የኢትዮጵያና ኤርትራ ዕርቀ-ሰላም መሪዎች በህዝቦች መካከል የፍቅርና መቀራረብ ድልድይ እንዲገነቡ ጠንካራ መልዕክት ያስተላለፈ ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት ተጠሪ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተጠሪ አሁና ኢዚያኮንዋ ኦኖች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ዕርቀ-ሰላም ለአፍሪካና ለመላው ዓለም ተምሳሌት ነው።
“መሪዎች በህዝቦች መካከል የጸብ ግንብ ሳይሆን የፍቅርና መቀራረብ ድልድይ እንዲገነቡ ጠንካራ መልዕክት ያስተላለፈ ነው” ብለዋል።
በሁለቱ ወንድማማችና ጎረቤት አገሮች መካከል የቆየው አለመስማማት እንዲያበቃ ልዩነቶችን በማጥበብ አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ይበልጥ ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዓለማችን መሪዎች በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በአገራት መካከል ልዩነትን የሚያሰፋ ግንብ ሳይሆን ፍቅርና መቀራረብን መገንባትን ሰላም ማስፈን እንደሚገባቸው ነው ያመለከቱት።
ሁለቱ አገራት በመካከላቸው የተጀመረው አስደናቂ የሰላም ስምምነት ለአፍሪካውያን ብሎም የመላው ዓለም ሕዝብን የሚያስተምርና አንድ እርምጃ ወደፊት የሚወስድ ታሪካዊ ክስተት ነው ብለዋል።
የዕርቀ-ሰላም ሂደቱ “ለኔም እንደ አፍሪካዊት የሚያኮራ ክስተት ነው፣ ለዓለምም ትምህርት የሰጠ ነው” በማለት ስሜታቸውን ገልፀዋል።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የተጀመረው ዕርቀ ሰላም በስኬት እንዲጠናቀቅ ድጋፉን ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል።
“የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ዘላቂ የሰላም ሂደቱን ለመደገፍ ይፈልጋል” ያሉት ተጠሪዋ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር የመንገድና የመሰረተ ልማት ስራዎችን መደገፍ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የጦርነት ስጋት በነገሰበትና ሰላም በሌለበት አገራት ሊገናኙና ያላቸውን ዕድል ተጠቅመው በጋራ ለማደግ የማይችሉ ሲሆን የሁለቱም አገራት እርምጃ መሰል ችግሮችን ለመፍታት በአስተማሪነት የሚወሰድ ነው ብለውታል።
ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉና ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች ደህንነታቸው ተጠብቆ መመላለስ እንዲችሉ በጥንቃቄ ማስተባበር አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ባለፉት ጥቂት ወራት የወሰዱት ቁርጠኛ የአመራር እርምጃና የሰላም ጥሪ በኤርትራ መንግስት በኩል ተቀባይነት በማግኘቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማድረግ ተችሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአስመራ ባደረጉት ጉብኝትም የወደብ፣ የአየር ትራንስፖርትና በሌሎችም ዘርፎች ግንኙነት ለመፍጠር የተስማሙ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ መደበኛ በረራ ጀምሯል።
ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አዲስ አበባን በጎበኙበት ወቅትም ተዘግቶ የነበረው የኤርትራ ኤምባሲ ተከፍቶ ሥራ የጀመረ ሲሆን ሁለቱም አገራት በየኤምባሲዎቻቸው አምባሳደር ሰይመዋል።