Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከስምምነቱ ባሻገር

0 595

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከስምምነቱ ባሻገር

ገናናው በቀለ

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ተከፍቷል። በዚህ አዲስ ግንኙነት ሁለቱ አገሮች የተስማሙባቸው በልዩ ልዩ ጉዳዮች ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በተለይም አገራቱ ጦርነትን ስለ ማቆም፣ ኤምባሲዎቻቸውን ስለ መክፈት፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸውን ስለ ማጠናከር፣ ስለ ስልክ ግንኙነት፣ ስለ የብስና የአየር ትራንስፖርት እንዲሁም የወደብ አገልግሎት ስለ መጀመር የመሳሰሉ ስምምነቶችን በመፈራረም ወደ ተግባራዊ ስራ ገብተዋል።

ሁለቱ አገራት ጦርነት ያስከተለባቸውን ጠባሳ ይገነዘባሉ። ከጦርነት ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እንጂ ሌላ ምንም ነገር እንደማይገኝ የዛሬ 20 ዓመት ካደረጉት አሰቃቂ ውጊያ ትምህብት ወስደዋል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ጦርነትን ለማቆም የተፈራረሙት ስምምነት ከዚህ አኳያ መታየት ያለበት ነው።

ጦርነት አገራቱ እስካሁን ድረስ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ አብረው እንዳይሰሩና በውስጣቸው ቁርሾ እንዲፈጠር ያደረገ ነው። ስለሆነም ጦርነትን የማቆም ስምምነት አገራቱ በእነዚያ ዓመታት ያጧቸውን ነገሮች መልሰው እንዲያገኙ የሚያደርጋቸው ነው።

ኢትዮጵያ በአስመራ እንዲሁም ኤርትራ በአዲስ አበባ ኤምባሲያቸውን መክፈታቸው ተቋርጦ የነበረውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል።

በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የነበረው የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲሳለጥና ህዝቦች እንደ አንድ አገር ነዋሪዎች እንዲታዩ የሚያደርግ ነው። ዶክተር አብይ አህመድ በቅርበየ እንደተናገሩት፣ እጅግ ጥቃቅን የሆኑ ችግሮች ምናልባት ካጋጠሙም በወንድማማች መንፈስ ተነጋግሮ ለመፍታትም የሚያስችል ነው። በተጨማሪም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ሁለቱ አገራት የተፈራረሙት ግንኙነት ላልቶ የነበረውን ይፋዊ ቁርኝት በአንድነትና በፍቅር ገመድ የሚያጠብቀው ነው።

ይህ ገመድ በደም፣ በጋብቻ፣ በታሪክ፣ በወግና በባህል አንድ ሆነው ነገር ግን ተለያይተው የነበሩ ህዝቦችን የሚያቆራኝ እንዲሁም ለጋራ ጥቅማቸው በአንድነት አብረው እንዲሰሩ የሚያደርግ መሆኑ ግልፅ ነው። በተለይም ሁለቱን አገራት በሚያዋስኑት የድንበር አካባቢ ህዝቦች በንግድ እንደተሳሰሰሩና የባከኑባቸውን ዓመታት መልሰው እንዲያገኟቸው ያደርጋል።

በአገራቱ መካከል የመደበኛና የሞባይል ስልክ ግንኙነት መከፈቱ እዚያና እዚህ ያሉ ወንድማማችና እህትማማች ህዝቦችን ለማገናኘት አስችሏል። የስልክ ግንኙነቱ እንደተከፈተ ሰሞን የነበረውን የደስታና የሲቃ ሁኔታ ሁለቱም ህዝቦች ያውቁታል። አንዳንድ ሰዎችም ከደስታቸው ብዛት የተነሳ ወደማያውቁት ሰው ይደውሉ እንደነበር ሲነገር ሰምቻለሁ። ይሀም ምን ያህል መፈላለግና መነፋፈቅ በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል እንደነበር የሚያሳይ ነው።

አገራቱ አየር መንገዶቻቸው በረራ እንዲጀምሩ መወሰናቸው የህዝቦችን ግንኙነት ከማጠናከር ባሻገር በንግድ ለመተሳሰር ዕድል ፈጥሮላቸዋል። ሰሞኑን ከአዲስ አበባ 450 ኢትዮጵያዊያንን ይዞ ወደ አስመራ የተጓዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በውስጡ የንግዱን ማህበረሰብ መያዙ አገራችን ከኤርትራ ጋር ስለሚኖራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ያለው ጠቀሜታ የላቀ መሆኑ ግልፅ ነው።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የአሰብን ወደብ ለመጠቀም እንቅስቃሴ እያደረገች ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ እንዳስታወቀው፣ ሁኔታውን ለማከናወን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ማሪታይም አገልግሎት ባለስልጣን፣ ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አካላት ያሉበት ግብረ ሃይል ተቋቁሟል። በኤርትራ በኩልም በተመሳሳይ ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራ ጀምሯል።

ይህ እንቅስቃሴ ተጨማሪ የወደብ አገልግሎት በመፍጠር የበኩሉን ድርሻ የሚያበረክት ነው። የኢትዮጵያ ባለሃብቶች በአሰብና በሌሎች የኤርትራ ከተማዎች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ፣ ኤርትራዊያንም ኢትዮጵያ ውስጥ ሃብታቸውን አፍስሰው በጋራ መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ ያመቻቻል።

በተለይ አገራቱ በተስማሙባቸው ጉዳዩች በተለይ ለኤርትራ አዋሳኝ የሆኑት የትግራይ ክልልና የአፋር የድንበር አካባቢ ህዝቦች በጦርነቱ ምክንያት የደረሰባቸውን ጉዳትና አሁን በመጣው ለውጥ የሚያገኙትን እፎይታ መኖሩ ግልፅ ነው።

እነዚህ ህዝቦች በለውጡ ከነበሩበት የሰቆቃ ህይወት ይላቀቃሉ። ያለ ስጋት ወደ ልማት ስራቸው ይዞራሉ። የድንበር ንግድም ስለሚከፈት ከንግዱ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ። እንደ ዛላንበሳ፣ አዲግራት፣ ራማ፣ ቡሬ ወዘተ የመሳሰሉ ከተሞች ወደ ቀድሞው የደመቀ ገፅታቸው ይመለሳሉ። ይህም የድንበር አካባቢዎች ተቀዛቅዞ የነበረው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲነቃቃና ህዝቦችንም ተጠቃሚ ያደርጋል።

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልም ይህን የሰላም ስምምነት አስመልክተው በቅርቡ ለጋዜጠኞች የሰጡት መግለጫ የሚያረጋግጠውም ይኸው ነው። ዶክተር ደብረጽዮን የኢትዮ-ኤርትራን ችግር ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ለትግራይ ህዝብ ይሁን ለአገራችን ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል። ደስተኛ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

ይህ የእርሳቸው አገላለፅ በተለይም የድንበር ህዝቦችን ማዕከል ያደረገ ይመስለኛል። የትግራይ ክልል ከኤርትራ ጋር የሚያወስኑት ቦታዎች ብዙ ናቸው። በአንዚህ ቦታዎች የሚገኙ ህዝቦች ላለፉት 20 ዓመታት ከድህነት በስተቀር የተረፋቸው ነገር የለም። በመሆኑም ሰላም ሊኖራቸው የግድ ይላል።

ጠቅላይ ሚነስትራችን የድንበር አካባቢ ህዝቦች አሁን በሚገኙበት አሳዛሽ ድህነት ውስጥ እንዳይቀጥሉ የወሰዱት የስምምነት እርምጃ ከባድ ነው። አንድ ለህዝብ ከሚያስብ የአገር መሪ የሚፈፅመው ይህንኑ ነው።

አንድ ህዝብ በስጋትና በችግር ውስጥ ሆኖ አገር መምራት ከባድ ነው። የህዝቡን ችግር ጠልቆ በማሳብ ለመፍትሔው መረባረብ ያስፈልጋል። የድንበር አካባቢ ህዝቦች ሰላምንና የህሊና እርካታን ምን ያህል እንደተጠሙና እንደተራቡ ወደዚያው በማቅናት ማረጋገጥ ይቻላል።

ስምምነቱ ቀደም ሲል በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አካባቢ ያለው ውጥረትን ከመቀነስ ባሻገር ለድንበር አካባቢ ዜጎች ከነበሩበት አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲላቀቁ የሚያደርጋቸው ነው። ይህም ራሳቸውን ጠቅው በአቅማቸው አገራቸውን እንዲያግዙ ያደርጋል። የስነ ልቦና ተጠቂነት እንዳይኖር ያደርጋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy