Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሚያዋጣን መደመርና መደመር ብቻ ነው!

0 652

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሚያዋጣን መደመርና መደመር ብቻ ነው!

አባ መላኩ

የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት በጣም ዘመናዊ ከሚባሉ ህገ-መንግስቶች መካከል የሚመደብ ነው። ህገመንግስታችን  ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ያካተተ በመሆኑ ከየትኛውም አገር ህገመንግስት ጋር የሚወዳደር ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ህገመንግስታችን የተዋጣለት ይሁን እንጂ አተገባበር ላይ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉበት የአደባባይ ሚስጢር  ነው። ህገመንግስታችንን በትክክል ተግብረነው ቢሆን ኖሮ አገራችን ከዛሬ ሶስት ወር በፊት ወደነበረችበት አስጠሊታ ሁኔታ ባላመራች ነበር። ባለፉት ሁለት ዓስርት ዓመታት ህገመንግስቱ በአግባብ አልተተገበረም በማለት አንዳንዶች በየአደባባዩ  በየመድረኩ ሲጮሁ አድማጭ አላገኙም ነበር፤ ያ ሁኔታ ደግሞ ውሎ አድሮ አገራችንን ለከፋ ቀውስ እንደዳረጋት ተመልክተናል።

በአገራችን  ይስተዋሉ ከነበሩ  ኢ-ህገመንግስታዊ ድርጊቶች መካከል የሰብዓዊ መብት  ጥሰት አንዱ ነው። በቅርቡ በቴሌቭዥን የተመለከትነው በማረሚያ ቤቶች አካባቢ ይካሄድ የነበረ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እጅግ ሰቅጣጭ፣ በምስል ባንመለከተው ለማመን የሚከብድ  ነው። በህግ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ዜጎችን መረጃ ለማግኘት ሲባል መግረፍ፣ ቶርች ማድረግ፣ ብልት ላይ ምናምን ማንጠልጠል፣ ጸያፍ ስድብ መስደብ ወዘተ ኢ-ህገመንግስታዊ ድርጊቶች ናቸው። ይህን አይነት ድርጊት የፈጸሙና ያስፈጸሙ አካላት  በህግ አግባብ መጠየቅ ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ። የደርግን መንግስት ስንኮንነው ስንረገመው የኖርነው በእንዲህ ያለ ቅጥ ያጣ ድርጊቱ አልነበረምን? ዛሬም ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ እያልን እንዲህ ያለ ተራና ርካሽ ነገር መፈጸም ምን የሚሉት ነገር ነው።     

አሁን ላይ የምናያቸውና የምንሰማቸው ነገሮች እያስገረሙኝ ነው። አንዳንድ ቡድኖችና ግለሰቦች ትላንት ህገመንግስት ሲጣስ ዝምታን  የመረጡ ወይም ራሳቸው ሲጥሱ የነበሩ ሃይሎች ዛሬ የህገመንግስት ጠበቃ ሆነው ህገመንግስት እየተጣሰ ነው፤ ህገመንግስት ይከበር ለማለት  መሞከራቸው አግባብነት ዮደለው አካሄድና አስተሳሰብ ይመስለኛል። በዕርግጥ ህገመንግስት ተጥሶና ከቅንነት የተሰጠ አስተያየት ቢሆን ኖሮ ተቀባይነት  ያለው ነበር። ይሁንና የሚሰጡ አስተያየቶች ከቅንነት ወይም ለአገር ከማሰብ አይመስለኝም። እንዲህ ያሉ ነገሮች ያስተዛዝባሉ፤ መተማመንንም ይቀንሳሉ። የዛሬ አነሳሴ እንኳን ይህን ጉዳይ ለማብራራት ባለመሆኑ ይህን ጉዳይ በዚህ ልለፈው።  ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ስለ ኢፌዴሪ ህገመንግስት አንዳንድ ሃሳቦች ለማንሳት ነው።

በአፈጻጸም  የሚስተዋሉ ህጸጾች ካልሆኑ በስተቀር  ህገመንግስታችን በይዘቱ የእውነትም እንከን የማይወጣለት እንደሆነ ማንም የሚመሰክረው ዕውነታ ነው።  በክፍል አንድ ውስጥ በህገ-መንግስታዊ ጥበቃ የሚደረግላቸው ሰብአዊ መብቶች በአስራ አምስት አንቀጾች ተዘርዝረው ተቀምጠዋል። ህገ-መንግስቱ የዜጎችን በህግ ፊት ያለምንም ልዩነት እኩል የህግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ደንግጓል። በዘር፣ በብሔር ብሔረሰብ፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ አመጣጥ፣ በሃብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም በሰዎች መካከል ልዩነት እንደማይደረግና ሁሉም ሰዎች እኩል ተጨባጭ የህግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው በግልጽ ያስቀምጣል። ይሁንና እነዚህ የሚያማምሩ አንቀጾችን  በተግባር ሲሸራረፉ ተመልክተናል። በመሆኑም በቀጣይ እነዚህን ነገሮች ልናስተካክላቸው ይገባል ባይ ነኝ።

ከዚህ በተጨማሪ የኢፌዲሪ በህገ-መንግስት ሰብአዊ መብትን በተመለከተ ያስቀመጠው አብይ ድንጋጌ በስብዕና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚመለከት ነው። በህገ-መንግስት አንቀጽ 28 ላይ እንደተመለከተው አገራችን ባጸደቀቻቸው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችና በሌሎች የኢትዮጵያ ህጎች በሰው ልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን የሰው ዘር የማጥፋት፤ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ፣  ሰውን የመሰወር፣ ድብደባ ድርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ እንደሌሎች ወንጀሎች በይርጋ እንደማይታገድና በህግ አውጭም ሆነ በማንኛውም የመንግስት አካል በይቅርታ እንደማይታለፉ ተሰምሮበታል። ይህ ድንጋጌ አገራችን ለዜጎች ሰብዓዊ መብቶች መከበር እስከምን ድረስ ጠንካራ አቋም እንዳላት የሚያመለክት ይሁን እንጂ በተግባር ላይ ሳንካ ገጥሞታል። በመሆኑም አሁንም በደንብ ማየት የሚገባን ጉዳይ መሆን መቻል አለበት።

የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት በክፍል ሁለት ስር የዴሞክራሲ መብቶችን በተመለከተ 16 አንቀፆች የተከፋፈሉ ድንጋጌዎች አስፍሯል። በእነዚህ አንቀፆች አማካኝነት የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ሕጋዊ እውቅና አግኝተዋል። በዚህም መሠረት የዜጎች የአመለካከትና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የፕሬስና የሌሎች የመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የሥነ-ጥበብ ፈጠራ ነፃነት ተረጋግጧል። ባለፉት ሥርዓቶች ይደረጉ የነበሩ የቅድመ ምርመራ እንቅስቃሴዎች በሕገ-መንግሥቱ አማካኝነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወግደዋል።  ይሁንና አገራችን የፕሬስ ነጻነት መረጋገጡን በይፋ ብታውጅም በተግባር ግን ውስንነቶች ይስተዋላሉ። በዚህም አንዳንድ ሚዲያዎችና ባለሙያዎች አገራቸውን ትተው እስከመሰደድ ደርሰው ነበር።

ሕገ-መንግሥታችን ዜጎች የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነት እና እንዲሁም በሕጋዊ መንገድ  የመደራጀት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ዜጎች በአገራቸው ውስጥ በነፃነት የመዘወዋወር፣ ሃብት የማፍራት መብት እንዳላቸው፣ በፈለጉ ጊዜ ከአገር ወጥተው የመመለስ መብታቸው የተከበረ መሆኑን ሕገ-መንግሥቱ ያስቀምጣል። ይሁንና በዚህ ላይ የምናስተውላቸው ህጸጾች ቀላል አይደሉም። በርካታ ንጹሃን ዜጎች ያለሃጢያታቸው በተለያዩ ቦታዎች ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣ ንብረታቸው ተዘርፋል፣ በመቶ ሺዎች ተፈናቅለዋል፣ በአጠቃላይ  በርታ መጥፎ ነገሮች ተከስተዋል። ይህን ሁኔታ በደንብ መፈተሽ የሚገባ ይመስለኛል። በቅርቡ እንደተመለከትነው ውጣልኝ፣ ሂድልኝ ማለት ለአንዱ እንደመብት የሚታይበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር በቅርብ የምናስታውሰው ጉዳይ ነው።

የህዝቦች ዴሞክራሲያዊ  መብት የሆነው የመምረጥና የመመረጥ መብትም  ህገመንግስታዊ ዋስትና አለው። በዚህም ከነጉድለቱም ቢሆን አገራችን  አምስት አገራዊና አካባቢያዊ ምርጫዎችን አካሂዳለች። ህዝቦች በመረጧቸው ተወካዮቻቸው መተዳደር ችለዋል። የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እስከመወሰን የሚያስችል መብት መጎናጸፍ የቻሉት በዚህ ህገመንግስት ነው። የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት ከመጎናጸፋቸው ባሻገር በፌዴራል መንግስቱ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብታቸው ተረጋግጧል። በዚህ ረገድ ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  በሁሉም የፌዴራል የስልጣን እርከን እኩል ውክልና እንዲያገኙ ስለአገራችው በእኩልነት የሚወስኑበት ሁኔታ ተመቻችቷል።

በአጠቃላይ ሕገ-መንግሥቱ የአገራችን ዜጎች ዴሞከራሲያዊ መብቶች ተከብረው ዜጎች በነፃነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር መሠረት ጥሏል። በሃይማኖት ምክንያት የሚደርሱ ተፅዕኖዎች ተወግደው ሁሉም ሃይማኖቶች በእኩልነት እየተስተናገዱ ይገኛሉ። ዛሬ በአገራችን መንግስታዊ ሃይማኖትም ሆነ ሃይማኖታዊ መንግስት የለም። ይህ በመሆኑም ሃይማኖቶች ሁሉ ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባት አገር መመስረት ተችሏል። ይሁንና በሁለቱ ሃይማኖቶች (በክርስትናና እስልምና) ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል ሴክቶች አገራችንን ሲያምሷት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ጋር  ያደረጉት ውይይት ይበል የሚያሰኝ ነው። በክርስትናም በኩል የሚስተዋሉ ልዩነቶች እንዲቀረፉ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። አሁን ላይ አገራችን የሚያዋጣት መደመርና መደመር ብቻ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy