Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለጋራ ልማት…

0 1,070

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለጋራ ልማት…

                                                        ደስታ ኃይሉ

“ሞት አልባ ጦርነት” የነበረው የኢትዮ- ኤርትራ ግንኙነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ትብብርና አጋርነት መንፈስ ተለውጧል። ከሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት ዋነኛ ተጠቃሚዎቹ በአገራቱ ድንበር አካባቢ የሚገኙ ህዝቦች ናቸው። እነዚህ ህዝቦች የሚኖሩባቸው የትግራይና የአፋር የድንበር አካባቢዎች ላለፉት 20 ዓመታት ምንም ዓይነት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የማይታይባቸው ፍዝ አካባቢዎች ነበሩ ማለት ይቻላል።

አካባቢዎቹ በስጋትና በጭንቀት የታጠሩም ነበሩ። በግጭት ወቅትም ቢሆን በእነዚህ አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች የመጀመሪያ ደረጃ ተጎጂዎች እንደነበሩ እናስታውሳለን። በአሁኑ ሰዓት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰላምና እርቅ ወዳድ አቋም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ሰላም፤ በተለይ የድንበር አካባቢዎችን በአጠቃላይ ደግሞ ሁለቱን አገራትን የሚጠቅም ነው። በቅርቡ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሁለቱን አገራት ግንኙነት በተመለከተ ሰሞኑን ያወጣውን መግለጫ አንዱ ማሳያ ይመስለኛል። ይህም በአሁኑ ሰዓት የአገራቱን የሰላም ተጠቃሚነት በማጎልበት ለጋራ ልማት መስራት መስራቱ ትክከለኛ መንገድ መሆኑን ያሳያል።

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ በሰላም እንዲጠናቀቅ ክልሉ በከፍተኛ ፍላጎት የሚቀበለውና የሚደግፈው መሆኑን አስታውቋል። የቆየውን ግጭት ለመፍታትና ዘላቂ ሰላም በሚያረጋግጥ፣ ግልፅነት ባለውና ህዝብን በሚያሳትፍ መንገድ እንዲቋጭ ክልሉ ጥሪ አቅርቧል። ይህም የድንበር ችግሩ በዋነኛነት የሚጠቅመው በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የክልሉን ህዝቦች እንደሆነ የሚያሳይ ነው።

ሰላም ከሌለ እንኳንስ በድንበር አካባቢዎች ቀርቶ በሀገር ደረጃም ምንም ዓይነት ተግባር መከወን አይቻልም። በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ወጥቶ መግባት አስቸጋሪ ይሆናል። ከውጥረት የሚገኝ ትርፍ የለም። ይህ ህዝብ ከትናንት በስቲያ በፊውዳላዊው አገዛዝ ስር የማቀቀ፣ ትናንት ደግሞ በአምባገነኑ የደርግ ስርዓት የአፈና መዋቅር ውስጥ ሁለንተናዊ መብቶቹ ተረግጠው በስቃይ ውስጥ የኖረ ነው። ዛሬ ደግሞ በፍቅር መፍታት እየተቻለ ባለው የኤርትራ ጉዳይ ሌላ ችግ ውስጥ መግባት የለበትም።

የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ሰላም ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት በገሃድ አይተናል። የትናንቱ የጥላቻና የውጥረት ዘመን ተመልሶ እንዲመጣ አይፈልግም። በጋራ ማደግና መለወጥ እየተቻለ ሁል ጊዜ በውጥረት ውስጥ ሆኖ መቀጠልም የለበትም። ዶክተር አብይ በከፈሉት ከባድ መስዋዕትነት የተገኘውን ሰላም አሟጦ መጠቀም ይገባል።

ሰላም ከቁሳቁስ መጥፋትና መውደም ጋር ብቻ የሚያያዝ አይደለም። ነገ የሚገነባው ትልቅ ምጣኔ ሃብት ያለውና ለዘመናት ተነፍጎት የነበረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባት ስር እንዲሰድም ያግዛል። የኢትዮጵያ ህዝብ ከኤርትራ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ከሰላም የሚገኙ ትሩፋቶችን መጠቀም ይሻል።

የአገራችን ህዝብ ከሰላም ምን ያህለ ተጠቃሚ እንደሆነ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ ያገኛቸውን ለውጦች በቀላሉ የሚገነዘብ ነው። ሰላም ካለ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ መደመርና አንድነት ምን ያህል እንደሚያብቡ አይቷል። ከአገር ውስጥ አልፎም በውጭ አገር ምን ያህል ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የሚያውቅ አስተዋይ ህዝብ ነው። ላለፉት 20 ዓመታት ህየወቱ በሰቆቃ የተሞላው የድንበር አካባቢ ህዝብ ደግሞ ስለ ሰላም ከማንም በላይ ያውቃል።

ከኤርትራ ጋር የሚዋሰኑት የትግራይና የአፋር የድንበር አካባቢ ህዝቦች እየገፉ የነበሩት የስቃይ ኑሮ በተፈጠረው ሰላም ያበቃል። በሁለቱም አገራት መካከል የሰለም አየር ይነፍሳል። ችግሮች ካሉም በመነጋገር አብረው ይፈታሉ።

በአገራቱ መካከል የነበረው ችግር ሁለቱን ወንድማማች ህዝቦችን የነጣጠለና ዳግም እንዳይተያዩ ያደረገ እንዲሁም በቀጣናው ውስጥ የሚፈለገው ሰላም እንዳይመጣ ምክንያት የሆነ ነው። ሁለቱ ህዝቦች በደም፣ በባህል፣ በወግና በታሪክ የተሳሰሩ ናቸው። ህዝቦቻቸው ሁለት ግን አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ናቸው። ሆኖም ችግሩ በዘለቄታዊ ጥቅማችን ላይ ምንም ዓይነት ረብ በሌለው እንካ ሰላንቲያ ውስጥ እንድንጓዝ ያደረገን ነው።

የጨለማው ተምሳሌት ነው። ውጥረት ውስጥ ሆንን አንዳችን በሌላችን ላይ ጣታችንን እንድንቀስር ምክንያት እንደሆነም እናስታውሳለን። ሁለታችንንም ጥላቻንና ቂም በቀልን እንደ ፀጋ ይዘን በውጥረት ውስጥ ማለፍ ግድ እንዲለን አድርጎናል። ለብዙ ልማታዊ ጥቅም ልናውለው የምንችለውን ሃብትና የሰው ሃይል ያለ ያለ ስፍራውና ያለ ቦታው እንድናባክንም ምክንያት ሆኖናል።

ከሰላም፣ ከፍቅርና ከመደመር የምናገኘውም ሁለንተናዊ ጥቅማችን በዜሮ እንዲባዛ ያደረገ ችግር ነው። የፀብና የቁርሾ መንገድ ተዘግቶ አዲስ የሰላም መንገድ መጀመሩ ለሁለቱም አገራት አዲስ ግንኙነትን ፈንጥቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በወሰዱት እርምጃ ሁለቱም አገራት የሰላምን ፅዋ እየተጎነጩ ነው።

ጥላቻና ብሽሽቅ አሁን በምንገኝበት የስልጣኔ ዘመን ትርጉም የለውም። ለሁለቱም አገራት የሚበጅም አይደለም። ዛሬ መደመር እንጂ፣ መነጠል ቦታ ምንም ዓይነት ትርፍ አያስገኝም። ይቅርታ፣ ሰላምና ተቻችሎ መኖር ለሁለቱም አገራት የሚበጃቸው አይደለም።

በሰላምና በፍቅር ሳንደመር ያጠፋነው ጊዜ ያሳዝናል። አሁንም ግን በአዲስ መንገድ መጓዝ እንችላለን። በጋራ ተጠቃሚነት እሳቤ ተባብሮ የመስራት ፍላጎቱ እስካለ ድረስ ተያይዞ ማደግና የሀገራቱን ህዝቦችን ተጠቃሚ የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም።

ከ20 ዓመት መለያየት በኋላ አሁን የተከፈተው አዲስ የሰላም መንገድ፤ ባለፉት ዓመታት የሁለቱ አገራት ህዝቦች ያጡትን ጥቅም የሚክስ ነው። ሰላም ካለ ሁለቱም አገሮች ያላቸውን የተፈጥሮ ፀጋዎችና የገበያ ሁነታን በአግባቡ ሊጠቀሙ ይችላሉ።

እዚህ ላይ የአገራቱ ግንኙነት ለቀጣናው የጋራ ልማትም ያለውን ጠቀሜታ በጥቂቱ ማንሳት ያስፈልጋል። በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት የሀገራቱ ህዝቦች እንዲተባበሩ ብቻ ከማድረግ ባሻገር የቀጣናውን ሀገራት በጋራ ሰላም አምጭዎች እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ነው።

በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሊገኝ የሚችለው ሰላምም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንደሚጠቅም ጥርጥር የለውም። ቀጣናው ስትራቴጃካዊ ከመሆኑም በላይ እጅግ በርካታ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በውስጡ አምቆ የያዘ ነው። እነዚህ ፀጋዎች ሁሉም ሀገራት ያላቸው አይደሉም። በሚገኘው ሰላም ሁሉም አገራት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ አንዱ የሌለውን ከሌላው በመጠቀም ዕድገትን ሊያሳልጡ ይችላሉ። ይህም ቀጣናው የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ እንዲገባ ያደርግና ሁሉም ሀገራት ተያይዘው እንዲያድጉ የሚያደርጋቸው ነው። ይህ ሁኔታም የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰላም ለቀጠናው አገራት ምን ያህል ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው። ለጋራ ልማት ምን ሰላምና መደመር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነም ያረጋግጣል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy