“ግድግዳ እያፈረሰ ድልድይ
እየተገነባ …”
አባ መላኩ
አገራችን ከሶስት ወራት በፊት የነበረችበትን ሁኔታ ስናስታውስ ዛሬም በርካታ ኢትዮጵያዊያን ያስፈራናል ያስደነግጠናልም። አዎ መሽቶ በነጋ ቁጥር የአገራችን እጣ ፈንታ ምን ይሆን? ስንል ራሳችንን እንጠይቃለን። በሰላም ወጥቶ መግባት ስጋት ሆኖ ነበር። “ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንደሚባለው የሁከትና ነውጥ መንገድ መዳረሻው አይታወቅምና ስጋታችን ዕውነታነት የነበረው ነው። ሶሪያን፣ ሊቢያን፣ የመንን፣ ኢራቅን፣ ሶማሊያን ያየ ሁከትና ነውጥ ምን ያህል አስፈሪ እንደሆኑ መረዳት አይከብድም። የእኛ አገር የዘር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የጎጥ ፖለቲካም ጽንፍ የወጣ እንደነበርም መዘንጋት የለበትም። እኔ ዛሬ ላይም በብሄር ስም የተቃቋሙ የእግር ኳስ ክለቦቻችን ስታዲዮም በገቡ ቁጥር ሁሉ ያሳስበኛል።
ዛሬ ነገሮች በእጅጉ መቀየር ጀምረዋል። ትላንት የት ነበርን? አሁንስ የት ነን? ነገስ የት እንሆን? ስል ራሴን አብዝቼ እጠይቃለሁ። የሚያዝናና ባይሆንም እፎይ የሚያስብል ሁኔታዎች በአገራችን ተፈጥረዋል። ይህን ሁኔታ ማሰቀጠል ከቻልን አገራችን ወደከፍታው ዘመን እንደምትሸጋገር ጥርጥር የለኝም። የዛሬው የአንድነት መንፈስ በህዝቦች መካከል መልካም ሁኔታዎች እንዲፈጠር እያደረገ ነው። ዛሬም አንዳንዶች የዘረኝነት መንፈሱ እንደተጠናወታቸው እዛው ቀድሞ የቆሙበት ቦታ ናቸው። ከዘረኝነት የሚገኝ ጥቅም ማንንም አይጠቅም፤ የማታ ማታ ሁሉንም ይዞ የሚጠፋ እኩይ ድርጊት ነው።
ኢህአዴግ ዛሬ ክፍተቶቹን ለመሙላት ጠንክሮ በመስራት ላይ ነው። አንዳንዶች ዶ/ር አብይን ከኢህአዴግ የመለየት አካሄድ ሲከተሉ እናያለን። አመንም አላመንም ዶ/ር አብይ የኢህአዴግ ውጤት ናቸው። ይህ ለውጥ ኢህአዴግ በመሪው በኩል እያካሄደው ያለው የለውጥ ሂደት ውጤት ነው። ዛሬ ላይ ኢህአዴግ የራሱን ክፍተት በዶ/ር አብይ የሞላው ይመስለኛል። እውነትም ኢህአዴግ ለመለወጥ እውነተኛ ውሳኔ ማሳለፉን መረዳት የቻልነው እንደዶ/ር አብይ አይነት አመራሮችን ወደፊት ማምጣት ሲጀምር ነው። ኢህአዴግ ዛሬ ክፍተቶቹን በደንብ ለይቶ በህዝቦች መካከል “ግድግዳን እያፈረሰ ድልድይ እየገነባ” ነው። ናይጄሪያዊያኖች እንደሚሉት “ብልህ በችግር ጊዜ ድልድይ፤ ሞኝ ደግሞ ግድብ ይገነባል”። አዎ ኢህአዴግም ዛሬ በህዝቦች መካከል ግድብ እያፈረሰ ድልድይ እየገነባ ነው። ችግርን በመለየት መፍትሄ መስጠት በመጀመሩ ዛሬ ላይ በአገራችን ተጨባጭ ለውጦች እየመጡ ነው።
ስሜታዊነት ምክንያታዊ እንዳንሆን ያደርገናል። ይሁንና ስሜታዊነት እውነታን ለጊዜው ይሸፍነው ወይም ያሳንሰው እንደሆን እንጂ በየትኛውም መስፈርት እውነታን ለዘለዓለሙ ሊደብቀው ወይም ሊያደበዝዘው አይችልም። ኢህአዴግ ያመጣውን ለውጥ ልናደንቅና ልንደግፈው ይገባል። ኢህአዴግ አዳዲስ አቅም ያላቸው አዳዲስ አስተሳሰብ ማፍለቅ የሚችሉ የወቅቱን የህዝብ ፍላጎት ማርካት የሚችሉ አመራሮችን ወደፊት አምጥቷል። ኢህአዴግ በርካታ የተማሩ ቁርጠኛ አቋም ያላቸው አመራሮችና አባላት ያለው ድርጅት በመሆኑ መተካካቱ ያጠነክረዋል እንጂ ከመስመር የሚያስወጣው አይሆንም። ድርጅቱ በየጊዜው የህዝብ ፍላጎትን ማርካት የሚችሉ አመራሮችን ወደ ሃላፊነት ማምጣት በመቻሉ ይመስለኛል ጠንካራና ተፎካካሪ መሆን የቻለውም።
ይህ ድርጅት ሺህ ጠንካራ ስብዕና ያላቸውን አመራሮች ያፈራ፣ ዛሬም እያፈራ ያለ ነገም የሚያፈራ የባለራዕዮች ፓርቲ ነው። ዛሬ በህዝብ የተወደዱትና የተወደሱትን ዶ/ር አብይን ጨምሮ አቶ ለማ መገርሳን የመሳሰሉ ወጣት አመራሮችን ያፈራው ኢህአዴግ ነው። አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የአገራችን ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ በሄደበት ሁሉ የህዝብን ቀልብ የመግዛት አቅም ያዳበሩት በኢህአዴግ ቤት ነው። ጠቅላያችን በውጭ አገር ጉብኝት ባደረጉባቸው አገራት ሁሉ የጠየቁት ሁሉ ማሳካት የቻሉት ወይም ብስል የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲከተሉ ያደረጋቸው ኢህአዴግ ቤት ባካበቱት ልምድ ነው።
ታዲያ እርሱን (አብይን) ወዶ ኢህአዴግን ጠልቶ ወይም አንኳሶ የሚያዋጣ አካሄድ ነውን? ወተቷን ወዶ እበትን ጠልቶ አይቻልም እንደሚባለው ኢህአዴግና ዶ/ር አብይንም ነጣጥሎ ማየት አይቻልም። ዶ/ር አብይም በተገኙበት መድረክ ሁሉ እያንዳንዱ የሚፈጽሙት ነገር የድርጅታቸውም የመንግስታቸውም ዕምነት መሆኑን በይፋ ይመሰክራሉ። ኢህአዴግ በርካታ ጠንካራ ስብዕና ያላቸው አባላት ስብስብ ነው። እንደ ዶ/ር አብይ አይነት ጠንካራ ስብዕና ያላቸው ሺህ አመራሮችን ያፈራ፣ አሁንም በማፍራት ላይ የሚገኝ፣ ነገም የሚያፈራ ፓርቲ እንደሆነም ሊታወቅ ይገባል።
አገራችን ህገመንግስታዊ አገር ናት። ነገ ከነገወዲያም ኢህአዴግም ሆነ ሌላ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ስልጣን ቢመጡ የሚፈጽሙትና የሚያስፈጽሙት ህገመንግስቱን ብቻ ነው። ሕገ-መንግስታችን ለፈጣንና ቀጣይ የኢኮኖሚ እድገታችን እንዲሁም ለአስተማማኝ ሰላማችን ዋስትና በመሆኑ ሁላችንም ልናከብረው ብቻ ሳይሆን ልናስከብረው ይገባናል። ሕገ-መንግስታዊ የፌደራል ስርዓታችን ብዝሃነትን የተቀበለ የአገራችንን አንድነት ያስጠበቀ፣ እያንዳንዱ ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ሁኔታዎችን ያመቻቸ በመሆኑ ሁላችንም ልንጠብቀው ይገባናል። የልማታችን፣ የዴሞክራሲያችን፣ የሰላማችንና የአንድነታችን ዋስትና የሆነውን ህገመንግስታችንን ለመጣስ የሚንቀሳቀስ ማንኛውንም ሃይል በጽናት መታገል የሁላችንም ስራ ሊሆን ይገባል።
ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ እንዲሁም የመንግስት ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ያስቀምጣል። በተጨማሪም ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማሕበራት እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ሕገ-መንግስቱን የማስከበርና ለህገ መንግስቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸውም በግልፅ ይደነግጋል። ይሁንና ባለፉት ሁለት ዓመታት ህገመንግስት ሲደፈጠጥ ዜጎች በጠራራ ፀሀይ መብቶቻቸው ሲጣሱ መንግስት ተገቢውን ጥበቃ አላደረገም፤ ዜጎችም ይህን አይነት ነገር አምርረን አልታገልንም። ያን ባለማድረጋችን ምን አይነት ዋጋ እንዳስከፈለን የሚታወቅ ጉዳይ ነው።
በአገራችን በመነጋገር ለችግሮች መፍትሄ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ተመቻችቷል። በመሆኑም ችግሮችን በሁከትና ብጥብጥ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በሰከነና በሰለጠነ መንገድ መፍትሄ መፈለግ የመጀመሪያም የመጨረሻም አማራጭ ሊሆን ይገባል። ይህን በማድረግ አገራችን የጀመረችውን ዘርፈ በዙ ለውጥ ማስቀጠል የአገር ወዳድ ዜጋ ሁሉ ግዴታ መሆን መቻል አለበት። መንግስት ዛሬ ላይ ለአገራችን የሚያስፈልጋትን ህክምና እየሰጣት ነው። የዶ/ር አብይ መንግስት የአገሪቱን አንድነት የሚያጠናክር፣ የህዝቦችን አብሮነት የሚያጎለብት ድልድይ እየገነባ በሌላ በኩል ህዝቦችን የሚነጣጥል ግድግዳ እያፈረሰ ነው። አዎ ሁላችንም ከመንግስት ጎን ልንቆምና በምንችለው ነገር ሁሉ ልንረዳው ይገባል።