Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አሁንም በቂ ትኩረት

0 398

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አሁንም በቂ ትኩረት

                                             ወንድይራድ ሃብተየስ

አሁን የምንገኝበት የመኸር ወቅት ነው። በአሁኑ ወቅት በመኸር ምርት ከ370 በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው። በሁሉም ክልሎች በቂ ዝግጅት ተገርጎ ወደ ስራ እየተገባ ነው። ለዚህ ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ በቂ ዝግጅት ተደርጎ ስራው እየተጀመረ ነው።

የመኸር ወቅት የግብርናው ምርታማነት የሚለውጥ ነው። የአገራችን ኢኮኖሚ ትርጉም ባለው ደረጃ እንዲያድግ ህዝባችንን ከድህነት ለማውጣት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት መስጠት የግድ ይላል። በመሆኑም መንግሥት ግብርናውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ተገንዝቦ እየሰራ ነው።

በአገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ታዲያ ግብርና እምቅ ሃብት ነው። ይህ ሃብት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ነው። ድህነትንም የመቀነስ አቅም አለው። ገና ምንም ያልተነካ እምቅ በመሆኑም ውጤት ሊያመጣ ይችላል። አገሪቱን ለመለወጥ ወሳኙ ሃብትም ነው።

መንግሥት ለዘመናዊ ግብርና ያልተደፈረውን የሀገሪቱን አርሶ አደር የአስተራረስ ዘይቤ የመለወጥን አስፈላጊነት ተገንዝቦ በቀየሰው መስመር ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው። አርሶ አደሩ በድርቅ በቀላሉ መጠቃት ምክንያቱም ደግሞ የዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ አለመኖር እንደሆነ በመረጋገጡ የተለያዩ ምርትን ከፍ የሚያደርጉ ተግባራት እየተፈጸሙ ነው።

መንግስት እየተከተለ ባለው የግብርና ልማት ስትራቴጂ ትርፍ አምራች ዜጋዎችን መፍጠር ተችሏል። እነዚህ አባቢዎች በድርቅ የተጎዱት አካባቢዎችን ጭምር እየሸፈኑ ነው። ይህም የድርቅ አደጋ ተጋላጭነት ቢኖርም ችግሩን በራስ አቅም ለመቋቋም በማስቻል ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው። በመሆኑም ለመኸር ምርት በቂ ትኩረት መስጠት ይገባል።

የመኸር ምርት ውጤታማ እንዲሆን ጠንክሮ መስራት ይገባል። ስለሆነም የመኸር አብቃይ አካባቢዎች የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት በመኖሩ በአሁኑ ወቅት ጥሩ የምርት ሁኔታ በእርሻ ማሳ ላይ መኖሩን መረጃዎች ይገልጻሉ። አርሶ አደሩም በእሸትና በቡቃያ ደርጃ ያሉ ምርቶችን በአግባቡ የመጠበቅ፣ በየጊዜው ማሳውን የመፈተሽ ሰብሉ በአረም እንዳይጠቃ ክትትል ማድረግ ይገባዋል።

ለዚህም ተባዮችን በባህላዊ መንገድ መከላከል ከአቅም በላይ በሚሆንበት ወቅትም ፀረ- ተባይ ኬሚካሎችን በመርጨትና በመከላከል በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ማሳ ላይ የሚገኘውን ምርት ወደ ጎተራው እስኪገባ ድረስ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ርብርብ ማድረግ አለባቸው።

እንዲሁም የሰብል ምርቱን ለማሳደግ አዳዲስና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ለማስተዋወቅ ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። በተጨማሪም የአርሶ እደሩን ጉልበት የሚያግዙ የሚደግፉና ጉልበቱን ውጤታማ የሚያደርጉ መጠነኛና አነስተኛ የሜካናይዜሽን ስራዎች እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ በመገፋፋት ለከርሞ ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።

የመኸር ምርት የጥራት ችግር እንዳይኖረውና ብክነትን እንዳያጋጥመው መከላከል ያስፈልጋል። በቅድመ ምርት ወቅት መደረግ የሚገባቸው የማለስለስ፣ የማዳበሪያና ሌሎች ለምርት ጥራት ወሳኝ የሆኑ ጉዳዩችን መጠቀም ያስፈልጋል። በአጨዳ፣ በመሰብሰብ፣ በመውቃት፣ በማበራየት፣ በመጓጓዝና በማከማቸት የማምረት ሂደት ወቅት የምርት ጥራት በከፍተኛ እንዳይቀንስ አርሶ አደሩን ከስር ከስር ማስተማር ይገባል። ምርት በወቅቱ ባለመታረሙ ምክንያትም በአረም ተውጦ ተገቢው ውጤት እንዳይገኝ ስለሚያደርግ አርሶ አደሩን በዘመናዊ መንገድ ምን ማድረግ እንደሚኖርበት ማስረዳት ይገባል።

እንደሚታወቀው አመራረቱ ተገቢ ላልሆነ የጥራት ችግር ከተጋለጠ ከምርቱ አግባብ የሆነ ገቢን ማግኘት አይቻልም። በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ ለመኸር ምርት የሚዘጋጅበት ነው። እናም ምርቱ ለጥራት ማነስ እንዳይጋለጥ አስቀድሞ ሊቀርበቡለት የሚገቡ ግብዓቶችን ማስረዳት ይገባል። ማሳን ማለስለስና ማዳበሪያን መጠቀም ወደፊት ለሚያገኘው ምርት ጠቀሜታው ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ማስገንዘብ ያስፈልጋል።

የምርት ጥራት መጓደል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚጎዱ እንደሆኑና መንግሰትም የአርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል በሚያደርጋቸው ተግባራት ላይ መጥፎ አሻራ ስለሚያሳርፉ በቅድመ ምርት ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርበት ማስተማር ያስፈልጋል። እናም አርሶ አደሩ አሁን በሚገኝበት የማምረት ሂደት ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች ከወዲሁ እንዲፈታ እገዛ ማድረግ ይገባል።

አርሶ አደሩ በስተመጨረሻ ለሚያገኘው ምርት መሰረቱ በአሁኑ ወቅት የሚያከናውነው ተግባር ስለሆነ ለቅድመ ምርት ስራዎቹ መጠቀም የሚገባውን ግብዓቶች እንዲሁም የማሳ አያያዙን በተመለከተ ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል። ይህም አገሪቱ ከግበርናው ምርት ለማሳካት የምትፈልገውን ውጤት እንድታገኝ ያደርጋታል።

አርሶ አደሩ በዚህ ወቅት ከማዳበሪያ ባሻገር በከርሰ ምድርና በገጸ ምድር ያለውን የውሃ ሃብት መጠቀም ይኖርበታል። በውሃ ማሰባሰብና ማቆር፣ የጉድጓድ ውሃን በመጠቀም የወንዝ ውኃን ጠልፎ ጥቅም ላይ የማዋል ጥበቦችን ከዚህ በፊት ከነበረው በላቀ መጠን መከወን ይኖርበታል።

እንዲሁም ከዝናብ ጥገኝነት በተላቀቁ አመራረት መጠቀም አለበት። የመስኖ ልማት ስራን በሚገባ በመያዝ ተገቢውን የምርት መጠን ለመሰብሰብ ከወዲሁ ማሰብ አለበት። በዚህ ረገድ የሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞች ከአርሶ አደሩ ጎን በመቆም ለምርት ዕድገት ተገቢውን አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው።

የግብርናው ዘርፍ በአስተማማኝ ሁኔታ ገበያው ሳያሳስበው ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ላይ ብቻ አተኩሮ ለልማት ለውጥ ሽግግሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የዘርፉ ተዋናይ የሆነው አርሶ አደር የሚጫወተው ሚና የሰፋ ነው። ይህን ሚናውን በሚገባ ለመወጣት ጉልበቱን በመኸር ምርት ላይ ማፍሰስ ይኖርበታል።

የግብርናው ዘርፍ በዚህ ሁኔታ ካደገ የኢኮኖሚውን የመሪነት ሚና ይዞ ይቀጥልና ወደፊት ሚናውን ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ሲያስረክብ ጠንካራ ግብዓት ሆኖ ይቀጥላል። ለዚህ መሰረቲ ደግሞ አርሶ አደሩ በመኸር ምርት ላይ የሚያፈሰው ጉልበት ነው። በአሁን ወቅት በማሳው ላይ የሚያከናውናቸው ተግባራት ውጤታማ ስለሚያደርጉት በመኸር ምርት ላይ ጊዜውን ማሳለፍ ይኖርበታል። ለዚህም ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ በቂ ትኩረት ማድረግ አለበት።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy