Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሃይማኖት ችግሮችን ለመፍታት…

0 1,864

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሃይማኖት ችግሮችን ለመፍታት…

ገናናው በቀለ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከመጅሊስና ከየሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር በቅርቡ ያደረጉት ውይይት፣ ሁለቱም አካላት ለመንግስት ያላቸውን አክብሮትና አጋርነት ያሳዩበት እንዲሁም መተማመንና የአንድነት መንፈስ የተንጸባረቀበት ነው። በአገራችን ህገ መንግስት ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ሁሉ ሃይማኖትም በመንግስት አሰራር ውስጥ ጣልቃ መግባት እንደማይችል ተደንግጓል። ይህ ህገ መንግስታዊ ገደብ አገራችን ውስጥ መንግስታዊ ሃይማኖት ወይም ሃይማኖታዊ መንግስት እንደሌለ የሚያስረዳ ነው።

ይሁን እንጂ መንግስት በሃይማኖት ሳቢያ አገር እንድትረበሽና ህዝብ እንዲከፋፈል እንዲሁም እንዲጋጭ የማይፈልግ አይፈልግም። ስለሆነም ሁሉም ሃይማኖቶች በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት ቁጭ ብሎ በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር፣ በመቀራረብና በፍቅር ተወያይተው መፍታት እንደሚኖርባቸው ያምናል። ይህም መንግስት የአገርን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ መወጣት ያለበትን ሚና የሚያመላክት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጅሊሱም ይሁን ከሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው ጋር ያደረጉት ውይይት ሁለቱ ወገኖች ምናልባት የመንግስትን ድጋፍ የሚሹ ከሆኑ መንግስት የተጠየቀውን ሁሉ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ያስታወቁትም ከዚህ እውነታ በመነሳት ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ምንም እንኳን መንግስትና ሃይማኖት አገራችን ውስጥ የተለያዩ ቢሆኑም፤ የአንድን ሀገር ህዝብ በተለያየ መንገድ የሚያገለግሉት መንግስትና ሃይማኖት ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም ባለት አይቻልም። ሁለቱም አካላት በአንድ  ማህበረሰብ ውስጥ በየራሳቸው የነጻነት ማዕቀፍ በመንቀሳቀሳቸው ብቻ ፈፅሞ የማይገናኙ ናቸው ብሎ መውሰድ አይቻልም።

የቀረቤታቸው ስፋትና ደረጃ ይለያይ ካልሆነ በስተቀር ሁለቱም አካላት ከሀገራቸው ዜጎች ጋር አብረው እስከሰሩ ድረስ አንደኛው ከሌላኛው ጋር አይቀሬ ይመስለኛል። ይህ ማለት የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት ምስጢር እንደ የሂሳብ ባለሙያዎች እንደሚሉት አይጠጌና አይነኬ (Asymptote) ዓይነት አይደለም ማለት ነው። ሊገናኙና ሊጠጋጉ ይችላሉ። ምክንያቱም መንግስት ህዝቦቹን በፍቅር፣ በይቅርታ፣ በመደመርና በአንድነት አገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ለማሰለፍ ሲያስብ እንዲሁም ሃይማኖቶች የእምነት ተግባራቸውን ሲያከናውኑ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መገናኘታቸው የማይቀር ስለሆነ ነው።

በኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የእምነት ነጻነትና የሃይማኖት እኩልነት ተረጋግጠዋል። አገራችን በምትከተለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ እነዚህ መብቶች ህገ መንግስታዊ ከለላና ጥበቃ ያላቸው ናቸው። ይህም ማንኛውም ዜጋ የመሰለውን እምነት በነጻነት ለመከተል  በሌሎች ሰዎች አምልኮ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ የሚከለክል ነው። ከዴሞክራሲ አስተሳሰብ አንጻር የራስን መብት ማክበር የሚቻለው፣ ተመጣጣኝ በሆነ ሁኔታ የሌሎችን መብቶች ባለመጋፋት ስለሆነ ነው። በአጭር ቋንቋ በራስህ ላይ እንዲሆን የማትፈልገውን ነገር በሌሎች ላይ አትፈፅም እንደሚባለው ዓይነት ነው።

ታዲያ ግለሰቦች የራሳቸውን የእምነት ነጻነት ለማስከበር በማሰብ በዓለም ላይ ካሉት እምነቶች ሁሉ የእኔ እምነት ትክክል ስለሆነ እኔን ብቻ ተከተለኝ በማለት ማስገደድ እይችሉም። ምክንያቱም ሌላውም ዜጋ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ያሻውን እምነት መያዝ ስለሚችል ነው። አንድ ግለሰብ የእምነት ነጻነቱ የሚከበርለት፣ የሌላው ግለሰብ  አምልኮአዊ ነጻነት በሚከበርበት ማዕቀፍ ውስጥ መሆኑ መዘንጋት አይኖርበትም። የግለሰብ መብቶች ሲከበሩ በተነፃፃሪ የብዙሃን መብትም ለሊከበር ይችላል።

ስለሆነም የሁሉም ዜጎች መብት ሳይሸራረፍ ገቢራዊ የሚሆነው፣ አዲሱ አመራር በአገራችን ውስጥ ዴሞክራሲን ለማጎልበት ካለው ፍላጎት አኳያ ነው። እናም የማንኛውም ሰው ሃይማኖታዊ የአምልኮ ነጻነት ሊረጋገጥ የሚችለው የሌሎችን ነፃ አመለካከት የመያዝ ዴሞክራሲያዊ መብት አክብሮ ከመንቀሳቀስ ጋር የሚያያዝ እንደሆነ መረዳት ጠቃሚ ነው።

ነገሩን ከሃይማኖት አኳያ ብንመለከተው እንኳን ማንኛውም ሃይማኖት ለምዕመናኑ ሲያስተምር ራሱ የሚከተለውን የእምነት መመሪያ በማስረፅ እንጂ የሌሎች እምነት  በማናናቅና ትክክል አይደለም እያለ አይደለም። እምነቱ ራሱ የሚከተለውን ሃይማኖታዊ ስርዓት ከመስበክ ውጭ፣ ከእኔ ውጪ ያሉት እምነቶች መከተል ያለባቸው መመሪያ ይህ ነው የሚል አግባብን ሊከተል አይችልም። ለዚህም ነው የእምነት ነጻነት መከበት አለበት የሚባለው።

በሌላ በኩልም የእምነት እኩልነት በአገራችን ውስጥ ተረጋግጧል። በዴሞክራሲያዊ አገራት  ውስጥ ሁሉም ዜጎች እኩል ናቸው። አይበላለጡም። የሚፈጽሟቸው ማናቸውም ጉዳዩች አይበላለጡም። አንድ ዜጋ የሚከተለው እምነት ከሌላው ሊበልጥም ሆነ ሊያንስ አይችልም። ይህም እንደ እኛ ባለው ዴሞክራሲያዊ የለውጥ አገር ውስጥ ሁሉም እምነቶች እኩል ስለ መሆናቸው አስረጅ ነው። አንዱ ሃይማኖት ያለው መብት ሌሎችም አላቸው።  

አገራችን ውስጥ ማናቸውም ሃይማኖቶች የበላይ ወይም የበታች ሊሆኑ አይችሉም። የእከኩልነታቸው መሰረት የሚመነጨው ኢትዮጵያ ከምትከተለው የዴሞክራሲ ስርዓት የእኩልነት መርህን በጥብቅ ስለሚያምን ነው። እኩልነት የዴሞክራሲ አንዱ መርህ በመሆኑ ይህን መርህ መሸራረፍ አይቻልም። መሰረታዊውን የዴሞክራሲ አሰራር ሊያናጋው ይችላልና።

ይህ ዴሞክራሲያዊ አተያይ መንግስትና ሃይማኖት እንዲለያዩ የሚያደርግ ነው። መንግስትና ሃይማኖት እስካልተለያዩ ድረስ የሃይማኖት ነጻነትና የእምነት እኩልነትን መሳ ለመሳ ማስኬድ አይቻልም። እርግጥም መንግስት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ የሚገባ  ከሆነ፣ አንድ የመንግስት የስራ ሃላፊ እንደ ከአመለካከቱና ከእምነቱ በመነሳት በሌላው ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል። ይህም በፊናው በእምነት ነጻነትና እኩልነት ላይ አሉታዊ አሻራ ያሳርፋል። የኢፌዴሪ መንግስት ድጋፍ እንዲሰጥ ካልተጠየቀ በስተቀር በየትኛውም ሃይማኖታዊ ተግባራት ውስጥ ጣልቃ እንይገባ በህገ መንግስቱ የተደነነገገውም ለዚሁ ይመስለኛል።

እርግጥም የዜጎችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ለማሳለጥ መስራት  የሚገባው መንግስት በፈጣሪውና በአማኙ መካከል ባለው ሃይማኖታዊ እምነት ጣልቃ  በመግባት ጊዜውን ማሳለፍ የለበትም። ይህን የሚከውን ከሆነ የተሰጠውን ምድራዊ ሃላፊነት በቅጡ ሊወጣ አይችልም።

መንግስት በሃይማኖቶች ውስጥ ጣልቃ ከገባ ጥበቃ ሊያደርግላቸው የሚገባውን የህዝቦች መብት ሊሸራሸራቸውና ከሃይማኖት ተከታዮች ጋር  ሊጋጭ የሚችልበት ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ያለፉት ጊዜያት ህያው ምስክሮች ናቸው። ዴሞክራሲን ከማክበር፣ የዜጎችን የእምነት መብት ከመጠበቅ እንዲሁም ግጭትን በራሱ እጅ ላለመፍጠር በማሰብ መንግስት ከሃይማኖት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ መግባት አይኖርበትም።

ሃይማኖትም በመንግስት ተግባሮች ውስጥ እጁን ማስገባት አይኖርበትም። አንድ ሃይማኖት  መንግስትን ይህን ፈፅም ያኛውን ደግሞ ምዕመኖቼ ስለማይፈቅዱ እንዳትፈፅም የሚል ከሆነ ሃይማኖቱ የመንግስት መመሪያ በመሆን አገርን ማስተዳደሩ አይቀርም። የሃይማኖት ብዝሃነት ባለበት አገር ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ “በአንድ ጭንቅላት እናስብ” ዓይነት እምነት ቦታ የለውም። የዜጎች የሃይማኖት ነጻነትና እኩልነትም ውሃ ይበላዋል። የሃይማኖት ጉዳይ ሰዎችን እጅግ ስሜታዊ የሚያደርግ በመሆኑ የግጭት መንስኤም በመሆን አገርን ሊበጠብጥ ይችላል። እናም መንግስትም ይሁን ሃይማኖት በራሳቸው ሜዳ ላይ መጫወት ይኖርባቸዋል።

ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ህዝቦቹን በዴሞክራሲያዊና ልማታዊ ተግባራት ዙሪያ አሰባስቦ በምድር ላይ እሰካሉ ድረስ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰራው መንግስት ምዕመናቸውን ከፈጣሪያቸው ጋር ለማገናኘት ሰማያዊ ፀጋ ለማስገኘት ከሚሰሩት ሃይማኖቶች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አይኖረውም ተብሎ መደምደም አይቻልም። መንግስት በሚያከናውነው ምድራዊ ሁኔታ ውስጥ ሊገናኙ ይችላሉ። ሁለቱ አካላት  የማይገናኙበት ወሰን አንደኛው ተገቢ ባለሆነና በህግ ከተደነገገው ውጭ በሌላኛው አሰራሮች ውስጥ ጣልቃ ለመግባት አለመሞከር ብቻ ነው።

ስለሆነም መንግስት የዜጎቹን  ሰላም፣ አንድነትና ፍቅር እንዲሁም ዴሞክራሲን ለማስፋት ሲሰራ ሃይማኖትም በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ ከመንግስት ጋር የሚያገናኘው ቁርኝት አለ። ይህ ቁርኝት የመንግስትን ድጋፍ የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። መጅሊሱና የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር የተወያዩት በዚህ መነሻ ይመስለኛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሁለቱም ወገኖች በመነጋገርና በመቀራረብ አብረው መስራት እንደሚኖርባቸው የገለጹት መንግስት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ መግባት ስለሌለበት ነው። ይሁን እንጂ መንግስት በእምነታቸው ውስጥ ጣልቃ ሳይገባ ከህግና ከስርዓት ጋር በተያያዙ ጉዳዩች የእምነቱ ተከታዩች ድጋፍ ከጠየቁ መንግስት የልዩነቱን ወሰን ጠብቆ ድጋፍ ሊያደርግ ይችላል። ዶክተር አብይ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ሃይማኖታዊ ችግር ለመፍታት የተከተሉት መንገድም ይህንኑ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ነው።     

  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy