Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

  የግብርናው  መዘመን እንጂ የነዳጅ መገኘት ምጣኔ ሀብቱን አይመራም!

0 330

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

  የግብርናው  መዘመን እንጂ የነዳጅ መገኘት ምጣኔ ሀብቱን አይመራም!

ይልቃል ፍርዱ

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚው ዋልታና ማገር  የግብርናው ዘርፍ ነው፡፡ይሄንን ለዘመናት ከትውልድ ትውልድ ሲሰራበት የኖረውን ኃላቀር የግብርና አሰራር ከመሰረቱ ለመለወጥና ዘመናዊ ለማድረግ መንግሰት በሀገር ደረጃ በሁሉም ክልሎች ሰፊ ስራዎችን ሰርቷል፡፡እየሰራም ነው፡፡

አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን በያለበት በማስተማርና አጫጭር ስልጠናዎች እንዲያገኝ በማድረግ ዘመናዊ እርሻን እንዲከተል፣ ማዳበሪያዎችን እንዲጠቀም፣ እንዴት በትንሽ መሬት ላይ ትርፋማ ሆኖ ሰፊ ምርት ማምረት እንደሚችል፣ የውሀ አጠቃቀምን በማሻሻል ከሁለት ጊዜ በላይ ማምረት እንዲችል በማድረግ እና በከፍተኛ ዝናብና ጎርፍ እየተሸረሸረ የሚሄደውን አፈር ለመታደግ በባለሙያዎች ሥልጠና እየታገዘ የእርከን ስራዎችን በሰፊው እንዲሰራ በመደረጉ የተነሳ በመሬት ላይና በሕይወቱ ላይ ተጨባጭ ለውጦችን  ማስመዝገብ ችሎሏል፡፡

ግብርናችንን ከማሳደግ አንጻር የመስኖ አጠቃቀምን ለአርሶ አደሩ በስፋት በማስተማር  ረገድም ሰፊ ሀገራዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡ በየአመቱ በመንግስት በኩል በተያዘ እቅድ እና በማህበረሰቡ ተሳትፎ በሚከናወነው ችግኝ የማፍላትና   የመትከል ስራ ሰፊ የተጎዳ የመሬት ክፍል በጥቂት አመታት ውስጥ በደን ተሸፍነዋል፡፡ ከባድ ዝናብ ሲዘንብ እንዴት ውኃውን አስርገው ማስቀረትና ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባቸው ባገኙት ስልጠና ውኃውን ያለብክነት መጠቀም የቻሉበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡

ለዘመናት መሬቱ በመራቆቱ ጠፍተውና ተሰደው የነበሩ የዱር አራዊትና አዕዋፋት  ጭምር ተፈጥሮ እያገገመች መምጣቷን ተከትሎ ወደ ተፈጥሮ ቦታቸው እየተመለሱ ይገኛሉ፡፡ ከግብርና ምርት አንጻር ሲታይ ሰፊ ሀገራዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡አርብቶ  አደሩ የእርሻ ስራን እንዲለምድ የተደረገው ስራ ለውጤት እየበቃ ይገኛል፡፡

ግብርናው የሀገሪቱ የኢኮኖሚ መሰረት ሁኖ የመኖሩን ያህል ዛሬም ወደ ዘመናዊ ግብርና በማሸጋገር ለሚገነቡት ቀላልና ከባድ ኢንዱስትሪዎች ግብአት በማቅረብ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ሁኖ እንዲቀጥል በሰፊው እየተሰራ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ  በጥቅም ላይ ያላዋለችው በርካታ የተፈጥሮ  ሀብት እንዳላት አያከራክርም፡፡ በጥናት በምርምር ወደፊት የሚታወቅ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ ያደረጉት  የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ የመገኘቱ ዜና ታላቅ ሀገራዊ ብስራት ሲሆን ለረጅም ዘመናት የተደከመበት የልፋት ውጤት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የነዳጅ ዘይት ፍለጋው ታሪክ ወደ 70 አመታት ያስቆጥራል፡፡ በንጉሱ፣ በደርግና በኢሕአዴግም ዘመን ፍለጋው እንደቀጠለ ነበር፡፡

የተፈጥሮ ነዳጅ ዘይት ፍለጋው ብዙ አስርት አመታትን የተሻገረ ቢሆንም አጥኚ ኩባንያዎቹ ብዙ ጥረት አድርገው የለም ብለው የሄዱበትንም ግዜ እናስታውሳለን፡፡በሌላ በኩል ፍለጋው ፍንጭ ነበረው የሚሉም አልጠፉም፡፡  ለምን የሚለው ጉዳይ ብዙ ሊያነጋግር ሊያከራክር ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ እንዳትለማ ሆን ተብሎ የተሰራ ደባና አሻጥር ነበር የሚሉም አሉ፡፡ያም ሆነ ይህ ዛሬ ላይ ውጤቱ ሀገሪቱና ሕዝቦቿ ሀሴት እንዲሰማቸው አድርጓል፡፡

ነዳጅ ዘይቱ መገኘቱ ትልቅ ብስራት ነው፡፡ነገር ግን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዛሬም ወሳኝ ሁኖ የሚቀጥለው ግብርናው እንጂ ነዳጅ ሊሆን አይችልም፡፡ የነዳጅ ዘይቱ መገኘት  ኢኮኖሚው ይበልጥ እንዲነቃቃ ተጨማሪ አጋዥ ኃይል ከመሆን ውጭ ወሳኝ ሊሆን አይችልም፡፡ ሀገራዊ ፍጆታችን በቀን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ጋሎን በመሆኑ አሁን በቀን እየወጣ ያለው 450 በርሜል ነዳጅ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ለችግሮቻችን  መቀረፍ አጋዥ ከመሆን የዘለለ አቅም የለውም፡፡

ብዙ ማልማት፣ ደረጃውን ማሳደግ፣ ሰፊ ድፍድፍና ነዳጁን የሚያጣሩ ጋኖችን መገንባት፣ የጥራት ደረጃውን ለመጠበቅ በመስኩ ኤክስፐርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቶ መስራት እና  በተጓዳኝ በዘርፉ ዜጎች በሙያው በከፍተኛ የትምህርት ደረጃ እንዲማሩና ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ በሀገሪቱ የነዳጅ ዘይት ተገኘ ማለት በአንድ ጀምበር ከድህነት ተላቀቅን ማለት አይደለም፡፡ መገኘቱ ተደማሪ አቅም መገንባት ያስችላል፡፡

በኢትዮጵያ ከነዳጁ በላይ እምቅ የተፈጥሮ ጋዝ በአለፉት አመታት መገኘት ችሏል፡፡ ይህንን ለማልማት ሰፊ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ሕብረተሰቡ ነዳጅ ተገኘ በሚለው ብቻ ስሜት የተሳሳተ ተስፋ ሊያሳድር አይገባውም፡፡ ብዙ መስራት፣ ያለንን አጎልብተን ለውጤታማነት መራመድ፣ ግብርናውን አሳድገን ወደ ዘመናዊነት በማሸጋገር የበለጠ ትርፋማ መሆን ያስችለናል፡፡ በሌሎች መስኮችም ለጀመርናቸው ሀገራዊ ታላላቅ የልማት ስራዎች ስኬታማነት መትጋትና መስራት ከድሕነት መውጫው ዋና አማራጭ ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል፡፡

በየቦታው በቢሊዮን በሚቆጠር ብድር ተጀምረው ሳይቋጩና ውጤታማ ሳይሆኑ እዳቸውን የትየለሌ የሆኑ ፕሮጀክቶች ብዙ ናቸው፡፡እነዚህን ተረባርበን በመጨረስ ስራ እንዲጀምሩ፣ ትርፋም ሆነው ገንዘብ እንዲያስገኙ፣ የሚያስችል አቅም ካልፈጠርን በስተቀር ኢኮኖሚው በምንፈልገው ፍጥነት ፈጽሞ ሊራመድ አይችልም፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ሀገሪቱ ግዙፍ በሆነ የውጭ ብድርና ጫና ውስጥ ነው የምትገኘው፡፡

ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘንድሮውን የመንግስት የስራ አፈጻጸም ሪፖርትና የቀጣዩን አመት በጀት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት የልማት ድርጅቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትክ ኃይል የበርካታ ቢሊዮኖች የብር እዳ እንዳለባቸው መጥቀሳቸው አይዘነጋም፡፡የዚህ እዳ ከፋይ ሀገሪቱ ናት፡፡

በሁሉም መስክ የተዘረጉት ፕሮጀክቶችን ሰላም ጠብቀን ትርፋማ እንዲሆኑ ቀን ከሌሊት መስራት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ እዳዎቻችንን መክፈል አያስችለንም፡፡ በሌላ በኩል  ሀገራዊ ቀውስ ውስጥ እንዳንገባ መጠንቀቅ ይገባል፡፡ በሀገሪቱ ነዳጅ መገኘቱ ታላቅ ደስታ ቢሆንም አሁን ባለንበት ደረጃ ለሀገራዊ ኢኮኖሚያችን አጋዥ እንጂ ራሱን ችሎ ወሳኝ ሊሆን አይችልም፡፡

ለዘመናት በተፈጥሮ የነዳጅ ዘይት ሀብት የኖሩት ሀገራት እንኳን ሀገራቸውን በበቂ ደረጃ ማልማትና ዜጎቻቸውን ከድሕነት ማውጣት አልቻሉም፡፡ የነዳጅ ሀብቱ መኖር ጭርሱንም ለእውቀትና ለምርምር እንዲተጉ፣ ዜጎቻቸው በእውቀት ልቀው ቴክኖሎጂውን እንዲመሩ ለማድረግ አላስቻላቸውም፡፡ዛሬም የሚጠቀሙት በውጭ  ኤክስፐርቶች እውቀት ነው፡፡ እኛ የበለጠ ትኩረት አድርን መስራት ያለብን የሰው ሀብትን በማልማት እና ከቴክኖሎጂ ጋር ቅርበትና እውቀት እንዲኖራቸው በማድረግ ላይ መሆን አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ከችግሮቻችን መውጪያ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን እንዲያፈልቁና አዳዲስ ገበያዎችን እንዲፈጥሩ ማድረግ ያስችላል፡፡

ከድፍድፍ ነዳጅ ዘይቱ የሚገኘው ገቢ በቀን ለማምረት ካለን የተመጠነ አቅም አንጻር፣ እንደገናም በአለም ገበያ ለማቅረብ አዲስና እንግዳ ከመሆናችንም ጋር ተያይዞ ብዙ መስራት የሚጠበቅብን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ማጠቃለያ

አሁን በታየው ጅምር የነዳጅ ዘይት መገኘትና ገቢው ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገትና ልማት አጋዥነቱ ለክርክር አይቀርብም፡፡ ለኢኮኖሚ እድገታችን ወሳኝና መሰረት ግን አይደለም፡፡ በተመጠነ  ደረጃ ነዳጅ ስላገኘን ብቻ ተንሰራፍቶ የኖረው ሀገራዊ የድሕነት ችግር ተራገፈ ወደሚል ቀቢጸ ተስፋ እንዳንገባ መጠንቀቅ አለብን፡፡የተጀመረውን ልማትና እድገት ለማስተጓጎል፣ በውስጥ ዘላቂነት ያለው ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፣ የተጀመሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ስራ እንዳይገቡ እና ትርፋማ እንዳይሆኑ የሚሰ’ሩ የኢኮኖሚ ደባዎችና ሴራዎችን በማምከን የነገን ሀገራዊ የስኬት ጉዞ የተሻለ ለማድረግ ሁሉም ዜጋ መረባረብ ይጠበቅበታል፡፡ በሀገሪቱ የነዳጅ ዘይት መገኘቱ ከረጅም ጊዜ አኳያ ተስፋ ሰጪ ሊሆን ይችላል፡፡አሁን የሚስተዋለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ አሁኑኑ መፍትሔ አይሆንም፡፡አንዳንዶች ዛሬውኑ የሀገሪቱ ችግሮች ሁሉ መፍትሔና እልባት ያገኙ የሚመስላቸው የዋሆችን እያስተዋልን ነው፡፡ በአግባቡ ካለመረዳት የተፈጠሩ የግንዛቤ ማጣት ችግሮች ናቸው፡፡ሊታረም የሚገባ አስተሳሰብ ነው፡፡  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy