Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጥላቻን መቀነስ ፍቅርን መደመር ነው

0 807

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

 

ስሜነህ

 

“የእኛ የመደመር እሳቤ ከሂሳብ የመደመር እሳቤ የላቀ ነው፡፡ የእኛ የመደመር እሳቤ የልዩነት ግንብን ማፍረስ ነው፡፡ እኔና ኢሳያስ ስንደመር ሁለት ሳይሆን እኛ ነው የምንሆነው፡፡ እኔና ኢሳያስ ስንደመር እኛ ሆነን እንባዛለን፡፡ ” የተከበሩ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ በቅርቡ ባመጡት የመደመር ስሌት መሰረት ብዙ ኢትዮጵያዊ ይህን መርህ ወዶት መፈክር አድርጎት ይታያል። ጠቅላይ ሚንስትር አብይ “ተደመሩ” ሲሉ ጽንሰ ሃሳቡ ምን ምን ይዘት እንዳለው በጥልቀት በሚሊኒየሙ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የማብሰሪያ መድረክ አብራርተዋልና ስለዚሁ ማውራት በራሱ መደመር ይሆናል።

 

በሃገራችን ሁኔታ የመደመር ፖለቲካ ከግልብ መረዳትና ህዝባዊ ንቅናቄ ታቅበን በተሻለ የመረዳት ከፍታ ላይ ሆነን የምናደርገው ትግል ነው መደመር። በጠቅላይ ሚንስትሩ ማብራሪያ መሰረት መደመር ማቀፍን ወይም (inclusion) ያሳያል። መደመር ነጠላነትን (homogeneity) የሚያራምድ ወይም የሚያበረታታ ሳይሆን ተገጣጥሞ ሰፋ ያለ መዋቅር መፍጠርን መያያዝን የሚያሳይ ጽንሰ ሃሳብ ነው። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ገዢ ኣሳብ የነበረው ነጠላነትን( homogeneity) የሚያበረታታ ብሄሮች “የራሴ” የሚሉትን ግዛት እያጠሩ የሚኖሩበትን ሁኔታ የሚያበረታታ ነበር። መደመር ግን ይህንን የሚያፈርስ ነውና በርግጥ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ይህን ኣሳብ ሲያፈልቁ ሃገራችን ወደ ሌላ የትብብር የመገጣጠም የህብረት ትርክት(narration) ውስጥ እየገባች እንደሆነ ያሳያል።

 

ቀድሞ የነበረው መደመርን የሚያኮስሰው የፖለቲካ ኣስተሳሰብ ብዙውን ሰው ኣስኮርፎ የቆየ ሲሆን ዛሬ የመደመር ፖለቲካ ሲመጣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በግልም በቡድንም ተደምረናል! ተደምረናል!  እያሉ ኣዲሱን ትርክት ሲደሰቱት በአንጻሩ ያለፈውን ትርክት አደባባይ ላይ ሲሰብሩት ይታያል። በመሆኑም መደመር ስንል እንግዲህ እኛ የተደመርን ሰዎች ይህንን መረዳት ብናየው መልካም ነው።  ይህ ክልል የነእገሌ ነው የሚለውን ትርክት ሽሮ ኢትዮጵያውያን በዋናው ቤታቸውም ይሁን  በስቴቶቻቸው ተደምረው እንዲኖሩ የሚያደርግ  ነው። የሃገራችን ሶሺዮ ፖለቲካ ጉዞ ወደ መለየት (separation) የመጣ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከፍ ብሎ የመጣው የመደመር ጥሪ ይህንን የመለየት (separation) ፖለቲካ የሚሽር ነው።  

 

እንደዶክተር አብይ መደመር ማለት ማነባበር ማለት ኣይደለም። መደመር ማለት የሚደመረው ነገር ተደምሮ የሚሰጠውን ዋጋ (value) ወይም እሴት በትክክል ማወቅና ማስላት መቻል ማለት ነው። የሚደመሩት ተለዋዋጮች ተደምረው ያላቸውን የጋራ እሴት መረዳት ካልቻልን የመደመር ጽንሰሃሳ ገባን ማለት ኣይቻልም። ስለሆነም እንደመር ስንል ተደምረን የሚኖረን የጋራ እሴት እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ጉዳይ፣ በፖለቲካው መስክ  የሚሰጠንን ትርፍ መተመን መቻል ማለት ነው።  የዶክተር አብይ የመደመር ኣሳብ ጥሩ ደጋፊ መሆናችን የሚለካው ተደምረን የምናገኘውን ዋጋ ቀድመን ባሰላነው መጠን ነው። ስለዚህ ከኛ ከደጋፊዎች ይህንን የመደመር ዋጋ ኣስልቶ የማየት ችሎታ ይጠይቀናል። ዋጋው በታየን መጠን ለትግሉ የሚከፈለውን ዋጋ ለመክፈል እንችላለን። ከሁሉ በላይ ይህ ጽንሰ ሃሳብ በአንድ ጊዜ ቦግ ብሎ የሚጠፋ የስሜት ነገር ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የአብሮነት መርህ በመሆኑ የመደመር ወይም የብዝሃነት ዋጋው በሚገባ ሊገባን ይገባል። ተደምሮ የመኖር ክህሎትንም ልናዳብር ይገባል።

 

ሌላው የመደመር ጽንሰሃሳብ የሚያመላክተው ነገር በተለይ ለተደራጁ የፖለቲካ ሃይላት የቅንጅት (Coalition) ወይም የመዋሃድ ጥሪን ነው።  ሃገራችን ወደ መቶ የሚጠጉ ፓርቲዎችን ይዛ ትወዛወዛለች። የአንድነት ሃይሎች ስለህብረት እያወሩ ነገር ግን ኣይደመሩም። ኣንድ ኣይነት ኣይዲዮሎጂና ፖሊሲ ይዘው የተለያየ ፓርቲ ሆነው ይኖራሉ። አሁን ጊዜው የመደመር የቅንጅት ጊዜ ነው። የመደመር ጽንሰ ሃሳብ ለነዚህ ፓርቲዎች ትልቅ ጥሪ ኣለው። መሰባሰብ መደመር ይጠበቅባቸዋል። የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ዋና ዓላማ ለህዝቡ ኣማራጭ ፖሊሲዎችን መፍጠር ነው። ከመቶ በላይ ፓርቲ ቢኖረን የዚህን ፓርቲ ሁሉ ኣሳብ ለማወቅና ለመምረጥ ራሱን የቻለ የአንድ ኣመት ኮርስ ሊወስድብን ይችላል። የፓርቲውን ስም ሸምድደን ለመያዝም አንችልም። ፓርቲዎች ጠጋ ጠጋ ብለው ቅንጅት ፈጥረው ሁለትና ሶስት ሆነው ለምርጫ ቢመጡ ልዩነቱን እየተመንን የተሻለውን ለመምረጥ እንችላለን።  

 

ሌላው የዚህ የመደመር ጽንሰ ሃሳብ ትምህርት ሊሰጠን የሚችለው ነገር ከራሱ ከምልክቱ የምንቀዳው ትምህርት ነው። የመደመር ምልክት (+) እንደሚያሳየው በአንድ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ግንኙነት ያሳያል። ወደ ላይ ያለው መስመር በመንግስትና በህዝብ መካከል የጠበቀ ግንኙነትን የሚያሳይ ሲሆን ወደ ጎን ደግሞ ግለሰብ ከግለሰብ (interpersonal relationship) እና ቡድን ከቡድን እጅ ለእጅ መያያዝን ቃልኪዳን መግባትን ያሳያል። ይህ መስቀለኛ ምልክት የኢትዮጵያውያን አብሮ የመኖር የኪዳን ምልክት ሊሆን ይችላልና ይህንን ምልክት  ከመንግስታችን ጋር  ባለመተማመን የተቆረጠውን መስመር የምንቀጥልበት፣ መንግስታችን በኛ ምርጫ የሚሾምበትና የሚሻርበት፣ ወደ ጎን እኛ ኢትዮጵያውያን ህብረት የምንፈጥርበት፣ ብሄሮች፣ ግለሰቦች በሙሉ ተደምረን የአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ህዝብ መሆናችንን የምናሳይበት ምልክት ሊሆነን ይችላል።   

 

መደመር ማለት ልዩነቶቻችን እንዳሉ ሆነው ግን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ኢትዮጵያዊ እንሁን ማለት ነው። ኦሮሞዎች፣ አማራዎች፣ ትግሬዎች፣ ጉራጌዎች፣ ወላይታዎች፣ አፋሮች ወዘተ ተደመሩ ሲባል አንድ ተደፍጥጦ የተፈጠረ ባህላዊ ቡድን ይሁኑ ማለት ኣይደለም። ስለዚህ መደመር ስንል በግድ የሆነ ምስለትን (assimilation) እናምጣ ሳይሆን ብዙህ ሆነን ግን በአንድ የጋራ ማንነት ስር ማለትም ኢትዮጵያዊነት ስር እንደር ማለት ነው።  

 

በመደመር ጊዜ በውጤቱ ላይ ምንም ለውጥ ወይም እድገት የማያሳየው ዜሮን ጨምረን የደመርን እንደሆነ ነው። ዜሮ ባዶ በመሆኑ በድምራቸን ላይ ተጽእኖ የለውም። የዶክተር አብይ የእንደመር ጥያቄ የአስተዋጾ ጥያቄ ነው። ተጨባጭ የሆነ ተፈላጊ ለውጥ እናመጣ ዘንድ የለውጥ ሃይላት ሁሉ የምንችለውን መወርመር አለብን። በሌሎች ዋጋ ተጨባጭ ለውጥን መናፈቅ ተደምሪያለሁ ከሚል ዜጋም ሆነ ቡድን አይጠበቅም።  የመደመርን ኣሳብ  እደግፋለሁ ስንል የምንደግፈው ግለሰብን ሳይሆን ኣሳቡን ስለመሆኑ መገንዘብ ይገባል። በለውጡ ሂደት ዶክተር ኣብይ ቢደክሙ ወይም ለውጡን ከዳር ባያደርሱ ተደምሪያለሁ ብለን ሲያጠፉ ሁሉ ዝምታ መደመር አይሆንም። ይህ የመደመር ስሌት የመርህ ጉዳይ ነው። ሃገራችንን ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ስርዓት የሚወስዳትን አመራር ሁሉ እየደገፍን የምንሄድበት መርህ እንጂ የግለሰብ ደጋፊነት አይደለም። በርግጥ ግለሰቦች ባላቸው ኣስተዋጾ ሊበረታቱ ሊደገፉ ይገባል። ነገር ግን የሙጥኝ ብለን የምንኖረው መርህን መሆን ኣለበት። ስለዚህ የመደመርን መርህ የምንከተለው ዶክተር ኣብይ ስልጣን ላይ እስካሉ ብቻ ሳይሆን ሄደውም ይህን መርህ ስንደግፍ ልንኖር ይገባል። ለውጥ የምናመጣው  ሁላችን አስተዋጾ ስናደርግ እሚደገፈውን ስንደግፍ የማይሆነው ላይ ደግሞ እምቢኝ ብለን ስንታገል ነው።

 

ፖለቲካ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ጉዳይ፣ በፖለቲካ ጉዳይ መደመርን  ማደግን ዓላማው ኣድርጎ የሚሄድ የአስተዳደር ጥበብ ነው። በሃሳብ ልቀት በፖሊሲ ልቀት ብዙዎችን እየማረከ የሚሄድ ጥበብ ነው። በሌላ በኩል እንደመር የሚለው ቃል የፍቅር ጥሪ ነው። የብሄራዊ እርቅና መግባባት ጥሪ አለው። የማግለል የመቀነስ ባህርይ የለውም። ስለዚህ በመደመር ትግላችን ወቅት ቡድኖችን የማግለል ስራ መስራት የለብንም። የምናገለውና የምናቅፈው ብለን የመለየት ስራ መስራት የለብንም። በፍቅር የመማረክ ስራ መስራትን ይጠይቃል። መደመር የፍቅርን የመቻቻልን ጥግ የምናሳይበት ምልክት ነው። በመሆኑም የዶክተር አብይን የመደመር ጥሪ የምንደግፈው ይቅርባይነትን፣ መማረክን፣ በፍቅር ማሸነፍን ታጥቀን መሆን ይጠበቅብናል። የጥላቻ ፖለቲካ ከምድራችን ነቅሎ ይሄድ ዘንድ የመደመር ፖለቲካ በጣም ፍቱን መድሃኒት ነው።

 

ነገር ግን አንዳንድ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታ የማይረዱ ጎታች የሆኑ አስተሳሶብችን መቀነስ እንደ መደመር የሚቆጠር መሆኑንም ልንገነዘብ ይገባል። ጥላቻን መቀነስ ፍቅርን መደመር ነውና። አለመተማመንን መቀነስ ማህበራዊ ሃብት ያድግ ዘንድ መደመር ነውና። ያለንን እውቀት ማካፈል፣ አስተዋጾዎቻችንን ማብዛት መደመር ነውና። በመሆኑም ለዶክተር አብይ የመደመር ጥሪ መቀነስን፣ ማካፈልን፣ ማባዛትን ሁሉ መደመር አድርገን ልንጠቀምባቸው እንደምንችል ማስላት በተለይ ለተደረጁ ሃይላት ያስፈልጋል። ኣደገኛ ጉዳዮችን ሁሉ ወደ በጎ ለውጥ የመቀየር ችሎታ መደመር ነው። ለውጣችንን የሚጎዱ ነገሮችን መቀነስ፣ መተማመንን የሚጎዱ ጉዳዮችን የመቀነስ  ፖለቲካ ማለት መደመር ፖለቲካ ማለት ነው ።

 

ስለሆነም በአለማዳመጥ ፣ በጥልቀት ባለማንበብ ፣ በችኮላና ብስለት ማጣት ፣ ትችትን በመሸሽ ፣ ውይይትን በመሸሽ ፣ ዘለፋን መሸሸጊያ በማድረግ ፣ ሮጠን የዘር ስልቻ ውስጥ በመደበቅ፣ በራስ አለመተማመን ፣ እውነትን በመሸሽ፣ ሚዛንን አዛብቶ ቡድንና ሕዝብን በመለየት፣ በሃሳብ ነጻነት አለማመን ፣ ወዘተረፈ ዋሻ ውስጥ ቁጭ ብለን ተደምረናል ማለት አይቻልም። አካሔዶችን መተቸት ማለት መደመርን አሊያም ዶክተር አብይን መቃወም ማለት አይደለም።

 

የዶክተር አብይ አስተዳደር ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ያሳያቸው መልካም ጅማሮዎች ወደ ተግባር እንዲለወጡ እያንዳንዳችን የዜግነት ግዴታ አለብን። ዶክተር አብይ በተናገረ ሰዓት ብቻ ማጨብጨብ ሳይሆን ንግግሩ ወደ ድርጊት እንዲለወጥ በግንባር ቀደምትነት ልንሰራ ይገባል። ይህን አይነት የተግባር ተሳትፎ ማድረግ ከቻልን ቃልን ወደ ድርጊት መለወጥ ከቻልን ዶክተር አብይ ብቻውን አይለፋም ፤አይደክምም። መደመር ማለት ይህ ነው። ከዚህ በተጨማሪም መደመር ማለት ለለውጥ በሚደረግ ጉዞ ውስጥ እክል ስለሚያጋጥም የሚመጡ ትችቶችን እንደ ጥንካሬ መውሰድ እንጂ ድንጋጤ ማሳየት ወደአልተፈለገ ዘራፍነት መለወጥ የለውጡን ባቡር ያዳክመዋል። አካሔዶችን መተቸት ማለት መደመርን አሊያም ዶክተር አብይን መቃወም ማለት አይደለም።

 

እያንዳንዱ ትችት ለእድገት ጠቃሚ ነው። በጭፍንነትና በመንጋ ሆኖ ማጨብጨብ ግን ለሃገርና ለሕዝብ ቀውስ መፍጠር ነው። ሃሳቦች ሲሰበሰቡ የተሻለ ነገር ይፈጥራሉ ። የተሰበሰቡ ሃሳቦች ሲዳብሩ ደግሞ የተሻለ ነገር እጅግ የተሻለ ነገር ይፈጥራል። ታሪክ ራሱን እንዳይደግም ጠንክረን በመስራት ለትውልዱ አዲስ የስኬት ታሪክ መፍጠርና ማሳደግ ይገባናል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy