Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከእሥር ቤቱ ጀርባ

0 256

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከእሥር ቤቱ ጀርባ

  ሜላት ወልደማሪያም

ኢትዮጵያ በ1987 ዓ.ም ያጸደቀችውና   እየተገለገለችበት የሚገኘው ሕገ መንግሥቷ ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ እየሆነ ነበር ለማለት አያስደፍርም፡፡ እንደውም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተከስቶ ለነበረው አለመረጋጋት እንደ ዋና ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው መንግሥት ሕገ- መንግሥቱን የማስፈጸም ቁርጠኛ አቋም ባለመውሰዱ ነው፡፡ ለጊዜው በሕገ መንግሥቱ ከተካተቱት ዘርፈ ብዙ ድንጋጌዎች ውስጥ ‹‹ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን›› አስመልክቶ በማረሚያ ቤቶች የተፈጸሙ የሕግ ጥሰቶችን በጥቂቱ እንመልከት።፡

በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ላይ ‹‹ሰብአዊ መብቶችና ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ  የሚመነጩ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው፤ የዜጎችና የሕዝቦች ሰብዐዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ›› በሚል ተቀምጧል፡፡ የዜጎችን ደህንነት ለማስከበር በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠው ይህ ሕግ በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ ሀገራችንን ወደ ከፋ ቀውስ እንድታመራ ዋና ምክንያት ሆኗል፡፡

ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ አንዳንድ ከተሞች የተጀመሩት ሕዝባዊ አመጾች እተባባሱ ሄደው ንብረት እንዳወደሙ፣ ህይወት እንደቀጠፉ፣ ህዝብን እንዳፈናቀሉና ሀገሪቱን ወደ መጥፎ ሁኔታ ሊያስገቧት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለዚህ ሁሉ ትርምስ የዳረጋትም የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የፍትህ መጓደል፣ ሌብነት፣ ግለኝነት፣ ዘረኝነት ወዘተ መሆናቸውን መንግሥት ለሕዝቡ ይፋ አድርጓል፡፡   

የጉዳዩ ዋና ተዋናዮች የነበሩትም የመንግሥት ወገንተኛ መስለው  የተሰጣቸውን ሃላፊነት ለግል ጥቅማቸው መገልገያ ያደረጉ ጥቂት አመራሮች ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ሕግ አስከባሪ መስለው ሕግ አፍራሽ ፤ የሕዝብ አገልጋይ መስለው ፀረ-ሕዝብ ፤ የመንግስት አስፈጻሚ አካል መስለው ፀረ- መንግሥት ተግባራትን የሚፈጽሙ ነበሩ፡፡ ለዚህም ነው ዕኩይ  ድርጊታቸውን የሚቃወሟቸውን ግንባር ቀደም የአገር ተቆርቋሪዎች የተለያዩ ስሞችን በመስጠት ሰብስበው እስር ቤት በማጎር ወንጀል ሲፈጽሙባቸው የነበረው፡፡

ዜጎቻችን ሕገ-መንግሥታዊ  መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተጥሷል፡፡ ከታራሚዎቹ አንደበት እንደሰማነው እነኳ  ታፍነው ወደማያውቁት ስፍራ ተወስደው ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል ፣ብርሀን እንዳያገኙ በጭለማ እስር ቤት ተወርውረዋል ፣ከቤተሰቦቻቸው እና ከጠበቆቻቸው ጋር  እንዳይገናኙ ተደርገዋል፤አንዳንዶች ታስረው በኤሌክትሪክ ሽቦ ተገርፈዋል፤ ጥፍራቸው ተነቅሏል፤ አይናቸው ፈሷል ፤ እግራቸው ተቆርጧል፡፡ አንዳንድ ወንድሞቻችን የዘር ፍሬያቸው ተኮላሽቶ ከጥቅም ውጭ እንዲሆን ተደርጓል፤ አንዳንድ እህቶቻችንም ሴትነታቸውን ተከትሎ  ዘግናኝ ግፍና በደል ተፈጽሞባቸዋል፤ አንዳዶችም በእስር ቤቱ ጥበት ተፋፍገው መኖራቸው ሳያንስ በእሳት ተቃጥለዋል ፤ ህክምና ተነፍገዋል፡፡ ጥቂቶች በእስር ቤት ውስጥ የሚደርሱባቸውን በድሎች በችሎት ፊት ቀርበው ቢያስረዱም እንኳን ሃይ ባይ ዳኛ ሳያገኙ ቀርተዋል ፡፡ አብዛኛዎቹ ግን ይቅርታ እና አመክሮ ለማግኘት ሲሉ የተፈጸምባቸውን  በደል እንኳን ለፍርድ ቤቶች ለማስረዳት አይደፍሩም ነበር ፤ ደግሞስ ማን ቢሰማቸው፡፡

እንግዲህ  ይህ ሁሉ የመብት ጥሰት በዜጎቻችን ላይ የተፈጸመው‹‹ ማንኛውም ሰው ጭቃኔ ከተሞላበት ኢ-ሰብአዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው›› የሚል ሕግ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 18 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ሰፍሮ ያለው በማን አለብኝነት በመጣስ ነው፡፡ እናም በሕገ-መንግሥቱ ላይ ሰፍረው ተግባራዊ ካልሆኑት ሕጎች አንዱ የሰብዐዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሕግ በሕገ-መንግሥቱ ላይ የተቀመጠ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ከተስማማቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት  ስምምነቶችም አንዱ ነው ፡፡ ያም ሆኖ ሕጉ ሊተገበር ባለመቻሉ ከባከኑት የሕገ-መንግሥታችን አንቀጾች አንዱ ነበር ማለት ይችሏል፡፡

ሕገ-መንግሥት ለአንድ አገር ዜጎች የሚያገለግል መተዳደሪያ ደንብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 2 እንደሚያስረዳው ‹‹ማንኛውም ዜጋ ፣የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ሌሎች ማኅበራት እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ-መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው›› ይላል፡፡

ይህ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የተደረገ የጋራ ስምምነት ወይም የመተዳደሪያ ደንብ ግን ለሁሉም ዜጎች ዕኩል አልሰራም፡፡  ሕጉ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተጠያቂ እንደማድረጉ በዜጎቻቸው ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ የነበሩ አመራሮች ግን ለዚህ ሕግ ተገዢ ሲሆኑ አልታዩም፡፡ከሁሉም በላይ የሚገርመው ደግሞ ሕግ አስከባሪ ናቸው በተባሉ የመንግሥት አካላት የሕግ ጥሰት መፈጸሙ ነው ፤ በሕግ ጥላ ስር ባሉ ታራሚዎች ላይ በደሉ መፈጸሙ ሲታሰብ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ አስከፊ ያደርገዋል፡፡

“ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” እንደሚባለው አንዳንድ በኃላፊነት ላይ ያሉ ዜጎች ከሕግ በላይ ሆነውና ሕግ እየጣሱ ሌሎችን ዜጎች ሕገ መንግሥቱን እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ሲጥሩ ነበር፡፡ ውጤቱ ግን ዜጎች ለሕገ መንግሥቱ ያላቸውን ታመኝነት ገልፀው አንዳንድ ባለስልጣናት በህዝብ ተገደው፣ ከፊሎቹም በገዛ ፈቃዳቸው ከኃላፊነት እንዲለቁ ያስቻለ ነው፡፡ ታዲያ ማነው ከማረሚያ ቤቶች በላይ ሕገ-መንግሥቱን ሊያስከብር ይችላል ተብሎ የሚታሰበው? ማረሚያ ቤት ያስፈለገው ሕገ ወጦችን ሕግና ሥርዓት ለመስተማርና መልካም ስነምግባር እንዲላበሱ ማድረግ፤ ፍርዳቸውን ጨርሰው ኅብተሰቡን ሲቀላቀሉም በጥሩ ባሕሪ የታነጹ አምራች ዜጎች እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡

ታራሚዎች ይገረፉ ፣ በጨለማ ቤት ይታሰሩ፣ ጥፍራቸው ይነቀል ፣ እግራቸው ይቆረጥ ወዘተ የሚል ሕግ በሕገ-መንግስታችን ላይ ከሌለ ከየት መጥቶ ሊሰራበት ቻለ? እነዚህ አካላት በታራሚው ወይም በተጠርጣሪው ላይ እንዲህ አይነት ግፍና በደልን እየፈጸሙ እንዴት ኅብረተሰቡ ቁጣውን አያሰማ? የወህኒ ቤት ፖሊሱም፣ ታራሚውም፣ ሕዝቡም በአጠቃላይ እያንዳንዱ ዜጋ በተወካዮቹ አማካኝነት ያጸደቀውን ሕገ-መንግሥት እኩል የማክበር ግዴታ አለበት ፡፡ ታራሚው በጥፋቱ ወህኒ እንዲወርድ ያስገድደው ሕግ እስከ ሆነ ድረስ በታራሚው ላይ የመብት ጥሰት የፈጸመው አካልም በዚያው ሕግ መሠረት መቀጣት ይኖርበታል፡፡

አብዛኛዎቹ ዜጎቻችን ከቀበሌ እስከ ማዕከላዊ እስር ቤቶች ገብተው ፍዳቸውን ሲያዩ የነበረው ስለሰረቁ ወይም ስለገደሉ አይደለም ፤ ብልሹ የመንግሥት አሠራሮችን ስለተቃወሙ ነው፤ ይህ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰወረ አይደለም ፡፡

ይህን ሁሉ በደልና ስቃይ በዜጎች ላይ መፈጸም ለምን አስፈለገ ? ለምንስ  ሃይ የሚል አካል ጠፋ ? ለምንስ በሕገ-መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውን የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መጣስ አስፈለገ ? ብለን እንጥይቅ ይሆናል ፤  መልሱ አንድና አንድ ነው፡፡ በሥርዓቱ ላዕላይም ይሁን ታዕታይ መዋቅር ውስጥ ጡንቻቸውን ያፈረጠሙ ጥቂት አመራሮች ያሻቸውን ለማድረግ እንዲያስችላቸው ድርጊታቸውን የሚቃወሙትን የሕዝብና የአገር ተቆርቋሪዎች በማፈን ሀገሪቱን ለመቦጥቦጥና የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ይህን መሰል ሕገ ወጥ ሥራ ሲሠሩ መክረማቸውን ሁሉም ዜጋ ተረድቶታል፡፡   

የሆነው ሆኖ  ኢህአዴግ በ 17 ቀን ግምገማው  የመልካም አስተዳደር ችግር ያለባቸው አመራሮች የፈጠሩት ችግር መሆኑን አምኖ ሕዝብን ይቅርታ ጠይቋል፤ እስረኞችንም በመፍታት በመላው አገሪቱ የይቅርታ  መንፈስን በማስፈን ሕገ- መንግሥቱን በቀጥታ የመተርጎም ጅምር አሳይቷል፡፡

ሚዲያዎቻችን በሕገ-መንግሥቱ የተሰጣቸውን የአመለካከትና ሀሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ መብታቸውን ተጠቅመው መሥራት እንዲችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸዋል፡፡ በተለይም የመንግሥት ሚዲያዎች  ቀደም ሲል የነበረውን አድሏዊ አሰራር አስወግደው ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩ ተበረታተዋል፡፡ ዛሬ የመንግሥት ሚዲያዎች የህዝቡን ብሶትና ምሬት ማውራት በመጀመራቸው ተደማጭነታቸው ከፍ ብሏል፡፡ ቀዳሚና ታማኝ የመረጃ ምንጭም እየሆኑ መጥተዋል፡፡   

በዚህም መሠረት ባልተለመደ መልኩ ከሰሞኑ ባስተላለፉት ፕሮግራም  በየእስር ቤቶቹ በዜጎች ላይ ይፈጸም የነበረውን ግፍና በደል አስመልክተውናል፡፡ እውነት ይህ ሁሉ ግፍ በአገራችን እስር ቤት የተከሰተነውን? በሚል እጃችንን በአፋችን ላይ ጭነን እንድንመለከት አድርገውናል፡፡ መንግሥት በራሱ አመራሮች በዜጎቹ ላይ የተፈጸመውን ግፍና በደል በራሱ ሚዲያ ለህዝቡ እንዲተላለፍ ማድረጉም አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ስለመጀመሩ አንድ ማረጋገጫ ነው፡፡ ሚዲያና የኮሚኒኬሽን ዘርፉ በእንደዚህ አይነት ኢሕገ-መንግሥታዊ ተግባር ላይ የተሰማሩ ኃይሎች እራሳቸው መታረም እንዲችሉ ማስተማር ይኖርበታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሚዲያችን ከዕለት ወደ ዕለት እያሳየ ላለው ለውጥ ሳናደንቅ አናልፍም ፡፡

ሚዲያው በፌደራል ማረሚያ ቤቶች የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በከፊል አሳየን እንጂ በክልል ማረሚያ ቤቶች ያለውም ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይሆንም፡፡ እንዲህ ዓይነት የኅብረተሰብ ብሶቶች የሚነሱባቸው ጉዳዮችን እየነቀሱ ማቅረብን ሚዲያው ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ የመብት ጥሰቶች ቀደም ሲል በሚዲያ የመዳሰስ እድል አግኝተው ቢሆን ኖሮ ጉዳቶችን በእንጭጩ መቅጨት በተቻለ ነበር፡፡     

ይሁንና አንዳንዶች ሲተላለፍ የነበረው የማረሚያ ቤቶች ወንጀል ለምን ለህዝብ ይፋ እንዲሆን ተደረገ በሚል ቅሬታ ሲያሰሙ ተደምጠዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ጉዳቸው ከተጋለጠ ለፈጸሙት አሰቃቂ ድርጊት ተጠያቂ እንሆናለን የሚል ስጋት ስላለባቸው ወይም ለውጡ ጥቅማቸውን ስለሚያጎድልባቸው ነው ፡፡ በሕግ ጥላ ስር ሆነው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ግለሰቦች ቀድሞ ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው ተገፎ ያን ያህል አካላዊ ጉዳት የተፈጸመባቸው መሆኑ ሳያንስ  ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ አሁን ደግሞ የተፈጸመባቸውን ግፍ እንኳን የመናገር መብታቸውን በመግፈፍ ሌላ የመብት ጥሰት ለምን አልተፈጸመም መባሉ የሚያስገርም ነው፡፡

ሚዲያ አንዱ አላማው ማስተማር ነው፡፡ ስለሆነም ይህ በዜጎች ላይ የተፈጸመው አካላዊና ስነልቦናዊ የመብት ጥሰት ትክክል ያለመሆኑን ለኅብረተሰቡ ማስተማርና በቀጣይም ስህተቱ እንዳይደገም ግንዛቤ ማስጨበጡ ተገቢ ነው፡፡ በእርግጥ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑና ግጭቶችን ሊያራግቡ የሚችሉ ዘገባዎችን ማቅረብ ሌላ ነገርን አስከትሎ ሊመጣ ስለሚችል ሚዲያዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ፡፡  መገናኛ ብዙኀን የአገሪቱን ሕገ-መንግሥትና የፕሬስ ሕጉን መሰረት በመድረግ አሁን የተፈጠረውን ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር ተጠቅመው የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጠበቁ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy