Artcles

መሬት ጠብ ያላለው ሃሳብ

By Admin

July 14, 2018

መሬት ጠብ ያላለው ሃሳብ

                                                         ዋሪ አባፊጣ

ቀደምት አባቶቻችን አንድ ጉዳይ በተገቢው ወቅት፣ በትክከለኛ ሁኔታ ተነግሮ ሲያበቃና ማህበረሰቡም ወዲያውኑ ተቀብሎት በስራ ላይ ሊያውለው ሲንቀሳቀስ አሊያም ሲተገብረው ሃሳቡን “መሬት ጠብ ያላለ ነው” ይሉታል። ይህም ሃሳቡ በማህበረሰቡ ተቀባይነት ያለው ከመሆኑም በላይ፤ ለተግባራዊነቱም በነቂስ ድጋፍ የሚቸረው እንዲሁም መሬት ጠብ ሳይል በአየር ላይ እንደሚያዝ ኳስ ወደ ህብረተሰቡ አዕምሮ በቀጥታ ዘልቆ የሚገባ መሆኑን ያስረዳናል ብዬ አስባለሁ። ሃሳቡ ወደ ሰዎች አዕምሮ በፍጥነት ዘልቆ ከመግባት ባሻገር፤ ሳይውል ሳያድር ፈጣን ግብረ መልስም የሚሰጠው ነው።

ታዲያ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ ናቸው— እንዲህ ዓይነቱን መሬት ጠብ የማይል ሃሳብ በማፍለቅ ተወዳዳሪ የሌላቸው። እነዚህ ሰዎች አስቀድመው በገነቧቸው በተጨባጭ በሚታዩ ድንቅ ተግባሮችና ለማህበረሰቡ ባደረጉት ሰናይ ክንዋኔያቸው ሳቢያ፤ የሚያፈልቋቸው ሃሳቦች ከጫፍ እስከ ጫፍ በቅብብሎሽ ይስተጋባሉ። እንዲህ ዓይነቱ አፅናፋዊ ተቀባይነት “መታደል ነው” ከማለት ውጭ ሌላ ስም ልንሰጠው የምንችል አይመስለኝም—“ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም” እንደሚባለው ማለቴ ነው።

ርግጥም አንድ ሰው የሚያቀርባቸው ሃሳቦች ሁሉ፤ ከመንደር እስከ ሀገር፣ ከሀገር እስከ ጎረቤት ሀገር፣ ከክፍለ አህጉር እስከ አህጉር፣ ከአህጉር እስከ ዓለም ምድር በአንዴ ሲስተጋባ መመልከት፤ ስለ ሃሳቡ ባለቤት በተመስጦ እያሰብን በአድናቆት መደመማችን የሚቀር አይመስለኝም። የግለሰቡን ብቃት፣ ክህሎት፣ የመሪነት አቅም፣ ተደማጭነት እንዲሁም የተናገረው ነገር ሁሉ ከመሬት ጠብ የማይል ሆኖ፤ ማህበረሰቡ ‘እርሱ ያለው ትክክል ነው!’ ብሎ እንደሚወስድ ስናስብም የአድናቆታችን ከፍታ እጥፍ ድርብ ሆኖ መጨመሩ አይቀርም።

ታዲያ በሀገራችንም በጥቂት ወራቶች ውስጥ እንዲህ ዓይነት ቅቡል ስብዕናን የተላበሱ አንድ ሰው ብቅ ብለዋል—የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ። ዶክተር አብይ በሀገር ቤትም ይሁን በውጭ የያዙዋቸው ጉዳዩች አሊያም ያፈለቋቸው ሃሳቦች ወይም ያቀረቧቸው ጥሪዎች ሁሉ ተግባራዊ ይሆናሉ። ምላሻቸውም ‘ከጄት የፈጠነ’ የሚሉት ዓይነት ነው። ምንም እንኳን ነገሩ ከሳር ቤት ላይ አንድ ሰበዝ የመምዘዝ ያህል ቢሆንብኝም፤ እዚህ ላይ ጥቂት ማሳያዎችን ማንሳት የግድ ይለኛል።…

ዶክተር አብይ በሀገር ቤት ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ሲኖሩ በማግስቱ ቦታው ድረስ በመገኘት፤ ‘እባካችሁ እንዲህ ዓይነት ነገር ለጀመርነው የፍቅር፣ የይቅር ባይነትና የመደመር እንዲሁም የአንድነት መንገድ አይበጀንም’ ብለው እንደተመለሱ፤ በግጭቱ ተሳታፊ የነበሩ ዜጎች ወዲያውኑ ለዘመናት በገነቧቸው የእርቅ ባህላቸው መሰረት ሰላም ፈጥረው ምላሽ ሲሰጡ ተመልከተናል። ወደ ውጭ ሀገር ሄደውም በተለያዮ ምክንያቶች የታሰሩ ዜጎቻቸው እንዲፈቱ ሲጠይቁ ምላሹ ፈጣን ይሆናል። በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሚዲያዎች ‘ምህዳሩን እያሰፋን ስለሆነ መጥታችሁ ለሀገራችንና ለህዝባችን አብረን እንስራ’ ባሉ ማግስት፤ ፖለቲከኞችና ሚዲያዎች አዲስ አበባ ገብተው ሲያድሩ እየተመለከትን ነው። ሌላው ቀርቶ 20 ዓመታት ሙሉ በጥላቻና በመቃቃር እንዲሁም በመጎዳዳትና በመካሰስ ላይ ተተብትቦ የነበረውን የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት፤ ‘…ለሁለቱ ሀገራት ሰላም ከልቤ እሰራለሁ’ ብለው ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ግንኙነቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ በፍቅርና በመተሳሰብ የዘመን ክስተት ሲቀይሩ ተመልክተናል፤ እየተመለከትንም ነው።

ማንኛውም የሀገሬ ሰው እንደሚያምነው፤ ይህ ክስተት ታሪካዊ ነው። ለሁለት አስርት ዓመታት በእሾህ የታጠረው የመለያየት ድልድይ ፈርሶ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ አስመራ እንዲሄዱ፣ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂም ወደ አዲስ አበባ መጥተው የፍቅርና የይቅርታ ፅዋን በአንድነት ሲጎነጩ እንድንመለከት አድርጎናል። ሌሎች በተግባር የተመነዘሩና ሊመነዘሩ የሚችሉ ለሀገር የሚጠቅሙ ጉዳዩችን ሲከውኑም በዓይናችን በብሌኑ ተመልክተናል። በየጊዜው ምክረ ሃሳቦቻቸው መሬት ላይ ሳይወድቁ ተፈፃሚ እንደሚሆኑም አይተናል።…የለውጡ ዘመን ተሳታፊዎችና እማኞች እንድንሆንም አድርገውናል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ፓርላማ ተገኝተው ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት፤ ካቀረቧቸው ምክረ ሃሳቦች ውስጥ አንዱ የሆነውና ዳያስፖራው (በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ) በቀን ከሚጠጣው ማኪያቶ ላይ አንድ ዶላር ለወገኑ በመለገስ ኢኮኖሚውን እንዲደግፍ ያቀረቡት ጥሪ ያገኘው ፈጣን ምላሽ እጅግ አስገራሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በውጭ በሚኖረው ኢትዮጵያዊ ምላሹን የሰጠው፤ ቃላቸውን እንደ ግብ ጠባቂ ከአየር ቀልቦት ነው ማለት ይቻላል። ጥሪያቸው መሬት ላይ ጠብ ሳይል የተቀለበ ሆኗል።

በእኔ እምነት እንዲህ ዓይነት ድጋፍና ተቀባይነት በሀገራችን ታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ የሚታወቅ አይመስለኝም። ዶክተር አብይ እየመሩ እንዳሉት መንግስት ተቀባይነት ያለውና የተናገረው ነገር ሁሉ ወዲያውኑ ተፈፃሚ የመሆንለት መንግስት በዚህች አጭር ዕድሜዬ አይቼ አላውቅም። ተፅፎም አካነበብኩም፤ ሲነገርም አልሰማሁም። የዕድሜ ባለፀጋዎችን ጠይቄም ‘የለም!’ የሚል ምላሽ ነው ያገኘሁት። ይህም የትኛውም ኢትዮጵያዊ መሪ እንዲህ ዓይነት ድጋፍና ተደማጭነት ከዳያስፖራው አግኝቶ እንደማያውቅ የሚያሳይ ይመስለኛል። ቀደም ሲል “ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም” ያልኩትም ለዚሁ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዳያሰፖራው አንድ ዶላር ከዕለታዊ የማኪያቶ ፍጆታው ላይ ለወገኑ እንዲሰጥ እየጠየቁ ባለበት ቀጥታ ስርጭት ላይ፤ የፌስ ቡክ ተመልካች ፈቃደኛነቱን ከሚኖርበት ሀገር ጋር እያያዘ ‘ዝግጁ ነኝ’ ሲል መመልከት ጥሪው መሬት ላይ ሳይወድቅ እንደምን በአየር ላይ እንደተቀለበ የሚያሳይ ነው። ተቀባይነቱ በሀገር ውስጥ ብቻ የታጠረ ሳይሆን፤ በውጭ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንንም ማንቀሳቀስ የቻለ መሆኑም ጭምር እንዲሁ።

የዳያስፖራው አባላት ዶክተር አብይ በጥሪያቸው ወቅት ከእነርሱ የሚሰበሰበው ገንዘብ በፍፁም እንደማይባክንና ከታሰበለት ዓላማ ውጭ ለምንም ዓይነት ጉዳይ እንደማይውል የገቡትን ቃል ከማመን ባለፈ በራሱ ተነሳሽነት ተግራዊ ምላሽ እየሰጠ ነው። ዳያስፖራው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል የማይታጠፍና በተግባር የሚገለፅ መሆኑን በበዓለ ሲመታቸው የመጀመሪያው ዕለት ‘እፈፅመዋለሁ’ በማለት ቃል ገብተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ካከናወኗቸው ተጨባጭ ድርጊቶች በሚገባ ይገነዘባል።

እናም የዶክተሩ ቃል፤ ታታሪዎቹ ጃፓኖች “ተግባርህን ንገረኝና ማንነትህን ልንገርህ” እንደሚሉት፤ ተግባራቸው ምግባራቸውን የሚገልፅ መሆኑን የተገነዘቡት ዳያስፖራዎች ለጥሪው የሰጡት ምላሽ የትኛውንም ወገን ያስደነቀ ሆኗል። እነዚህ ወገኖች ጥሪውን በዕውቀታቸው፣ በቁሳቁስ፣ በገንዘብ እንዲሁም በሃሳብ ለመፈፀም ከፍተኛ ተነሳሽነትን እያሳዩ ነው። ይህ እውን ሊሆን የሚችል ምላሻቸው ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ፤ ኢኮኖሚያችንን መደገፍ የሚችልና በውጭም አገራዊ አንድነትን በመፍጠር ረገድ ደርሻው ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም።

ርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር ጊዜ በሀገር ውስጥ ሰላምን ማስፈናቸው፣ ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከራቸው፣ በህዝቦች መካከል የይቅር ባይነትና የፍቅር መንፈስ እንዲረብ እንዲሁም መቻቻል እንዲጎለብት ብሎም የአብሮነትና የመደመር ፖለቲካ ስር እንዲሰድ ያደረጓቸው በግልፅ የሚታዩ ተግባሮቻቸው፤ በዳያስፖራው ንቁ የሀገር ፍቅርና የአንድነት ስሜት መደገፍ ይኖርበታል። ምክንያቱም በለውጥ ምህዋር ውስጥ ያለችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ያለው ዜጋ ብቻ ሳትሆን፤ በውጭ የሚገኙ ኢዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዞሮ መግቢያቸው ስለሆነች ነው። ኢትዮጵያ የጋራ ሃብታችን ስለሆነች ነው። የክብራችን መገለጫም ስለሆነች ነው። እናም ይህችን ሀገር ቀና ለማድረግ በዶክተር አብይ መሪነት በተጀመረው የለውጥ ሂደት ውስጥ ማለፍ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድርሻ ነው። የዳያስፖራው ሀገራዊ ተሳትፎም ከዚህ አኳያ የሚታይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ዳያስፖራውን ለማነጋገር በቅርቡ ወደ ሀገረ አሜሪካ ያቀናሉ። በሶስት በተመረጡ ቦታዎች በዚያ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ውይይት ያደርጋሉ። በውይይቶቹ ላይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ያሻውን ሃሳብ ይዞ መግባት ይችላል። መድረኩ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ክፍት ነው። ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ ሊሳተፍም ይችላል። ዳያስፖራው በወቅቱም አሁን እየተንቀሳቀሰበት ያለውን ሀገራዊ ድጋፍ በተቀናጀ ተግባር ሊገልፀው ይችላል። መንግስት በሚያመቻቻው የገቢ ማሰባሰቢያም ይሁን በዕውቀት፣ በሃሳብና በሌሎች የብልፅግና መንገዶች ሀገራቸውን መጥቀም የሚችሉ የዳያስፖራ ወገኖች የለውጥ ሂደቱ ተጨባጭ ተደማሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ሀገራቸው እነርሱን እንደምትፈልገው ሁሉ፤ እነርሱም ሀገራቸውን ይፈልጓታልና። እናም ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥሪ የሰጡትንና በወቅቱም የሚሰጡትን ድጋፍ በዚህ አጋጣሚ ሳላደንቅ ማለፍ አልፈልግም።

እንዳልኩት ዶክተር አብይ ለየትኛውም ወገን የገቡትን ቃል በተግባር የሚፈፅሙ የህዝብ ልጅ ናቸው። የተናገሩትም መሬት ጠብ አይልም—ተቀባይነት ያገኛል። በተጨባጭ ክንዋኔው ህዝብን አንድ በማድረግ ከጎኑ ያሰለፈ ማንኛውም ኃይል የሚያገኘው ግብረ መልስ አፍታም አይቆይም። የሀገር ውስጥ ተፎካካሪውም፣ መደበኛ ዜጋውም፣ ሲቪክ ማህበረሰቡም፣ በውጭ የሚገኝ የፖለቲካ ፓርቲውም፣ መንግስታዊ ያልሆነው ድርጅትም፣ በውጭ የሚኖረው ዜጋም ሁሉም የሚያዳምውና ጥሪውንም ተቀብሎ ወዲያውኑ ምላሽ የሚሰጠው መሪ ሀገራችን ማግኘቷ ታድለናል፤ ታድላችኋል። እናም በእኚህ መሪ የተጀመረው አዲስ የለውጥ ምዕራፍ በተግባር የሚገለፅ አጋር መሆናችንን ደግመን ደጋግመን ማሳየት ይኖርብናል እላለሁ።