Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ወደ ላቀ ደረጃ…

0 346

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወደ ላቀ ደረጃ…

                                                           ሶሪ ገመዳ

መንግስት የጀመረውን ዴሞክራሲን የማስፋት ጥረት የህዝብን ፍላጎት መሰረት ማድረጉን ከሚያረጋግጡት ነገሮች መካከል ቀዳሚው በአራቱም የአገሪቱ ማዕዘኖች እየታየ ያለው ህዝባዊ ድጋፍ ነው። ህዝቡ በሁሉም ጫፎች ያለ ምንም ቀስቃሽና ጎትጓች መንግስት እያደረገ ላለው ለውጥ ድጋፉን በጥልቅ ስሜት በመግለጽ ላይ ይገኛል። ለውጡን ለመደገፍ በየአቅጣጫው እየተጠራራ ሰለማዊ ሰልፍ እያደረገ ነው።

ይህ ለውጥ መንግስት እንደው በዘፈቀደ ያመጣው ሳይሆን፣ የ17 ቀናቱ የኢህአዴግ የጥልቅ ተሐድሶ ውጤት መሆኑ ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መንግስታቸው እየፈጸመው ያለውና እርሳቸውም እያስፈጸሙ ያሉት የድርጅታቸውን ውሳኔ ነው።

በዚህ መሰረትም በአሁኑ ወቅት በአገራችን ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው አደረጃጀት ከአስር ሺህ በላይ ታራሚዎች በይቅርታ መፈታታቸውንና ይህ ታራሚዎችን የመልቀቅ ሂደት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን፣ በአገሪቱ የይቅርታ ህግ ላይ ብቻ የተመረኮዘ ነው።

በተጨማሪም የተፈቱት ታራሚዎች በሙሉ በሶስተኛ ወገን ላይ ጉዳት ያደረሱ አለመሆናቸው በደንብ ተጣርቶ እየተከናወነ ያለ ተግባር ነው። ይህ ክንዋኔ ይቅርታው የሚመለከታቸው ታራሚዎችን በመለየት በቀጣይም እየተጣራ የሚቀጥል ይሆናል።

በኡኑ ሰዓት ዴሞክራሲው እንዲሰፋ በመደረጉ ምክንያት በትጥቅ ትግል ላይ የተሰማሩ ሃይሎች ትግላቸውን አቁመው ሰላማዊ ትግሉን እየተቀላቀሉ ነው። ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግም በሰላማዊ መንገድ ሲታገሉ ከነበሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በፈለጉት ርዕሰ ጉዳይ ለመነጋገር አሁንም ዝግጁ ነው።

ለውጡ በውጭ የሚገኙ በርካታ ሚዲያዎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚያስችል ምህዳር ነው። የአገር ውስጥ ሚዲያዎች (በተለይም የመንግስት ሚዲያዎች) ዘገባቸውን ሚዛናዊ ማድረግ መጀመራቸው እንዲሁም አንዳንድ የአገሪቱ ህጎች በተለይም እንደ የፀረ-ሽብር ህግ፣ የመያዶች ህግና የፕሬስ ህግን የመሳሰሉ ከዴሞክራሲ ስርዓቱ ጋር ቀጥታ ግንኙነት አላቸው ተብለው የተለዩ የህግ ማዕቀፎች አንዳንድ አንቀጾቻቸው እንዲሻሻሉ በባለሙያዎች እየታዩ ነው። እነዚህ ተግባሮች ዴሞክራሲውን ለማስፋት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች አካል ናቸው። ተግባሮቹ የአገራችንን ዴሞክራሲ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ መሆናቸው በተጨባጭ እየታየ ነው።

ዴሞክራሲ የትኛውም አካል ስለፈለገ ለዜጎች የሚሰጠው፣ ሳይፈልግ ደግሞ የሚነፍገው ጉዳይ አይደለም። የአገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ እስካልወደቀ ድረስ ዴሞክራሲን መንፈግ አይቻልም።

እንዲያም ሆኖ ቢነፈግ እንኳን በከፊል እንጂ ሙሉ ለሙሉ ሊገደብ አይችልም። በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደ ነበረበት ሁኔታ እንዲመለስ መደረግ ይኖርበታል። ይህ ሃቅ በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ አገር ውስጥ የሚሰራበት ይሰራበታል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት የተካሄዱት ትግሎች መነሻቸው አንዱ የዴሞክራሲ መብቶች በአግባቡ አለመከበራቸው ነው። ይህ የአገራችን ህዝቦች የዘመናት ጥያቄ በተለይ በአዲሰሱ አመራር በቂ ምላሽ እንዲያገኝ እየተደረገ ነው። ከዴሞክራሲ ጋር የተገናኙና መብቱን ይነፍጋሉ የተባሉ ህጎች በመስኩ ሙያተኞች ማሻሻያ እየተደረገባቸው ያለው በዚሁ ምክንያት ነው።

የዜጎች ዴሞክራሲዊ መብቶች በአገራችን ህገ መንግስት ላይ በግልፅ የተመለከተና በተግባር እየተተረጎመ የሚገኝ ነው። በአሁኑ ሰዓት እየተካሄደ ያለውና በአብዛኛዎቹ ጉዳዩች መግባባት ላይ እየተደረሰባቸው የሚገኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይቶችና ወደ አገር ቤት የመግባት ሁኔታ ከዚህ አንጻር የሚታይ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በህዝቡ ፍትሐዊ ድምጽ ላይ የተመሰረተ ነው። የስርዓቱ ምሶሶ የሆነው ህገ መንግስታችን ደግሞ በሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ፍላጎትና እምነት ፀድቆ ስራ ላይ የዋለ ሰነድ መሆኑ ይታወቃል።

ስለሆነም በሰነዱ ላይ የተመለከቱትን ዴሞክራሲያዊ መብቶች መንፈግ ከራስ ጋር እነደመጋጨት የሚቆጠር ነው። አዲሱ አመራር ዴሞክራሲውን ለማስፋት የሚያደርጋቸው ማናቸውም ክንዋኔዎች ይህን ሃቅ የተመረኮዙ ናቸው።  

የአገራችንን ዴሞክራሲ ስንመለከተው ውሳኔ የሚሰጠው ፍትሐዊው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። ይህ ህዝብ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ለውጡን እያስኬደለት የሚገኘው አዲስ አመራር አለው። አዲሱ አመራር በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚደገፍ በመሆኑ ለዴሞክራሲው መስፋት ተግቶ እየሰራ ነው። ይህ ትጋቱም የህዝቡ ፈላጎት ስለሆነ በምንም ዓይነት የሚቋረጥ አይደለም። አመራሩ የህዝቡን ፍላጎት እንዲሁም ህገ መንግስቱን ተንተርሶ የሚሰራ ስለሆነ በአሁኑ ሰዓት እያካሄደ ያለው የዴሞክራሲ ሪፎርም እነዚህን እውነታዎች ታሳቢ ያደረገ ነው።

መንግስት በአሁኑ ሰዓት እያከናወነ ያለው ዴሞክራሲውን የማስፋት ተግባር የህዝቦችን ተደማጭነት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፣ ሁሉም ዓይነት አስተሳሰቦች አደባባይ ላይ ወጥተው ግንዛቤ እንዲወሰድባቸው የሚያደርግ ነው። ወደፊትም ሁሉም ፓርቲዎች በፓርላማው ውስጥ ውክልና ሲያገኙ የአሳታፊነት መንፈስ እንዲነግስ ያደርጋል።

በአንድ ወቅት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሲናገሩ እንዳደመጥኩት፣ የእስራኤል ፓርላማ ለተቀናቃኛቸው ለፍልስጤማውያን ጭምር የሚሟገቱ የተወሰኑ አባላት የሚገኙበት ነው። እነዚህ አባላት ፍልስጤማውያን አይደሉም—እስራኤላዊ ናቸው።

ይህም በአንድ አገር ፓርላማ ውስጥ ዴሞክራሲው እስከየት ድረስ ሊጓዝ እንደሚችል በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ያዳመጥን ዜጎች የተረዳነው እውነታ ነው።

ዴሞክራሲ በአገር ውስጥ ስላሉ ኩነት ማውሳት ቀርቶ ተቀናቃኝ ለሆኑ ሃይሎች ጭምር እስከ መከራከር የሚያደርስ አውድ መሆኑንም ያስረዳል። እነዚህ ሃይሎች ጥቂት ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን በዴሞክራሲ አውድ ሃሳባቸው ይደመጣል።

በአገራችን ውስጥም በአሁኑ የለውጥ ወቅት እየተካሄዱ ባሉት ሰልፎች ምናልባትም እንኳንስ የአገራችንን ባዴራ ቀርቶ የኡጋንዳን ወይም የብሩንዲን ባንዴራ ሰዎች ይዘው ሊወጡ ይችላሉ። ይህ ምንም የሚደንቅ አይደለም።

እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በለውጥ ሂደት ውስጥ የሚጠበቅ ከመሆኑም በላይ፣ የዜጎችን ፍላጎትና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እንደሚከበር ማሳያዎች ናቸው። የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱም እንዲያድግም ተደማሪ መሰረት ይጥላል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በሀገራችን ውስጥ እንዲፈጠር የሚፈለገውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ እንዲል የሚያደርገው ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy