የቅናሹ አንድምታ
ዳዊት ምትኩ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን የውጭ ምንዛሬን አስመልክተው በሰጡት መግለጫና ለህብረተሰቡም ባስተላለፉት ጥሪ፣ የአገራችን የዶላር ክምችት እየጨመረ በአንፃሩም በጥቁር ገበያ ላይ ያለው የውጭ ምንዛሬ ዋጋ እየቀነሰ መጥቷል። ይሀም በርካታ የህብረተሰብ ክፍል ዶላርን በጥቁር ገበያ ከመመንዘር በመታቀብ ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገባ አድርጎታል።
መረጃዎች እንዳመለከቱት ዶክተር አብይ በወሰዱት የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንቅስቃሴዎች በጥቁር የውጭ ምንዛሬ ገበያ የዶላር የምንዛሬ ዋጋ ከሰሞኑ አሽቆልቁሏል። በአሁኑ ወቅትም በጥቁር የውጭ ምንዛሬ ገበያ ያለው የውጭ ምንዛሬ ተመን ወደ ባንኮች ተመን እየተጠጋ ነው።
ምንም እንኳን ባለፉት ጊዜያት የአገሪቱ አምራች ኢንዱስትሪ የሚጠበቅበትን የውጭ ምንዛሬ ማምጣት ተስኖት አለመረጋጋቱም ተጨምሮበት የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ከፍተኛ የሚባል ደረጃም ላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ህብረተሰቡ ከዶክተር አብይ በቀረበለት ጥሪ መሰረት በእጁ ያለውን ዶላር በህጋዊ መንገድ ባንክ ወስዶ በመመንዘሩ የባንክና የጥቁር ገቢታው ዋጋ መሳ ለመሳ ሊሆን ችሏል።
ቀደም ሲል ምን እንኳን ዘላቂ መፍትሄ አይሁን እንጂ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሁለት ቢሊየን ዶላር በኢትዮጵያ ለሚደረግ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲሁም አንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማቃለል በቀጥታ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ማድረጓ እጥረቱን አስታግሶታል። ይህም በጥቁር የውጭ ምንዛሬ ገበያ የዶላር ምንዛሬ ዋጋ መቀነስ ላይ በተወሰነ ደረጃ ለውጥ ማምጣቱ አይዘነጋም።
ከሁሉም በላይ ዶክተር አብይ አህመድ ፓርላማ በመገኘት “አዳዲስ ዶላሮች እየገቡ ስለሆነ በጥቁር ገበያ ዶላር የያዛችሁ ሰዎች በአፋጣኝ በባንክ ገበያ የማትለውጡት ከሆነ እናንተንም ችግር ውስጥ ስለሚያስገባ ብታስቡበት” በሚል መልክት ማስተላለፋቸውና ህብረተሰቡም ይህንኑ ሰምቶ ወደ ህጋዊ መንገድ መመለሱ የባንክና የጥቁር ገያ የዶላር ምንዛሬ መሳ ለመሳ ሆኗል ማለት ይቻላል። በዚህም አንድ የአሜሪካ ዶላር በጥቁር የውጭ ምንዛሬ ገበያ ከ28 ብር እስከ 30 ብር ድረስ ወርዶ ወደ ባንኮች ተመን ተጠግቷል።
እርግጥ የጥቁር የውጭ ምንዛሬ ገበያ ሁኔታን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎችና ባለሙያዎች በጥቁር የውጭ ምንዛሬ ገበያ እንዲዳከም ምክንያት የሆነው በአገሪቱ እየታየ ያለው ለውጥ መሆኑ ግልፅ ነው። ይህ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የህብረተሰቡ የማያቋርጥ ድጋፍ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ኢኮኖሚውን በመደገፍ የዋጋ ንረትን ስለሚቀንስ ነው።
የዶላር የምንዛሬ ዋጋ መቀነስ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው እንድምታ ግልፅ ነው። በተለይ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ውጭ የሚገቡ የዋጋ ንረትን በመከላከል የኑሮ ሁኔታን ያረጋጋል። ለምሳሌ ነጋዴው በከፍተኛ የምንዛሬ መጠን በዶላር ገዝቶ የሚያመጣው ሸቀጥ በአገር ውስጥ ገበያ ሲሸጥ በዋጋ ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ ነው።
ይህን ጫና ለመቋቋም ታዲያ የዶላር ዋጋን መቀነስ እጅግ ያስፈልጋል። ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት በዶላር ምንዛሬ ላይ በመጣው ለውጥ ሳቢያ በርካታ ግለሰቦች በህጋዊ መንገድ በባንክ እየመነዘሩ ናቸው። ይህ ህጋዊነትም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ህብረተሰቡ ከዚህ አኳያ የህጋዊነትን መንገድ በመከተል መንግስት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚያደርጋቸውን ጥረቶች መደገፍ አለበት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ምጣኔ ሃብታችን በፍጥነት እያደገ ነው። ለፓርላማ እንደተናገሩት ኢኮኖሚያችን 9 እና በ10 በመቶ መካከል ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ አሁን ባለንበት ሁኔታ በኤክስፖርትና በኢምፖርት መካከል ክፍተት መኖሩ ግልፅ ነው።
ባለፉት ዓመታት የታየው ደካማ የኤክስፖርት አፈፃፀም አስተማማኝ የውጪ ምንዛሬ ግኝት በማረጋገጥ ለፈጣን ዕድገታችን አስፈላጊ የሆኑ መሣሪያዎችና ዕቃዎች ከውጪ በማስገባት ዕድገታችን ለማስቀጠል አና ከውጪ ብድርና ዕርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅ ትልቅ ማነቆ ሆኗል ማለት ይቻላል።
በግሉ ዘርፍ የሚካሄዱ ሰፋፊ የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በመንግስት የሚካሄዱ ትልልቅ የመሰረተ ልማት፣ የኢንዱስትሪና የማህበራዊ ልማት ኘሮግራሞች ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የሚፈልጉ በመሆናቸው የኤክስፖርት መዳከም እየተፋጠነ ያለውን ልማት ሊያደናቅፍ ይችላል።
እርግጥ ይህ የሆነው ለኤክስፖርት ገቢ አፈፃፀም መዳከም ዋናው ምክንያት የማምረት አቅማችን በሚፈለገው ደረጃ አለማደግና በዚህም ምክንያት የማኑፋክቸሪንግና የግብርና ሸቀጦች በከፍተኛ መጠን፣ በተለያየ ዓይነትና በከፍተኛ የጥራት ደረጃ እንዲቀርቡ ባለመደረጋቸው ነው።
ባለፉት ዓመታትበሁሉም ሰብሎች ኤክስፖርት የተደረገው መጠን ይደረጋል ተብሎ ከታቀደው በእጅጉ ያነሰና በማኑፋክቸሪንግ ነባሮች ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ አቅማቸውና በጥራት እንዲያመርቱና በተጨማሪም አዳዲስ ኢንቨስትመንትን በስፋትና በጥራት መልምሎ ወደ ሥራ ማስገባት በታቀደው ልክ መራመድ አልቻለም። ይህም ለኤክስፖርት የማምረት አቅማችን ዝቅተኛነት ምክንያት ሆኗል።
በዚህ ላይ ደግሞ ህገ ወጥ የዶላር ዝውውር የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ክምችት በእጅጉ ጎድቶታል። ኢትዮጵያ አገራቸው ያልሆነች ያህል ኢኮኖሚውን ለማዳከም የሚሰሩ አካላት መኖራቸውም ግልፅ እየሆነ መጥቷል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ፖሊስ ከአገር ሊወጣ ሲል የያዘው 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ዶላር የዚህ ማረጋገጫ ይመስለኛል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አቶ ዘይኑ ጀማል ሰሞኑን እንደገለፁት፣ ጥናትን መሰረት በማድረግ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የኦሮሚያ እና አዲስ አበባ ፖሊስ በጋራ ባካሄዱት ዘመቻ ይህን ያህል ዶላር በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።
በህገ ወጥ መንገድ ተይዞ የተገኘውም ዶላር ሆነ ተብሎ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማዳከም የሚፈፀም ሴራ መሆኑ ግልፅ ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ የአገርን ኢኮኖሚ ለማዳከም የሚጥሩ ሃይሎችን እንደተለመደው ከፖሊስ ጋር በመተባበር ሊታገላቸውና በህግ ጥላ ስር ሊያውላቸው ይገባል።
ታዲያ ይህን መሰሉ ዘመቻ በቀጣዩቹ ሳምንታት እንደሚካሄድ ፖሊስ ገልጿል። በመሆኑም ህብረተሰቡ የራሱ ንብረት የሆነውን የውጭ ገንዘብ በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ለማስወጣት በሚሞክሩ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል። ምክንያቱም መንግስት በውጭ ምንዛሬ ላይ በወሰዳቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ምክንያት የዶላር የጥቁር ገበያ ዋጋ መቀነሱ ህብረተሰቡ በዋጋ ንረት እንዳይጎዳ ስለሚያደርግ ነው።