ቃልአብ እያሱ
ኢትዮጵያ የአብራኳ ክፋይ የሆኑት ልጆቿ በማህበራዊ መስተጋብራቸውና በአገራዊ ጉዳዮቻቸው ዙሪያ በጋራ እየመከሩና እየዘከሩ ከትውልድ ትውልድ ያሸጋገሯት አገር ናት፡፡ ሕዝቦቿ የጋራ አገራዊ መግባባት በመፍጠር ከሠሯቸው አኩሪ ታሪኮቻቸው አንዱ የቅኝ ገዢ ወራሪዎችን በተባባረ ክንዳቸው አሳፍረው መመለሳቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብዙ ሲሆኑ አንድ፤ አንድ ሲሆኑ ብዙ ሆነው ኖረዋል፤ እየኖሩም ነው፡፡ ኢትየጵያ በጉያዋ ያቀፈቻቸው ብሄረሰቦች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና፣ ኃይማኖቶች በነጠላ ጥለት ላይ እንደሚታይ ፈርጥ ህብረ ቀለማት ያላቸውና ውበትን ያላበሷት ጌጦቿ ናቸው፡፡
በሕዝቦቿ መካከል ለረዢም ጊዜ የቆየው የመቻቻልና አብሮ የመኖር ዕሴትም ለሌሎች ሀገሮች ምሳሌ መሆን የሚችል ነው፡፡ ተመሳሳይ ቋንቋና ሐይማኖት ባላቸው የጎረቤት ሀገሮች መካከል አሳማኝ ምክንያት ሳይኖር ለረዢም ጊዜ የቆየ የእርስ በእርስ ግጭት ተፈጥሮ ሲታይ የኢትዮጵያ የመከባበር፣ የመቻቻልና የአንድነት ዕሴት ከምንም በላይ ትልቅ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን እንረዳለን፡፡
እያንዳንዱ ብሄር ፣ ቋንቋ ፣ሃይማኖት፣ ባህልና እምነት የኢትዮጵያ መገለጫ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የእነዚህ ብቻ ሳትሆን የወንዝ የተራራው ፣የደን የመሬቱ ፣የሳር የቅጠሉ፣ የአእዋፍ የእንስሳቱ ፣የአትክልት የአዝርዕቱ ድምር መገለጫም ናት፡፡ እነዚህ ሁሉ ተስማምተውና ተደጋግፈው የሚኖሩባት ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ ሕዝቦቿ በየሥርዓተ መንግሥቱ የሚከሰቱትን ኢ-ዴሞክራሲያዊና ኢ-ፍትሐዊ አስተሳሰቦችንና አሰራሮችን በጋራ በመሆን የመታገል ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ በተለይም ኢሕአዴግ በ1983 ዓ.ም ሀገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ የሚመራበት ሥርዓተ መንግሥት የሕዝቦችን ዴሞክራሲያዊ መብት የማስከበር ዕድልን የፈጠረ ነው፡፡ በዚህም ሕዝቦች መብትን የመጠየቅና ኢሕገ- መንግሥታዊ አሠራሮችን የመቃወም ልምዳቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡
ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የታዩት ቀውሶች የመልካም አስተዳደር ችግር እየተንሰራፋ መምጣቱን ተከትሎ አልፎ አልፎ በአንዳንድ ክልሎች ፍትሐዊ፣ ሰብዐዊ ፣ኢኮኖሚያዊና መሰል የመብት ጥያቄዎች ተንተርሰው የተነሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እየተንቀሳቀሰ ባለበት በዚያን ወቅት የተፈጠረውን አጋጣሚ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ በመምራት የማንንት ና የድንበር ጥያቄዎች ተነስተው አገሪቱን ወደከፋ ትርምስ እንድትገባ የሚያደርግ ስጋት ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡በዚህም ምክንያት በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የኖሩት የመቻቻልና የመከባባር ዕሴቶቻችንን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ክስተቶች ተስተውለዋል፡፡ ሕይወት ተቀጥፏል፤ ህዝብ ተፈናቅሏል፤ ንብረት ወድሟል ፡፡
ኢህአዴግ ባደረገው ጥልቅ ግምገማ የመልካም አስተዳደር ችግር ያለባቸው አመራሮች የፈጠሩት ስህተት መሆኑን አምኖ ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቋል፡፡ አዲስ መሪውን መርጦ የፖለቲካ ምሕዳሩን ለማስፋትም በተደረገው ጥረት አዲስ አስተሳሰብ በሀገሪቱ ላይ እየሰፈነ ይገኛል፡፡ ይህ ሕዝብን አንድ ያደረገው የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር የመደመር አስተሳሰብ የአገሪቱን ዜጎች በአንድ ላይ ያሰባሰበና ፍቅርን ያላበሰ ነው፡፡ ዛሬ በውጭም ይሁን በሀገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ እጅግ ደስተኛ ሆነዋል፡፡ ለውጡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ልዩነታቸውን እንደያዙ ሀሳባቸውን በነጻነት ለማራመድ ከተሰደዱበት አገር ወደ እናት ሀገራቸው እንዲመለሱ አድርጓቸዋል፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በበዓለ ሲመታቸውና በተለያዩ መድረኮች ካሰሟቸው ማራኪ ንግግሮች ወዲህ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍና ተቀባይነትን አግኝተዋል፡፡ በየመድረኮቹ የተናገሯቸውን እና ቃል የገቡትንም በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ እየፈጸሙ መገኘታቸው ተአማኒነታቸውን ከፍ ያደረገ ነው፡፡ በሀገር ውስጥም በውጭም የሚገኙ በርካታ እስረኛ ዜጎችን አስፈትተዋል፡፡
በዜጎች መካከል እርቅና ፍቅር እንዲነግሥ ጥላቻም እንዲከሰከስ አድርገዋል፡፡ ሙሰኞችና ሌቦችን በአደባባይ አውግዘዋል፡፡ ከአዲስ አስተሳሰብ ጋር የሚጓዙ አዳዲስ አመራሮችን ሾመዋል፡፡ ኢትዮጵያዊ አንድነት እንዲያብብና ልዩነትም እንዲከበር ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ ከጎረቤት ሀገራት ጀምሮ እስከ መካከለኛው ምስራቅ ድረስ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ የኢትዮጵያን ዕድገት በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይም አበክረው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ደክተር ዐቢይ አህመድ ላመጡት ለውጥና ላሳዩትም መልካም ጅምር ኅብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት በሀገር ውስጥ በተለያዩ ከተሞች እንዲሁም በተለያዩ የዉጪ ሀገሮች በዜጎቻችን የድጋፍ ሰልፍ ሲያደረግላቸው ሰንብቷል፡፡ ሀገራዊ መግባባትና አንድነት እንዲፈጠር የሠሩትን መልካም ሥራቸውን ተከትሎም ሕዝቡ በነቂስ እየወጣ በድጋፍ ሰልፉ ላይ አንድነትን የሚሰብኩ መፈክሮችን በመያዝ አጋርነቱን አሳይቷል፡፡ በተለያዩ ከተሞች በተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ‹‹ፍቅር ያሸንፋል›› ፣ ‹‹ስልጣን ማገልገያ እንጂ መገልገያ አይደለም››፣ ‹‹ኢትዮጵያዊያን ለውጥ እንጂ ነውጥ አንፈልግም›› የሚሉ ሀሳቦች ተላልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች ድምር ናት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ‹‹እንደመር›› የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ ሲጠቀሙ ይሰማሉ ፡፡ ይህ ሲባል በዋናዋና አገራዊ ጉዳዮቻችን ዙሪያ በጋራ እንቁም ማለታቸው እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠውን መብታቸውን ተገፈው አንድ ቋንቋ ይናገሩ ፤አንድ አስተሳሰብ ያራምዱ ማለት አይደለም፡፡ እነዚህ ሕዝቦች የሚለያዩባቸው ማኅበራዊ ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው አገራዊ መግባባትና አንድነታቸው ጥብቅ ይሁን ማለት ነው፡፡
በተለያዩ ከተሞች የተደረገው የድጋፍ ሰልፍ በመንግሥት አስተባባሪነት የተደረገ ሳይሆን ጠሪም ሆነ ተጠሪ ሳይኖር ሕዝቡ በራሱ ተነሳሽነት ያከናወነው ነው ፡፡ ዓላማው ጠቅላይ ሚንስትሩን መደገፍ ሆኖ የተለያዩ ፍላጎቶችም የተንጸባረቁበት ነበር፡፡ የተለያዩ ባንዲራዎች ተውለብልበዋል፤ የተለያዩ መፈክሮችና መልዕክቶችም ተላልፈውበታል፡፡ እናም ባየነውና በሰማነው ነገር ለምን? እንዴት? የምንል ከሆነ አገሪቱ የነበረችበትን ነባራዊ ሁኔታ ረስተናል ማለት ነው፡፡ አሁን እንዲህ አይነት ጥያቄ የምናነሳበት ሰዓት አይደለም ልዩነታችንን ይዘን ተደምረናል አበቃ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትራችን በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተስተዋሉ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለይተው ወደፊት ማስተካከያ እንደሚሰጡበት አያጠራጥርም፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከአርቲስቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ያስተላለፏቸው መልዕክቶች ለአገራዊ መግባባት ያላቸው ፋይዳ ጥልቅ በመሆኑ ሚዲያውና የኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ እንደ ግብዓት ወስዶ ሊጠቀምባቸው ይገባል፡፡ አርቲስቶች በኅብረተሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተደማጭነት ተጠቅመው የተጀመረው ለውጥ መስመር እንዳይለቅና ፍሬያማ እንዲሆን ሙያዊ ድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ የመገናኛ ብዙሃንም እንዲሁ የሚዲያ ነጻነት መብታቸውን ተጠቅመው ብልሹ አሠራሮችን እየተቹ ኅብረተሰቡ ከተሳፈረው የለውጥ ባቡር ላይ ሳይወርድ እስከ ጉዞው መዳረሻ መቀጠል እንዲገባው አቅጣጫዎችን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ይህ ያለንበት ወቅት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አዲስ ምእራፍ የተከፈተበት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የኅብረተሰቡን ቅሬታ የሚያዳምጥና አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ የሀገር መሪ ተገኝቷል፡፡ ሀገራዊ መግባባቱና ፍቅራዊ ትስስሩ በኅብረተሰቡ ዘንድ አዲስ ተስፋን የሰነቀና መነቃቃትን የፈጠረ ነው፡፡ አሁን በመንግሥት በኩል እየሆነ ባለው ነገር ሕዝቡ እየተደሰተ የሚገኘው በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረው የመፈራረስ አደጋ እልባት ያገኘ በመሆኑ ነው፡፡ለዚህ ደግሞ ትልቁን ድርሻ የያዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይና ከጎናቸው የቆሙት የለውጥ ደጋፊዎቻቸው ናቸው፡፡ ለውጡ ያልተመቻቸው ጥቂት አካላት የተገኘውን ትልቅ ድል እንዳያደናቅፉም ሁሉም ዜጋ ነቅቶ ሊጠብቃቸው ይገባል፡፡
ዶክተር ዐብይ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት አገሮችም የፍቅርን አሸናፊነት ያስተማሩ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ ሁሌም በንግግራቸው ደጋግመው የሚያነሱት የመደመር መንፈስ የአገሪቱን ድንበር አቋርጦ ለሃያ ዓመት ተለያይተው የነበሩትን የኢትዮጵያና የኤርትራ ወንድማማች ሕዝቦችን ማስተሳሰር ችሏል፡፡ አንድነቱና መግባባቱ በአገራችን ሕዝቦች መካከል ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በድንበር አዋሳኝ አገሮች በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ለሚገኙት አገሮች ሁሉ መርህ ሆኖ የአካባቢውን ሠላም መታደግ የሚያስችል ነው፡፡