን ላሙ ወደብ እንድታለማ እንዲሁም በሶማሊያ ያሉትን አራት ወደቦች በጋራ በማልማት ቀጠናውን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር እያደረገች ያለችውን ጥረት የሚያለብት ነው። ከፍታ ላይም የሚያወጣት ነው።

ዶክተር አብይ ከሀገር ውስጥ እስከ ጎረቤት ሀገራት እያስተላለፉት ያለው አፍሪካዊ የአንድነት መልዕክትም የኢትዮጵያን የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው። አገራችን ትናንትም ይሁን ዛሬ ለፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ያላትን የመሪነት ቦታ የሚያስጠብቅም ጭምር ነው።

እንዲሁም አገራችን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ እንድታጠናክር በአጭር ጊዜ ውስጥ  ያደረጓቸው እንቅስቃሴዎች፤ ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ተስፋ ሰጭ ናቸው። ይህ ተስፋም የቀጠናው አገራት በሰላም ውስጥ ሆነው ልማታቸውን በማጠናከር ተያይዘው እንዲያድጉ የሚያስችል ነው።

በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ውስጥ ደማቅ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካን ክፍለ አህጉር በኢኮኖሚ የማስተሳሰር ሃለፊነት ያለባት ናት። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በአራቱም ማዕዘናት ካሉ ጎረቤቶች እንዲሁም ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር እየፈጠሩ ያሉት የኢኮኖሚ ትስስር የዚህ አውነታ አመላካች መሆኑ ግልጽ ነው።

ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ገና ሶስት ወራትን ብቻ ያስቆጠሩ ቢሆንም በሀገር ውስጥና በውጭ ጉብኝታቸው ያደረጓቸው የአንድነት ንግግሮች የኢትዮጵያን የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ይበልጥ በማጠናከር የቀንዱ አገራት አውራ የሚያደርጋት ነው።

እንዲሁም በአጭር ጊዜ ውስጥ ያከናወኗቸው ስራዎች ስጋትን የሚያርቁ ተስፋን የሚሰንቁ ናቸው። የጦርነት ተምሳሌት በነበረው ምስራቅ አፍሪካ ውስጥ የስጋት ደመና ተገፍፎ፣ የተስፋ ብርሃን እንዲታይ ማደረግ እንደሚቻል ለቀጠናው አገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሳዩ መሪ ናቸው።

ከዚህ አኳያ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ቢቻልም ከቀጠናው አገራት ጋር በመሰረተ ልማት ለመተሳሰር የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ለመደረጉ ማሳያ ከጅቡቲ ጋር በመሰረተ ልማት ለመተሳሰር ኢትዮጵያ ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማውጣቷን መግለፅ በቂ ነው።

በተጨማሪም ኢትዮጵያና ኤርትራ በመካላቸውን ያለውን ልዩነት በውይይት አስወግደው የሁለቱን አገራት ዜጎች እኩል ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል አዲስ መንገድ መከፈቱ ከጸብ ሳይሆን ከፍቅር ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ያሳየ ተግባር ነው። እነዚህ ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ ተግባሮች አገራችን በከፍታ ላይ ከፍን እየጨመረች የጋራ ተጠቃሚነት እንዲኖር የምታደርጋቸውን ተግባሮች የሚያመላክቱ ናቸው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy