Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከ“እኔ” ይልቅ “እኛ” የሚል

0 534

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከ“እኔ” ይልቅ “እኛ” የሚል

አስተሳሰብ

አባ መላኩ

ክቡር ጠቅላይ  ሚኒስትሩ በአሜሪካ  ለሚገኙ ኢትዮጵየዊያኖችና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኖች ባደረጉት ንግግር ላይ አገራችንን ወደፊት ለማራመድ እኔ ከሚል አስተሳሰብ ወደ እኛ የሚል አስተሳሰብ መሸጋገር እንደሚገባው አጽዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል። ዶ/ር አብይ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ የእኔ አመራር ውጤት ነው ለማለት አልፈለጉም፤ ይልቁንም  የአገራችን የለውጥ ስኬት የሁሉም ጥረት ውጤት መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል። አዎ ከ“እኔ” ይልቅ “እኛ” በሚል አስተሳሰብ ቢተካ አካሄዳችን የበለጠ ይጠነክራል፤ ተቀባይነትም ያገኛል።

አንዳንድ ሰዎች የኢህአዴግ እህት ፓርቲዎች  የለውጡ አጋር እንዳልሆኑ አድርገው ለማቅረብ  የሚያደርጉት አካሄድ አግባብነት የጎደለው ይመስለኛል። ኢህአዴግ የአራት ፓርቲዎች ግንባር ነው። እውነት እንነጋገር ከተባለ  በኢህአዴግ ቤት የብዙሃኑ ድምጽ ገዢና የበላይነት ያለው አሰራርን የሚከተል ፓርቲ ነው። በኢህአዴግ ቤት የሃሳብ ፍጭት ከተካሄደ ብኋላ ለዚያ ሃሳብ ተግባራዊነት የሁሉም አመራሩ ርብርብ ማድረግ ይመስለኛል ኢህአዴግ የውስጠ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ጠንካራ ነው የሚባለው። ከሃሳብ ፍጭት ብኋላ  ተወደደም ተጠላም ማንም ሆነ ማን ለዚያ ሃሳብ ተገዢ የመሆን ያንን ሃሳብ የማራመድ ያንን ሃሳብ የመደገፍ ግዴታ ነው። አሁን ላይ እየተካሄደ ያለው ለውጥም በዚሁ አግባብ እየተካሄደ ያለ ነው። ከዚህ በፊት ህውሃት ለኢህአዴግ የለውጥ ሞተር እንደነበር መካድ አይቻልም። አሁን ላይ ደግሞ የለውጥ ሞተሩ ኦህዴድ ሆኗል። ነገ ደግሞ ሌላው ሊሆን ይችላል። ይህን አይነት አካሄድ ለእኔ ክፋቱ አይታየኝም።   ይህ ነገር ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ በኢህአዴግ እህት ድርጅቶች መካከል ሚዛናዊ አቅም እንዲፈጠር ያግዛል ባይ ነኝ።

ኢህአዴግ/ ኦህዴድ  እንደነ ለማ መገርሳና  ዶ/ር አብይ አህመድ ያለ ጠንካራ  አመራሮችን መፍጠር በመቻሉ ሊኮራ ይገባዋል። ኦህዴድ በዋነኝነት ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም ቆሜለሁ የሚል ፓርቲ ነው። የኦሮሞ ህዝብ የሚታወቀው ደግሞ በገዳ ስርዓቱ ነው።   የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ አገር በቀል የሆነው የዴሞክራሲ ስርዓታችን “የገዳ አስተዳደር”  በዓለም ዓቀፍ የማይዳሰሱ ቅርስ  መዝገብ  ላይ ሲሰፍር ለአገራችን ኩራት ሆኗል። ምክንያቱም የሰው ዘር መገኛ  የሆነችው አገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጀማሪ መሆኗም እውቅና ሲቸረው  ለእኛ ኢትዮጵያዊ ተደማሪ ኩራት ቢሆን የሚበዛብን አይደለም። ለውጥ መቼም የትም  ቢሆን በጥቂት ሃይላት ይጀመርና በርካቶችን ማስከተል ከቻለ ለውጡ ውጤታማ እንደሚሆን  ምሁራን ይናገራሉ። የአሁኑ ለውጥ የኦህዴድ ጥረት ብቻ እንዳልሆነ ቢታወቅም የለውጡ ፊትአውራሪ መሆኑን ግን መካድ አይቻልም። በቅንነት ለተመለከተው ኦህዴድ  የህዝብን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ለውጥ ማምጣት በመቻሉ በአጭር ጊዜ በርካታ ተከታዮችን ማፍራት ችሏል።

በገዳ ስርዓት  በስልጣን ላይ ማንም እንደፈለገ  መቆየት አይችልም። በገዳ ስርዓት የስልጣን ሽኩቻ እንዳይኖር  በየስምንት ዓመቱ ምርጫ የግድ ነው። በዚህ ስርዓት እኔ ስልጣን ካልያዝኩ  የሚል አካሄድ ከቶ አይኖርም። ይህን እውነታ ዛሬ በተግባር አይተነዋል። በቅንነት ለተመለከተው  የአቶ ለማ መገርሳ ድርጊት እጅግ አስገራሚ ነው። ይህን እውነታ ታሪክ ከትቦት ለነገው ትውልድ መማሪያ  ሊሆን የሚችል እኛ በአይናችን የተመለከትነው ዕውነታ ነው። እንዲህ ነው የገዳ ስርዓት ውጤት፤ ከእኔ ይልቅ አንተ ትብስ  መባባል። ከላይ እንዳነሳሁት ዓለም ስለዴሞክራሲና ስለእኩልነት፣ ስለነጻነትና አብሮነት እሳቤው ሳይኖረው የኦሮሞ ህዝብ ይተገበረው   በነበረው የአስተዳደር ስርዓት ሳቢያ ስልጣንን ያለምንም ሽኩቻ ይቀባበል ነበር።

ጊዜና ቦታ  ለእውነታ ቦታ አላቸው ይባላል።  አቶ ለማ መገርሳ የአገራችንን ነባራዊ  ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ከራስ ወዳድነት የጸዳ አካሄድ  በመከተላቸው ለውጡ ስኬታማ እንዲሆን አድርገዋል። ሁሉም  አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ለአቶ ለማ መገርሳ ቅን አስተሳሰብ ትልቅ አክብሮት እንዳለው በየአደባባዩ ሲነገር አድምጠናል፤ ተጽፎም አንብበናል። አቶ ለማ መገርሳ  አገራችን በሞትና በህይወት መካከል ሆና ትቃትት በነበረችበት ወቅት ራሳቸው መስዋዕት አድርገው ዶ/ር አብይን ወደሃላፊነት በማምጣት ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ታድገዋታል።   ይህን እውነታ ዶ/ር አብይም በየአደባባዩ መስክረዋል። ሰሞኑን እንኳን በአሜሪካ ያደረጉት ንግግር ላይ “የትላንት አለቃዬ የዛሬ የቅርብ አማካሪዬ” ሲሉ ለአቶ ለማ መገርሳ  ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል። አዎ ኢትዮጵያችን ወደተሻለ ደረጃ ልትሸጋገገር የምትችለው እኔ የሚለው አስተሳሰብ ቀርቶ እኛ የሚል አስተሳሰብ ሲጠነክር ብቻ ነው። ዛሬ ዶ/ር አብይ አገራችንን ከመፈራረስ  አደጋ የታደጓት እርሶ መንገዱን ስላመቻቹላቸው፤ እርሶ ሁኔታዎችን ስላደላደሉላቸው እንደሆነ የአደባባይ ሚስጢር ነው።

አሁንም ኢህአዴግ/ ኦህዴድ ከለውጥ ሃይሎች ጋር ያለውን  ግንኙነት አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝብን ፍላጎት ይበልጥ ማርካት  ይኖርበታል፤ ትግሉንም ወደ ህዝብ ያስተላልፍ። ከማይመቹኝ የኢህአዴግ  አካሄዶች መካከል ሁሉን ነገር ሚስጢራዊ የማድረግ አካሄዱ ነው። ይህ ባህል  እኛ ኢትዮጵያዊያንን ጎድቶናል ባይ ነኝ። በክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት ጊዜ አንድ የሩማንያ ጋዜጠኛ   ኢትዮጵያዊያንን በተመለከተ “Secretive society” በሚል የጻፈው መጣጥፍ ትዝ ይለኛል። የመጣጥፉ ጭብጥ በአጭሩ ኢትዮጵያዊያን እያንዳንዱን ነገራቸውን በድብቅ  ማድረግ የሚወዱ፤ ግልጽነት የሚጎላቸው ህዝቦች ናቸው የሚል ነበር። ይህ አይነት አካሄድ አገራችንን ጎድቷታል። ኢህአዴግ ሁሉንም አሰራሩን ግልጽ ያውጣው የሚል አቋም ባይኖረኝም ሁሉንም ነገር  ከህዝብ መደበቅ አለበት ብዬ ደግሞ አላምንም።

አሁን ላይ በአገራችን  እየታየ ያለው ለውጥ ጥቅማችንን ይነካል፣ እኛ  ኢትዮጵያን ካልመራናት ትበጣጠስ፣ የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ሃይሎች እያደረጉ ያሉት አፍራሽ እንቅስቃሴ  አገራችንን ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይከቷት እሰጋለሁ። በዕርግጥ ትዕግስት እንኳን ለመንግስት ለግለሰብም  አስፈላጊ እንደሆነ አምናለሁ። ይሁንና የመንግስት ትግስት ለከት ሊኖረው ይገባል። በጠራራ ጸሃይ ዜጎች በየአደባባዩ የሚገደሉ ከሆነ የህግ የበላይነት እምኑ ጋ ይሆን?   እንደእኔ እንደእኔ የህግ የበላይነት መቼም የትም ለድርድር የማይቀርብ መሆን መቻል አለበት። መንግስት የሕግ የበላይነት ለሰላም መረጋገጥ የመጀመሪያውና ትልቁ መስፈርት መሆኑን  ተገንዝቦ የህግ የበላይነትን በተመለከተ ቀይ መስመር ሊያበጅ ይገባል። በአገራችን ትላንት መልካም ነገሮች እንደተከናወኑ ሁሉ በርካታ ጸያፍ ድርጊቶችም መኖራቸውን መካድ አይቻልም። አገራችን ባለፉት 15 ዓመታት  ባለሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገብ እንደቻለች ሁሉ የተወሰኑ ሃይሎች ተደራጅተው ሲሰርቁና ሲያሰርቁ፤ ሲገርፉና ሲያስገርፉ፤ በህዝብ ላይ በደል ሲፈጽሙ እንደነበር መካድ አይቻልም።

በየትኛውም አገር መንግስት መንግስት ሊባል የሚችለው በስልጣን ላይም መቆየት የሚችለው፣ በህዝቦችም ዘንድ ተቀባይነት  የሚኖረው የህግ የበላይነትን ማረጋገገጥ ሲችል፤ ዜጎች በነጻነት ወጥተው መግባት የሚችሉበትን ሁኔታ ማረጋገጥ  ሲችል ብቻ ነው። ዛሬ ላይ ዜጎች ፍራቻ እየገባቸው ይመስላል። የመስቀል አደባባዩ የግድያ ሙከራ፣ የዳንጎቴው ስራስኪያጅ  ግድያ፣ የኢንጂነር ስመኘው ግድያ እንደው በዘፈቀደ የተካሄዱ ድርጊቶች እንዳልሆኑ መገመት የሚከብድ አይመስለኝም። አዎ ሁሉም ድርጊቶች  የኢትዮጵያ ህዝብ ፍትህ ይፈልጋል። ለህግ የበላይነት መረጋገጥ መንግስት የማይተካ ሚና ይኑረው እንጂ ህብረተሰቡም ያለው አስተዋጽዖም ከፍተኛ በመሆኑ  ሁላችንም ለውጥ ፈላጊ ሃይሎች ከመንግስት ጎን ልንቆም ይገበል። የእውነት መንግስት ብቻውን የሚያመጠው ለውጥ አይኖርም፤ በመሆኑም ለውጥ ፈላጊዎች ሁሉ ከመንግስት ጎን የምንቆምበት ጊዜ አሁንና አሁን ነው።  

ፖለቲካ ከጥቂቶች  ጥቅም አኳያ የሚመዘን ከሆነ ውድቀት  ከዚያ ይጀምራል። ዴሞክራሲያዊ አካሄድ  ታሳቢ የሚያደርገው ሁሌም ብዙሃኑን በመሆኑ  ኢህአዴግ የቀደሞውን ህዝባዊነቱን ሊተገብር ይገባል። ጥቅመኛ ፖለቲከኛው ትላንት በሰራው ስህተት ከቶ የተጸጸተ አይመስልም፤ ንሰሃ መግባትም ሆነ  ህዝብን ይቅርታ ለመጠየቅ ፍላጎት አላሳየም፤ እንኳን ንሰሃ ሊገባና ይቅርታ ሊጠይቅ ቀርቶ አርፎ መቀመጥን አልመረጠም። በዕርግጠኝነት መናገር ባይቻልም  በአገራችን እየተካሄዱ ካሉ የግድያዎችና የግድያ ሙከራዎች እንዲሁም ሁከቶች ጀርባ ጥቅመኛ ፖለቲከኞች በህቡ ያደራጇቸው ሃይሎች መሆናቸው መገመት የሚከብድ አይደለም። ይህ ሃይል በህዝብና መንግስት ጠንካራ ትብብር ማስቆም ካልተቻለ ነገ ማን ይሆን ባለተራ  እያልን ዋቢ ሊሆኑ የሚችሉ ሃይሎችን አንድ በአንድ መሸኘት እንዳይመጣ እሰጋለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy