Artcles

ለጥፋት ኃይሎች…

By Admin

July 24, 2018

                                                        ደስታ ኃይሉ

በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች በህዝብ ላይ ጉዳት እያስከተሉ ነው። ለዘመናት አብረው በፍቅርና በመተሳሰብ ይኖሩ የነበሩ ህዝቦችን ያለ ፍላጎታቸው ጥላሸት ለመቀባት እየሞከሩ ነው። እነዚህ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት ህብረተሰቡ አስቀድሞ በመነጋገር የችግሮቹን ቀዳዳዎች በመድፈን አስቀድሞ መከላከል እንደሚኖርበት ያስረዳል።

ሚዲያውም ቢሆን ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር ጉዳዩን ከማራገብ ይልቅ ህብረተሰቡ ባለው የግጭት አፈታት ባህል መሰረት ችግሮቹን እንዴት አስቀድሞ መከላከል እንዳለበትና ከተከሰቱም በኋላ እንዴት መፈታት እንደሚገባው ማስተማር ይኖርበታል። በዋናነትም ችግሮቹ የሚፈቱ መሆናቸውን የማስገንዘብ ሚና መወጣት አለበት። እንዲሁም በየትኛውም አካባቢ የሚገኝ ህዝብ ሰላም መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ፣ የበስተጀርባ የጥፋት ሃይሎች መጠቀሚያ ላለመሆን ችግሮችን በውይይትና በመነጋገር ብቻ መፍታት ይገባል።

በመወያየትና በመነጋገር የማይፈታ ችግር የለም። ሆኖም ግጭቶች ችግሮቻችንን የሚያወሳስብ ስለሆነ ልንከላከላቸው ይገባል። ምክንያቱም እዚህ አገር ውስጥ የሚካሄዱ ግጭቶች አንዳንዴም አሳፋሪ ከመሆናቸው ሌላ ግጭቶቹ ፈፅሞ የህዝቡን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አለመሆናቸው ነው።

በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች መነሻውን ወሰን በማድረግ የሚከናወኑ የግጭት ተግባራት አሉ። እነዚህ ግጭቶች መነሻቸው ህዝብ አይደለም። ህዝብ ለሰላም እንጂ ለግጭት ቦታ ሊኖረው አይችልም። ይሁንና አሁንም ቢሆን ለግጭት የሚሆን ምህዳርን በተቻለ መጠን ማጥበብ ይገባል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ከመልካም አስተዳደር ችግርና ከሙስና ጋር በተያያዘ ህዝቡን በማወያየት እርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሱ ነው። በክልሎች በተካሄዱ ሰፋፊ የውይይት መድረኮች ከህዝቡ በተገኘው ግብዓት መሠረት ጥፋት በፈፀሙ አመራሮች ላይ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው።

በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተወሰዱት እርምጃዎች ለሌላው ትምህርት ሰጪዎች ይመስሉኛል። ምክንያቱም ግጭትን በቀሰቀሱ አመራሮች ላይ ክልሉ እስከታች ባለው መዋቅር ድረስ ወርዶ የወሰዳቸው እርምጃዎች አስተማሪ ስለሆኑ ነው።

ግጭትን መከላከል የሚያስፈልገው ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት መሰረት ስለሆነ ነው። መንግስትም ይህን ተገንዝቦ በጥልቅ ተሃድሶው ወቅት ለተፈጠረው ችግር ሃላፊነቱን በመውሰድ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቋል።

መንግስት ችግሮቹን ለሚፈታበት መንገድ ተባባሪ መሆን ሲገባ አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ ግጭት ለመግባት የሚደረገው ጥረት ህዝቡን የማይወክል በመሆኑ በምንም ዓይነት መንገድ ተቀባይነት የሌለው ነው።

እርግጥ ከማናቸውም ችግሮች በስተጀርባ ግጭቶችን ተገን አድርገው የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳከት የሚጥሩ ፀረ ለውጥ ሃይሎች መኖራቸው ከማንም የተሰወረ አይደለም። እነዚህ ሃይሎች የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ በመሯሯጥ ላይ የሚገኙ ናቸው።  

ያም ቢሆን ለግጭት የሚሆኑ ምክንያቶችን አስቀድሞ መድፈን ይገባል። ለግጭት ሃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳርን ማሳጣት ያስፈልጋል። ይህን ለመከወን የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ…አልፎ ደግሞ ድብቅ አጀንዳን ይዘው የሚንቀሳቀሱት ጥቂት አካላትን ፍላጎት ማምከን ያስፈልጋል።

ግጭቶች በለውጥ ሂደት ውስጥ ሂነው አንድነትን እያጎለበቱ ባሉ ህዝቦች ውስጥ ቦታ የላቸውም። መደመርን እውን እያደረግን ባለበት ወቅት ፍቅርን የሚያጠፉ ጉዳዩች መከሰት የለባቸውም። ሁሉም በአገሩ ውስጥ በእኩልነት መንፈስ ተፈቃቅሮ እንዲሰራ እየተነገረበት ባለበት ወቅት አንድነትን የሚሸረሽሩ ተግባሮች መታየት የለባቸውም።

የኢትዮጵያ ህዝቦች ከግጭት የሚሰንቁት ምንም ዓይነት ተስፋ የላቸም። ተስፋቸው የተመሠረተው ከሰላም፣ ከልማትና ከዴሞክራሲያዊ ነው። ከፍቅር ከይቅርታና ከመደመር ነው።

እርግጥ ከግጭት የሚጠቀም ህዝብ ባለመኖሩም እነዚህን ተስፋዎች በማይነቃነቅ ፅኑ መሰረት ላይ በማኖር አስተማማኝን ሰላም መፍጠር ይገባል። ከዚህ አኳያ በቅርቡ በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች የተሰተውን ብንመለከት ምንም ዓይነት ህዝባዊ መሰረት የሌለ ሆኖ እናገኘዋለን።

ለበርካታ ዓመታት በሰላም የኖሩት የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝቦችም እንደ ማንኛውም ህዝብ ጥቅማቸው ያለው ከሰላም እንጂ ከግጭት አለመሆኑን የሚገነዘቡ ናቸው። በሁለቱ ክልላዊ መንግሥታት ህዝቦችም መካከል ግጭት የሚፈጠርበት መሰረታዊ ሁኔታ የለም።

ሆኖም የራሳቸውን ፍላጎት ለማራመድና ለውጡን ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ሃይሎች በወሰን አካባቢዎች ግጭት መፍጠራቸው ለዘመናት በፍቅር አብረው የኖሩትን የሁለቱን ተጎራባች ህዝቦች ፍላጎት የሚወክል አይደለም።

የትኛውም የህበረተሰብ ክፍል ከሚፈጠረው ግጭት ተጠቃሚ አይሆንም። የሚያስከፍለው ዋጋም ከባድ ነው። ግጭት በዶክተር አብይ አህመድ መሪነት እየተካሄደ ያለውን ለውጥ የሚመለከት አይደለም። ምክንያቱም ለውጡ ሁሌም ስለ ሰላምና ስለ ፍቅር ስለ አብሮ መኖርና ስለ መቻቻል እንዲሁም ስለ ኢትዮጵያዊ አንድነት ስለሚያቀነቅን ነው።

የአገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ውስጥ ክልሎቹ ሊወጡት የሚገባቸውን የተናጠልና የአብሮነት ሚናን ያቀጭጫል። በሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥ ላይም እንቅፋት ይሆናል።

ስለሆነም እንዲህ ዓይነቶቹን ወሰን መካለል ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ዘላቂ ጥቅሞችን ለማኮስመን ሆን ተብለው በፀረ ለውጥ ሃይሎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን ዘላቂ በሆነ መንገድ መዝጋት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ህብረተሰቡ የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል።

ህብረተሰቡ የግጭቱ ዋነኛ ተጠቂ በመሆኑም በድብቅ አጀንዳ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በማጋለጥ ለውጡን ሊያጠናክር ይገባል። ከህዝብ የሚሰወር ነገር ባለመኖሩም የግጭት መንስኤዎችን ከስር ከስር እየተከታታለ በመፍታት መንግስት ሰላም ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ አለበት። ይህም ለጥፋት ሃይሎች ምቹ ያልሆነ ቦታን በመፍጠር ሰላምንና ልማትን የሚያሰፍን ይሆናል።