Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከንቱ መፍጨርጨር

0 320

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከንቱ መፍጨርጨር

ዳዊት ምትኩ

በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው መልካም ግንኙነት ዛሬ የተፈጠረ አደለም። የነበረ፣ የሚኖርና ወደፊትም የግንኙነቱ ደርዝ እየሰፋ የሚሄድ ነው። ይህን ሃቅ ያልተገነዘቡ አንዳንድ አካላት በአሁን ሰዓት ሆን ብለው በሁለቱ አገራት መካከል ግጭት ለመቀስቀስና የህዝቡን የለውጥ አቅጣጫው ለማሳት ጥረት ሲደርጉ ይስተዋላል። ይሀን እንጂ ይህ መሯሯጣቸው የማይሰምርና ከንቱ መፍጨርጨር ነው።

የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ለሱዳን መንግስትና ህዝብ ትልቅ አክብሮትና ፍቅር እንዳለን ይታወቃል። ሁለቱም አገራት ይህን ሁኔታ በተለያዩ ወቅቶች እያከናወኑ መጥተዋል። ኢትዮጵያ ለሱዳን፣ ሱዳንም ለኢትዮጵያ የምታስብ እርስ በርስ የተያያዙ አገሮች ናቸው። ምንም እንኳን በአገራት ድንበር ይቅርና በክልሎች የአስተዳደር ወሰን ውስጥም ትናንሽ ግጭቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ግልፅ ቢሆንም፤ ትናንሽ ግጭቶችን ለማራገብ የሚደረጉ ጥረቶች ግን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ፈፅሞ አይገልፁም።

ስለሆነም አንዳንድ አካላት ጥቃቅን ግጭቶችን በማራገብ በህብረተሰቡ ላይ የስነ-ልቦና ጫና በመፍጠር የለውጥ ሂደቱን አቅጣጫ ለማስቀየር የሚያደርጉት ከንቱ መፍጨርጨር የትም የማያደርስ ነው። ምክንያቱም ሁለቱ አገራት በመንግስት ለመንግስት ያላቸውን ግንኙነት በድንበር አካባቢ በአርሶ አደሮች መካከል የሚታየውን ሁኔታ ስለማይገልፀው ነው።

ሰሞኑን የየኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹምና የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ለአዲስ ዘመን የሰጡት ማብራሪያም ይህን የተመለከተ ነው። ጄኔራሉ ከጋዜጣው በጎንደር ጠረፍ አካባቢ የሱዳኖች ዘልቆ መግባትን በተመለከተ ጉዳዩ ተነስቷል። ይሄን እንዴት ያዩታል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ሁኔታው የቀየ መሆኑን በማስረዳት፣ እስከ ዛሬ የድንበር ማካለል ስራ አለመከናወኑን አውስተዋል። የኢትዮጵያም ይሁን የሱዳን አርሶ አደሮች ተቀላቅለው የሚያርሱት መሬት እንዳለና በዚህም በሱዳንና በእኛ በኩል ያለው ድንበር በግልጽ ተሰምሮ አለመካለሉን አንስተዋል። የድንበር አካባቢ ሰዎች አብረው እንደሚኖሩና ሱዳኖችም ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት እንደሚያከራዩ አንስተዋል። ልክ እንደ ሌላው ቦታ ሁሉ አንዱ መሬት ያለው፣ አንዱ ደግሞ መሬት የሌለው መሆኑንም ገልፀዋል። የእኛም ይሁን የሱዳን ወገኖች ሚሊሽያ ያላቸው መሆኑንና የሚጣሉትም በእርሻ መሬት መሆኑንም አስታውቀዋል። ያም ሆኖ የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል ለወገኑ እንደሚሰራ ግልፅ አድርገዋል። ከዚህ ውጭ በመንግስታት መካከል እየተደረገ ያለው አርሶ አደሮቹን በማስታረቅ ወደ ግጭት እንዳይገቡ ማድረግ ነው። ከዚህ ውጪ ያለው አሉባልታ መሆኑንም አስድተዋል።

ይህ የጄኔራሉ ማብራሪያ የሚያሳየን ነገር ቢኖር፣ ግጭቱ እንደማንኛውም ድንበር አካባቢ በነዋሪዎች የሚፈፀም መሆኑን ነው። አንዳንድ ለውጡን የማይሹ አካላት ህዝቦች ተረጋግተው እናዳይኖሩ ‘ሱዳን መሬትህን ወሰደችብህ’ በማለት ግጭት ለመቀስቀስ የሚያደርጉት ጥረትም ከአሉባልታ ያልዘለለ መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም።

እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ በህብረተሰቡ ውስጥ የሌለ ውዥንብር በመንዛት ከንቱ መፍጨርጨር እያደረጉ ነው። ይህን ከንቱ መፍጨርጨር ህዝቡ ሊገነዘበው ይገባል። እየተወራ ያለው አለሉባልታ የህዝቡን ፍላጎት የማያንፀባርቁ ከመሆናቸውም በላይ የሁለቱን አገራት የጠለቀ ግንኙነት የማያውቁ ናቸው። ኢትዮጵያ የሱዳን አጋር አገርና ለሰላሟ ስትሰራ የቆየች ናት። የግንኙነቱ መሰረት ጠንካራም ነው።

ሱዳን ረጅም ኪሎ ሜትሮችን የምትዋሰነን በጎረቤት አገር ናት። በተለያዩ ወቅቶች በአገሪቱ ግጭቶች ሲቀሰቀሱ ኢትዮጵያ ቀዳሚ መፍትሔ አፈላላጊ ናት። ይህች አገር ለበርካታ ዓመታት በዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ስታልፍ ኢትዮጵያ ሰላሟ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ስታግዛት ነበር።

በጐረቤት ሀገር ሱዳን የተቀሰቀሰውን አለመረጋጋት እልባት ከመስጠት አኳያ የአንበሳውን ድርሻ ከተወጡት የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት። በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል የነበረውን አለመግባባት በመፍታት፣ በዳርፉርና በአብዬ የተከሰቱ ችግሮችን በመቅረፍና የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በማሰማራት ሀገራችን የተጫወተችው ሚና እጅግ የላቀ ነው። ይህን ሱዳኖች አሳምረው ያውቃሉ። የኢትዮጵያን አስተማማኝ ጉርብትናም ይገነዘባሉ።

የኢትዮጵያ መንግስትም ሱዳን ሊተማመኑባት የሚገነጨባ አገር መሆኗን ያውቃል። በጋራ የማደግ ተስፋቸውም አጓጊ ሊሆን እንደሚችልም ይገነዘባል። ጠቅላይ ሚኒስትረ ዶክተር አብይ የሱዳን ወደብን በጋራ ለማልማት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይህን ሃቅ የሚያረጋግጥ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳን የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት እያደረገች ያለችውን ጥረት በመደገፍ ያላትን አቋምም ይገነዘባል። የሱዳን ሰላም መሆን የሁለቱ ጎረቤት ሀገሮች እድገት እንደሚፋጠንም ያውቃል። እናም ሁለቱ አገራት መፃዒ እድል የተሳሰረ በመሆኑ በአገራቱ መካከል ጠንካራ ግንኙነት ሊመሰረት ችሏል።

በአገራችን እየመጣ ያለውን ትክክለኛ ለውጥ የሚቃወሙ ሃይሎች ግን ይህን ጠንካራ ትስስር ሳያውቁ ወይም እያወቁ ሁከት ለማስነሳት ‘ሱዳን መሬትህን ወሰደችብህ’ በማለት አሉባልታ ሲነዙ ይስተዋላል። ክብሪትና እሳት በማያዝ በአሉባልታ ፈረስ ላይ እየጋለቡ ህዝብን ከህዝብ ጋር ሊያጋጩ ይሯሯጣሉ። ሩጫቸው ከንቱ መፍጨርጨር መሆኑን አልተገነዘቡም። የህዝብ ለውጥን መቃወም እንደማይቻል ታሪክ ያላስተማራቸው ናቸው።

ለውጡን በማይቀበሉ ሃይሎች የሚሰነዘረው አሉባልታ የለውጡ ባለቤት ለሆነው ህዝብ ተጨማሪ ጉልበት የሚሰጥ መሆኑ አልገባቸውም። እነዚህ አካላት እንደሚሉት ሱዳን በሃይል የወሰደችው መሬት የለም። መሬት ላይ ያለው ዕውነታ እነርሱ ከሚሉት ጋር የሚጣረስ ነው። ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ እንዳሉት እንደማንኛውም ቦታ በድንበር አካባቢ የሚፈጥሩት ግጭት እንጂ ከመሬት መውሰድ ጋር የተያያዘ አይደለም።

ያም ሆኖ ለውጡን ለማደናቀፍ በከንቱ የሚፍጨረጨሩ አካላት የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ለማደፍረስ እየተሯሯጡ ነው። ስለሆነም በየቦታው ሁከት፣ ረብሻና ስርዓት አልበኝነት እንዲነግስ በሙሉ ሃይላቸው እየሰሩ መሆናቸውን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባዋል።

የየእነዚህ ሃይሎች የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት የመጋፋት ተግባር ትርጉም የለሽ ነው። በአሉባልታ የሚፈርስ ህዝብና ከጀመረው የለውጥ ሂደት ዝንፍ የሚል ህዝብ የለም። ህዝቡ አሁን ያገኘውን ሰላም ያመጣው በትግሉ ነው።

የህዝብን የለውጥ ፍላጎት የሚታገሉ አካላት ይህን እያወቁ የህዝቡን ፍላጎት ለማሽመድመድ የሚያደርጉት ተግባር ብዙ ርቀት የሚያስጉዛቸው አይደለም። ይሁን እንጂ ህዝቡ አሁንም ቢሆን በየአካባቢው አለሉባልታ እየነዙ ሰላሙን ለማደፍረስና ከጀመረው የለውጥ ሂደት እንዲስተጓጎል የሚደረጉ ከንቱ መፍጨርጨሮችን እንደ ሁል ጊዜው ተከታትሎ ሊያከሽፋቸውና በእነርሱም መንገድ አለመጓዝ ፊቱን ወደጀመረው ለውጥ ማዞር ይኖርበታል።  

 

 

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy