Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፍቅርና መደመር— በኢትዮ-ኤርትራ ሰማይ ስር

0 696

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

                                                      እምአዕላፍ ህሩይ

(ክፍል አንድ)

እንደ መግቢያ

እንዲህም ሆነ።…አስመራ፣ ከረን፣ ምፅዋ (ባፅዕ)፣ መንደፈራ…ወዘተርፈ የሀገሪቱ ከተሞች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ለ20 ዓመታት አይተውት የማያውቁት ነገር አስተናገዱ። ከወትሮው የተለየ እንቅስቃሴ በውስጣቸው ሲከናወን አፍ ቢኖራቸው ኖሮ ብዙ በተናገሩ ነበር። በተለይ ለእሁድ አጥቢያ ቅዳሜ አመሻሹ ላይ የኤርትራ ከተሞች ሸብ ረብ ሲሉ፣ ተረስቶ የነበረን አንድ ባንዴራ በውስጣቸው ሲያውለበልቡ፣ በየቦታው ፍቅርና ደስታ እንደ ዝናብ ሲፈስና ምድሮቻቸውን ሲያረሰርስ እንዲሁም ቂም በቀል፣ ጥላቻና ውጥረት እንደ ጠል ደመና ስፍራቸውን ለቀው ብን ብለው ሲጠፉ ተመልክተዋል። ግና ከተማዎች የሚወክሉት ሰዎችን በመሆኑ፤ በውስጣቸው ያሉት ነዋሪዎች ብዙ ተናግረዋል። ደህ ሰንብት ጦርነት፣ ደህና ሰንብቱ ቂምና መጠላለፍ፣ ደህና ሰንብት የተናጠል ጉዞ ብለዋል። የመነጠል ድስት ውጣ፣ የፍቅርና የመደመር ድስት ግባ ብለዋል።…

…ዕለተ እሁድ፤ ሐምሌ 01 ቀን 2010 ዓ.ም። ከአዲስ አበባ ጧት ማልዶ ወደ ኤርትራ ያቀናው የአገራችን ጢያራ፤ መዳረሻውን ያደረገው በዘንባባ የተሸፈነችውን አስመራ ከተማን ዞሮ አውሮፕላን ማረፊያዋ ውስጥ ነው። ታሪካዊ ክስተት። ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝብ ፍላጎት የተካሄደው የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የሰላምና የመደመር ለውጥ ያስገኘው አዲስ ክስተት። የ20 ዓመታትን ከንቱ ውጥረት ያስቀረ። የኤርትራ ህዝብን በፍቅርና በወንድማማችነት የደመረ ወደር የሌለው ምርጥ ትዕይንት።

የትዕይንቱ መሪ ተዋናዩች፤ በኢትዮጵያ በኩል፤ በሀገር ቤቱ የለውጥ መሃንዲስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተወከሉት እንዲሁም በኤርትራ በኩል በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አማካኝነት የተወከሉት የሁለቱም ሀገራት ሰላም ወዳድ ህዝቦች ናቸው። በደም፣ በታሪክ፣ በባህል፣ በወግና በትውፊት ዛሬም እንደ ትናንቱ በፍቅርና በሰላም ለመተሳሰር የሻቱት የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ናቸው። ሌላ ማንም አይደለም። ሊሆንም አይችልም።

የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የመደመርና የሰላም ዘንባባን ይዞና በዶክተር አብይ አህመድ ተመርቶ አስመራ አውሮፕላን ማረፊያ የተገኘው የኢትዮጵያ ልዑክ፤ በሀገሪቱ ፕሬዚዳንትና በአስመራ ነዋሪዎች የተደረገለት ከልብ የመነጨና እውነተኛ የአቀባበልን ትዕይንትን በቴሌቪዥን መስኮቶች ስንከታተልን ለነበርነው ሰዎች የዳግም ልደት ያህል የሚቆጠር ይመስለኛል። ይህ ልባዊ አቀባበልና እውነተኛ ሰላም ፈላጊነት በሌሎች የኤርትራ ከተማዎች ውስጥም እንደሚኖር በርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

ህዝቡ በአስመራ ጎዳናዎች ጥግ ጥጉን ተሰልፎ በሆታና በእልልታ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያናዊ ሽብሸባና መዝሙር ከተማውን አድምቆታል። በእያንዳንዱ ወንድምና እህት ኤርትራዊያን ፊት የሚታየው ደስተኝነትና የፈገግታ ፀዳል መጪው የፍቅርና የመደመር ጊዜ የፈካና የደመቀ እንዲሁም ምርጫቸው ህዝቦች በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘው ማደግ ብቻ መሆኑን የሚናገሩ ናቸው።

የአስመራ ህዝብ በየጎዳናው ለኢትዮጵያዊው ወንድሙ ምን ያህል ፍቅር እንዳለውና በወንድማማቾች መካከል የተፈጠረው መለያየት ከሞት የከፋ ያህል እንደሆነ በቃልም ይሁን በተግባር ሲገልፅ መመለከት በእጅጉ አንጀት ይነካል። ያሳዝናል። የፍቅርና የመደመር ፍላጎቱ እንደ ሁለት ሀገር ሳይሆን እንደ አንድ ሀገር ህዝብ መሆኑን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ካሳየው በስስት የተሞላ እጅግ የደመቀ አቀባበል ለማወቅ ነብይ መሆንን አይጠይቅም።

እናም ዛሬም እንደ ሁልጊዜው ያንን ፍቅርና ሰላም አዋቂ ወንድምና እህት ህዝብ በእጥፍ ድርቡ ላከብረው ግድ ብሎኛል። ክብር የጥላቻና የመቃቃር  መጋረጃን ሽርክትክት አድርገው ለቀደዱት ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ህዝቦች። ክብር ህዝቦችን ወክለው ይህን የፍቅርና የሰላም ጎዳና ቦይ አስፈተው እየቀደዱ ላሉት ለሁለቱም ሀገር መሪዎች። ክብር የሰላም ዘንባባ ዝንጣፊን ይዘው ለሚዘምሩ የቀጣናው ህዝቦች።…

በጋራ ፍላጎት በተቀደደው የሰላም ቦይ አስመራ የገቡት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተነግሯል። ውይይቱ በርካታ ጉዳዩች ተነስተዋል። የጥላቻና የቂም በሮች መዘጋታቸው ተወስቷል። ሁለቱ ሀገራት መደበኛ ግንኙነታቸው እንዲጀምርም ተስማምተዋል። የሀገራቱ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በአዲስ ምዕራፍ መታደሱም ተወስቷል። በውጥረት ውስጥ የነበረው የሀገራቱ ግንኙነት የሰላምና የመተባበር ብስራት በፍቅር የተዘመረባት ከተማ ሆናለች—አስመራ። የጥላቻ መጋረጃ የተቀደደባት ከተማ።

 

የሀገራቱ አየር መንገዶች በጢያራቸው በኢትዮጵያና በኤርትራ ሰማይ ላይ እንዲበሩ፣ የየብስ ትራንስፖርታቸው አቀበትና ቁልቁለቱን እንዲወጡና እንዲወርዱ እንዲሁም ህዝቦቻቸው ባሻቸው ጊዜና ወቅት ተገናኝተው የሆድ የሆዳቸውን እንዲጫወቱ ብሎም በጋራ አልምተው እኩል ተጠቃሚ ወደሚሆኑበት አዲስ ምዕራፍ መሸጋገራቸውን በፍቅርና በመደመር መንፈስ የሰላም እምቢልታ የተነፋባት ከተማ ሆናለች—አስመራ። በዶክተር አብይ አህመድና በፕሬዚዳንት ኢሳይያስ መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ቀጣናውን የሰላምና የልማት ዞን እንደሚያደርገው ምንም ጥርጥር የለውም።

 

ለቀጣናው—አንድም ሁለትም

 

የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች አንድም ሁለትም ናቸው። ርግጥ የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች ተለያይታችሁ ኑሩ ቢባሉ ሊለያዩ የሚችሉ አይደሉም። ያለፏቸው የህይወት መንገዶች የቁርኝት ሰንሰለታቸውን አጋምዶታል። የቋንቋ፣ የደም፣ የአብሮነት፣ የመቻቻልና አብሮ የመኖር መስተጋብራቸው እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አብሯቸው እስከ መጨረሻው የሚዘልቅ እንደ ድርና ማግ የተዋደደ ትስስር ያለው ነው። እናም እነዚህ ህዝቦች ከአንድነትና ተሳስቦ በእኩል ተጠቃሚነት ከመኖር እንጂ በተናጠል ህይወትን መግፋት አያዋጣቸውም። የሀገራቱ በጋራ መኖር በቀጣናው ያለውን የተፈጥሮ ፀጋ እየተሳሰቡ ሊጠቀሙ ይችላሉ። ለዚህም ነው— የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “…በቀጣናው ያለውን እምቅ አቅም ተጠቅሞ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይቻላል” በማለት በአስመራ ቆይታቸው ወቅት የተናገሩት።

“ትናንት ዛሬ አይደለም” የሚል አባባል አለ። በእኔ እምነት አባባሉ ትናንት ዛሬን ሊወክል አይችልም የሚል አንድምታ ያለው ነው። ትናንት ለዛሬ መሰረት አይደለም ማለቴ ግን አይደለም። ትናንትን በዛሬ መነፅር ልንመለከተው ግን አንችልም። ትናንት…ትናንት ነው። ዛሬ ግን አይደለም። ዛሬ…ዛሬ ነው። እናም ኢትዮጵያና ኤርትራ ትናንትን ዛሬያቸው ውስጥ አምጥተው ሊመለከቱት አይገባም። ለዚህም ይመስለኛል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ “…ከ20 ዓመት በፊት የተከሰተን ግጭትና ጥፋት ረስተን በጋራ መበልፀግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ እየመከርን እንሰራለን” በማለት ነገሮችን በዛሬው ልከረታ እየሰፈሩ መመልከት ተገቢ መሆኑን የገለፁት።   

በፍፁም ደስታ ውስጥ ሆነው “የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች እንኳን ለዚህች ቀን አደረሳችሁ” ያሉት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የዶክተር አብይ የሰላም ጥሪ ከልብ የመነጨና እውነተኛ መሆኑን አስረድተዋል። ሁለቱ ሀገራት ባለፉት ጊዜያት ወደ ሰላም ለመምጣት ጥረት ማድረጋቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ፤ በአሁኑ ወቅት ጥረቱ መሳካቱ ለዶክተር አብይ ምስጋናቸውን ችረዋል። ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላምና ፍቅር እንዲነግስ የመሪዎቹ ፍላጎት ፅኑ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ታዲያ ይህ ፅኑ ፍላጎት ከፍላጎት ባሻገር ወደ ተጨባጭ ርምጃዎችም ተሻግሮ ሰላም አብሳሪ ክንውን ተፈፅሟል። የተነፋፈቁት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በስልክ የአየር ሞገድ አማካኝነት ተገናኝተዋል።

የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ የአየር ሞገዱ ተካፋይ ነበርኩ። ኤርትራ ውስጥ ዘመድ አዝማድ የለኝም። ሆኖም በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው እውነተኛ የሰላም ድባብ ወደማላውቀው አንድ ስልክ መታሁ። ጎርነን ያለ የሴት ድምፅ ‘መን ክብል?’ ሲል ወደ እኔ መጣ—‘ማን ልበል?’ ማለታቸው መሆኑ ገብቶኛል። ስሜን ነገርኳቸው። አከታትዬም ‘አያውቁኝም፣ የደወልኩትም ከኢትዮጵያ ነው። በግሌ ላለፉት 20 ዓመታት የተዘረጋውን የመለያየት ፅላሎትን እየቀደድኩ ነው አልኳቸው— ዕድሜያቸውን ከድምጻቸው ለመገመት እያስቸገረኝ።። ደስ አላቸው። ወዲያውኑም ስማቸውንም ነገሩኝ።…

…በእውነቱ በሴትየዋ ውስጥ የተፈጠረውን ስሜት በዚህ ፅሑፍ ላይ ለማሰፈር ይቸግረኛል። ብቻ የሚቆራረጥ የደስታ ሲቃ፣ ምርቃት፣ ሁለቱ ሀገሮች አንድ ስለመሆናቸው፣ የሚለያየን አጥር እንደሌለ ብዙ…ብዙ ነገሮችን በአየር ሞገዱ ውስጥ አሉኝ። የቅርብ ዘመዴን የማናገር ያህል ተሰማኝ። በዝምታ ተዋጥኩ። ውስጤም ተረበሸ። እኔም ስለተናገሩት ሁሉ አመሰገንኳቸው። ምናልባት አስመራ ከሄድኩ ዘመዴ እንደሚሆኑ ነገርኳቸው። ርሳቸውም እየሳቁ ዘመድ ተገኝቶ ነው፣ ለዛውም 20 ዓመት ያህል የጠፋ የሚል ቃና ያለው ምላሽ ሰጡኝ። በዓይኖቼ እምባ ግጥም ሲል በድጋሚ አመስግኜ ተሰናበትኳቸው።…በውስጤም የሰላም መንገዱ ተደማሪ አንዱ እኔ ነኝ ስል አሰብኩ።…

ከአስመራዋ ሴት ጋር ያደረግኩት አጭር ቆይታ ለዶክተር አብይ የተደረገላቸውን ከልብ የመነጨ ደማቅ አቀባበል እውነተኛነትን ያረጋገጠልኝ ነው። ሰላምን፣ ፍቅርንና መደመርን በሁለቱም ወገን ያለነው ዜጎች ምን ያህል እንደተጠማን ቁልጭ አድርጎም አሳይቶኛል። አየር መንገዳችን ስራ ሲጀምር ምልባትም ቀዳሚው ተደማሪ እኔ ሳልሆን የምቀር አይመስለኝም። እስቲ የዚያ ሰው ይበለን።…

በዚህ ክፍል ፅሑፌ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኤርትራ ጉብኝት ማሳያነት የሁለቱ ሀገር ህዝቦች ለሰላም፣ ለፍቅርና ለመደመር ያላቸውን ከልብ የመነጨ ፍላጎትን አሳይቻለሁ። አንድም ሁለትም የሆኑት እነዚህ ህዝቦች በመሪዎቻቸው አማካኝነት የተፈራረሟቸው ስምምነቶችን ከቀጣናው ሁኔታ ጋር በማያያዝ አመላክቻለሁ። ቀሪው የፅሑፌ አካል በቀጣዩ ክፍል የሚነበብ ነው። አብረን ወደዚያው እንዝለቅ።…

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy