Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የድንበር ጉዳዮች ዕረፍት ይነሳሉ፤ማሰብ ይፈልጋሉ

0 478

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የድንበር ጉዳዮች

ዕረፍት ይነሳሉ፤ማሰብ ይፈልጋሉ

ክፍል ሁለት

አሜን ተፈሪ

ባለፈው ሣምንት በሰሜን ምዕራብ እና በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ሁለት የጠረፍ ከተሞች በተለያዩ መነሾዎች የተከሰቱት ጠንከር ያሉ ግጭቶች በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ማስከተላቸው ሰምተናል፡፡ እነዚህ ግጭቶች የተከሰቱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀው የጠረፍ ከተሞችን ችግሮች የመዳሰስ እና የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን የመቀመር  ዓላማ ይዞ የተካሄደው አውደ ጥናት በተጠናቀቀ ማግስት ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ሞያሌ፣ ቋራ እና መተማን ከመሳሰሰሉ የጠረፍ ከተሞች የመጡ ሰዎች ተሳታፊዎች በዚሁ ጉባዔው ተሳታፊ እንደነበሩ እና ከአዲስ አበባ ወደ መጡበት በመመለስ ሳይ ሳሉ ነበር ግጭቶቹ ተከሰቱት — የመተማው ግጭት ሰኔ 27 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሞያሌው ደግሞ በማግስቱ ሰኔ 28 2010 ዓ.ም፡፡ በቋራ እና መተማ አካባቢ የተከሰተው ግጭት በመከላከያ ኃይል ጣልቃ ገብነት ቢቆምም፣ ግጭቱን ለዘለቄታው ለመፍታት እንዲያስችል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር የላኩትን መልዕክት መላካቸው ታውቋል፡፡

ከቋራ እና መተማው ግጭት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ውጥረት ተለይቷት በማታውቀው የኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ የተከሰተው ጎሣን መሠረት ያደረገ ግጭት መሆኑን እና የመተማው ደግሞ ከእርሻ መሬት ጋር የተያያዘ እንደሆነ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የጠቀሱ ሲሆን፤ ከሁለቱ ከተሞች የመጡት የጉባዔው ተሳታፊዎች በስብሰባው ላይ ከሰጡት አስተያየት መረዳት እንደሚቻለው ግጭቶች በተደጋጋሚ  ይከሰታሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ ከሁለት ወር በፊት ሚያዚያ 28/2010 ዓም ተፈጥሮ በነበረ የጎሣ ግጭትበርካታ ሰዎችን ለጉዳት የዳረገ እና ንብረትም ያወደመ ግጭት መከሰቱን የሚታወስ ሲሆን፤ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ሰኔ 28/2010 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ዳግም ባገረሸው ጎሣን መሠረት ባደረገ ግጭት ከሁለቱም ወገን ሰዎች መሞታቸውን እና ከመሐል ሐገር ወደ ሞያሌ የሄዱ ዘጠኝ የጭነት መኪኖችም መጋየታቸውንም አመልክተዋል፡፡

በሞያሌ በሚገኘው የፌደራል ገቢዎች እና ጉምሩክ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ላይ ጉዳት መድረሱን የጠቀሱት ምንጮቻችን፤ በገሪ እና ቦረና ጎሣ አባላት መካከል የተከሰተውን ይህን ግጭት ለማብረድ የጸጥታ ኃይሎች ጥረት ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ግጭቱ በዘመናዊ መሣሪያ የተደገፈ በመሆኑ ጉዳቱን ከፍ እንደሚያደርገው እና የጸጥታ ኃይሎች ግጭቱን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ጥረት አስቸጋሪ እንደሚያደርገውም በዚሁ ስብሰባ ያገኘኋቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸውልኛል፡፡

በኦሮሚያ እና በኢትዮ-ሶማሌ ክልል ለሥር ለሚተዳደሩ ሁለት ወረዳዎች መቀመጫ በመሆን በምታገለገልው እና የአንዳንድ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች መቀመጫ በሆነችው የሞያሌ ከተማ፤ ከሁለት ወራት በፊት ከአስፋልት ግራ እና ቀኝ በመሆን በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ  በርካታ የከተማው ነዋሪዎች ለአካል ጉዳት እና ለሞት መዳረጋቸውን እንዲሁም ንብረት መውደሙን ያስታወሱት እነዚሁ ምንጮች፤ ከተማዋ ዘወትር በውጥረት የምትኖር እና ባልረባ ምክንያት ግጭት እንደሚቀሰቀስ፤ የሁለቱ ጎሣ አባላት በመበቃቀል መንፈስ እንደሚጠቃቁ፤ የከብት ዝርፊያ እንደሚካሄድ እና በከተማው በሰፊው በሚታዩ የሞተር ሳይክሎች የታገዘ የሰዎች ጠለፋ አንደሚፈጸም ተናግረዋል፡፡

በአንድ የአስፋልት መንገድ ግራ እና ቀኝ  የተለያይተው የሚገኙት የሁለቱ መስተዳድሮች የሚታዘዙ የጸጥታ ኃይሎች  በግጭቱ ተሳታፊ እንደሚሆኑ የሚጠቅሱት ምንጮቻችን፤ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል እና የኦሮሚያ ክልል አድማ በታኝ ኃይል አባላት እንዲሁም የቀበሌ መስተዳድር ሚሊሻዎችን በስም ይጠቅሳሉ፡፡ ሰኔ 28 በገሪ ጎሣ አባላት (ሶማሌ) እና በቦረና ጎሣ አባላት (አሮሞ) በተከሰተው ግጭት ከሁለቱም ወገን ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል፤ ሱዳንን ከኢትዮጵያ በሚያዋስነው የምዕራብ ጎንደር ዞን፣ መተማ አካባቢ በሚገኝ የእርሻ መሬት ይገባኛል ጥያቄ ለግጭቱ ምክንያት መሆኑን የጠቀሱት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘላለም ልጃለም ‹‹ሱዳኖች በኢትዮጵያ መሬት ላይ የሚያነሱት የይገባኛል ትክክል አይደለም›› ማለታቸውን የአማራ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡

‹‹የእርሻ ስራ በሚያከውኑ የአካባቢው የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ላይ ትንኮሳ በመፈጸማቸው ምክንያት ግጭቱ ተከስቷል›› ያሉት ኃላፊው፤ የአካባቢው አርሶ አሮችም የመከላከል አጸፋ መውሰዳቸውን እና አሁን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በቋራ እና መተማ ጥበቃ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የዞኑ አስተዳዳሪ እና አርሶ አደሮች እንደተናገሩት አሁን ላይ ግጭቱ የተረጋጋ ቢመስልም፤  በሱዳን ወታደሮች ትንኮሳ ምክንያት በአካባቢው ባሉ ሌሎቹ የኢትዮጵያ መሬቶች ላይ የእርሻ ስራ ማከናወን አልተቻለም ብለዋል፡፡

ከአማራ ብዙሃን መገናኛ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክት፤ በግጭቱ ምክንያት በመተማ ደለሎ በኩል ከሚገኝ የሱዳን ጦር አንድ የሱዳን ሻለቃ አመራር ህይወቱ አልፏል፡፡ በቋራ ነፍስ ገበያ በኩል በተፈጠረው ግጭትም 7 የሱዳን ወታደሮች መሞታቸውን እና 2 መኪናዎችን  እና 7 የጦር መሳሪያዎችም መማረካቸውን አቶ ዘላለም ተናግረዋል ያለው የአማራ መገናኛ ብዙሃን፤ ሶስት የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች እና ሁለት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ህይወታቸው ማለፉን፤ 6 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል መግባታቸውን አመልክቷል፡፡ ከነዚህም መካከል ሁለቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ናቸው፡፡ ለጣምራ የጸጥታ ቁጥጥር በሚል በአካባቢው የሰፈረው የሱዳን ጦር በተለያዩ ጊዜያት ትንኮሳ እንደሚፈጽም የአካባቢው ነዋሪዎች እና ዋና አስተዳሪው አስረድተዋል፡፡ በተደጋጋሚ በሰላማዊ መንገድ ቦታውን ለቀው እንዲወጡ ጥረት ቢደረግም ፈቃደኛ አለመሆናቸውንም አመለክተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በሁለቱ አገሮች ድንበር አካባቢ የሚነሱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ መሰራት እንደሚያስፈልግ የሚገልጽ መልዕክት የያዘ ደብዳቤ ከኢትዮጵያው ጠ/ሚ ሚኒስትር ደረሳቸው፤ የሱዳን ፕሬዚዳንት አማር ሀሰን አል በሽር እንዲህ ዓይነት ግጭት የሁለቱን አገሮች ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እንደማይጎዳው እና ሰዳን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር አገራቸው እንደምትሠራ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በበኩላቸው፤ ሰሞኑን በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር አከባቢ በአርሶ አደሮች የተፈጠረው ግጭት አዲስ እንዳልሆነ እና ክረምት፤  በመጣ ቁጥር የሚከሰት በመሆኑ፤ ይህን ችግር ለመፍታት ሁለቱ አገሮች ይበልጥ መሥራት እንዳለባቸው የገለጹ ሲሆን፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከሱዳኑ አቻቸው አል ዲርዲሪ መሐመድ አህመድ ጋር ተገናኝተው በተወያዩ ጊዜ፣ በሁለቱ አገሮች ድንበር አካባቢ የሚነሱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡

ሰኔ 23 እና 24/2010 ዓ.ም የተካሄደው እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀው ገባዔ እንዲህ ባሉ ድንበር አካባቢ ችግሮች ነው፡፡ በቅርቡ ጠ/ሚ አቢይ አህመድ ለፓርላማ እንደተናገሩት የአፍሪካ ሐገራት ድንበሮች እቲፊሻል እና የተወሳሰበ ችግር የሚታይባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ በጠረፍ አካባቢ ያሉ መንደሮች እና ማህበረሰቦች ከፍተኛ ጫና የሚፈጥር የተጠላለፈ ህይወት የሚመሩ ናቸው፡፡ አንድ ቀን በዓይኑ አይቶት ወይም በእግሩ ረግጦት የማያውቀውን አካባቢ በእርሳስ እያሰመረ እንደ ፈቀደው ካርታ እየሰራ ቅኝ ገዢ በፈጠረው ድንበር ለመኖር የተገደዱ ናቸው፡፡ ይህም ካርታ የአፍሪካ ሐገራት ድንበር ሆኖ ጸና፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ ሐገራት ድንበሮች፤ በወታደራዊ ቁርቋሶዎች፤ በከብት ዘረፋ፤ በሽብርተኝነት፤ በመገንጠል እንቅስቃሴ፤ ኮንትሮባንድ ንግድ፤ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፤ ግዛት በማስፋፋት ጥረት እና በገበሬዎች የአመጽ እንቅስቃሴ የሚታመስ አካባቢ ነው፡፡

ከፍ ሲል የተጠቀሱት ችግሮች በአፍሪካ የድንበር አካባቢዎች ዘወትር የሚስተዋሉ ናቸው፡፡ ሆኖም የድንበር ችግር በአፍሪካ ሐገሮች የተወሰነ አይደለም፡፡ የሩሲያ እና የዩክሬን ሁኔታ ለዚህ ማስረጃ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚወሳሰብ ችግር  የሚታይባቸው የአፍሪካ ድንበሮች፤ በጥበብ ካልተያዙ በቀር፤ ጊዜ ጠብቆ ሊፈነዳ የሚችል ችግር የታቀፉ ናቸው፡፡

የአፍሪካ አህጉር መንግስታት ከቅኝ ግዛት ዘመን በፊት ድንበራቸውን ለመወሰን ባደረጉት ጥረት ከሞላ ጎደል ትክክለኛ ድንበር ወይም የታወቀ ወሰን ፈጥረው ነበር፡፡ ሆኖም ‹‹ከበርሊን ኮንፈረንስ›› በኋላ ሁኔታዎች በእጅጉ ተለወጡ፡፡ ቅኝ ገዢዎችም ድንበሩን እንዳሻቸው አደረጉት፡፡

የበርሊን ኮንፈረንስ የአፍሪካን ድንበር ለመወሰን ጥረት የተደረገበት አይደለም፡፡ ድንበሩም በዘፈቀደ ሲሰመር የነበረ ነው፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ በርካታ የአፍሪካ ሐገራት በድንበር ጉዳይ ተፋጥጠው ይገኛሉ፡፡ በአህጉሪቱ ወደ መቶ ገደማ የሚሆኑ የድንበር ይገባኛል ውዝግቦች አሉ፡፡  ከእነዚህ ድንበሮች አንደ በኢትዮ-ኤርትራ መካከል ያለው እና በሺዎች ለሚቆጠሩ የሁለቱ ሐገራት ዜጎች ህይወት መጥፋት መንስዔ የሆነው የባድመ ውዝግብ አንዱ ነው፡፡ ለምሳሌ ኬንያ፤ ከሰሜን ሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን እንዲሁም ከዩጋንዳ ጋር የድንበር ውዝግብ አላት፡፡ በደቡብ፣ በሰሜን፣ በምሥራቅ፣ በምዕራብ ተመሳሳይ ችግር አለ፡፡ ይህን ችግር በመረዳት የአፍሪካ መንግስታት በአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) በኩል የቅኝ አገዛዝ ድንበር እንዲጸና ውሳኔ አሳለፉ፡፡ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ባትገዛም ከጎበረቤቶቿ ጋር ያላት ድንበር በቅኝ ግዛት ኃይሎች የተወሰነ ነው፡፡ ይህም ውስብስብ የድንበር አካባቢ ‹ዳይናሚክስ›› እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy