Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለውጡ  የይቅርታና የዕርቅን መፈክር ከፍ ያደረጉ

0 344

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለውጡ  የይቅርታና የዕርቅን መፈክር ከፍ ያደረጉ

ልባሞችን ይሻል

ዮናስ

 

የኢትዮጵያ ሰላም የኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ውስጣዊ ለውጥም የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፡፡ኢትዮጵያ በምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ የአንዱን አገር ኋላቀርነት የሌላው መመንደጊያ፣ የአንዱን ቂልነት የሌላው መብለጫ የማድረግ ሩጫ ተበላጩን ብቻ ሳይሆን ብልጥ ልሁን ባዩንም ይዞ የሚጠፉ መሆኑን መረዳት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ የአንዱን የሰላም ዕጦትና ወደ ኋላ መቅረት ሌላው ተጎራባች እንደ ራሱ መታመስና ወደ ኋላ መቅረት አድርጎ እንዲያይና ያንን ለመቀየር፣ መረዳዳትን ግድ የሚሉ ሁኔታዎች ላይ ተደርሷል፡፡

 

ዛሬ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የቀይ ባህር ጥቅማቸውን ማስከበር ተስኗቸው የማዶ ጎረቤታቸው የመን ዓይናቸው እያየ የተወረረችውና የወደመችው፣ ኤርትራ በጊዜያዊ የገንዘብ ጥቅም የዚህ ጥፋት ተቀጥላ የሆነችው፣ የባህረ ሰላጤው መጠማመድ በቋፍ ባለችው የሶማሊያ መንግሥታዊ አካላት ውስጥ አለመግባባቶች ሊሰነቅር የቻለው፣ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች በድህነትና በውስጣዊ ትርምስ ስለደከሙና ኅብረት ስላጡ የነበር መሆኑንም አሁን ያለንበት ተጨባጭ ሁኔታ እናስታውስ ዘንዳ ያስገድደናል፡፡  

 

በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ የእያንዳንዱ ጎረቤት አገር የውስጥ ጉዳዩ፣ ግስጋሴውና ሰላሙ ከሌላው ጋር የመያያዙ ነገር ከመከከለኛ ምሥራቅ እስከ ህንድ ውቅያኖስ ድረስ የተጠላለፈና አድማሱ የሰፋ መሆኑን የቀንድ አገሮች መንግሥታት ሁሉ በቅጡ መገንዘባቸው፣ ማነቆዎቻቸውን ለመበጣጠስ መሠረታዊ መነሻ ነው፡፡ በኃይል፣ በኩርፊያ፣ በማሳደም ወይም በእጅ አዙር ዘዴ ልቅጣ ባይነት የከሸፈና የጋራ ጥቅምን የሚጎዳና የሚያስጠቃ ስለመሆኑ ማውራት ለቀባሪው እንደማርዳት ይሆናል።

 

ብዙ ጎስቋላ አገሮች ውስጥ ሕዝብ እልል ያለለት የዴሞክራሲ ምርጫ ተካሂዶ፣ ሕዝብ እምነት የጣለበት መንግሥት ተደራጅቶ ግን እንደተገመተው ሳይሆን የሚቀርበት፣ ዘረፋን ማሸነፍ አቅቶት ባለበት እየረገጠ የሚመክንበት ወይም የግልበጣ ሲሳይ የሚሆንበት የሰላም እጦት ልምድ ተደጋግሞ ታይቷል፡፡ ይህን መሳዩ ልምድም ዴሞክራሲ መገንባትን ከባድ ነገር አስመስሎታል፡፡  

 

መልከ ብዙ የሆነው ነቅዞ አንቃዥነት መስፋፋትና መንሰራፋት የቻለው በእርጉም ሰባኪያን አማካይነት አይደለም፡፡ እንዲያ ሆኖ ቢሆን ኖሮ፣ እርጉሞቹን ሰባኪያን ለቅሞ በብሩክ ሰባኪያን በመተካት በተገላገልነው ነበር፡፡ በሁሉም የኑሮ ዘርፍ ውስጥ ፈጣን፣ ቀጥተኛና ፍትሐዊ አገልግሎቶች የጠፉት በልግመት፣ በሽፍንፍን ሥራና በጉቦ ልውውጥ ተቦዳድሰው ነው፡፡ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ዕውቀትና ክህሎትን በአግባቡ እየተጎናፀፉ ደረጃ ከማለፍ ይልቅ፣ በሐሰተኛ መንገዶች (በኩረጃዎች፣ በአስተዳደራዊ ውሳኔዎችና በሥውር የጥቅም ግንኙነቶች) ያልደከሙበትን ነጥብ ማፈስ፣ ጭራሽ የትምህርት ገበታ ላይ ሳይገኙ ሐሰተኛ ውጤት ማሠራት መቅለሉ፣ ምስክር ወረቀት የተሸከሙ ችሎታና ዕውቀት የለሾችን ሲያመርት ኖሯል፡፡ በሥራ ገበታዎች ዘንድም በችሎታና በብቃት ከመቅጠርና በሥራ ፍሬ ከማደግ ይልቅ ለመንግሥት ፖለቲካና ለሹም አዘጥዛጭ በመሆን፣ የጥቅም ትስስር በመፍጠር መንገዶች መሄድ መቅለሉ ችሎታ የለሽነትን ከትልልቅ ሥራዎች፣ ከትልልቅ ኃላፊነቶችና ከትልልቅ ጥቅሞች ጋር አገናኝቷል፡፡ ከትልልቅ ኃላፊነቶች ጋር የተገናኘ የብቃት ማነስና ሐሳዊ ብቃት ደግሞ ጉዱን የማለባበስ፣ በጥቅም አፍ የማስያዝና መሰናክልን የመዝለል ተግባር ውስጥ እየገባ ብልሹ ሥራና ንቅዝትን ስር እንዲሰድ አድርጓል፡፡ ይህ በሆነበት አግባብ አሁን የተያያዝነውን ለውጥ የማስቀጠል በጥሞና እና በእውቀት ካልተመራ በእነዚህ እና ንቅዘትን ኑሯቸው ባደረጉ ሃይሎች ሰላማችን የሚታወክ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።

 

ለውጡ ከሰላም  ውጭ ውጤታማ አይሆንም ። እነዚህን ከላይ የተመለከቱ ሃይሎች የመጠራረግ ጉዳይ ይህንን የርባታ ስንሰለት የመበጠስ፣ ዕውቀትና ችሎታ የለሽነትን የመጠራረግ፣ ተምሮ ማወቅን ለሁሉም ተማሪ የማቅለል፣ ከሐሰተኛ መንገዶች ይልቅ በእውነተኛ የሥራ ፍሬ የመለካትን መንገዶች ቅርብ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንንም ተዓምር በእርግጠኝነት ሕዝብን በነዘረና እንደ ሰደድ እሳት በሚዛመት ለውጥ ማዳረስ ይቻላል፡፡ግን ከምክንያታዊነት ውጪ በሚደረግ ሰሞኑን በምንመለከተው አይነት የጥላቻ ዘመቻ አንዳች ስንዝር መንፏቀቅም የማይቻል መሆኑን አብሮ ማስላት ይገባል።

 

በኢትዮጵያ ዴሞክራሲንና አዲስ የሥራ ባህልን በአጥለቅላቂ ለውጥ ሥር የማስያዝ ሚስጥር ደግሞ ምልዓተ ሕዝቡ በተለይም የወጣቱ ኃይል በታመቀ የለውጥ ፍላጎትና የወኔ ሙላት የሚቁነጠነጥበትን ምዕራፍ የመሳፈርና የእንድርድሮሹ ፍጥነት (የስሜት ሙላቱ) ሳይበርድ፣  በምክንያት የለውጥ ስንቅ እየመገቡ እንቅስቃሴውን የማጋፈር ጉዳይ ነው፡፡

 

ከኢሕአዴግ የተመዘዙ የዴሞክራሲ ወገኖችና ከተቃዋሚ ውስጥ የተፈለቀቁ የዴሞክራሲ ወገኖች ከኢትዮጵያ ሕዝቦችና ወጣቶች ጋር አንድ ላይ የገጠሙበት ይህ የለውጥ ኃይል፣ በሩብ ምዕት ዓመት ሮሮና መስዋዕትነት ላይ የበቀለ ከመሆኑ ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ቁርጠኛ ትግል ባለውለታ የመሆኑን ያህል ኢሕአዴጎችም ቅዋሜን በመሰባበር ተግባር ውስጥ ጭው ብሎ መንጎድ ለማንም የማይበጅ የመቀመቅ ጉዞ መሆኑን ዓይተው፣ ለእርማት ዓይናቸውን የመክፈታቸውም ባለውለታ ነው፡፡ ይህ የአሁኑ የለውጥ ምልዓት ከሁለት ወገን ውለታም በላይ የሁለት ወገን ልባምነትንም ለመጎናፀፍ የታደለ ነው፡፡

 

የለውጥ ምልዓቱ እስከ ዛሬ በተሠሩ የአፈና ጥፋቶች ተጠልፈን የበቀል እራት የምንሆነበት ቀዳዳ በሒደት ቢከፈትስ በሚል ሥጋት ያላፈገፈጉና ሕዝብን በአዲስ ታሪክ ለመካስ የመረጡ ቆራጦችን ከኢሕአዴግ በኩል እንዳገኘ ሁሉ፣ ከጥቅም ገበታ ከመገፋት አንስቶ ተወንጅሎና ታስሮ እስከመገረፍ ድረስ በደልን በየዓይነቱ ከቀመሱ ሰዎችም በኩል በግል የደረሰባቸውን በደል ከመበቀል ይልቅ፣ በጥቅል ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የሚያተርፉትን ድል ያስተዋሉና የይቅርታና የዕርቅን መፈክር ከፍ ያደረጉ ልባሞችን ይሻል፡፡

 

ለውጥን የሚፃረሩ የአምባገነንነትና የዘረፉ ኃይሎች ለቅልበሳ የሚመች ሁኔታና ማመካኛ እስኪያገኙ እያደቡና ምናልባትም ውስጥ ለውስጥ ቋጠሮ እያበጁ ያሉበት ፈተና ከቀኝ በኩል እንዳለ ሁሉ፣ ከለውጥ ፈላጊውም ረድፍ ውስጥ ኢሕአዴጎችን በመበቀል የሰከሩ፣ ያውም ይህ ነው የሚባል ፍዳ ሳይቀምሱ አሜሪካና አውሮፓ ተቀምጠው ግፍ የዋለ ሰው በይቅርታ ማምለጡ እንዳይለመድ አሳቢ በመምሰል በቀልን እያቀነቀኑ ለቅልበሳ ኃይሎች የሰው ኃይል አበራካች የመሆን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ “የሽግግር መንግሥት ይቋቋም” ያሉትን ወገኖች በጅምላ ለበቀል ያደቡ አድርጎ ማሰብ ትልቅ ስህተት ቢሆንም፣ በቀለኞቹ ያለውን መንግሥት ከእነ ሕገ መንግሥቱ ሰርዞ (አፍርሶ) በሽግግር መንግሥት በኩል ሥር ነቀል ለውጥ ማካሄድ የሚል ዕቅድ የሚያቀነቅኑ መሆናቸው እየተገለጠ ነው፡፡

 

በቀለኞቹ የእነ ዶ/ር ዓብይንም የለውጥ ዕርባና የሚመዝኑት ለዚሁ የሽግግር መንግሥት መንገድ ከመጥቀሙና ካለመጥቀሙ አኳያ ነው፡፡ እነ ዓብይ እሺ ካሉ እነሱን ይዞ፣ እሺ ካላሉ እነሱንም አስወግዶ የሽግግር መንግሥት ላይ የሚደረሰው በቀለኞቹ የሆነ የፖለቲካ መተት ሠርተው ሳይሆን፣ እነሱ አሜሪካ ተቀምጠው አመራር እየሰጡና የውጭ ምንዛሪ ሸምቀቆን እያጠበቁ በኑሮ ምሬት የሚተክኑት ሕዝብና ወጣቶች በባዶ እጃቸው ከታጠቀ ኃይል ጋር እየተናነቁና እየረገፉ አገዛዙን እንዲገረስሱላቸው ነው የሚፈልጉት፡፡ የሕዝብንና የወጣቶችን የደም ግብር ከቁጥር ብናወጣው እንኳ በዚህ መንገድ ለመሄድ መሞከር የሚያደርሰን የተባበረ የሽግግር መንግሥት ውጤት ላይ ብቻ አይሆንም፡፡ በውስጣችንና በክፍለ አኅጉራዊ አካባቢያችን ውስጥ ውስብስብ የፖለቲካ ፍላጎቶች እንደመኖራቸው ከእስካሁኑ የበለጠ ጎሰኛ ክትክቶችና የልማት ውድመቶች ደርሰው ሻል ካለ በወታደራዊ ፈላጭ ቆራጭነት መመታት፣ ባስ ካለ ከቁጥጥር ባመለጠ ትርምስ መበታተንና የማይጠፋ የመጨራረስ አዙሪትን ለቀጣናችን ማውረስ ነው፡፡

 

የአሁኑ የዓብይ አህመድ መንግሥት ከመደላደሉ በፊት ወደ መነጠል ለመሄድ ቀዳዳ ማስፋት፣ ከመነጠል በመለስ ሆኖም  ብሔሬ፣ ለብሔሬ ልጆች በሚል እሳቤ በኢንቨስትመንትም ሆነ በሌላ መልክ “ሀብት አጫራሽ ባዕዶች”ን የማፅዳት ሩጫም፣ የአገሪቱን ከወጪ ንግድ የውጭ ምንዛሪ የማፍራት ውሱን አቅም አሰነካክሎና ለከፋ የዕቃዎች እጥረት (ለከፋ የዋጋዎች ግሽበት) ዳርጎ፣ ወደ ተፈራው የመንኮታኮትና የመባላት አዘቅት ያደርሳል፡፡

 

ስለዚህም ፀረ ዴሞክራሲ ኃይሎች፣ በቀለኞችና ከአፍንጫ ያልራቁ ብሔረተኞች ሳይተዋወቁ ተጋግዘው የለውጥ ምልዓቱን ከመከፋፈላቸውና ከማስመታታቸው በፊት፣ በውስጥና በውጭ ከሰላማዊ ትግል እስከ ትጥቅ ትግል ድረስ የተሰማሩ፣ ነፃነትና እኩልነት የተዘረጋባት ፌዴራላዊ አገር ለመገንባት የቆሙ ኃይሎችን ሁሉ በይቅርታና በእርቅ አሰባስቦ ለውጡ ግለትና ወኔው ሳይበርድ እንዲገሰግስ ማድረግ አጣዳፊ ነው፡፡  

 

ለዴሞክራሲ ድል ግድና ተቀዳሚ ከሆኑ ማሻሻያዎች በስተቀር ብዙ የሚያወዛግበውን አጠቃላይ የሕገ መንግሥትና የፌዴራል አካባቢዎች አወቃቀር ክለሳ ጉዳይንም ሌሎች አዘላለቃችንን የሚወስኑ አደጋዎችን እስከምናመክን ድረስ፣ በእንጥልጥል ማቆየቱ ስለሰላማችን ይበጃል፡፡ የሚሻለውም ይኼው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም (1983 ዓ.ም. መጨረሻን ይዞ) ጥቂት ብሔረተኛ የፖለቲካ ልሂቃን ራሳቸውን የአገሪቱ ፌዴራላዊነት መሐንዲስ አድርገው ከራሳቸው አልፈው በብሔረተኛነት ያልተሳሳቡትን ማኅበረሰቦች ሁሉ፣ በአገረ ብሔርነት አስተጫጪና ደልዳይ እስከመሆን ድረስ በአገሪቱ ሕዝቦች ዓብይ ጉዳይ ላይ ፍላጎታቸውን በእናውቅለታለንና በውክልና ዘዴ በመጫን የሠሩት ስህተት ሳያንስ፣ አሁንም ያለመታረም አዝማሚያ ብቅ ብቅ እያለ ነው፡፡

 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ ልዩ ልዩ አካባቢዎችና በጎረቤት አገሮች የሥራ ጉብኝት ማካሄዳቸው ውስጣዊና ክፍለ አኅጉራዊ ተቀባይነት ላይ ጉልህ አዎንታዊ ውጤት እያስገኘ ቢሆንም፣ የልማት ሥፍራን ማጥቃትና ማፈናቀል ብቅ ብቅ ማለቱ (ለምሳሌ በጎጀብ እርሻ ልማት፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በሞያሌ በጌዲዮ እና ጉጂ ) የለውጥ ሒደቱን ለመቀልበስ ሩጫው መፋፋሙን የሚጠቁም ነው፡፡ የሥልጣን ክፍተት የተፈጠረ ይመስል ከቀን ወደ ቀን ባሰኘ ሲጨምር የሚታየው የዋጋ ንረትም የሕዝብን የለውጥ ቀልብ  በምሬት እየሰረቀና እየሰረሰረ ይገኛል፡፡ ስለዚህ የዋጋ ንረትን ከማስታገስ ጋር የምልዓተ ሕዝቡን ትኩረት ወደ ለውጥ ሒደት መልሶ ማምጣትና የለውጥ ጥማቱንና ጉጉቱን ከለውጥ ጋር እያገናኙ እንዲራመድ ማገዝ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

 

የሕዝብ/የወጣቶች የለውጥ ተነሳሽነት ትክክለኛ ማገዶ ካላገኘና ባሰለቸ የስብከት መንገድ ልነዝንዝህ ካሉት ለወረቱ ያህል ተፍጨርጭሮ ከመቆርፈድ አያመልጥም፡፡   ከቤት እስከ ትምህርት ቤትና መሥሪያ ቤት ድረስ የተንሰራፉትንና የደደሩትን ላለመደማመጥ የሚካሄዱ ብልሹ የውይይት ልማዶችን፣ ሳይግባቡ “መግባባት”ን፣ ከጀርባ ዞሮ ስም ልጠፋን፣ የዝርክርክነትና የአበያነት ምርኮኝነትን፣ የሸርና የሾኬ ልማደኝነትን፣ ያልዘሩትን የማጨድ ሩጫን፣ ወዘተ ለማበራየት ለመታገልና ቅንነትን፣ መተራረምን፣ ተቆርቋሪነትን፣ ጥንቁቅነትን፣ ተፍጨርጫሪነትን፣ ትጋትንና ጨዋነትን በአጠቃላይ ትድድራችን ውስጥ ለማጎልበት መትጋት ይገባል፡፡ ከሥራ ገበታዎች ጋር በተያያዘ በዚህ የለውጥ ሒደት ውስጥ የዕውቀትና የችሎታም ሆነ የምግባር ጉድለት ጉርስ በማሳጣት የማይቀጣበትን፣ ድክመት ወደ ጥንካሬ የሚለወጥበትን የእነፃ ሥርዓትና ለችሎታ ከሚመጥን የሥራ ድርሻ ጋር የማገናኘት መፍትሔን ማዘጋጀት የለውጡን ስኬታማነት በእጅጉ ይወስናል፡፡

 

በዴሞክራሲና በባህል ለውጥ አማካይነት ነፃነትና የሰው ልጅ ክቡርነት ያበራባት፣ ግፍ ሠርቶ መሸሸግና ከፍትሕ ማምለጥ የተሸነፈባት፣ ባለዕውቀትና ባለችሎታ ሠራተኝነት፣ ትጉህና ትሁት አገልጋይነት፣ የጠራ የሥራ ውጤት መፍለቅ ገና በጅምር የተቃናላት፤ የፖለቲካ ሰላምን፣ የሃይማኖቶች እኩልነትንና መከባበርን የተቀዳጀች፣ ሰላማዊ ጉርብትናን፣ ፍትሐዊ ንግድንና ተጋግዞ መልማትን የምትተነፍስ አገር በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ብቅ ካለች በሰፊ ዙሪያዋ እንደ ንጋት ጀንበር አብሪ መሆኗ፣ የለውጥ ብርሃኗ ምንም ዓይነት የገዥዎች ኩርፊያና የአፈና አጥር ሳያግደው እንደ ተስቦ መዛመቱ የማይቀር ነው፡፡ ኢትዮጵያና የቅርብ ጎረቤቶቿ ዛሬ ከሚታሰበው በላይ ተቀናብረው በቀይ ባህር ጂኦፖለቲካ ውስጥ ተሰሚነታቸውንና ጥቅማቸውን በአግባቡ ማስጠበቅ የመቻላቸውም ነገር ሩቅ አይሆንም፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ እነ ሞያሌን፣ ጋምቤላን፣ አሶሳንና መተማን ሁሉ ወደ የብስ ወደብነት የቀየረ ባለብዙ መንገድ በሚሆንበት ጊዜም፣ የባህር በር የለሽነቷም የአጭር ጊዜ ታሪክ ሆኖ ማለፉ የማይቀር ይሆናል፡፡  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy