Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ይህ ሰው ዕውነትም ነብይ ይሆኑ እንዴ?

0 579

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ይህ ሰው ዕውነትም ነብይ ይሆኑ እንዴ?

እዩዔል ወልደሃና

ወዳጆቼ እኔ በነብይም በወልይም የማምን ሰው አልነበርኩም። ይሁንና አሁን ላይ የማስተውላቸው ነገሮች አግራሞትን የጫሩብኝ  ጀምረዋል። ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ አንድ መቶ ቀናት ሞላቸው። በዚህ አጭር የስልጣን ጊዜያቸው ያከናወኗቸውን  ተግባራት በቅን ልቦና ለተመለከተው እጅግ አስገራሚ ነው። የለውጥ አደናቃፊዎች ከዚህም ከዚያም እየተጓተቷቸው ባሉበት ውቀት እኚህ ሰው ህዝብ የፈለገውን  ህዝብ የተጠማውን ለውጥ ማራመድ ችለዋል።

አንድ ወዳጄ እንደህ ሲል አጫወተኝ እኚህን ሰው አለማድነቅ ከቶ አይቻልም። ከችሎታቸው እስከ  ደም ግባታቸው፤ ከአገር መውደድ እስከ ቅንነታቸው ከትምህርታቸው እስከ ክህሎታቸው ወዘተ በሁሉም ነገር ምልዑ የሚባሉ ናቸው።  አንድ ወዳጄ እስኪ በየትኛው ድክመታቸው ላሳንሳቸው? ሲል ጥያቄ አዘል አስተያየቱን አጋራኝ። ዕውነት ነው። እኚህ ሰው ይህ እንከን አለባቸው ለማለት የሚያስደፍር አንድም ምክንያት አጣሁባቸው። አረናንተ ሆዬ እንዲህ ያለ  ሰውም እንዲህ ያለ መሪም አለ ለካ? እኚህ ሰው በዚህች ከሶስት ወር ብዙም ባልዘለለ የስልጣን ዕድሜያቸው ያከናወኗቸውን አንዳንድ ጉዳዮች እኔ በመሰለኝ መልኩ ላካፍላችሁ። የእኔ አስተሳሰብ ይጋባባችሁ እንደሆን እስኪ አንድ ሁለቱን ነገር ላንሳላችሁ።  

እኚህ ሰው ወደ ስልጣን የመጡበት ወቅት በሁሉም ረገድ አገራችን እጅግ ፈታኝ የሆኑ ጉዳዮች ውስጥ የነበረችበት  ወቅት ነበር። መንግስት የህግ የበላይነትን ማስፈን ተስኖት ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የተገደደበት፣ ጎጠኝነት የገነገነበት፣ ስርዓት አልበኝነት የነገሰበት ወቅት ነበር።  ዜጎች ያለምንም ሃጥያታቸው የሚገደሉበት፣ የሚደበደቡበት፣ ንብረታቸው የሚዘረፍበት ወቅትም ነበር። የአገሪቱ ኤኮኖሚ የመጨረሻው እስትንፋሱ ላይ የደረሰበት በተለይ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ጫፍ የደረሰበት፣ የኢህአዴግ ተደማጭነቱ በዓባላቱ ጭምር  እጅግ የቀነሰበት የበላይ አመራሩ እርስ በርስ መደማመጥ ተስኖት በየሚዲያው ሲዘራጠጥ የሚውልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።

እኚህ ሰው ገና ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት  ያደረጉት ንግግር በህዝቡ ላይ የነበረውን የጭንቀት መንፈስ ከመግፈፍ አንጻር ከፍተኛ ሚና ነበረው። በዚህ ንግግራቸው ስለአንድነት፣  ስለዴሞክራሲና የሃሳብ ብዝሃነት ከሁሉም በላይ ደግሞ ባለፉት 27 ዓመታት ብዙም ትኩረት ስለማይሰጠው ኢትዮጵያዊነት መሆኑ የህዝብን ቀልብ በቀላሉ መግዛት አስቻላቸው።  “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን” ያሏት ንግግር በህዝቡ ውስጥ ተስፋን እንዲፈነጥቅ አድርጓል። ከዚህም ባሻገር በተዘዋወሩባቸው የአገሪቱ ክፍሎች  ሁሉ የየአካባቢውን ቋንቋ በመቀላቀል፣ የአካባቢውን ባህል በመምሰል፣ የህብረተሰቡን ትክክለኛ ፍላጎት በማንጸባረቅ፣ የቸኩና የተሰለቹ ቃላትን ባለመጠቀም፣ ማንም የፈለገውን ሃሳብ በነጻነት  እንዲንሸራሸር በመፍቀድ በህዝብ ልብ ውስጥ የበለጠ ጠልቀው መግባት ቻሉ። ዛሬ እሳቸውን አለማድነቅ ከቶ አይቻልም። ከህጻን እስከ አዛውንት፣ ከምሁር እስከ አልተማረው፣ ከሃብታም እስከ ደሃው፣ ወዘተ እኚህን ሰው  መርሳት ወይም ስለእርሳቸው አለማሰብ ከቶ የማይቻልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።

የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና  ይቅር ባይነትን ለማንገስ የተለያዩ እርምጃዎችን  ወስደዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማንሳት፣ በኢህአዴግ የማይወደደውን ህዝብን በይፋ  ይቅርታ መጠየቅ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ማሞገስና አገራቸውን  እንዲረዱ ጥያቄ ማቅረብ፣ በፖለቲካ ሳቢያ የታሰሩ በርካታ እስረኞችን መፍታት፣ በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ  ድርጅቶችን ከአሸባሪ ሊስት ውስጥ ማስወጣት፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተወዳዳሪነትና በአጋርነት አጠራር ‘ተፎካካሪ’ እያሉ መጥራትና ተባብሮ ለመስራት ፍቃደኛ መሆን፣  በውጭ የሚገኙ ቀድሞ ጽንፈኛ ተብለው ይጠሩ የነበሩ ሚዲያዎችን ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረብ፣ በርካታ ድረገፆችንና ጦማሮችን በነጻነት እንዲሰሩ ማድረግ መቻላቸው በአገር ውስጥ  ለዴሞክራሲ መጎልበት ያላቸውን ጽኑ ዕምነት አሳይተዋል። ይህን የለውጥ ፍላጎታቸውን የተመለከተው በውስጥም በውጭም ያሉ ግለሰቦችና ድርጅቶችም ሳይቀሩ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከለውጡ ጎን እንዲቆሙ አድርጓቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድብቅነቱ  ይታወቅ የነበረውን የኢህአዴግ አሰራር  ለህዝብ ይፋ እንዲወጣ በማድረግ በህዝብ  ዘንድ ያላቸውን አመኔታ ማጠናከር ከመቻላቸውም በላይ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መንገድ ማመቻቸት  ቻሉ። በተለያየ ምክንያት ትችት ይሰነዘርባቸውና አይነኬ በመባል የሚታወቁትን፣ በሌላ በኩል በህዝብ ዘንድ  አመኔታን ማትረፍ ያልቻሉትን እንደህንነትና የመከላከያ ሃይል ሪፎርም እንዲካሄድባቸው በማድረግ ጠንካራነታቸውን በተግባር አሳይተዋልል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ከፍተኛ ልዩነት ከፈጠሩባቸው ጉዳዮች አንዱ የውጭ ግንኙነት ስራቸው ነው። እኚህ ሰው እጅግ ጠንካራ  የተግባቦት አቅም ያላቸው በመሆኑ ማንንም ማሳመን የሚችሉ ናቸው። ለጎረቤት አገራት ጋር መልካም ግንኙነት የህዝቦችን አንድነት ያጠናክራል፣ የቀጠናውን ሰላም ያረጋግጣል፣ በሚል  ዕምነታቸው በሁሉም ጎረቤት አገራት ጉብኝት በማድረግ እጅግ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን አከናውነዋል። ከኤርትራ ጋር የነበረውን የጠብ ግድግዳ እንዲናድ በማድረግ ‘ሞት አልባ ጦርነት’  የተባለውን ፍጥጫ ወደ መልካም ጉርብትና መቀየር ችለዋል።

እኚህ ሰው  በሁለቱ አገራት  መካከል ሰላም ለማስፈን  ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ወደ አስመራ የልዑካን ቡድን በመላክ ፈንታ ራሳቸው ወደ  ኤርትራ በማምራት ለሰላምና ፍቅር ያላቸውን አቋም አረጋግጠዋል። በዚህም ድርጊታቸው  በአጭር ጊዜ በሁለቱ አገራት መካከል ተደንቅሮ የነበረው ‘ጥቁር መጋረጃ’ ቀዳደው ጥለውታል። ሌላው በታላቁ የህዳሴ ግድብ ሳቢያ አንዳንዴ ፍጥጫ በሌላ ጊዜ ደግሞ በመጠራጠር ላይ የተመሰረተውን  የኢትዮጵያንና የግብጽን ግንኙነት ወደመተማመን እንዲሸጋገገር አድርገውታል። በርካታ ኢትዮጵያዊያንን በሄዱባቸው አገራት ሁሉ ከእስር እንዲፈቱና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አድርገዋል። በእነዚህ ተግገባራቸው እኚህ መሪ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ቤት በቀላሉ መገባት ችለዋል። ዛሬ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ዶ/ር አብይን ሳይጠራ ወይም ስለእርሳቸው ሳይሰማ ወይም ሳያነብ ወይም ከሌሎች ጋር ሳይወያይ  የሚውል ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም።

የአገራችን ኢኮኖሚ ላለፉት አስር ዓመታት በፍጥነት እያደገ እንደነበር  ቢነገርም፣ ባለፉት ሶስት ዓመታት በአገራችን በተከሰተው አለመረጋገጋት እና በአገሪቱ  በገነገነው ሌብነት ሳቢያ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እጅጉን ተዳክሞ ነበር። ከዚህም ባሻገር የወጪ ምርት  መቀነስ፣ የመንግስት የብድር መጠን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማደግ በሌላ በኩል ደግሞ የአገሪቱ የመክፈል አቅሙ መዳከም ለአገሪቱ ብድር የሚያቀር  አካል አልተገኘም። ከዚህም ባሻገር በአቅም ማነስና በሌብነት ሳቢያ ለረጅም ጊዜ እየተጓተቱ የመጡ የመንግስት ሜጋ ፕሮጀክቶች የታሰበውን ውጤት  ማፍራት ባለመቻላቸው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ወድቆ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስፈልጋቸው  በመሆኑ ለመንግስት ተጨማሪ ችግር ሆነውበታል። በባንክና በጥቁር ገበያ ምንዛሪና መካከል ሰፊ ልዩነት በመፈጠሩ ህዝቡ በብር ላይ እምነት እንዲያጣ ሊያደርገውና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከጥያቄ ውስጥ ሊከተው ከአፋፍ ተደርሶ  ነበር። የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ አሚር ጋር ባደረጉት ውይይት ከወትሮው ከተለየ መልኩ አንድ ቢሊዮን ዶላር በቀጥታ ብሄራዊ ባንክ እንዲገባ በማደረግ የአገሪቱን የዶላር ጥማት  ጊዜያዊ እርካታ እንዲገኝ ያደረጉ ሲሆን በዘላቂነት ደግሞ የወጪ ምርትን ለማሳደግ መስራት፣ የብሄራዊ ባንክ የአሰራርና አመራር ስርዓት ማሻሻያዎች መደረጋቸው ይጠቀሳል።

እንግዲህ  ዶ/ር አብይ  በዚህ አጭር የስልጣን ጊዜያቸው ያከናወኗቸውን  ተግባራት በቅን ልቦና ለተመለከተው እኚህ ሰው እውነትም ነብይ ናቸው ቢባል  የሚበዛባቸው አይመስለኝም። ለማነጻጸር ከባድ ቢሆንም በመቶ ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ  ያልተከናወኑ ተግባራት በመቶ ቀን መወጣት መቻል “ነብይ” ቢያስብል ማጋነን አይሆንም። አንድ እናት  “ይሄ ምን አብይ ነው ነብይ እንጂ” ያሉት እውነታቸውን ሳይሆን ይቀራል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy